Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኦዴፓና የኦነግ የ‹‹ሰላም ስምምነት›› ተስፋና ሥጋት

የኦዴፓና የኦነግ የ‹‹ሰላም ስምምነት›› ተስፋና ሥጋት

ቀን:

በቁምላቸው አበበ

እንደ ሰላምና ዕርቅ ዓለም አቀፍ ረቡኒው (መምህሩ)፣ አሸማጋዩ፣ አደራዳሪው፣ ፕሮፌሰር ህዝቅያስ አሰፋ አስተምህሮ ሰላም ጦርነትንና ሁከትን ማስቆም ሳይሆን፣ ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሔዎችን መሻት ነው፡፡ ግጭት ወደድንም ጠላንም በሰው ልጆች መሀል ሁልጊዜ የሚኖር መርገምም፣ በረከትም ነው፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅሞ በጊዜ ግጭቱን ለፈታ ተፈጥሯዊ በረከት ሲሆን፣ በአንፃሩ ላልተጠቀመበት ደግሞ መርገምት ነው፡፡ የሚያስከትለውን ቀውስ፣ ዳፋና መዘዝ በመፍራት ብንሸሸውም እንደ ጥላችን ሲከተለን ይኖራል፡፡ ግጭት በሕይወታችንም ሆነ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት በሚገባ ትኩረት ሰጥተን ያልፈተሽነው ጉዳይ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ በበጎ ከተረዳነው ለሁሉ የሚበጅ መፍትሔ ለመሻት ወደሚያግዝ መልካም አጋጣሚ ልንቀይረው እንችላለን፡፡

በአገራችን ባለፉት ሦስት ሺሕ ዓመታትም ሆነ ከዚያ ቀደም ወደኋላ በሚስበው ታሪካችን በሺዎች በሚቆጠሩ ግጭቶች፣ መቆራቆሶችና ጦርነቶች ያለፍን ቢሆንም፣ እነዚህን የታሪክ ወሳኝ መታጠፊያዎች ዘላቂ ሰላምና ዕርቅ ለማስፈን እንዲያግዙ አልተጠቀምንባቸውም፡፡ ይሁንና ግጭት የአርባ ቀን ዕድላችን ሆኖ በእኛ ላይ ብቻ የተጫነ  የታሪክ መርገምት ተደርጎም መወሰድ  የለበትም፡፡ ግጭት የሰው ልጅ በኃጢያቱ ከገነት ከተባረረበት ከዚያ ሩቅ ዘመን ጀምሮ ኖሯል፣ ወደፊትም ይኖራል፡፡ የሰውን ልጅ ከብሉያት ዘመን አንስቶ እስከዚች ሽርፍራፊ ሰከንድ “Nano Second” ጦርነት ተለይቶት አያውቅም፡፡ በፋርስ፣ በባቢሎን፣ በቤዛንታይን፣ በሮማውያን፣ በኦቶማን ዘመን፣ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተካሄዱ ግጭቶችን የቀሰቀሱ ምክንያቶችን በዘላቂነት መፍታት ባለመቻሉ ባህሪያቸውን፣ ዓይነታቸውንና አውዳሚነታቸውን እየቀያየሩ ለዛሬው ትውልድ በዕዳ ቢተላለፉም ዛሬም ሙሉ በሙሉ አለመወገዳቸው፣ የግጭትንና የሰውን ልጅ የኖረ ቁርኝት ያሳያል፡፡

የዩጎዝላቪያ፣ የእኛ የእርስ በርስ ጦርነት፣ የኢትዮ  ሶማሊያ፣ የአፍጋኒስታን፣ የሶማሊያ፣ የኢራቅ፣ የሶሪያ፣ የሊቢያ፣ የኢትዮ ኤርትራ ዘግናኝ ጦርነቶች፣ የአልቃይዳ፣ የታሊባን፣ የአይሲኤስ፣ የቦኮ ሐራም፣ የአልሻባብ፣ ወዘተ አማፅያን መነሳት የሰው ልጅ ዛሬም ያልፈታቸውና ያልተሻገራቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ከፊቱ መኖራቸውን ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው ፕሮፌሰር ህዝቅያስ ግጭት እንደ ጥላችን በምንሄድበት ሁሉ ይከተለናል ያሉት፡፡ ዛሬ በአገራችን ባለፉት አሥር ወራት ብቻ እንኳ ብንመለከት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች፣ በደቡብና በኦሮሚያ፣ በጅግጅጋ፣ በድሬዳዋ፣ በአማራ ክልሎች ግጭቶች፣ ውጥረቶና መፈናቀሎች ተከስተዋል፡፡ ዛሬ መፈናቀሎችና ግጭቶች በአንፃራዊነት ቢረግቡም፣ የግጭቶችን መነሻ ምክንያቶች ግን አልተፈቱም፡፡ ተዳፈኑ እንጂ አልጠፉም፡፡ ነገ ገላልጦ የሚሞቃቸው ጦር አውርድ የሚል ኃይል ከተነሳ መልሶ ሊያቀጣጥላቸው ይችላል፡፡

ኦዴፓ ከዳውድ ኢብሳው ኦነግ ጋር የፈጸመው ዕርቅም የዚህ ዓይነት ነው፡፡ በአባ ገዳዎች ኅብረት አንተም ተው፣ አንተም ተው ተባሉ እንጂ ለግጭት የጋበዟቸውን ልዩነቶች ገና በውል አንጥረው አልለዩዋቸውም፡፡ በተለይ ኦነግ ለግጭት ገፍተውኛል በሚል ያነሳቸው ሰበቦች አሳማኝ ስላልሆኑ፣ ምን እንደሚፈልግ ግራ ከማጋባቱ ባሻገር ሌላ ሥውር ደባ ያለው ይመስላል፡፡ ቢሮ ካልተለቀቀልኝ፣ እነ ጄኔራል ከማል ገልቹ ከሥልጣን ካልወረዱ፣ ካምፕ የገቡ የሠራዊት አባላትን ካልጎበኘሁ፣ የመንግሥት የደኅንነትና የመከላከያ አካላት ገለልተኛ መሆንን በ‹‹ላብራቶሪ›› ካላረጋገጥሁ ትጥቄን አልፈታም በማለት በምዕራብ ኦሮሚያ ከፍ ሲልም በአገሪቱ ደቅኖት የነበረውን አደጋ፣ ‹‹ቲም ለማ›› በማስተዋልና በጥበብ በጥንቃቄ ባይዘው ኖሮ አደጋው ከዚህ የከፋ ይሆን ነበር፡፡ እውነት ለመናገር የኦነግ ጥያቄዎች ከላይ የተዘረዘሩት ብቻ ቢሆኑ ኖሮ ጠንከር ያለ መግለጫ ከመስጠትና ቅድመ ሁኔታ ከማስቀመጥ ያለፈ ዕርምጃ የሚያስወስዱ አልነበሩም፡፡

በአንፃሩ ኦነግ ባለፉት ጥቂት ወራት የፈጸማቸው ጥፋቶች ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ክልሉንም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱን ወደ ቀውስ የሚያንደረድሩ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበትን ለውጥ የመቀልበስ አቅም እንደነበራቸው መካድ አይቻልም፡፡ ይህ የኦነግ የዝንጀሮ መንገድ ለራሱም ፖለቲካዊ አጥፍቶ መጥፋት ነበር፡፡ እንደ መንፈሳዊ አባቱ በሚቆጠረው ሜጫና ቱለማ መቃብር ላይ ከተመሠረተ ወዲህ ማለትም ባለፉት 50 ዓመታት ከገጠሙት ፈተናዎች ሁሉ ምናልባት ይኼኛው፣ ወደ ዘለዓለማዊ ግብዓተ መሬት የሚያወርደው የስህተቶች ሁሉ ስህተት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የአባ ገዳዎች ኅብረትና እነ ኦቦ ጃዋር ደርሰው ባይታደጉት ኖሮ የ50 ዓመታት ታሪኩ ምዕራፍ ድንገት ሊዘጋ ተቃርቦ ነበር፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ወገኖች የአምቦውን የሰላም ስምምነት ከአገራዊ ፋይዳው ይልቅ ኦነግን ከፖለቲካዊ ሞት እንደ መታደጊያ ሥልት አድርገው የተመለከቱት፡፡ ምክንያቱም ከሕዝብ እየተነጠለ፣ ራሱ በለኮሰው እሳት እየተለበለበ ነበርና፡፡ ይኼን ታሪካዊ ጥፋት እንደ ቀደመው ወደ ሸኔ ኦነግ፣ ሽግግር ኦነግ፣ የተባበሩት ኦነግ፣ ከማል ገልቹ ኦነግ፣ ኦዴግ እንደ አሜባ በመከፋፈል እንደ ግራምጣ በመሰነጣጠቅ በቀላሉ የሚያልፈው አልነበረም፡፡ ምሥጋና ለአባ ገዳዎች ኅብረት ይሁንና ከሞት ተርፏል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች በዚህ ዕርቅ ከኦዴፓ ይልቅ ኦነግ ዕጥፍ ድርብ አትርፏል የሚሉትም ለዚህ ነው፡፡

በዚህም አለ በዚያ በአባ ገዳዎች ኅብረት ያላሰለሰ የሽምግልና ጥረት በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና በኦቦ ዳውድ ኢብሳ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መካከል ሰላምና ዕርቅ መውረዱ ሁላችንንም ዕፎይ አስብሏል፡፡ የኦሮሞ ሰላም የኢትዮጵያ ሰላም፣ የኦሮሞ አንድነት የኢትዮጵያ አንድነት ነው በሚል ቅን እምነት፣ እንደ ማንኛውም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሰላም ስምምነቱንና ዕርቁን ከቁጥብነት ጋር (With Reservation) የደገፍነው ለዚህ ነው፡፡ ዕርቁ የማይቀለበስና ዘላቂ እንዲሆን ግን በቀጣይ ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት በነበሩ ሰበቦች ላይ ቁጭ ብሎ መወያየትና ከሥር መሠረቱ መፍታት፣ የስምምነቱ ቀጣይ ተግባር ሆኖ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ስምምነቱ ነገ የማይቀለበስበትና መልሶ የማይጣስበት ምክንያት የለም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ይህ ዕርቅ ዕውን እንዲሆንና ከቀውሱ መፈጠር አንስቶ የሰከነ አመራር የሰጠው ኦዴፓ የአንበሳውን ድርሻ ስለሚወስድ ባርኔጣዬን አንስቻለሁ፡፡ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲቄዎች፣ ኦቦ ገብሬና ኦቦ ጃዋር የነበራቸው ሚናም ቀላል ስላልነበር ከመቀመጫዬ ተነስቼ ገለቶማ ብያለሁ፡፡ እንደ ዳውድ ኢብሳው ኦነግ ክፉ ሐሳብ ሆኖ ቢሆንማ ኖሮ ነገሩ ሌላ ነበር፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከማንም በላይ በዚህ ዕርቅ ያተረፈው የኦቦ ዳውድ ኦነግ ነው፡፡ በፈጸመው ፖለቲካዊ አጥፍቶ መጥፋትም (Political Suicide) ዛሬ ለቅሶ ደራሽ ወይም ቅቤ በአናት ነበር፡፡

ዕርቁ ኦነግ የተገነዘበትን ገመድ ፈቶ፣ ከፈን ቀዶ እንዲነሳ አድርጎታል፡፡ ይሁንና ዛሬም ‹‹ልጡ እንደተራሰ፣ ጉድጓዱ እንደተማሰ›› ነው፡፡ ኮከብ ቆጣሪ፣ ሞራ ገላጭ፣ አድባር ቆሌ ተለማማኝ ባልሆንም፣ ለኦነግ ይህ የመጨረሻ ዕድሉ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ይሁንና ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአገር አንድነት፣ ለሰነቅነው ተስፋ፣ ወዘተ ስንል ዕርቁን ብንቀበለውም ከኦነግ ተፈጥሯዊ ማንነት፣ ከቀደመ ታሪኩ ተነስተን መሥጋታችን ግን አልቀረም፡፡ ሥጋታችንም በሥጋት ላይ ያነጣጠረ ዝም ብሎ ሥጋት ወይም ሟርት አይደለም፡፡ የሚዳሰስና የሚጨበጥ እንጂ፡፡ ሥጋት አንድ አባ ገዳዎችም ሆኑ እነ ኦቦ ጃዋር ካላቸው ተፅዕኖ የመፍጠር፣ እጅ የመጠምዘዝ አቅም የተነሳ  ከማሸማገልና ከማስታረቅ አልፈው የመንግሥትን ተግባር እንዳይተኩ እንሠጋለን፡፡ ይኼን ለማለት የተገደድኩባቸውን አራት ነጥቦችን እንመልከት፡፡

  1. በዚህ ዕርቅ መሠረት ስምምነቱ ቢጣስ አንደኛው ወገን የተናጠል ዕርምጃ መውሰድ አይችልም መባሉ፣ በተለይ ኦነግ እንደለመደው ስምምነቱን ከጣሰ ኦዴፓ/የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ሕግንና ሥርዓትን የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን፣ ግዴታውን ሊወጣ አይችልም ማለት ነው፡፡ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ በሕይወት የመኖር፣ ደኅንነት፣ ሰላም ማስከበር፣ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማትን ንብረትን መጠበቅ አይችልም ማለት ነው፡፡ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ይህን ማድረግ ካልቻለ ሕዝብ የጣለበትን ውክልና ጥያቄ ላይ ከመጣሉ ባሻገር ሥልጣንና ተግባሩን ለአባ ገዳዎች ኅብረት አስረክቧል በሚል ሊያስወግዘው ይችላል፡፡ አንዳንድ የሕገ መንግሥት ተንታኞች ከዚህም በላይ ስምምነቱ ከክልሉም ሆነ ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጋር ይጣረሳል ሲሉ የሚደመጡትም ለዚህ ነው፡፡ ለኦነግ ስምምነቱ ከለላ፣ ጋሻና ጠበቃ ስለሚሆነው ይህ ከሞራልም ከሕግም አንፃር ተቀባይነት የሌለው ከመሆን አልፎ ሕዝብንም፣ መንግሥትንም ታጋች (Hostage) የሚያደርግ ነው፡፡ ስለሆነም በጥንቃቄ እንደገና ሊታይና ሊመረመር ይገባል፡፡
  1. የኦነግ ሠራዊት በተለይ በወለጋ ዞኖች ንፁኃንን፣ አመራሮችንና ፖሊሶችን መግደሉንና አካል ማጉደሉን ራሱ ኦዴፓ ደጋግሞ ነገሮናል፡፡ የሕዝብንና የመንግሥትን ሀብትና ባንክ ዘርፏል፣ አቃጥሏል፣ አውድሟል፡፡ ሆኖም በዚህ ስምምነት ኦነግ ለፈጸመው ወንጀል እንደማይጠየቅ ሰምተናል፡፡ ይህ ሕጋዊ ካለመሆኑ ባሻገር የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕግ መንግሥት ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ታዲያ በየትኛው የሕግ አግባብ ነው ከዚህ ሁሉ ወንጀሉ ያለ ፍትሕ ሒደት ነፃ የሚሆነው? በፈጸመው ወንጀል በሕግ አይጠየቅም መባሉ ሕገ መንግሥቱን፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን የሚጥስ ከመሆኑ ባሻገር፣ የሕግ የበላይነትን ለማክበር በሚደረገው ጥረት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ የሚቸልስ ስለሆነ እንደገና ሊታይ ይገባል፡፡
  2. ከላይ የተነሱ ሥጋቶችን ከመፍታት ጎን ለጎን፣ ኦነግ በተለይ ባለፉት ሦስት ወራት በፈጸመው ወንጀል የተነሳ በለውጡ ላይ ደቅኖት የነበረው ሥጋት ሆነ ያስከተለው ጉዳት በመላው ኢትዮጵያውያን ላይም ስለሆነ፣ በይፋ የክልሉንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡
  3. በኤርትራ ተደርጎ እንደነበረው ስምምነት ውሎ አድሮ ውዝግብ እንዳያስነሳ፣ የአምቦው ስምምነትና ቀጣይ አፈጻጸም ለሕዝብ ይፋ ሊሆን ይገባል፡፡

ፕሮፌሰር ህዝቅያስ እንደሚሉት ሁለተኛው ሥጋት ሰላም ጦርነትን ወይም በገሃድ የሚታይ ሁከትንና ብጥብጥን (Violence) ማስቆም ነው ከሚለው ያፈነገጠ ብያኔ የሚመነጭ ነው፡፡ ሁከትም ሆነ ብጥብጥ በኃይል በመሣሪያ ሊቆም ይችላል፡፡ ከአንገት በላይ በሆነ ዕርቅ ጊዜያዊ ሰላም ሊወርድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ወርዷል ማለት አይደለም፡፡ በአገራችን በተለይ እስካለፈው መጋቢት ወር ድረስ ለሦስት ዓመታት በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ተቀስቅሰው የነበሩ ብጥብጦችንና ሁከቶችን አገዛዙ በኃይልና በጉልበት ሊያዳፍናቸው፣ ሊያፍናቸው ሞክሮ ነበር፡፡ ዘላቂ ሰላምንና ዕርቅን ግን ማውረድ አልቻለም፡፡

በአንፃሩ የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ከመጣ ካለፉት አሥር ወራት ወዲህ ችግሮችን ለማስቆም ሳይሆን፣ ከምንጫቸው ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የብጥብጦችና የሁከቶች ምንጭ ጭቆና፣ አፈና፣ ኢፍትሐዊነት፣ ኢዴሞክራሲያዊነት፣ ወዘተ መሆናቸውን ለይቶ ማሻሻያዎችን በማድረጉ አበረታች ለውጦችን እያስመዘገበ ነው፡፡ ይሁንና ከዳውድ ኢብሳ ኦነግ የገጠመው ፈተና ግን ለየቅል ነው፡፡ ፈተናው አይደለም ኦዴፓ፣ የክልሉ መንግሥት፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ የብጥብጡ፣ የሁከቱ፣ የቀውሱ ቀፍቃፊ ኦነግ ራሱ ለምን ወደ ግጭት እንደገባና ምን እንደሚፈልግ አያውቅም እስከ ማለት አድርሷል፡፡ ስለሆነም በወለጋ በኦነግ የተቀሰቀሰውን ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት ከአምቦው የሰላም ስምምነት ባሻገር የግጭቱን መንስዔ በጥልቀት መመርመር፣ ለኦነግም ያልተገለጠለትን ፍላጎት ወይም አውቆ የሰወረውን ደባና ቋጠሮ በመብራት ፈልጎ ማግኘትና መፍታት ይጠይቃል፡፡

ኦነግ ባለፉት ጥቂት ወራት በምሥራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በቦረና ዞኖች ኦዴፓም ሆነ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት 30 የኦዴፓ አመራሮች ተገድለዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ንፁኃን ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ታግተዋል፡፡ መንግሥታዊ መዋቅሩ ተነጥቋል፡፡ ከ18 የግልና የመንግሥት ባንኮች በታቀደና በተቀነባበረ መንገድ በሦስት ቀናት ብቻ ወደ 500 ሚሊዮን ብር  የሚጠጋ የሕዝብ ሀብት እንደተዘረፈ፣ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ተገድቦ እንደቆየ፣ በተለይ በምዕራብ  ወለጋ 1,763 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ተዘግቧል፡፡ እና ኦነግ ይኼን ሁሉ ግፍ የፈጸመው ቢሮው ስላልተመለሰትና ቀደም ሲል በዘረዘርናቸው ሰንካላ ምክንያቶች የተነሳ ነበር!? መልሱ እንደ ሀ፣ ሁ . . .  ቀላል ነው? አይደለም? ስለዚህ የኦነግን ዓላማና ፍላጎት ከመጋረጃው ጀርባ በጥንቃቄ መርምሮ ማግኘት ለዘላቂ፣ ለአስተማማኝና ለማይቀለበስ ሰላምና ዕርቅ የማዕዘን ድንጋይ ስለሆነ ትኩረት ይሻል፡፡ እንግዲያውስ ኦዴፓም፣ የዳውድ ኢብሳው ኦነግም እነ ኦቦ ጃዋርም ለቀጣዩ የዕርቅ ሒደታቸው የሚከተሉትን ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ ፕሮፌሰር ህዝቅያስ አሰፋ ‹‹የሰላምና ዕርቅ ትርጉምና መንገዶች›› በሚለው መጽሐፋቸው ይመክራሉ፡፡

1ኛ. በግጭቱ ተካፋይ የነበሩ ወገኖች በሌላው ላይ የፈጸሙትን በደልና ጉዳት በሀቀኝነት ማመን፣

2ኛ. በተፈጸመው በደል እውነተኛ ፀፀትን መግለጽ፣

3ኛ. የተበደለውን አካል ከልብ ይቅርታ መጠየቅ፣

4ኛ. የተበደለው አካል ከልብ ይቅርታውን በመቀበል ይቅር ማለት፣

5ኛ. ተበዳዩን ጉዳት ከመድረሱ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ፣

6ኛ. በደሉ እንደገና እንደማይፈጸም አስተማማኝ የሆነ ማረጋገጫ መስጠት፣

7ኛ. ከግጭቱና ካስከተለው ጉዳት በመማር የሁለቱንም ወገኖች ጥልቅ ፍላጎትና ጥቅም የሚያራምድ፣ የሚያጎለምስና የሚያስተሳስር አዳዲስ ግንኙነቶችን መመሥረትና ዕቅዶችን መንደፍ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...