ወንድማገኝ ገዛኸኝ (ዶ/ር)፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ
በአገሪቱ ከሚገኙ ነባር ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና የጀመረ ተቋም ነው፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የመሐንነት ሕክምና መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ ሆስፒታሉ ሌሎችም አዳዲስ የሕክምና ዘውጎችን በኢትዮጵያ ለማስጀመር እየሠራ ይገኛል፡፡ የሆስፒታሉን እንቅስቃሴና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን የሆስፒታሉን ፕሮቮስት ወንድማገኝ ገዛኸኝን (ዶ/ር) አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ የተመረቀው የመሐንነት ሕክምና መስጫ ማዕከል ሕንፃውን በውድ ዋጋ ከግለሰብ እንደተከራያችሁ፣ ሕክምናው ይጀምራል ከተባለ አምስት ዓመታት ሊሞላው ወራት እንደቀረው፣ ይህንን ሁሉ ጊዜ ግን አገልግሎት መስጠት ሳትጀምሩ ለሕንፃው ኪራይ በሚሊዮኖችን እንደ ዋዛ አውጥታችኋል ይላሉ? ይህንን እንዴት ይመለከታሉ?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- የተከራየነው ሕንፃ ብቻውን ቆሞ አልቀረም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአጥንት ሕክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው፣ ከአንገት በላይ ሕክምና የመሳሰሉትን ስንሠራበት ነበር፡፡ የመሐንነት ሕክምናው በወቅቱ እንዳንጀምር የነበረብን ትልቁ ችግር የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ መሣሪያዎች የገቡልን ጨረታውን ከጨረስን ከዓመት በላይ ቆይቶ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሳየው ግን ከዕቅድ ጋር የተያያዘ ችግርም ነበረበት፡፡ ብዙ ጊዜ ነገሮች ቶሎ ይሳካሉ በሚል እሳቤ ፈጥኖ ወደ ሥራ መግባት እንዲህ ያሉ ግልጽ ስህተቶችን እንድትሠሪ ያደርግሻል፡፡ ከዚህ ባለፈ የመሐንነት ሕክምና የሚሰጥበት ሕንፃ ኪራይ በዓመት ሰባት ሚሊዮን ብር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ጳውሎስ ምን ያህል ቦታዎች ላይ ኪራይ ይከፍላል?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- የእኛ ትልቁ ኪራያችን የአደጋ ጊዜና የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት የምንሰጥበት አቤት ሆስፒታል ነው፡፡ ለአቤት ሆስፒታል በዓመት 18 ሚሊዮን የሕንፃ ኪራይ እንከፍላለን፡፡ ዋናው ነገር ግን ሆስፒታሉ ምን ያህል ሰዎችን ታደገ? የሚለው ነገር ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ከአራት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ አልጋዎች ከ90 አይበልጡም ነበር፡፡ አቤት በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ34 ሺሕ ሕመምተኞችን በላይ ያስተናግዳል፡፡ ከመንገድ ደኅንነት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ወደ 70 በመቶ የሚሆኑትን የድንገተኛ ሕክምናዎች የሚሰጠው በአቤት ነው፡፡ 14 አልጋ ያለው የአይሲዩ ኬር አለው፡፡ ሐኪሞቹም እንደሁ የ24 ሰዓታት አገልግሎት ነው የሚሰጡት፡፡ ዕይታችን ከገንዘቡ ጋር ብቻ ሳይሆን ገንዘቡ ምን አስተዋጽኦ አደረገ የሚለውንም ቢሆን ደስ ይላል፡፡ የአቤትንም ሆነ የመሐንነት ሕክምና ማዕከሉን አገልግሎት በኪራይ ቤት ግን አንቀጥልም፡፡ የኢዲስ አበባ መስተዳደር ከረዥም ጊዜ በኋላ ጉለሌ አካባቢ አሥር ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ሊሰጠን ነው፡፡ እዚያ ገንብተን እንወጣለን፡፡ የመሐንነት ሕክምውን በጳውሎስ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የቤተሰብ ምጣኔ እንዲውል ተደርጎ እየተገነባ በሚገኘው ሕንፃ እንዲዘዋወርም እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- የሰብስፔሻሊቲ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ምን ያህል ሐኪሞች አሏችሁ?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- እኛ ወደ 15 የሚሆኑ የሰብስፔሻሊቲ ሥልጠና ፕሮግራሞች አሉን፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ56 እስከ 60 የሚሆኑ ሰብስፔሻሊስቶችም አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- የሰብ ስፔሻሊቲ ሕክምና አገልግሎቶችን በምን በምን ረገድ ትሰጣላችሁ?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- ከእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ጋር በተያያዘ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች ይበዛሉ፡፡ ከሴቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደ የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ባሉ እስከ አምስት የሚደርሱ የሰብስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ፡፡ በሕፃናት ሕክምናውም እንደዚሁ እስከ ሰባት የሚደርሱ የሰብስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች አሉን፡፡ በራዲዮሎጂ አሜጂንግ ክፍልም ወደ አምስት የሚሆኑ የሰብሽፔሻሊቲ አገልግሎቶች አሉን፡፡ የውስጥ ደዌ ሕክምና ላይም በርከት ያሉ የሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎቶች አሉን፡፡ የሥነ ደዌ፣ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶቻችም ላይ እንደዚሁ፡፡ የሰብስፔሻሊቲ ሕክምና አገልግሎቶችን በዲፓርትመንት ደረጃ ቁጥሩን እያሳደግን ነው፡፡ ምክንያቱም ተርሸሪ የሕክምና ማዕከል እየሆንን በመጣን ቁጥር ሌሎች ተቋማት መስጠት የማይችሉትን አገልግሎት ነው መስጠት የሚጠበቅብን፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ሰዓት በሌሎች የሕክምና ማዕከላት የማይሰጡ በጳውሎስ ብቻ የሚገኙ የሕክምና ዓይነቶችን ምን ምን ናቸው?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- አንድን ተቋም ልዩ የሚያደርገው የተማረ ሰው መያዙ ሳይሆን፣ አገልግሎት መስጠቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው ተምሮ ማገልገል ካልቻለ ስሙን ይይዛል እንጂ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ እኛ ብዙ እየሠራንበት ያለው ከኩላሊት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አገልግሎቶች ላይ ነው፡፡ ይህንን የንቅለ ተከላ ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ የትራንስንፕላንት ሰብስፔሻሊቲ ያላቸው ሒኪሞች የሚሠሩት ነው፡፡ ንቅለ ተከላውን የሚሠሩት ሰርጂኖች ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለውን አገልግሎት ግን የሰብ ስፔሻሊስት ደረጃ ትራንስፕላት ኒውሮሎጂስት የሚሠራ ነው፡፡ ከትራንስፕላንቱ በላይ ሌላ ተለጣፊ የሆኑ አገልግሎቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የፓቶሎጂ አገልግሎታችን ላይ ከዚህ ቀደም ውጭ ልከን ይሠራ የነበረውን የኩላሊት ምርመራ እዚሁ መስጠት ጀምረናል፡፡ ከኩላሊቱ ላይ ናሙና ተወስዶ የበሽታው መንስዔ ምንድነው የሚለው ይለይበታል፡፡ ይህ በራሱ በጣም ውድ ነበር፡፡ ውጭ ልኮ ለማስመርመር ለአንዱ ብቻ ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ያስወጣ ነበር፡፡ ይህንን አቅማችንን በመገንባት አገልግሎቱን እዚሁ መስጠት ጀምረናል፡፡ ትልቁ ችግራችን የሚሆነው ግን አገልግሎቱን ማስቀጠል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አገልግሎቱን ለማስቀጠል የተጋረጠው ችግር ምንድነው?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- በሰብስፔሻሊቲ አገልግሎቶች ላይ እንደ አገር ያለው ትልቁ ችግር የምንጠቀምባቸው ግብዓቶች ምን ያህል አስተማማኝ በሆነ ቀጣይነት ባለው መልኩ ይቀርባሉ የሚለው ነው፡፡ ተገልጋዩስ ከፍሎ ለመጠቀም አቅሙ ይፍቀዳል ወይ? የሚለውም ሌላው ችግር ነው፡፡ በአጠቃላይ በተለያዩ ዘርፎች ማስተማር ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱንም ማስጀመር እንደ ግዴታ ነው የምናየው፡፡ አንድ ሰው ሰብስፔሻሊቲውን ከሠራ በኋላ አገልግሎቱን ለመጀመር ወደኃላ አንልም፡፡ ሐኪሞቻችን ካላቸው አጠቃላይ ሕክምና ዕውቀት በተጨማሪ ደግሞ በሰብስፔሻሊቲ ሙያቸው እያገለገሉ ነው፡፡ በከተማ ደረጃ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ሳይበላሽ የኤምአርአይ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ጳውሎስ ነው፡፡ እዚህ ብቻ የታዩትን ሳይሆን ከየትኛውም ሆስፒታል የሚላኩልንን ሰዎች እንቀበላለን፡፡ ውጤቱን ማንበቡም በዚያው መጠን ጫናው ይጨምራል፡፡ እኛ ምናስነብበው በዚህ ሙያ በሰብስፔሻሊቲ ደረጃ የተማሩትን ነው፡፡ ለምሳሌ ከጭንቅላት ጋር ተያያዥ የሆኑ ኤሜጆችን የሚያነቡት ኒውሮራዲዮሎጂስቶች ናቸው፡፡ ከሆድ ዕቃ ጋር የተያያዙ የኤምአርአይ ይሁን የሲቲ ስካን የተነሱ ኢሜጂንጎችን ሰብስፔሻሊቲያቸውን ቦዲ ላይ የሠሩ ራዲዮሎጂስቶችን ነው እንዲያነቡ የሚደረገው፡፡ ሰብስፔሻሊስቶች ከሌሉን ጄኔራሊስቶቹ ያነቡታል ግን በመሠረታዊ ዕውቀት ላይ የጨመሩት ልዩ ክህሎት ከሌላ የማንበብ አቅማቸው ውስን ይሆናል፡፡ ካለው ጫና አንፃር ሥራ ላይ መንጓተት ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም በቀዶ ሕክምና ብቻ ይሰጡ የነበሩ የሕክምና ሒደቶች ራዲዮሎጂስት ሆነው ኢንተርቬንሽን በተማሩ ሰዎች ድጋፍ እየተደረገ ታማሚዎች በመጠነኛ ዕገዛ ሰላም የሚያገኙበት ያገኛሉ፡፡ ይኼኛው አገልግሎት ከሌሎቹ የመንግሥት የጤና ተቋማት ልዩ ያደርገናል፡፡
በቀን ከ25 እስከ 30 የሚሆን አስከሬን እኛ ጋር እየመጣ ይሠራል፡፡ በዚህ ረገድ በጣም ከፍተኛ ጫና ነው ያለብን፡፡ አንድ ባለሙያ አንድን አስከሬን በትክክል መርምሮ ለመጨረስ በትንሹ ሦስት ቀን ይፈጅበታል፡፡ ምክንያቱም የሕግ ጉዳይ ያለበት ስለሆነ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ወደ እኛ ጋር ሲመጣ ግን ካለው ጫና አንፃር በቀን 25 ያህል ይሠራል፡፡ ያሉን የፎረንሲክ ባለሙያዎች ግን አራት ብቻ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ 12 ስፔሻሊቲ እየተማሩ ያሉ ሐኪሞች ናቸው ያሉን፡፡ ያለውን ፍላጎት ለእያንዳንዱ ብናከፍል አንድ ሰው በቀን አንድ ወይም ሁለት ማየት አለበት ማለት ነው፡፡ አብዛኛውን አስክሬን የሚያመጡት ፖሊሶች ናቸው፡፡ ተቀብረው ለረዥም ጊዜ የቆዩ ሁሉ እየመጡ ይሠራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የሰብስፔሻሊቲ የሕክምና አገልግሎቶችን ለመጀመር የግብዓት አቅርቦትና የታካሚዎች የመክፈል አቅም ውስን መሆን እንቅፋት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ የማይሰጡ ሕክምናዎችን ፍለጋ በየጊዜው በሺዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያወጡ ሲታከሙ ይታያል፡፡ ሁለቱን ማጣጣም እንዴት አልተቻለም?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- ትክክለኛ ችግሩን ልንገርሽ፡፡ አብዛኞቹን የጀመርናቸውን አገልግሎት ማስቀጠል ችለናል፡፡ ችግሩ ሁልጊዜ እሳት እያጠፋሽ፣ የመጨረሻ አማራጭ እያልሽ ነው የምትሠሪው፡፡ ለምሳሌ የልብ ሕክምናችንን ላንሳልሽ፡፡ የልብ ሕክምናችን ላይ የምንጠቀምባቸውን ግብዓቶች በተገዙበት ዋጋ ታካሚዎች ከፍለው ይታከሙ ቢባል ምን ያህሉ ናቸው አቅም ኖሯቸው የሚከፍሉት? አንድ ሰው እኛ ጋር ልቤን አመመኝ ብሎ ለምርመራ ሲመጣ ለአንድ ሰው የሐኪሙንና የማሽኑን ሳይጨምር ብቻ እስከ 40 ሺሕ ብር ይወጣል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በግል ሆስፒታሎች ለተመሳሳይ ሕክምና እስከ 110 ሺሕ ብር ያስከፍላሉ፡፡ እኛ እየጠየቅን ያለነው ለአንድ ሕመምተኛ የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብዓቶችን ዋጋ ክፈሉ ብንል ምን ያህሉ ሰው አቅሙ ይፈቅዳል የሚለውን ነው፡፡ ሁለተኛ ጳውሎስን የመሳሰሉ ተቋማት ግብዓቶች ላይ መሥራት አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ እኛ እንደ ተቋም ማዘጋጀት ያለብን ብቁ የሕክምና ባለሙያ፣ የሚሠሩ ማሽኖች፣ መሥሪያ ቦታና የመሳሰሉትን ነው፡፡ እኛ ከኮንሲውመብል (አላቂ የሕክምና ግብዓቶች) አቅርቦት ጥያቄዎች ባወጣን መጠን የአገልግሎት ጥራታችንን እናሳድጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ መንግሥት ኮንሲውመብሎችን ያቅርብ ነው የሚሉት?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- መንግሥትም ይሁን የግሉ ዘርፍ በበቂ ያቅርብልን፡፡ ነገር ግን የኮንሲውመብል ዋጋው በጣም ውድ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ህንድ ያሉ አገሮች የሚጠቀሟቸው በጣም ርከሽ የሆኑ ኮንሲውመብሎችን ነው፡፡ እነሱ ሚጠቀሙት እኛ ጋር ቢመጡ ግን የዋጋቸውን አምስት ስድስት ዕጥፍ ሆነው ነው የሚሸጡልን፡፡
ሪፖርተር፡- እናንተ ከማነው እየገዛችሁ የምትጠቀሙት?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- ጨረታ አውጥተን ከቬንደሮች ነው የምንገዛው፡፡ እንደ አገር ትልቁ ችግራችን አቅማችን ውስን መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የዲያሌሲስ አገልግሎታችንን ብታይው ኢትዮጵያ በዓመት ከ50 ሺሕ በላይ የምትሠራ አይመስለኝም፡፡ ግብፅ ግን ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ትሠራለች፡፡ ብዙ በተሠራ ቁጥር ዋጋውም በመቀነስ በብዛት ማትረፍ ይቻላል፡፡ አንደኛው የእኛ ችግር የምንሰጠው አገልግሎት ውስን ነው፡፡ ለምሳሌ ከአገር ውስጥ ከሚገኙ የተሻለ የሚባል ጴጥሮስ የሚገኝ ካትለብ (ዘመናዊ የልብ ሕክምና ላቦራቶሪ) አለ፡፡ ባለን አቅም በዓመት እስከ 2,000 መሥራት አለብን፡፡ ነገር ግን በዓመት ከ300 በላይ አንሠራም፡፡ የሚያስፈልጉንን ኮንሲውመበልስ የሚቀርቡልን አካላት ትርፋቸው በምንሠጠው ውስን የአገልግሎት መጠን ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ጳውሎስ ያሉ ተቋማት ፕሮግራሞቻቸውን ለማስቀጠል በጣም ይቸገራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- መፍትሔ የሚሉት ነገር ምንድነው?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- እንደ ተቋም ለብቻችን ቀርበን ግዥ ከመፈጽም በመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ በኩል ሁሉም ተቋማት አንድ ላይ ሆነን ጨረታ በማውጣት ዋጋውን ማውረድ እንችላለን፡፡ በዚህ የኮንሲውመብል ዋጋን ልንቆጣጠር እንችላለን፡፡ ነገር ግን እንደዚያውም ሆኖ እንደ አገር ያለን አቅም በጣም ውስን ስለሆነ ዋጋው በተወሰነ መጠን ነው ሊቀንስልን የሚችለው፡፡ ውድ ከመሆኑ አንፃር ገበያ ላይ የሚቀርብበትን ዋጋ በጋራ በመሆን መቆጣጠር የምንችልበት ዕድል ቢኖርም፣ ቅናሽ የሚባለውን ገንዘብ ከፍሎ የመታከም አቅም ያላቸውም ውስን ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጴጥሮስ የሚገኘው ካትላባችን አገልግሎት የሚሰጠው በነፃ ነው፡፡ ምክንያቱም ኮንሲውመብሉ የተገዛበትንም ዋጋ ብቻ እንዲከፍሉ እያደረግን አገልግሎት እንስጥ ብንል እንኳን መክፈል የሚችሉት 20 በመቶ አይሆኑም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ድጎማ እያደረገበት ነው የምንሰጠው፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት አገልግሎቶች ዋጋቸው ከፍተኛ ስለሆነ መንግሥት ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡ ገንዘብ ይመጣሉ እንጂ ማምጣት አይችሉም፡፡ እንደ እኔ እንደ ጳውሎስ ያሉ ተቋማት የአገልግሎት አቅርቦትና ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ፣ አቅርቦት ላይ ደግሞ መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ገፍቶ እንዲገባ በማድረግ መሥራት ቢቻል አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት ማቅረብ ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ከሁለት ዓመት በኋላ ጳውሎስ የጉበት ንቅለ ተከላ ሕክምና ይጀምራል የሚል መረጃ ደርሶናል፡፡ ሕክምናውን ለመጀመር ምን ያህል ርቀት ሄዳችኋል? እስካሁን በሆስፒታሉ ያለው አጠቃላይ የጉበት ሕክምና ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- የጉበት ንቅለ ተከላ ሕክምና ከኩላሊት ንቅለ ተከላ በጣም የተለየ ነው፡፡ እንደ ኩላሊቱ ቀላል አይሆንም፡፡ ከንቅለ ተከላው በኋላ ግን በታካሚዎቹ ሕይወት ላይ የሚኖረው ለውጥ በጣም የተለየ ነው፡፡ በዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ሕክምናውን መስጠት የሚችሉ ሁለት ሰዎች እያሠለጠንን ነው፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ሰዎች እንዲቀላቀሉም እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ከጉበት ንቅለ ተከላ በፊት የሚሠሩ ቅደም ተከተሎች አሉ፡፡ እነሱን መሥራት ጀምረናል፡፡ ይህም የታመመውን የጉበቱን ክፍል ቆርጦ የማውጣት ሕክምና ሲሆን፣ አገልግሎቱንም በቅርቡ መስጠት ጀምረናል፡፡ ከጉበት ንቅለ ተከላ ጋር በተያያዘ ትልቁ ፈተና የሚሆነው በቀዶ ሕክምና ጊዜ የሚያስፈልጉ ኮንሲውመብሎች አቅርቦት ነው፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላን ከዚህ ለየት የሚያደርገው ቀዶ ሕክምናው በአንፃራዊ ሲታይ ቀላል መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ዕድሜ ልካቸውን የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ከፍተኛ መሆን፣ ደከም ሲሉ ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚሠራላቸው የኩላሊት እጥበት አጠቃላይ ዋጋውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ የተቀየረው ኩላሊት ከአሥርና ከ15 ዓመታት በላይ አይቆይም፡፡ እንደገና ንቅለ ተከላ ያስፈልገዋል፡፡ የጉበት ንቅለ ተከላ ሕክምና ሒደት ግን ከባድ ነው፡፡ የአንድ ሰው ከሰባት እስከ አሥር ሰዓታት ይፈጃል፡፡ በቀዶ ሕክምና ሒደቱም በጣም ውድ ኮንሲውመብሎች ይፈልጋል፡፡ ለአንድ የጉበት ንቅለ ተከላ በአማካይ እስከ 7,000 ዶላር የሚፈጁ ኮንሲውመብሎች ያስፈልጋሉ፡፡ ንቅለ ተከላው ከተደረገ በኋላ የሚኖራቸው ሕይወት ግን የተለየ ነው፡፡ በጣም ጥቂት መድኃኒት ነው የሚወስዱት፡፡ እንደ አገር የሚያሳስበው ነገር ከአልኮል ጋር በተያያዘ፣ ካሉት በሽታዎች አንፃር በሕክምና መዳን የሚችሉ ብዙዎች ይሞታሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች አጢነን ነው ሕክምናውን ለመጀመር ያሰብነው፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ድጋፍ ይጠይቃል፡፡
ሪፖርተር፡- ጉበትን ከጥቅም ውጪ የሚያደርገው የሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ሥርጭት በአገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የመድኃኒቱ አቅርቦቱ ዜሮ ነው ማለት በሚያስችል መጠን ችግር ነው፡፡ ካለው የአቅርቦት ችግር አንፃር ሂፒታይተስ ቢ ያለባቸው ፀረ ኤችአይቪ እንዲወስዱ ሁሉ ይደረጋል፡፡ ይህንንም ማግኘት የሚችሉት ከስንት አንድ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ እጅግ ውድ የሚባለውን የጉበት ንቅለ ተከላ ሕክምና እንጀምራለን ትላላችሁ፡፡ ዕቅዱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ነው ወይ?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- እንደ ተቋም የምናምንበት ነገር አለ፡፡ ሆስፒታሉ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ነው በፍጥነት የተቀየረው፡፡ በተገኘው በአጋጣሚ የራሳችንን ባለሙያዎች ማፍራት ካልቻልን እንደ አገር ከአቅም በላይ ይሆናል፡፡ ሕዝባችን ወደ ውጭ እየሄደ እየታከመ፣ ወይም አቅሙ ያለው እየታከመ የሌለው እየሞተ መቀጠል ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በቻልን መጠን ማስታገስ አለብን፡፡ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያው የመሐንነት ሕክምና ማዕከሉ ነው፡፡ አንድ ሰው ልጅ የመውለድ መብት አለው፡፡ አቅሙ ያለው ገንዘብ አውጥቶ ውጭ ሄዶ እየታከመ ሲወልድ፣ አቅም የሌለው ደግሞ ጎረቤቱ አራት አምስት ልጅ ሲወለድ እያየ ዝም ብሎ የሚኖርበት አገር መሆን የለበትም፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ሁሉ እንፈታለን ብለን አይደለም ፕሮግራሙን የጀመርነው፡፡ ቢያንስ ግን ተስፋ መኖር አለበት፡፡ አንድ ቦታ ካልተጀመረ ሌሎች ቦታዎች ላይ የመጀመር ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አዳዲስ ሕክምናዎችን እንጀምራለን፣ ከዚያ ሌሎች ይከተላሉ፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላውን ብንመለከት ጳውሎስ ብቻውን አይችልም፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ መሰጠት አለበት፡፡ ነገር ግን መጀመርያ እንደሚቻል ማየት አለባቸው፡፡ ምንሠራው የማደፋፈር ተስፋ የመስጠት ሥራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ያህል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ተሠርቷል? ካለው ፍላጎት አንፃርስ ምን ያህል መሥራት ተችሏል?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡– እስካሁን 170 ንቅለ ተከላ ተሠርቷል፡፡ ቀጣይነት ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ችግር አለ፡፡ በተለይ አንድ ጊዜ ሕክምናውን ከወሰዱ በኋላ መቋረጥ የሌለባቸው መድኃኒቶች አሉ፡፡ ከ300 በላይ የሚሆኑ በህንድ አገር የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና የተሠራላቸው ሰዎች ክትትል የሚያደርጉት እኛ ጋር ነው፡፡ አንዴ ሠርተሽ የምትገላገይው ነገር አይደለም፡፡ በየጊዜው እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ እንደ ተቋም ተነሳሽነቱን ወስደሽ ትጀምሪያለች፡፡ ከዚያ ሌሎች ይከተላሉ፡፡ ተቋማት ራሳቸውን እያበቁ ተደጋግፈን መሥራት አለብን፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በዘመቻ መልክ የሚሠራውን ትተን በየሳምንቱ እየሠራን ብዙዎን የመድረስ አቅም እንገነባለን፡፡ ነገር ግን እንዲያም ሆኖ አስቸጋሪ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ያለው የበሽታ ጫና ከፍተኛ ሆኖ ሳለ የሐኪሞች ቁጥር ግን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታየው የሥራ ጫና ምን ይመስላል?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- እንደ ተቋም ጳውሎስ በጣም ትንሽ ሐኪም ነው ያለኝ ብሎ ቅሬታ አያሰማም፡፡ በአንዳንድ ስፔሻሊቲ አገልግሎት ላይ ያለውም ችግር እንደ አገር ነው፡፡ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንደ ተቋም በተለያዩ ዲፓርትመንቶች ላይ በቂ ቁጥር ያላቸው ሐኪሞች አሉ፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከመቶ አራት ሺሕ በላይ ሕመምተኞችን አስተናግደናል፡፡ ነገር ግን ትልቁ የእኛ ችግር አሁን ያለው የሕዝቡ የሕክምና ፍላጎት በጄኔራል ፕራክቲሽነር የሚመለስ አይደለም፡፡ ትልቁ ፈተናም የስፔሻሊስቶችን ቁጥር መጨመር ነው፡፡ የስፔሻሊቶችን ቁጥር በተለይ በተሪሸሪ ሆስፒታሎች ላይ መጨመር አለብን፡፡ ግን ሌላው ትልቁ ጉዳይ ያለውስ ሐኪም ምን ያህል ተነሳሽነት ኖሮት እየሠራ ነው የሚለው ነው፡፡ አንድ ሕመምተኛ ከተለያዩ ሆስፒታሎች በሪፈር ወደ እኛ ሲመጣ ሊያየው የሚገባ ልምድ ያለው ሐኪም ነው፣ ነገር ግን እኛ ይህንን እያደረግን አይደለም፡፡ የትኛውም ቦታ ብትሄጂ ይኼ ነው እየሆነ ያለው፡፡ አንደኛ የሐኪሞቻችንን ፍላጎቶች እያሟላን ነው ወይ? የሚደርስባቸው ወቀሳስ ትክክል ነው ወይ? የሚለውን ማየት አለብን፡፡ ለምሳሌ አንድ ሐኪም ስፔሻላይዝድ ባደረገበት የሕክምና ቦታ በሦስትና አራት ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 40 ሕመምተኛ ያያል፡፡ ለአንዳንዱ ታካሚ ሰላምታ ላይሰጥ ሁሉ ይችላል፡፡ ይህንንም እያደረገ የሚሰጠው ድጋፍ ምን ያህል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ በተለይ ከደመወዝ አንፃር ብዙ ቅሬታዎች ይሰማሉ?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- የደመወዝ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እንደ ጳውሎስ ባሉ ተቋማት የሥራ ከባቢን ከማሻሻል አንፃር ብዙ ማስተካከል አለብን የምንላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ሐኪሞቹ መሥራት ብቻ ሳይሆን የሚያርፉበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዋርድ ውስጥ ተሰብስበው የሚወያዩበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያንን ግን እያደረግን አይደለም፡፡ ይህንን እንደ ተቋም ማሻሻል አለብን፡፡ ምክንያቱም ሐኪሞቻችን ሁሉ የሚጠይቁን ብር ሳይሆን መሟላት ያለባቸውን መሠረታዊ ነገሮችን ነው፡፡ የሚሠሩባቸው መሣሪያዎችስ በትክክል ተሟልቶላቸዋል ወይ የሚለው ጉዳይ ሌላው ነው፡፡ ሐኪም ስሙን ሳይሆን መሥራት ይፈልጋል፡፡ ብዙ ሆስፒታሎች ላይ ሄደሽ ብታይ ሰብስፔሻሊቲ ያላቸው ሰዎች እየሠሩ አለመሆኑን ትመለከቻለሽ፡፡ ምክንያቱም ዕቃ አልተሟላላቸውም ወይም ተበላሽተው ቆመዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታም ቢሆን በጳውሎስ አምስት በሚሆኑ ዲፓርትመንቶች አዳር የሚሠሩት ልምድ ያላቸው ሐኪሞች እንጂ ተማሪዎች አይደሉም፡፡ ይህንን ሁሉ እያደረጉ ሥርዓቱ ግን ድጋፍ አያደርግላቸውም፡፡ ማስተዋል ያለብን የሐኪሞችን ቁጥር ሳይሆን ያሉንን ምን ያህል እየተጠቀምናቸው ነው የሚለውን ነው፡፡ የጤና አገልግሎት ላይ ማንም ልብ የማይለው ትልቁ ኃይላችን ለሆኑት ለነርሶችስ ምን እያደረግንላቸው ነው፡፡ ምሳሌ ልስጥሽ አንድ ጳውሎስ ውስጥ የሚሠራ ነርስ ደመወዙ 3,000 ወይም 3,400 የሆነ፣ የቡራዩ ተከራይቶ የሚኖር አለ፡፡ የቤት ኪራይ ምን ያህል ውድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነኚህ ሰዎች ምን በልተው እንደሚኖሩ የትስ እንደሚያድሩ አይታወቅም፡፡ የጤናው ዘርፉ ግን ይህንን ሁሉ አካቶ የሚይዝ የሰው ኃይል ነው የሚፈልገው፡፡ አንዳንድ በጣም ወሳኝ በሆኑ ቦታዎች በአይሲዩ ትልቁን ሥራ የሚሠሩት ነርሶች ናቸው፡፡ ሐኪሞቹ የሚመጡት በኋላ ነው፡፡ የአንድ አይሲዩ ዋና ስኬት ነርሶቹ ናቸው፡፡ እኛ ግን የሰው ኃይላችንን በምን ያህል ደረጃ እየደገፍነው ነው? የሚለው እንደ አገር ያሳስበኛል፡፡ ቁጥር ላይ ትኩረት አድርገን ስንሠራ ትልቁን ጉዳይ እንስታለን፡፡ የሆነ ጊዜ አንድ ሐኪም ለአምስት ሺሕ ሰው ሬሾ ላይ እንዲደርስና ግን ምንም የማይሠራ የሰው ኃይል ይኖረናል፡፡ እኔ የሚያሳስበኝ ይኼ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ወሳኝ የሚባሉ መሣሪያዎች አቅርቦትና ወቅቱን የጠበቀ የጥገና አገልግሎትን በተመለከተ ያለውስ ችግር ምን ይመስላል?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡– የብዙዎቹ ዋና ዋና መሣሪያዎች የጥገና አገልግሎት ውል አለን፡፡ ሲቲ ስካናችንን፣ ኤምአርአያችንን ከገዛነው ኩባንያ ጋር የጥገና ውል አለን፡፡ ኤምአርአያችን ሦስስ ዓመት ያህል ተበላሽቶ አያውቅም፡፡ ቢበላሽም ለአንድና ሁለት ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም ወዲያው መጠገን ስላለበት ይጠገናል፡፡ ጥገና በጣም ውድ ነው፡፡፡ ዕቃውን መግዛት ብቻ ሳይሆን ጥገናውም መታሰብ አለበት፡፡ አንድ የመሣሪያ ካፒታል ኢንቨስትመንት ሲኖር በየዓመቱ ለጥገና መታሰብ አለበት፡፡ መሣሪያው የተገዛበትን እስከ ሰባት በመቶ ለጥገና በየዓመቱ ወጪ መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ በአንድ ሚሊዮን ብር ለተገዛ መሣሪያ በየዓመቱ ለጥገና እስከ 70 ሺሕ ብር ወጪ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ይህ በተቋም ደረጃ ስንቶቻችን አቅደን እንሠራለን? ታቅዶስ አስፈላጊውን ድጋፍ ስንቶቻችን እናገኛለን? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ተቋማት መሣሪያዎቻቸው ማሽኖቻቸው ተበላሽተው ቆመው ሲቸግሩ ይታያል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በጤና ሚኒስቴር ደረጃ በጉዳዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በጳውሎስም በጥገና ፕላን ውስጥ ያካተትናቸው አብዛኞቹ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ብልሽት እንደገጠመው ወዲያው እንነግራቸዋለን፡፡ ለምሳሌ ሲቲ ስካኑ በተበላሸ በአሥረኛው ቀን መጥተው ካልጠገኑት ጳውሎስ ውስጥ ታካሚ ለሆኑ ሲቲ ስካን ለታዘዘላቸው ሕምተኞች መጥተው ከፍለው ሲቲ ስካን ያስነሱላቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የማሽኖች ጥገና ጉዳይ በአገር ውስጥ ባለሙያ ለማከናወን ምን እየተሠራ ነው? ምክንያቱም ሰዎች ተገቢውን ሥልጠና ወስደው ቢሰማሩ ለዜጎች የሥራ ዕድልም ከመፍጠር አኳያ መታየትስ የለበትም ወይ?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- እንደ ተቋም የጥገና ሥራ የሚሠራባቸው ባዮ ሜዲካል ላብራቶሪ አለን፡፡ ነገር ግን በጣም ውስብስብና ውድ የሆኑ ማሽኖችን እዚሁ ለመጠገን ኩባንያዎቹ ራሳቸው አይፈቅዱም፡፡ ይህንን የመብታቸውም አካል ያደርጉታል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ኩባንያዎች ትርፋቸው ማሽኑን ሲሸጡ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ባለው ሒደት የሚገኘው ጥቅም ነው፡፡ መለዋወጫ ዕቃዎችን በማምረት፣ የጥገና ሥራ በመሥራት ነው ገንዘብ የሚያተርፉት፡፡ ነገር ግን የአንዳንድ ማሽኖችን ጥገና በተመለከተ የእኛ አገር ዜጎች ሌቭል አንድና ሌቭል ሁለት ሥልጠና ወስደው መሥራት እንዲችሉ እየጠየቅን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ ለምን ያህል ዜጎች ተደራሽ ነው?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- ቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል አንድ ብቻ አይደለም፡፡ ከዋናው የሕክምና ማዕከል ውጪ አቤት የሚባል 250 አልጋዎች ያሉት የትራውማ ሕክምና ማዕከል አለ፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ውስጥም ደግሞ በጳውሎስ ሥር የሚገኝ የልብ ማዕከል አለ፡፡ 22 አዲስ ሕይወት ሆስፒታል ጎን ደግሞ የመሐንነት ሕክምና የሚሰጠውም አዲሱ የሕክምና ፕሮጀክት በጳውሎስ ሥር ነው የሚገኘው፡፡ ከዚህ 83 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው 500 አልጋዎች ያሉት ወራቤ ሆስፒታልም በቅዱስ ጳውሎስ ሥር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም በተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎችን እየመደብን ሙያዊ ድጋፍ የምናደርግበት አሠራር አለን፡፡ በተለይም ከእናቶች ጤና ጋር በተያያዘ በደንብ እንሠራለን፡፡ ከጤና ጣቢያዎች ጀምሮ እስከ ስድስት ከሚሆኑ ሆስፒታሎች ጋር አብረን እንሠራልን፡፡ የጨቅላ ሕፃናት የሕክምና አገልግሎትን ጨምሮ የእናቶች ጤና ላይ የሚሠሩ ሐኪሞችን በየተቋሙ እየላክን እንዲያገለግሉ እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ በየአቅጣቸው ተሰማርቶ አገልግሎት የሚሰጥ ሰፊ ተደራሽነት ያለው ተቋም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ወራቤ ሆስፒታል ቅዱስ ጳውሎስ ድጋፍ ያደርግለታል ወይስ ሙሉ ለሙሉ በሥሩ የሚገኝ ተቋም ነው?
ዶ/ር ወንድማገኝ፡- ወራቤ በእኛ ሥር ያለ ሆስፒታል ነው፡፡ ፋይናንስ የምናደርገውም እኛ ነን፡፡ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔላዝድ ሆስፒታል ነው፡፡ ከሰከንደሪ እስከ ተሪሸሪ ሌቨል ያሉ ሕክምናዎችን ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚሰጥ ትልቅ ማዕከል ነው፡፡