Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበታሪካዊ ቀናቸው ዕውን የሆነው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኪነ ቅርፅ

በታሪካዊ ቀናቸው ዕውን የሆነው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኪነ ቅርፅ

ቀን:

ከከፍተኛ ራስ ወርቅ እስከ አፍሪካዊ ሐውልት

በመጨረሻም ዕውን ሆነ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) ሐውልት በአፍሪካ ኅብረት ጠቅላይ ጽሕፈት ግቢ ቆመ፤ በታሪካዊቷ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም.፡፡ ተፍጻሜተ ዘውዳዊ መንግሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በንጉሠ ነገሥትነት ከ1923 እስከ 1967 ዓ.ም. በወታደራዊ ደርግ እስከ ተገለበጡ ድረስ ኢትዮጵያን ገዝተዋል፡፡ ከአፄነታቸው በፊት ከ1909 እስከ 1922 ዓ.ም. በባለሙሉ ሥልጣን አልጋ ወራሽነት በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመን የመንግሥተ ኢትዮጵያ መሪ ነበሩ፡፡

ለስድስት አሠርታት ግድም የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሪ የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በ1950ዎቹ አጋማሽ ለተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ለአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት (አኅ) ከወጣኒዎቹ ግንባር ቀደም ሆነው ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት በሠሩት ላቅ ያለ ተግባር በኅልፈተ ሕይወታቸው 45 ዓመታት በኋላ በመናገሻ ከተማቸው የክብራቸው መገለጫ የሆነ ኪነ ቅርፅ (ሐውልት) በዕለተ ሰንበት የአፍሪካ መሪዎችና ንጉሣዊ ቤተሰብ በተገኙበት ተመርቋል፡፡

ከሁለት አሠርታት ግድም በፊት አአድየተካው የአፍሪካ ኅብረት ሃቻምና ባካሄደው 29ኛው የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ በሚገኘው የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት ሐውልታቸው እንዲቆም መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ከዓመታት በፊት የጋናው ፕሬዚዳንት ለነበሩት ክዋሜ ንኩሩማ ብቻ ሐውልት መቆሙ በተለያዩ መልክ ትችት ሲቀርብበት የነበረው ኅብረቱ ለተነሳበት ጥያቄ ዘንድሮ ምላሹን በመስጠት ሐውልቱን ዕውን አድርጓል፡፡

ሦስት ሜትር ርዝመት ያለውን በነሐስ የተበጀው የቀኃሥ ኪነ ቅርፅ የተነደፈውና የተቀረፀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ኪነ ቀራፅያን በቀለ መኰንን፣ መስፍን ተስፋዬና ሔኖክ አዘነ መሆኑ ታውቋል፡፡

    ሐውልቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት፣ በሩዋንዳና ጋና ፕሬዚዳንቶች ፖል ካጋሚ እና ናና አኩፎ አዶ የተመረቀበት የካቲት ወር፣ ከጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ ጋር የሚያስተሳስር ነገር አለው፡፡ ከ102 ዓመታት በፊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ልጅ ኢያሱን ተክተው ቅብዐ መንግሥት ተቀብተው ዘውድ የደፉትና እንደዚሁም ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኰንን ለአልጋ ወራሽነት የሚገባው ሥርዓት ተደርሶላቸው፣ ከፍተኛውን ራስ ወርቅ ያሠሩት የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም. ነበር፡፡

‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት››

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) 1955 .. የአአድ መሥራችና አባቱም የሆኑለት ከድርጅቱ ዋናዎቹ አንቀሳቃሾች አንዱ እንደነበሩ ምስክርነት የሰጠው የጋናው ዘጋኔያን ታይምስ በጁላይ 24 1972 (ሐምሌ 17 ቀን 19614 ..) ዕትሙ ነበር፡፡

የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር ቀኃሥ 80 ዓመታቸውን ባከበሩበት ሐምሌ 16 ቀን 1964 .. (ጁላይ 23 1972) ባወጣው ዕትሙ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› (Haile Selassie I of Ethiopia: Father of The O.A.U.) በሚል ርዕስ ሐተታ አውጥቶ ነበር፡፡

እንደ ሰንዴይ ኦብዘርቨር አገላለጽ፣ ቀኃሥ ስለ አፍሪካ ያላቸው ውጥን እጅግ በጣም የተዋጣና የተቃና መሆኑን ጠቅሶ፣ አዲስ አበባ ‹‹የፓን አፍሪካን መዲና›› (የአፍሪካ አንድነት ከተማ) ለመባል የበቃችበትን ምክንያት አስታውሶ ነበር፡፡

‹‹የዚህ ምክንያት አስቀድሞ የአፍሪካ አገሮች በሞላ የተገኙበትና እንዲሁም ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም ውሳኔ የተላለፈበት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ 1955 .. የተያዘው አዲስ አበባ ላይ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህም በላይ በይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ኢትዮጵያ የእንግሊዝኛን ወይም የፈረንሣይኛን ቋንቋ ዓይነተኛ አድርጋ አለመውሰዷ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ውስጥ እጅግ ረዥም የሆነ የነፃነት ዘመናት ያላት አገር ናት፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት በፊት የአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ውስጥ ተቋቀሞ ነበር፡፡ ዳሩ ግን በራሴ አስተያየት ንጉሠ ነገሥት የመናገሻ ከተማቸው የአፍሪካ አንድነት ከተማ እንድትሆን ባይተጉበት ኖሮ እነዚህ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ምንም ለውጥ ባላስከተሉም ነበር፡፡

‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የአፍሪካ ኃይሎች ራሳቸውን ለመከላከል ይተባበሩ ዘንድ ግርማዊ ጃንሆይ ባላቸው እምነት መሠረት ፈቃዳቸውን ከግቡ ማድረሳቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ በዚህም እምነት መሠረት፣ በየትኛም የአኅጉሩ ክፍል አምባጓሮ ቢነሳ ተገቢው ስምምነት እንዲፈጸም ግርማዊነታቸው ዓይነተኛ መድኅን ሆነዋል፡፡ በዚህም መሠረት የናይጄሪያ ችግር በተፈጠረበት ጊዜ የአስታራቂነት ዕርምጃ የወሰዱ ሲሆን ይህም ፍጻሜ እንዳገኘ በችግሩ ምክንያት አለመግባባት የተፈጠረባቸውን አፍሪካውያን መሪዎችን ፈጥነው ለማስማማት ችለዋል፡፡ ከዚህ በስተቀር ጃንሆይ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ድርጅት ጋር በመተባበር የወጠኑት ከባድ ሥራ 16 ዓመታት የፈጀውን የሱዳንን ችግር በማስወገድ በቅርቡ አንድ ታሪካዊ ስምምነት እንዲፈጸም አስችሏል፡፡

ግርማዊነታቸው ሴኔጋልና ጊኒ አለመግባባታቸውን ለማስወገድ በተስማሙበት ይኸውም በላይቤሪያ ዋና ከተማ በሞንሮቪያ ውስጥ በተደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ሊቀ መንበር ሆነው መርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀደም ሲል ጀምሮ የታሪክ ሥፍራቸውን መያዛቸው ጉልህ ነው፡፡

‹‹በውጩም ዓለም ቢሆን አፍሪካ ግንባራቸው ሳይታጠፍ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከእስያ መሪዎች ጋር ለመቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ መሪዎች ያላት መሆኑን ግርማዊ ጃንሆይ በሚገባ አስመስክረዋል፡፡ ይልቁንም የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መፈጠር፣ ቀደም ብለው እንደነበሩት እንደቸርችል፣ ኔህሩ፣ ቶማስ ጀፈረሰንና እንደሌኒንን ሁሉ የሰውን ልጅ ዕድል ለማሳደግ የረዳ መሆኑ አሁን ጃንሆይን ሊያረካ የሚችል ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ጋዜጦች በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛና ጣሊያንኛ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ ፕሬስ ክፍል 1957 እስከ 1966 .. ይታተም የነበረው መጽሔት የቀኃሥን ተግባሮች መዘከሩ ይታወቃል፡፡ አንዱ የጠቀሰው ለንደን ታይምስ (The Times London) በጁላይ 22 1972 (ሐምሌ 15 ቀን 1965 ..) ዕትሙ፣ ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጽኑ ሥልጣን በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ታፋሪነትን አትርፎላቸዋል›› (Emperor’s firm authority earns respect among the Leaders of Africa) በሚል ርዕስ ሐተታውን አስፍሮ ነበር፡፡

‹‹ኢትዮጵያን ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰውነትና ክብር ጋር የተያያዘ በአፍሪካ ውስጥ ከሁሉም ልቆ የሚገኝ አቋም አላት፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የአፍሪካ መሪዎች ተቀዳሚ መሪ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን ከኢጣሊያውያን ወራሪዎች ነፃ ለማውጣት ያደረጉት ተጋድሎም የዘመናዊቷን አፍሪካ ልደት የሚያበስር ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንድትሆን ተመርጣለች፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኢትዮጵያ ስለአፍሪካ ሕዝብ የፖለቲካ ደኅንነት ላላት ተቆርቋሪነት ጉልህ ምልክት ነው፡፡ ድርጅቱ የተቃቋመውም በድንገት ከተፈጠረ ስሜት አልነበረም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በእርጋታና አንዳንድ ጊዜም በግላቸው የአፍሪካ አገሮች ገና ነፃነታቸውን ሳይጎናጸፉ የወደፊት መሪዎች ለሚሆኑት ሰዎች የትምህርትን ዕድል በመስጠት ረድተዋል፡፡ ግርማዊነታቸው በአፍሪካ አኅጉር ያላቸው ተሰሚነት አገራቸው ከድንበሮቿ ውጭ ካላት ተሰሚነት የተገኘ ሳይሆን ንጉሠ ነገሥቱ ካተረፉት የመከበር ዕድል ነው፡፡

‹‹የብሔራዊና የኢንተርናስዮናል መሪ መሆን ጥቅም ሊኖረው ይችላል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበርነት በየዓመቱ የሚለወጥ ነው፤ ነገር ግን የፈረስ ኮቴ በሚመስለው የጉባዔ ጠረጴዛ አባል አገሮች ሲቀመጡ የኢትዮጵያ ሥፍራ ከጠረጴዛው ጫፍ በመጀመርያ ላይ ሲሆን፤ ንጉሠ ነገሥቱም በጉባዔዎቹ ሁሉ በሰፊው ይሳተፋሉ፡፡ በሰሜንና ደቡብ ሱዳን ግዛቶች መካከል ለብዙ ዓመታት የቆየውን ግጭት ከፍጻሜ ለማድረስ በቅርቡ ለተደረገው የሰላም ንግግር የተመረጠችው አዲስ አበባ ነበረች፡፡

‹‹በአብዛኛው የአፍሪካ ክፍል የጎረቤት አገሮች ግንኙነቶች ውስብስብ ከሆነ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለኡጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛኒያ የጋራ አገልግሎት የሚውለው በእንግሊዝ አስተዳደር የተጀመረው የምሥራቅ አፍሪካ ኮሙዩኒቲ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ ከዚሁ የተለየ ራሱን የቻለ ነው፡፡

‹‹እንደዚሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፖለቲካ የተከፋፈሉ ሁለት ወገኖች ከሆኑት የእንግሊዝኛና የፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች ከቶውንም ወገን ለይታ አባል ሆና ስለማታውቅም ከሌሎቹ የምትለይበት ራሱን የቻለ አቋም አላት፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በማንኛውም አከራካሪ ጉዳይ ገለልተኛነቷን ጠብቃ መሸምገል ትችላለች፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ የሆነበትም ምክንያት የአገሪቱ ከማንኛውም ወገን ነፃ የሆነ ይዞታ ነው፡፡

‹‹ንጉሠ ነገሥቱ በአፍሪካ የፖለቲካ ንቅናቄ ግንባር ቀደም ሆነው እንዳሉ ናቸው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ባለፉት አሥር ዓመታት [1955 እስከ 1965 ..] በሚገባ ከመርዳታቸውም በስተቀር በአፍሪካ የቀረውን የአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ርዝራዥ በተለይም የፖርቱጋልን የአፍሪካ አገሮች ቅኚ ገዥነት በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡

45 ዓመት በፊት ለፊጋሮፓሪስ (Le Figaro-Paris) የተሰኘ የፈረንሣይ ጋዜጣ በፈረንሣይኛ በነሐሴ 1 ቀን 1964 .. (8 Aout, 1972) ዕትሙ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰማንያኛ የልደት በዓላቸውን ያከብራሉ›› (Hailé Sélassié, Vient de fêter ses 80 ans.) በሚለው ርዕሱ መንደርደርያ ያደረገው እንዲህ ነበር፡፡

‹‹ትልቁ አንበሳ ደስ ስላለው አገሳ፡፡ ጠባቂው ልዩ የተቆረጠ ሙዳ ሥጋ በአሉሚኒዬ ሣህን አመጣለት፣ ግርማዊ ጃንሆይ ከዚህ አንድ አንዱን እያነሱ ሰጡት፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀጥለው በእጆቻቸው ጎፈሩን ደባበሱት፡፡ የፊታቸው ገጽ ብሩህ ነው፡፡ አንበሳውን ተናግረውት ድምፃቸውን አሰሙት፡፡ በመጨረሻም ግርማዊነታቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው መለስ ብለው አጭር መሪ ቃል ነገሯቸው፡፡

‹‹ግርማዊ ጃንሆይ፣ እነዚህ አንበሶች በቤተ መንግሥትዎ መዝናኛ አትክልቶች ውስጥ፣ የግርማዊነትዎ በሆኑ ዓርማዎች ውስጥ፣ ለክብር ዘበኞች እንደ መልካም ዕድል፣ ለብሔራዊ የአየር መንገድ ኩባንያ ደግሞ ሕያው ማስታወቂያ እየሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው እንዲህ የሚታዩበት ምሳሌ ትርጉሙ ምንድር ነው? እንደሚያስረዳውም ድል አድራጊ አንበሳ የአገራችን አምሳል የነፃነት ምስያ ነው፡፡››

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...