Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአፍላቶክሲንን መጠን ለመቀነስ ጥናት ተጀመረ

የአፍላቶክሲንን መጠን ለመቀነስ ጥናት ተጀመረ

ቀን:

በተለያዩ ሰብሎችና ምግቦች ላይ የሚከሰተውን የአፍላቶክሲን ክምችት መቀነስ የሚያስችል ጥናት መጀመሩን የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በወተት፣ በከብቶች መኖ፣ በለውዝ፣ በበቆሎ፣ በማሽላና በሰሊጥ ላይ የተጀመረው ምርምሩ፣ ምርት በማሳ ላይ እያለ በአፍላቶክሲን እንዳይጠቃ ማድረግና ከምርት በኋላ ለውጭ ንግድ የተዘጋጁ ምርቶች ውስጥ የሚገኘውን የአፍላቶክሲን ክምችት መቀነስ የሚያስችል መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የአፍላቶክሲን የሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ብርሁን አዲሴ  (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በወተት ላይ የሚደረገው ምርምር ዚኦላይትና ቤንቶናይትን የተባሉ ማዕድናትን በመጠቀም በአፍላቶክሲን M1 የተበከለን ወተት ማከም፣ የብክለት ደረጃውን መቀነስና እንዲሁም እንዲጠፋ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተሠሩ የምርምር ሥራዎች ትኩረት ያደረጉት አፍላቶክሲን B1 ከእንስሳት መኖ አልፎ ወተት ላይ እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ከመኖ አልፎ በወተት ላይ ቢከሰት እንዴት መቀነስ ይቻላል? የሚለው ምርምር አዲስ እንደሆነ ተቋሙ አመልክቷል፡፡

ሥነ ሕይወታዊ ዘዴን በመጠቀም ሰብሎች ማሳ ላይ እንዳሉ የሚታከሙበትን ምርምር ለመጀመር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰብል ናሙና ተወስዶ በውስጣቸው ያለውን የአፍላቶክሲን ክምችት የሚያሳይ የመነሻ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ዶ/ር ብርሁን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ የሰሊጥ፣ የለውዝ፣ የማሽላና የበቆሎ ናሙናዎች ከየአካባቢው ተወስደው እየታዩ ይገኛሉ፡፡ በለውዝና በበቆሎ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን አምጭ ፈንገሶች ክምችት ታይቷል፡፡ በማሽላም እንዲሁ በአንፃራዊነት ታይቷል፡፡ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን አምጭ ፈንገሶች ክምችት የታየውም በምሥራቅ ሐረርጌ ባቢሌና ጉርሱም አካባቢ የሚመረቱ የለውዝ ምርቶች ላይ ነው፡፡

በአካባቢው የተሰበሰቡት ናሙናዎች መቶ በመቶ የአፍላቶክሲን አምጭ ፈንገሶች ክምችት አለባቸው፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ፓዌ አካባቢ ከተሰበሰቡ ናሙናዎች መካከልም እንዲሁ በ93 በመቶዎቹ ላይ ፈንገሱ ተስተውሏል፡፡ በሥነ ሕይወት ዘዴ አፍላቶክሲን አምጭ ያልሆነ ፈንገስ አምጭ የሆነውን ፈንገስ እንደሚቆጣጠር በማድረግ የምርትን ብክለት ለመቀነስ ያለመው ጥናቱ በሌሎች አገሮች ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ እየተደረገ የሚገኘው ጥናት ባህር ማዶ የተሠራውን ከማስገባት አገር ውስጥ መኖሩን ማረጋገጥና ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

 ‹‹ምክንያቱም በሌላው የዓለም ክፍል ውጤታማ የሆነ ቴክኖሎጂ እዚህ መጥቶ ውጤታማ ላይሆን ይችላል፤›› ብለዋል ዶክተሩ፡፡ ፈንገሶቹ በተለያዩ አካባቢዎች ባህሪያቸው የተለያየና አፍላቶክሲን የማመንጨት አቅማቸው ለየቅል በመሆኑ እንደየአካባቢው ሁኔታ እየተጠና መሠራት ግድ ነውም ብለዋል፡፡

የአፍላቶክሲን ሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ምርምር በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚደገፍ የሦስት ዓመት ፕሮጀክት ነው፡፡

ምርቶች በእርጥበትና በታፈነ ሁኔታ ሲከማቹ አስፓርጊለስ ፍላቨስና አስፐርጊለስ ፓራሲቲከስ ለተባሉ የፈንገስ ዝርያዎች ምቹ መራቢያን ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ፈንገሶች አፍላቶክሲን የተባለውን መርዛማ ውህድ ይፈጥራሉ፡፡

ስድስት ዓይነት የአፍላቶክሲን ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ B1 የተባለው ከፍተኛ የካንሰር አምጭ ውህድ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ አፍላቶክሲን በቆሎ፣ ስንዴ፣ የጥጥ ፍሬና የመሳሰሉት የግብርና ምርቶች በይበልጥ ያጠቃል፡፡ በአፍላቶክሲን B1 የተበከለ መኖ በተመገበ ከብት አካል ውስጥ በሚካሄድ ሜታቦሊዝም ወደ አፍላቶክሲን M1 ይቀየራል፡፡ በዚህም ጊዜ ከከብቱ የሚገኝን የምግብ ተዋጽኦ የተመገቡ አፍላቶክሲን ወደ ሰውነታቸው ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየው የመኖ የጥራት ችግር አሳሳቢ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት እምብዛም በመሆኑ በወተት ላይ የሚታየው የአፍላቶክሲን ክምችት ከዓለም አቀፍ የደረጃ ጣሪያ በላይ እንዲሆን መንገድ ከፍቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...