በሔለን ተስፋዬና በተመስገን ተጋፋው
የፌዴራል ፖሊስና መከላከያ የቀይ መስቀል ዓርማን በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ያላግባብ እየተጠቀሙ መሆኑን የቀይ መስቀል አዲስ አበባ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡
የቅርንጫፉ ዋና ጸሐፊ አቶ አበባው በቀለ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የቀይ መስቀልን ዓርማ ከፌዴራል ፖሊስና መከላከያ አንዳንድ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ ሌሎች ተቋማት እንደሚጠቀሙት በጥናት ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ከቀይ መስቀል ውጪ ያሉ አካላት፣ የቀይ መስቀል ዓርማን በተሽከርካሪ ላይ በመጠቀም የተለያዩ ጥፋቶችንና ጉዳቶችን ሲያደርሱ እናያለን፣ አንዳንድ ጊዜ ታራሚዎችን ሲያመላልሱበት ይስተዋላሉ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህንንም በተመለከተ በቪዲዮና በፎቶ በማስደገፍ በየቢሮው በግንባር ለመጠየቅ መሞከሩንና ዓርማውም ከየሕንፃዎችና ከመኪናዎቻቸው ላይ እንዲነሳ አሳስበው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ‹‹የቀይ መስቀል ዓርማ ያደረገ መኪና ሁሉ የቀይ መስቀል አይደለም›› በማለት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ እንደሚተላለፍና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ መሞከራቸውን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ በስልክ የጠየቅናቸው የመከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ሙሉ ሞገስ፣ ስለጉዳዩ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ፣ በአሁኑ ሰዓት በርካታ ሰብዓዊ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡
ቅርንጫፉ ከሚያከናውናቸው የገቢ ማመንጫ ተግባራት መካከል፣ የመጀመርያ ዕርዳታ ሕክምና ሥልጠናና የኮሜርሻል አምቡላንስ አገልግሎት ይገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ በታገዙ የሀብት ማመንጫ ዘዴዎች ረገድ ውስንነቶች አሉ፡፡
ዘንድሮ በአጭር መልዕክት አገልግሎት ኤስኤምኤስ አማካይነት አባላትን ለማበራከትና ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ውል ተፈርሟል፡፡ በቅርቡም አገልግሎቱ በይፋ ይጀመራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ከተመሠረተ 83 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህም በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 195 ሺሕ ያህል አባላትን ይዟል፡፡ በአማራ ክልል በ11፣ በኦሮሚያ በ14፣ በትግራይ በአራት ዞኖችና ወረዳዎች የቀይ መስቀል ማኅበር የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ከአፍሪካ አገሮች አንደኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ከዓለም ደግሞ 48ኛ ደረጃን እንደያዘም ተነግሯል፡፡