Friday, January 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአገር አቀፍ ችግርን ለማስወገድ መፍትሔው ምን ይሆን?

አገር አቀፍ ችግርን ለማስወገድ መፍትሔው ምን ይሆን?

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ                  

አንድ አገር ሊቸገር የሚችለው ዘርቶ ማፍራት ሳይችል፣ የውኃ እጥረት ሲኖርበት፣ የሠራተኛ ጉልበት ሲታጣ፣ ወጣቱ በጦርነት ወይም በተውሳክ ሲያልቅ ያኔ አዛውንቱ መሥራት ያቅተውና አገር ወገን ችግር ላይ ይወድቃል። ሌላው ደግሞ ለራሱ ብቻ የሚያስብ፣ ስለሕዝቡ እምብዛም ግድ የለሽ አመራርና ጭፍሮቹ በሚፈጽሙት ሰብዓዊነት በጎደለ ሁኔታ ሕዝቡ ሲሰቃይ አገሩን፣ ወንዙን፣ ተራራውንና ሸንተረሩን፣ ዘመድ አዝማዱን ጥሎ በመኮብለል ችግር ይፈጠራል። የኢትዮጵያ መሬት 60 በመቶ ለእርሻ ተስማሚ ነው፡፡ ወጣት የሚሠራውን አጥቶ የቻለው ባገኛት አናሳ ሶልዲ በየመጠጥ ቤቱ ሲያሟሙቅና የኮማሪት አጫዋች ፈዜኛ ሆኖ በከንቱ ጊዜውን ሲያባክን፣ ሌላው የሚቀምሰውና የሚልሰው አጥቶ ፍርፋሪ ከተጣለበት ለቃቅሞ ሆዱን ለመሙላት በየቆሻሻው መጣያ ሲባዝን እያየን፣ ምን ዓይነት ልቦና ኖሮን ነው አለን ብለን ራሳችንን እንደነዋሪ ቆጥረን የምንዝናናው? ያሳዝናል፡፡

ወጣት ሴት ልጅ ታቅፋ ወይም አዝላ፣ ወጣት ልጆች አባባ ራበኝ እያሉ ሳንቲም ሲለምኑ፣ አገሩን በሚችለው አገልግሎ ኑሮ መጦር ሲገባው መጦሪያ አጥቶ በየጎዳናው ሲለምን ማየት ዜጋ መሆን ቀርቶ የሰው ፍጡር በመሆናችን ብቻ አናፍር ይሆን? ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በእርሻ ኢኮኖሚ፣ በእርሻ ምሕንድስና፣ በዕፅዋት፣ በእንሰሳትና በደን ልማት የተራቀቁ (በቃላት ማለቴ ነው) ሞልተው ተርፈው ሳለ፣ ኢትዮጵያ ከዕለት ወደ ዕለት የልመና ኮረጆ ተሸክማ ስትዞር ተማርን ባዮችም ይህችኑ ደሃ አገር አሟጥጠው በገንዘቧ ከተማሩ በኋላ አንዳች ነገር ፈጥረው ሊረዷት ሳይበቁ በየሰው አገር ሄደው በማገልገል የራሳቸውን ኑሮ ብቻ በማደላደል ይገኛሉ፡፡ ያገኟትንም ይዘው መጥተው ባገኙት ልምድና ዕውቀት እንዴት እንርዳት ሳይሆን፣ አሁን የግል ኑሯችንን እንዴት የተደላደለ እናድርግ በማለት ይሯሯጧሉ።

ታዲያ ይህ ነው ትምህርት? በሌላ በኩል አስቸጋሪ የመንግሥት አካላት የሆኑ ባለሥልጣናት ስለወገንና ስለአገር ፍፁም የማያስቡ፣ የራሳቸውን ሥልጣን ለማጠናከርና ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ እንዳሉ እጅ ከፍንጅ ለማጋለጥ ይቻላል። እስቲ መረጃ አምጣ የሚለኝ ባለሥልጣን ደፍሮ በሕግም ይሁን በፈለገው ቀርቦ ያነጋግረኝ በቂ ማስረጃ ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ። ኢትዮጵያ ከቶውኑ ልትቸገር አይገባትም! ላስረዳ፡፡ የዓረብ አገሮች በቅርባችን በዘይት ሀብት በልፅገውና ተንደላቀው ይኖራሉ፡፡ ለምግብ ስንዴ፣ ሩዝ፣  በቆሎ፣ ቦለቄ፣ ማሽላ፣ ለቅባት እህል ሰሊጥ፣ ኑግና የመሳሰሉትን፣ ቡናና የሻይ ቅጠል፣ ሥጋ፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ እንዲያው ስንቱን ላውራ? ዝንጅብሉን፣ ኮሮሪማውንና የቅመማ ቅመም፣ የጎጃሙ ማር፣ የሲዳማው ገተሜ ማር፣ የአርሲ፣ የባሌ፣ የካፋ ወፍ ዘራሽ ቡና የሚለቀምባቸው የተፈጥሮ ስጦታን መጠቀም ያለመቻላችን ለምን ይሆን? አትክልትና ፍራፍሬ ሌሎችም ሞልተው ተርፈው ሳለ ለምን ተቸገርን?

ገበያ አጣን እንዳንል ከላይ የጠቀስኳቸው በትክክል መደቡን ጠብቀን ካቀረብን ከማንም የተሻለ የእኛን እንደሚፈቅዱ አረጋግጬ መናገር እችላለሁ፡፡ የእኛ ያለመዘጋጀትና ለሕዝቡ ሁሉ ቁም ነገር ባለመስጠት ችግረኞች የተባልነውን በአዎንታነት ተቀብለን እየኖርን ነው። በቃ ብለን እንነሳ፣ ተባብረን እንሥራ፣ የዓለም መሳቂያ አንሁን፡፡ የተፈጥሮ ፀጋና የተማረ ባይኖረን ምድረ በዳ ላይ ያለን ብንሆን ይገባኛል።                                                                          

የዓረብ አገሮችን ያነሳሁበት ዋናው ምክንያት አንደኛ በቅርበታችን፣ ሁለተኛ በሰው ሠራሽ ሁኔታ የተዛባ ሰውነት መጠን የማይቀይር የተፈጥሮ ፀጋን የተመላ ጥራጥሬና ሰብል ልናቀርብ እንደምንችል በማመን ሲሆን፣ በታዘዘ በ24 ሰዓታት ውስጥ ለማቅረብ የሚያስችለን የቅርበትና የአየር ሁኔታ ስለሚፈቅድልን ነው፡፡ ሁለተኛ በቅርበቱ ምክንያት ዋጋችን ተመጣጣኝ ሊሆን ስለሚችል፣ ሦስተኛ በባህልም ሆነ በሃይማኖት እምብዛም ስለማንለያይና በታሪክ ሰንሰለትም የተሳሰርን በመሆናችን ነው፡፡ ገንዘቡ ዓረቦች ዘንድ ሰብሉ እኛ ዘንድ ሆኖ ከአውሮፓና ከአሜሪካ በአሥር ሺሕ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ከሚያጓጉዙ የእኛ በቅርበትም በትኩስነትም (ፍሬሽ) የሚሻል በመሆኑ ተመራጭነት ስላለው ነው።

የዓረብ አሮችን ጠቀስኩ እንጂ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ እስከ 1970ዎቹ መጀመርያ ድረስ የአበባ ጎመን፣ ሰላጣና ቲማቲም፣ የፈረንጅ ቃሪያ የሚባለውን ለፈረንሣይ ማርሴል፣ ለእንግሊዝ አገር ኮቬንት ጋርደን ማርኬት ድረስ ስናቀብል የተቀባዮቹን ደስታ ለመግለጽ ያስቸግራል። ዶሮና እንቁላል ለሳዑዲ ዓረቢያ፣ ለኳታር፣ ለኤምሬትስ፣ ለባህሬን፣ ጂቡቲንና የመንን ጨምሮ እናንበሸብሽ ነበር። ታዲያ ዛሬ ምን ተፈጥሮ ነው ለራሳችን እንኳ ያልበቃነው? የመንግሥት ምክንያት የሚሆነው ያኔ የሕዝባችን ቁጠር አናሳ ነበር ይሆናል። ይኼንን አልቀበልም።

ሌላው ቀርቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ብቻ ስድስት መቶ ሺሕ ሊትር ወተት ሲያስፈልግ እኛ ማግኘት የምንችለው በውኃ የተበረዘ ከስልሳ ሺሕ ሊትር የማይበልጥ ነው። ለምን? መሬት አጥተን? ውኃ ጠፍቶ? ጨርሶ ድርቅ መቶን? ወይስ አዋቂ በየሙያው ጠፍቶ? የጉልበት ሠራተኛ ጠፍቶ? ወይስ ማስተዋል አቅቶን ይሆን?                                     ራሳችንን መርዳት ያልቻልን እንዴት ወደ ሌላ አገር ለመላክ እንችላለን? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ትክክል ነው። የቡና የመጀመርያዋ አብቃይ አገር ቁጭ ብላ እነ ኮሎምቢያ ታዋቂ ሲሆኑ፣ ዛሬ ቬትናም ከሁሉም በኋላ ተነስታ በአንደኝነት ስትገሰግስ፣ እኛ የት ነን? ጤፍ ዛሬ እግር እያወጣና የቡናን ምሳሌ ለመከተል በመሽቀዳደም ላይ ነው፡፡ እንዴት ሁሌ የበይ ተመልካች ሆነን እንቀራለን?

ምሁራን  ወገኖቼ ዶላር ጠፋ፣ ምንዛሪ አሻቀበ፣ ሰማይ ምድር ላይ የተደፋ ይመስል በየሬዲዮና ጋዜጣ መለፈፉ ችግራችንን ሊያቃልል አይችልም። በእንስሳት ሀብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አምስተኛ ሆነን ሥጋ ከውጭ በምንዛሪ ስናስገባ፣ የዱቄት ወተት ዓይናችን እያየ የውጭ ምንዛሪ ሲከፈልበት አናፍርም? ታዲያ ምንዛሪ ጠፋ አሻቀበ እያልን የምንወተውተው ለምን ይሆን? ለይስሙላ ወይስ ለማስመሰል? የእኛ የከብት ሥጋ እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓረቦች ተሽቀዳድመው ነበር የሚገዙት፡፡ ዛሬ ግን ዘመን ተለውጦ በሀብት ቀድመውን ሄዱና የእኛን ከብት ሥጋ ለታችኛው ድሃው የኅብረተሰብ ክፍል ካልሆነ አይበሉትም፡፡ ለምን ብለን ብንጠይቅ የእኛ አያያዛችን ተፈጥሮአዊ በመሆኑና ሥጋው ጠንካራ ነው ስለሚሉ ነው።

ታዲያ ይኼንን አሻሽለን የዓለምን ገበያ ለመወዳደር ምን የሚከለክለን ነገር አለ? የመንግሥታችን ስንፍና የሚሠራውን ከማበረታታት ይልቅ፣ እንዳይሠራ ብዙ እንቅፋት ስለሚሆን ነው። ይኼንን ለማስረዳት ማንም ኃላፊ ነኝ የሚል በሕግና በአግባቡ መረዳት የሚፈልግ ካለ በደስታ ለማወያየት ዝግጁ ነኝ። ሰሊጣችን በዓለም ተፈላጊ ሆኖ ምርቱ ግን የለንም፡፡ ለምን? ከላይ እንደጠቀስኩት መሬት፣ ውኃ፣ ሠራተኛ ወይስ በመስኩ የተሰማራ ባለሙያ ጠፍቶ? ይኼንን መመለስ የሚችል በመስኩ አግባብ ያለው የመንግሥት ተጠሪ መሆን አለበት።

ያለንን የተፈጥሮ ሀብት ሳንጠቀም ለመመካከርና ለመወያየት ጊዜ ሳይሰጠን፣ ስለችግር ብቻ ማውራት የጋዜጦችን ዓምድና የቴሌቪዥን አየር ሰዓት ከማጣበብ የዘለለ ምንም ሊቀይር አይችልም፡፡ በቢሮ ውስጥ ተቀምጦ ከማውራት ይልቅ አገራችንን እንዴት ነው የምናሻሽለው የሚል ጥያቄ የየክፍሉን መሪዎች መጠየቅና ማበረታትና በሥራቸው እንዲያተኩሩ ቢደረግ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላልና በቅጡ ይታሰብበት። ሹመት ጌጥ አይደለም ወይም የቁንጅና ውድድር አይደለም፡፡ ውድድርም ከሆነ በመስኩ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንጂ፣ በየስብሰባው ተገናኝቶ ውስኪ ለመጎንጨት መሆን የለበትም። የመንግሥት መሪዎችም የሚሾሙት ለይስሙላና የዚህ ወገን ወይም የዚያ ወገን ሳይሉ፣ ለሥራው በቂ ዕውቀት አለው ወይ ብለው አገርን በሚረዳ መንገድ ቢሾሙ ጥሩ ውጤት ያመጣልና ይታሰብበት።

በየመንገዱ ቆመው ከሚለምኑት ባገኘሁት ጥናት በቀን 113 ብር በአማካይ ስለሚያገኙ፣ ቆርጠው ወደ ሥራ ለመሰማራት አይሹም ይሆናል። ለዚህም መንግሥት ቆራጥና የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ አለበት። ሕፃናት ልጆቻቸውም በልመና አድገው ለማኝ ሆነው እንዳይቀሩ መንግሥት መላ ሊመታ ይገባል። አንድ ምሳሌ ላቀርብ ወደድኩኝ፡፡ በ1940ዎቹ መጨረሻው ላይ ይመስለኛል ክቡር ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የአርሲ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው ይሾማሉ፡፡ የመጀመርያ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ፣ ‹‹ሌባ በእኔ ግዛት  ውስጥ አይኖርም፣ ከተገኘም አይቀጡ ቅጣት ነው የሚቀጣው፤›› አሉ፡፡

ታዲያ የለመደ በማስፈራራት ስለማይታቀብ ሌቦቹ ሥራቸውን ቀጠሉ፣ ተያዙም፡፡ ደጃዝማቹም ቀልድ አይያውቁምና ያሉትን የቅጣት አዋጅ ፈጸሙ። ታዲያ የሌቦች አለቃ ምን ብሎ ገጠመ፣ ‹‹ሠርቼ እንዳልበላ እጄ ለሰለሰ፣ ሰርቄም እንዳልበላ ገረሱ ደረሰ፤›› አለ ይባላል። ጀግናው ገረሱም ሌብነቱን ላቆመ ሁሉ ሥራ ፈጥረው ከአሰላና ከአጎራባቾቹ በጠቅላላው ሌብነት ጠፋ ይባላል። አጻጻፌ የሚያስቀይማቸው ይኖሩ ይሆናል፡፡ ግን ለምን እንዲህ ጻፍክ ብለው ቢጠይቁኝ እንጂ፣ በኩርፊያና በቁጣ የትም ስለማንደርስ ይልቅስ ተባብረንና ተግባብተን ብንሠራ በዓለም የነበረንን መደነቅ አግዝፈን አሁንም የተደነቅን ልንሆን እንችላለን ባይ ነኝ። ልመናን ለማጥፋት የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የሁላችንንም ትብብር ስለሚጠይቅ ተኮፋሽ ሚኒስትሮችም ሥራቸውን በአግባቡ ቢሠሩ ሁሉም መስመሩን ይዞ ከችግር ልንወጣ እንችላለንና እንነሳ።

በተለይም ፈቃድ ሰጪው ክፍል እዚያ ሂድ እዚህ ና ከማለት ይልቅ፣ በሥራቸው ኃላፊነት ተሰምቷቸው በሚገባ ከሠሩና ሁሉም በአግባቡ ከተፈጸመ ገበሬው ግብርናውን ነጋዴውም ንግዱን በትክክለኛው ከሠራ፣ የምን ምንዛሪ (ከረንሲ) አነሰ በዛ ነው? ምርታችንን በሚገባ ከሸጥንና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ከሆንን የምን ችግር ነው የምናወራው? ወጣቱ በየመንገዱ አላስቆም አላስቀምጥ የሚለው ስለቸገረው ምን ይቀርብኛል በማለት እኮ ነው። ተስፋ የቆረጠ ሰው ለሕይወቱ ግድ የለውም። ለምን? ተስፋ የለውማ! የተሾመ የሚወርድ አይመስለውም፣ ልክ የተራበ የሚጠግብ እንደማይምስለው ሁሉ። 

‹‹እንዲህ ልጠግብ ነው በሬዬን ያረድኩት…›› የሚለውን አነጋገር ታስታውሱ ይሆን? ተስፋ ሳንቆርጥ ተበረታትተን በአንድነት ለጋራ አገራችን መሻሻል አብረንና ተባብረን እንነሳ። አንድ ባለሥልጣን ቢሮ ለቁምነገር ከሄዱ እሳቸው ከሚወዱት ጋር ቡና ሲያንጫልጡ፣ ለእውነተኛ አገር ጉዳይ 50 ደቂቃ ቁጭ ብሎ መጠበቁ መቅረት አለበት።

ሹማምንት ልቦና ይስጣችሁ፡፡ ይኼንን ሁሉ የምወርድባችሁ አድራጎታችሁንና የሥራ ፍቅር ጉድለታችሁን በቅርቡ ስለተመለከትኩ ነውና፡፡ ምን ማለቱ ነው ከማለት ይልቅ ተባብረን ብንሠራ ለአገራችን አመርቂ ውጤት እናመጣለንና እጅ ለእጅ ተያይዘን ያለፈውን ከመውቀስ ይልቅ፣ የራሳችንን ድርሻ ለመወጣትና አገራችንን ሌሎች ወደ ደረሱበት ለማድረስ ተግተን እንነሳሳ፡፡ ኅብረትም ቁም ነገር መሆኑን እናስተምር፡፡ እንደ ኢነርጂ ሚኒስትሮች አንሁን። ዛሬ ዓለም በእጃቸው ያለች የሚመስላቸውን እነሱን እርሷቸው። ልቦና እንዲሰጣቸውም ይመከሩ፣ ይወቀሱ፡፡

ወቀሳ ብቻ እንዳይሆን መፍትሔ ብዬ የማስበውንም ጠቆም አድርጌ ልለፍ፡፡ ለአራሹ ገበሬ የበሬ ግንባር የምታህል መሬት ሰጥቶ በዚያች ሠርተህ ኑር ማለት የትም የማያደርስ የህልም ሩጫ እንዳይሆንበት፣ የመሬት ጉዳይ በደንብ ተጠንቶ ሠራተኛውና ሥራ ተዋህደው የሚያረካ ውጤት እንዲያመጣ መደረግ ይኖርበታል። አሁን ባለው ሁኔታ የትም መድረስ አይቻልምና የመሬት ይዞታ ሁኔታ መቀየር ይኖርበታል።

በምን ዓይነት ይቀየር? ተመካክረን ድብብቆሽ በሌለበት ሁኔታ ተጠንቶ ነው።                                                                                             አንድ ገበሬ በዓመት አርሶ፣ አርሞ፣ ጎልጉሎና አሰባሰቦ የዓመት ገቢውንና ወጪውን አገናዝቦ መሬቱ በሠለጠነ መንገድ ቢሠራበት ምን ያህል ፍሬያማ ሊሆን እንደሚችል ታውቆ ቢቻል በማኅበር (Cooperative) መልክ ፍሬያማ እንዲሆን ተደርጎ ቢሠራበት፣ ያለበለዚያም የመሬት ዋጋ ተከፍሎት ከቀዬው ሳይርቅ በሙያ ሥልጠና ተሰጥቶት በሚገባ እንደማንኛውም ሠራተኛ ተቀጥሮ የሚሠራበት ሁኔታ ቢዘጋጅ ጥሩ ነው፡፡ የሁሉም ጥቅም ተጠብቆ አገሪቱም የምትጠቀምበትን መንገድ በመፍጠር፣ ለልጆች ትምህርት ቤት፣ ለሠራተኛውና ለቤተሰቡ ሕክምና የሚያገኝበት አመቺ ሁኔታ በመፍጠር የሠለጠነና የማያዳግም አንዱ የበላይ ሌላው የበታችነት ሳይሆን፣ ሙያን በተመለከተ መከባበርና መተሳሰብ የሚኖርበት ሁኔታ ተፈጥሮ ሰውም በሥራውና በራሱ እምነት ኖሮት በአገሩ ፍቅር፣ ክብርና መተሳሰብ ተዳምረው ሁሉም አገሬ የሚልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይመከርበት፣ ይዘከርበት፣ በቁርጠኝነት ታጥቀን እንነሳበት እላለሁ።

የጎደለን ነገር ቢኖር ለእሱ ሳይሆን፣ ለእኔ የሚለው አስተሳሰብ ነውና እዚህ ያደረስን፡፡ ይኼንን ትተን ለጋራ ዕድገትና ለአገር ልማት ሌት ተቀን ማሰብ መሥራት አለብንና እንነሳ እንተባበር። ሁላችንም ከተባበርን ጥላቻም ውጊያም የለም፣ ሰላም ይሰፍናል፡፡ ሥራውን ትቶ ወዲያና ወዲህ የሚል አይኖርም። አፍ ሥራ ሲያጣ ወዳጁን ያማል ይባል የለ? ሰዎች አሜሪካ ለመሄድ ምን አሰኛቸው? አንደኛ ሠርተው ለማግኘት፣ ሁለተኛ በሕጉ መሠረት ከተንቀሳቀሱ ማንም ስለማይነካቸው፣ ሦስተኛ የፈለጋቸውን ለማድረግ ሕጋዊ እስከሆኑ ድረስ ደጅ ጥናት ስለሌለባቸው (ነፃ) አገር በመሆኑና በመሳሰሉት ጉዳዮዎች የተሻለ ሆኖ ስለተገኘ ብቻ ነው። ያለበለዚያ አየሩ ነው? ባህሉ ነው? ወይስ ንጣትና ጥቁረት ሁልጊዜ ባይነገርም እንኳ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ነው የተመረጠው? በየመልካችን፣ በየባህላችንና በየቋንቋችን ተከባብረን፣ ተዛዝነንና ተዋደን የምንኖርባትን አገር እንድንለያት የሚያደርጉን የፖለቲካ ሰዎች በሚፈጥሩት ቀውስ ሁላችንም ተጎድተናልና አሁን ወደ ልቦናችን እንመለስ ነው ጥሪዬ።     

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን  በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...