በንጉሥ ወዳጅነው
በአገራችን ኢሕአዴግ መራሹ አዲስ የለውጥ ኃይል የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋትና የፖለቲውን አየር ከወደቀበት የጥላቻና የፀረ ዴሞክራሲያዊነት ዕዳ ለማላቀቅ፣ በተነሳሽነት እርምት መውሰድ ከጀመረ ወዲህ አገራዊ ተስፋዎች እየታዩ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ በፖለቲካም ሆነ ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ ዳፋ ወደ ወህኒ የተወረወሩ ሁሉ ነፃ ወጥተዋል፡፡ በስደት ያሉት በተለይም በትጥቅ ትግል በየበረሃው የነበሩ ሸማቂ ፖለቲከኞች (ምንም እንኳን በአንድ ጊዜ የተሟላ ሰላም የሚረጋገጥበት ሒደት ባይሆንም) ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ የተለያዩ ጋዜጠኞችና ጦማርያንም ብዕራቸውን እያነሱ፣ በኅትመትም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ሐሳቦቻቸውን ማንሸራሸር ይዘዋል፡፡
እነዚህ መልካም መልዕክቶች ብቻ ሳይሆኑ እየታዩ ያሉት በራሱ በገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶችም ውስጥ የዴሞክራሲያዊነት መልዕክቶች መታየታቸው አልቀረም፡፡ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ከማዕከላዊነት እግረ ሙቅ በመላቀቅ አመራርና አሠራር ብቻ ሳይሆን፣ ስያሜና ሕገ ደንብ እስከ መቀየር ሄደዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረትና በራሳቸው ነፃነት ተመሥርተው ፖለቲካዊ ጥንካሬ የሚያስገኙላቸውን ነባር ካድሪዎች (ከስደትና ከእስር ከተመለሱ በኋላ) ማካተት ጀማምረዋል፡፡ ነበሩንና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጥብቅ ቀኖና የሚታማውን ኃይልም በተለያየ መንገድ ከመድረኩ ገለል የማድረጉ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ይህም በአገሪቱ አዲሱን ትውልድ የሚመጥን የፖለቲካና የዴሞክራሲ መስተጋብር ለመገንባት የሚረዳ እንደሆነ ብዙዎች ተማምነዋል፡፡
ያም ሆኖ አሁንም ብቅ ጥልቅ የሚሉ ግጭቶች፣ የሕዝብ መፈናቀሎችና የልማት መጓተቶች መታየታቸው ለውጥን ለማስቀጠል ቀዳሚ ሥጋቶች መሆናቸው አልቀረም፡፡ የሕግ የበላይነትንም ያዳክማል፡፡ በእርግጥ ችግሮቹ የሚመነጩት ለዘመናት ከተጣባን የጥላቻ ፖለቲካና መበቃቀል ብሎም የተካረረ ብሔርተኝነት እንደ ሆነ ዕሙን ነው፡፡ ከዚህ ለመውጣትም በተለያየ መንገድ በፖለቲካ ኃይሎችና በልሂቃን መካከል የተጀማመሩ ውይይቶች ተስፋን የሚዘሩ ናቸው፡፡ በመገናኛ ብዙኃን እየወጡ ሐሳባቸውን በስፋት የሚያነሱ ምሁራንና አንጋፋ ፖለቲከኞች (የደርግ ባለሥልጣናት ጭምር) ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ይህ ተጨባጭ እውነት ደግሞ ከሁለት ዓመት ያነሰ ዕድሜ የቀረው ምርጫ 2012 ዓ.ም. ወቅቱን ጠብቆ መካሄድ አለበት ወይም የለበትም የሚል ንትርክንና ክርክርን ይዞ ብቅ ካለ ሰነባብቷል፡፡ በእርግጥ እስካሁን ባለው ሒደት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ብዙዎቹ የመንግሥት ኃላፊዎች ይካሄዳል የሚል ሐሳብ ነው ሲያራምዱ የሚደመጡት፡፡
በእርግጥ “ዴሞክራሲ ማለት የሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ በሕዝብ የቆመ ሥርዓት ነው” ካልን፣ ዴሞክራሲ የአማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን በሁሉም ወገኖች በኩል ከልብ መወሰድ አለበት ነው፡፡ ለሥልጣን ከመቋመጥ በላይ ምርጫን ለአገር ጥቅም ማሰብ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በዋናነት በሕዝባዊ ምርጫ በመሆኑ ምርጫ የዘመናዊ ፖለቲካ ሕይወት ነው፡፡ ይኼን ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሀቅ መሬት ለማስነካትና ብሎም እንደ ሥርዓት ለመገንባት ደግሞ፣ ከመንግሥትና ከፖለቲከኞች ዝግጁነት ባሻገር የሕዝቡ ሚናም ተኪ የሌለውና አስፈላጊ እንደ መሆኑ በተለያየ መንገድ ሕዝቡም ሐሳቡ ሊደመጥ የግድ ነው፡፡
ምርጫ የሚካሄደው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ገዥና ተቃዋሚ ሳይባባሉ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ መሠረቶች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ ፖለቲከኞች እንደሚሉት የግለሰቦች የፖለቲካ ትግል ፍሬ ቢስ ባይባልም፣ ውጤቱ ግን ሰፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም የተደራጀ ትግል በወሳኝነት አስፈላጊያችን ስለሆነ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሊያስገኝልን እንደማይችል ከወዲሁ በማጤን፣ ጠንካራና ካለፉት ጊዜያት የተሻለ መሰባሰብና መተማመን ያለበት አደረጃጀት ሊታይ ይገባዋል፣ ያስፈልጋልም፡፡
ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው እንደሚሉት የተሰባሰቡና የተወሀዱ ፓርቲዎች ሲኖሩ ሕዝቡ ከመደናገር ከመውጣት ባሻገር፣ መንግሥትም ቢሆን ለመደራደርም ሆነ ለመደገፍ እንዳይቸገር ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም እዚህ ላይ አልሞ መሥራት የምርጫውን ጊዜ ጠብቆ ለመሄድም ይረዳል፡፡
እንደ ሕዝብም በምርጫ የሚመሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖረን ከፈለግን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስፈላጊነት ማመንና መቀበል ብቻ ሳይሆን በአባልነትና በደጋፊነት መሳተፍ፣ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩና በሒደት ኅብረ ብሔራዊነትን እንዲላበሱ የማድረግ ተነሳሽነት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንደ ለውጥ ኃይልም አገራዊ ግዴታችን ነው ብለን መነሳት አለብን፡፡ አደናቃፊና ወደ ጨለማው ዘመን የሚጎትተንን ፓርቲንም ሆነ የፖለቲካ ኃይልን በሰላማዊ መንገድ መታገልም እንዲሁ፡፡ በመሠረቱ ምርጫ የሚካሄደው በተቆረጠለት ጊዜ ገደብ ውስጥ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ብሎም በዴሞክራስያዊ ተቋማቱ በኩልም የተጠናከረና ሁሉም የተስማማበት አሠራርና መዋቅር ዕውን መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በየትኛውም የነቃ ማኅበረሰብ ውስጥም እንደሚታወቀው፣ ዋነኛ የምርጫ ተዋናይ የሆኑት ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና የሚያድግበት አመቺ የፖለቲካ ምኅዳር ዕውን መሆን ይኖርበታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብን በአስተሳሰቦቻቸውና በባህሪያቸው ዙሪያ በማሳባሰብና በማደራጀት፣ ለብዙኃኑና ለአገር ጥቅም መትጋት የሚችሉበት ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ መረጋገጥም ይኖርበታል፡፡
በመሠረቱ ወጥና ሰብሰብ ብለው ተደራጅተውም ቢሆን ፓርቲዎቹ ‹‹ቆመንለታል›› የሚሉትን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጭ ሐሳቦችን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ማራመድ ካልቻሉ፣ ምርጫ ቀረበም ራቀም ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ተዋናዮች ሐሳቦቻቸው ለቆሙለት ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በጠቅላላው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ መታገል መጀመር አለባቸው፡፡ የሕግ የበላይነትና ለብሔራዊ ጥቅም የሚያግዝ ባህል ተሻሽሎ መታየት አለበት፡፡
ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ብሎም የዴሞክራሲያዊ ተቋማት፣ በገለልተኝነትና በነፃነት ተዋቅረው መገኘት አለባቸው፡፡ ብቃታቸውና አቅማቸው መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ሁሉም መንግሥታዊ አካላትም አገራዊ ደኅንነትን የመጠበቅ ሚናቸው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ግዴታቸውም ነው፡፡ በዚህ የለውጥ መልዕክት መንቀሳቀስ ከተቻለ ምርጫው በወቅቱ ተካሄደም በወራት ዕድሜ ጭማሪ ተደረገ፣ ጥቅሙ የጋራ ይሆናል፡፡ በአገራችን የማይዋዥቅ ዴሞክራሲያዊ ባህል ሲገነባ፣ ሚዛናዊ አስተሳሰብና ከጽንፈኝነት የፀዳ የፖለቲካ አተያይ እንዲዳብርም ዕድል እየተፈጠረ መሄዱ አይቀርም፡፡ ፖለቲከኞች ከዜሮ ድምር ፖለቲካ እየወጡ በመሄድ፣ ለአገርና ለሕዝብ መጨነቅ የተግባራቸው ሁሉ አልፋና ኦሜጋ ይሆናል፡፡ ከፍተኛ ኃላፊነትን የመውሰድ ባህልም ይጠናከራል፡፡
በመሠረቱ በአሁኑ ወቅት የአገራችን መላ የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት መንቀሳቀስ መጀመራቸው ይበል የሚሰኝ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ከበፊቶቹ የውድቀት ዓመታት ተምረው፣ በብቃትና በመደማመጥ ተደራጅተው፣ በዝርዝር የተተነተኑ ሐሳቦችን ይዘው፣ መብትና ግዴታቸውን የሚያውቁ አባላትና ደጋፊዎችን አሠልፈው፣ እንዲሁም በሕገ ደንብና በሥነ ምግባር የሚመራ አመራርና ጉባዔተኛን አቅፈው መንቀሳቀስ ካልጀመሩ ምርጫ በቅርብ ጊዜ ማካሄዱ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ እንዲያውም ለውጥ መራሹን ኃይል እየደገፉና እያበረታቱ ተጨማሪ ዕድል ሰጥቶ ማየት እንደ አገር ሊበጅ ይችላል ባይ ነኝ፡፡
በግል እምነቴ መጭው ምርጫ እንዲራዘምም ሆነ በታቀደለት ወቅት እንዲካሄድ ከመንግሥት ዝግጅት ባሻገር፣ የፓርቲዎች መሰባሰብና ኅብረት መፍጠር ጉዳይ ላይ ደጋግሞ ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየን እንዳለነው አብዛኛው በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ድርጅቶችና ግለሰቦች በዕርቅ መንፈስ መነጋገርና ወደ አንድነት የመምጣት ምልክት እያሳዩ ነው፡፡ ገና ሰፊ ሥራና ትግል የሚጠይቅ ተግባር ቢሆንም፣ በሌላ በኩል እንደ ግንቦት 7፣ ኢዴፓ፣ ሰማያዊ ፓርቲና የመሳሰሉ ኃይሎችም በኅብረ ብሔራዊነት ለመሰባሰብ ሥራዎችን መጀመራቸው እየተደመጠ ነው፡፡ ሌሎችም እንቅስቃሴ መጀመራቸው አይቀሬ እየሆነ ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ግን እስካአሁን በታየው የአገራችን የፖለቲካ ጉዞ የፊተኞቹን ኢሕአፓና መኢሶንን ጨምሮ፣ የቅርቦቹን ቅንጅትና ኅብረትን፣ እንዲሁም የአሁኖቹን አንድነትን፣ ኢዴፓና ሰማያዊን የመሰሉ ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ያለፉበት መንገድ መፈተሽ አለበት፡፡ የፖለቲካ ኃይሎቹ ለምን የአንድነትና የኅብረት ጥንካሬ አጥተው ቆዩ ብሎ ማየት ይበጃል፡፡ እነዚህ አገራዊ ድርጅቶች ተጠናክረው አገራዊ ኃላፊነትን ለመረከብ ከመታገል ይልቅ፣ በየጊዜው ምን በታተናቸው? አዳከማቸውስ? ብሎ ወደ ውጭ ጣትን ከመቀሰር ባለፈ ወደ ውስጥ መመልከትና ለጋራ ትግል እንቅፋት የሆኑ አገራዊ ትብትቦችን ለይቶ መፍታት የራሳቸው የፖለቲከኞቹና የዘርፉ ምሁራን ድርሻም መሆን አለበት፡፡
እስካሁን እንደታየው ሕዝቡም በምኅዳሩ ላይ እየተንቀሳቀሱ ካሉት ፓርቲዎች መካከል፣ የግራ ቀኙን ሰምቶና መዝኖ ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ በራሱ ፈቃድ በነፃ ምርጫ መምረጥ ለምን ተስኖት ቆየ? ድምፁን ሰጥቶ በነፃነት እንዳይመርጥ እያወከው ያለውስ ምንድነው? ብሎ መጠየቅና እንዳይደገም መፍትሔ ማስቀመጥም ይገባል፡፡ በእርግጥ ከዚህ በኋላ የፈለገው ፓርቲ የሕዝቡን ይሁንታ ለማግኘት ሲል ምንም አድርጎ ማሳሳት እንዳይችል የሚረዳ ሕዝባዊ መነቃቃት እየተፈጠረ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲም ቢሆን እንዳለፉት ዘመናት ሕዝቡን ‹‹በግድ እኔን ምረጥ›› ብሎ እጁን ይዞ በምርጫ ወረቀቱ ላይ ምልክት እንዲያደርግለት ቢያባብለው እንኳን (ሌላው ቀርቶ በገጠርም ቢሆን)፣ ማስገደድ የማይችልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ሕዝቡ በተለይ ወጣቱ እንኳንስ በሰላማዊ ምርጫ ተገዶ ሊመርጥና የመንግሥትን ጠመንጃና ኃይልም መፍራት ያቆመ እየመሰለ መምጣቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለምርጫው ሁሉም ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ጊዜ ተወስዶ ማሰብ ከተቻለ፣ ያለ ጥርጥር ትውልድ ተሻጋሪ የሚሆንና አስተማሪ ምርጫ ለማካሄድ ይቻል ይሆናል፡፡
ከዚህ አንፃር ከመንግሥትም (ገዥው ፓርቲ) ሆነ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚጠበቀው አጭበርብሮም ሆነ በሕዝብ ላይ ያልተገባ ተፅዕኖ አሳርፎ ለማሸነፍ መባከን ሳይሆን፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ሕዝብን አሳምኖ ለመመረጥ መትጋት ብቻ የግድ ይላል፡፡ ይህ ከታመነ ደግሞ የሚያስጨንቀው የምርጫው ጊዜ መርዘምና ማጠር ሳይሆን፣ ያለ ምንም ዓይነት የጎላ ግጭትና ወደኋላ የሚመለስ ክስተት የማይኖርበት፣ ለአሸናፊም ሆነ ለተሸናፊ እኩል አገራዊ ድል የሚያጎናፅፍ ምርጫ እንዲካሄድ መነሳሳት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡
በመሠረቱ በዴሞክራሲ ሥርዓት መርህ ሕዝብን ሊያሳምኑ የሚችሉ ፓርቲዎች የሚባሉት የአገሪቱን ሕግ አክብረው፣ የሕግ ማዕቀፉን ጠብቀው፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱት ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአሁኑ የመደመርና የዕርቅ ፍልስፍና ሁሉንም ወደ ሜዳው እንዲሰባሰብ ማድረጉ ትልቅ ተስፋ ሆኗል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ፓርቲዎች ለቀጣዩ የ2012 ዓ.ም. ምርጫ (ሩቅ ቢመስልም ቅርብ መሆኑን ልብ ይሏል) የየራሳቸውን ዝግጅት ከወዲሁ ሲያደርጉ፣ በመንግሥትና በሚመለከታቸው አካላት በኩል ያለው ዝግጅት ይሟላ አይሟላ እየመረመሩ ለመሄድ ይቻል ይሆናል፡፡
እንደ አገር ሌላው በሁሉም ተፎካካሪዎች በኩል መተማመን ሊፈጠርበት የሚገባው ቁም ነገር ቅድመ ምርጫ ዝግጅቶች ከመብጠልጠል ወጥተው፣ ተቀራራቢ መተማመን የተፈጠረባቸው መሆኑ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫ በመጣ ቁጥር በፓርቲዎችና ተወዳዳሪዎች በኩል የሚደጋገመው ጩኸት ‹‹የምርጫ ቦርድ ነፃ አይደለም. . . በመንግሥት ቁጥጥርና ተፅዕኖ ሥር ነው. . . በዚህ ቦርድ አመራር ፍትሐዊ የምርጫ ውጤት አናገኝም. . .›› ወዘተ. የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ እንዲስተካከልና እንዲቀየር መንግሥት ተስፋ ሰጭ ዕርምጃ መውሰዱ ባይካድም፣ በተሟላ ብቃትና ዝግጁነት ላይ መገኘቱን ወቅቱ ሲደርስ በጋራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የምርጫ ጊዜን በጋራ ለመወሰን ይረዳል፣ ያስችላልም፡፡
በእርግጥ በየትም አገር ቢሆን ምርጫ ቦርድ ድምፅ አይሰጥም፡፡ ግን በሁሉም ወገን የታመነበት ነፃና ገለልተኛ ካልሆነ ውጤት ሊቀይርና ሊያጭበረብር ይችላል፡፡ ስለሆነም የቦርዱን ነፃነትና ብቃት ከማረጋገጥ ባሻገር ሕዝቡ ድምፁን በኮረጆ ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ መታዘብና መከታተልም ይኖርበታል፡፡ ክፍተቱን በትግል ማረምም ይጠበቅበታል፡፡ ለነገሩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ታዛቢዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት ኮሮጆው ተከፍቶ በግልጽ እንዲቆጠር ማድረግም፣ ተዓማኒነቱን ስለሚያጎላ በዚህ ረገድ መንግሥት የሚኖረው ቁርጠኝነት መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ይህም ተጨባጩን የምርጫ ጊዜ ለመወሰን አንዱ ግብዓት መሆኑ አይቀርም፡፡
በሌላ በኩል ምርጫው ዛሬም ተካሄደ ነገ አገር በሰላም እስከ ቀጠለች ድረስ ዴሞክራሲ እንደ ሥርዓት ባህል ሆኖ እንዲገነባ መትጋት እንጂ፣ የውድቀት መንገድን መመኘት ለማንም የሚበጅ አይሆንም፡፡ ስለሆነም እንዳለፉት ጊዜያት በተዋንያን በኩል ሕጋዊና ሕገወጥ አካሄድን በመከተል ሕዝብን ማደናበር ሊገታ የሚገባው ተግዳሮት ነው፡፡ ካለፈው ስህተት መማር ይሏልም ይህንኑ ነው፡፡
በመሠረቱ እንደ ፓርቲ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዕድገት ሲባል፣ በምርጫው መሸነፍ ቢኖርም እንኳ መወዳደር ያስፈልጋል፡፡ ከሽንፈት ብዙ ትምህርት ይገኛልና፡፡ የመራጩን ሕዝብ አቋምም ለመለካት ያስችላል፡፡ ስለሆነም “ሥልጣን ወይም ሞት!!” የሚባል ኋላ ቀር ብሂል ብዙ ርቀት የማይሄድ ብቻ ሳይሆን፣ ተንገጫግጮ ለመቆም የሚያስገድድ ስለሆነ መታሰብ ያለበት እንደ አገር ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ፓርቲም ሁሉም ይህን አስተሳሰብ መተግበር ላይ ሊሆን ይገባል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ አገራዊ ሁኔታ አንዱ ተስፋ የተጣለበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ አካሄድን እስከ ተከተሉ ድረስ፣ በምርጫ ወቅት አንዳችም ዓይነት ወከባ፣ አፈና ወይም ወደ ገጠር አካባቢዎች ለቅስቀሳ እንዳይወጡ የሚያደርግ ማዕቀብ እንደማይደርስባቸው ነው፡፡ ይኼንንም ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማረጋገጣቸውም በላይ፣ የሕግ ማዕቀፎችም እየተበጁ ነው፡፡ ይህ በጎ ሐሳብ ምንም እንኳን በታችኛው የመንግሥት መዋቅር በእምነት ተይዞ ተቋማዊ ድጋፍ እያገኘ መሄዱ ፈታኝ መሆኑ ባይቀርም፣ በቀጣዮቹ ወራት የሚጀመረው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምርጫውን ጊዜ ለመወሰን ሌላኛው ግብዓት እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ምርጫ ሲነሳ ሌላው የሚታሰበው ፓርቲዎች መልዕክታቸውን ለሕዝብ የሚያደርሱበት ምቹ ሁኔታን የመፍጠሩ ጉዳይ የ2012 ዓ.ም. ምርጫ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ በአገራችን ከዚህ ቀደም እንደ ነበረው ሆነ ዓለም እንደሚያደርገው በምርጫ ወቅት ለሕዝብ በቀጥታ በሚዲያ የሚተላለፍ የፓርቲዎች የፖለቲካ አቋም ክርክር እንዲኖር ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ጠንካራና ገለልተኛ አወያይ ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎችም ሊሆኑ ይችላሉ) በተዓማኒነት ብቅ ብቅ ማለት አለባቸው፡፡ ይህ ዋነኛው የቅድመ ዝግጅት ምሰሶ ነው የሚባለውም ሒደቱን የመወሰን ዕድል ስላለው ነው፡፡
ከዚህ አንፃር በምርጫ ወቅት የጎላ ድርሻ ያላቸው ሚዲያዎች በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎች (ከዚህ ቀደም የነበሩ ውስንነቶችን በመቅረፍ) የፓርቲዎችን የክርክር ነጥብና አቋምን ሚዛናዊ በሆነ ሙያዊ አሠራር መረጃዎችን ለሕዝቡ የማድረስ ዝግጁነትና ተግባር ከወዲሁ ሊያጅባቸው ግድ ነው፡፡ ይህ እውነታ ተሻሽሎ መታየት ከጀመረና ከላይ የተነሳሱት ቅድመ ሁኔታዎችም መስመር እየያዙ ከመጡ፣ ምርጫን ከመደበኛ ወቅቱ መግፋት የሚያስፈልግ አይደለም፡፡ እነዚህ እውነታዎች ካልተሟሉና ተጨባጭ ለውጦች መታየት ካልጀመሩ ግን፣ አንዴ ሳይሆን ሁለት ሦስት ጊዜም ቢሆን ምርጫ አራዝሞ ዴሞክራሲያዊነት ማረጋገጥ የሚበጅ ይሆናል፣ ግድም ይላል፡፡
በአጠቃላይ ከተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንፃር ምርጫው በወቅቱ ይካሄድ፣ ይራዘም የሚለው ክርክር ወቅታዊና ተገቢ መሆኑ አይካድም፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እየተነቃቃ ከመታየቱ አንፃር ስለምርጫ 2012 ዓ.ም. ከወዲሁ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳትም መንግሥት፣ ሕዝቡ፣ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ እያሰቡ ራሳቸውን ያዘጋጁ ዘንድ ሐሳብ ለመጫር የሚረዳ ነው፡፡ በአጽንኦት መታየት ያለበት እውነታ ግን የክርክሩ አንድምታ በማናቸውም የፖለቲካ ኃይሎች በኩል ቢሆን የራስን ጥቅም ከማስቀደምና ከመስገብገብ ሳይሆን፣ የአገርን አትራፊነትና የሕዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መንገድ የሚቃኝ መሆን ይኖርበታል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻችን [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡