[የክቡር ሚኒስትሩ ልጆች ግቢው ውስጥ ሲጨቃጨቁ ክብር ሚኒስትሩ ወጡ]
- ምን ሆናችኋል ልጆች?
- ምነው ዳዲ?
- በጣም እየረበሻችሁኝ ነው ማረፍ አልችልም እንዴ?
- ይቅርታ ዳዲ፡፡
- ምንድነው የሚያጨቃጭቃችሁ?
- የማን ይቁም የሚለው ላይ መስማማት አቅቶን ነው፡፡
- ምንድነው የሚቆመው?
- ሐውልት፡፡
- የምን ሐውልት?
- በቃ ለቤተሰባችን መታሰቢያ የሚሆን ሐውልት ማቆም ፈልገን ነው፡፡
- የት?
- እዚህ ግቢ ውስጥ፡፡
- ለምንድነው ሐውልት ማቆም የፈለጋችሁት?
- ያው ቤተሰባችን በጣም ስኬታማ ስለሆነ ለማስታወሻ ግቢ ውስጥ ሐውልት ቢቆም ብለን ነው፡፡
- ይኼ እኮ የመንግሥት ቤት ነው፡፡
- የመንግሥት ቢሆንም ይህ ቤተሰብ በአገር ደረጃ ራሱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለሆነ ሐውልቱ ቢቆም ችግር የለውም፡፡
- ለመሆኑ አንተ የማን ሐውልት ይቁም ነው ያልከው?
- እኔማ የአያታችን ሐውልት መቆም አለበት እያልኩ ነው፡፡
- ለምን እሱን መረጥከው?
- ዳዲ የዚህን ቤተሰብ ህዳሴ ያመጣው ማን ነው?
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- በዚያ ላይ የቤተሰቡ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ያደረገው ማን ነው?
- እሱ ነበር፡፡
- ለቤተሰባችን ጤናማ የሕይወት ዘይቤን ያስተማረን እሱ እኮ ነው፡፡
- እንዴት?
- ሁሉም የቤተሰቡ አካል በየግቢው አረንጓዴ ቦታ እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡
- እሱስ እውነትህን ነው፡፡
- በዚያ ላይ ሁላችንም አመጋገባችን ሳይቀር አረንጓዴ እንዲሆን አድርጓል፡፡
- ልክ ብለሃል፡፡
- ስለዚህ የቤተሰባችን ወኪል ሆኖ ሐውልት ሊቆምለት የሚገባው እሱ ነው፡፡
- አንቺስ ምንድነው ሐሳብሽ?
- የአያታችን ሐውልት ሊቆም አይገባም ባይ ነኝ፡፡
- ለምን?
- በእርግጥ እኔ አያቴን እወደዋለሁ፣ ግን እሱ ከወንድሙ ጋር በመጣላቱ ምክንያት ነው እስካሁን ቤተሰቡ የተከፋፈለው፡፡
- እ. . .
- እንዲያውም አንተ ነህ እኮ አስታርቀሃቸው ሰላም መውረድ የቻለው፡፡
- እሱስ ልክ ነሽ፡፡
- ስለዚህ የእሱ ሐውልት እዚህ ሊቆም አይገባም፡፡
- የማን ሐውልት ይቁም እያልሽ ነው ታዲያ?
- የቅድመ አያታችን ነዋ ዳዲ፡፡
- አንቺ የት ታውቂዋለሽ እሱን?
- እንዴ ዳዲ ይኼ ቤተሰብ እንዲሰባሰብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረው እሱ አይደል?
- በምን አወቅሽ?
- ዳዲ ትልቁን የቤተሰባችንን ማኅበር የመሠረተው እሱ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
- ይኼን ማን ነገረሽ?
- ሁሌ ማኅበራችን ላይ ሲወራ እሰማለሁ፡፡
- እሱስ ልክ ነሽ፡፡
- እንዲያውም አያታችን በቅድመ አያታችን ይቀና እንደነበር አውቃለሁ፡፡
- ወይ የዛሬ ልጆች?
- እውነቴን አይደል ዳዲ?
- አሁን ምን እያላችሁ ነው?
- እኔ የአያታችን ሐውልት ይቁም እያልኩ ነው፡፡
- አንቺስ?
- እኔማ የቅድመ አያታችን ሐውልት ነው መቆም ያለበት የምለው፡፡
- ለማንኛውም እዚህ መቆም ያለበት ሐውልት የማን እንደሆነ ታውቃላችሁ?
- የማን ነው?
- የእኔ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]
- አንተ ሰውዬ ምን ሆነሃል?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ስልክ ብደውል ብደውል አታነሳም እኮ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ቢዚ ሆኜ ነዋ፡፡
- ምንድነው ቢዚ ያደረገህ?
- ስብሰባው ነዋ፡፡
- የምን ስብሰባ?
- የመሪዎቹ ስብሰባ ነዋ፡፡
- ጉረኛ አንተ ደግሞ ምን አገባህ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር ዋናው የዶላር ሥራ አሁን አይደል እንዴ?
- እሱን ስታጧጡፍ ነዋ ሌላኛውን ቢዝነስ የዘነጋኸው?
- የቱን ቢዝነስ ክቡር ሚኒስትር?
- ስብሰባው ላይ እኮ አንድም የእኛን መኪና አላየሁም፡፡
- የእኛ መኪኖችማ ሁሌም ሥራ ላይ ናቸው፡፡
- አንድም አላየሁም ስልህ?
- ማለቴ ከተማ ውስጥ እኮ የታክሲ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
- ምን ነካህ እነዚያን ዘመናዊ መኪኖች ታክሲ እያሠራሃቸው ነው?
- ክቡር ሚኒስትር የከተማችን የታክሲ አገልግሎት እኮ ዘመናዊ ሆኗል፡፡
- እሺ እነዚያ ዘመናዊ ቫኖች ምን እየሠሩ ነው?
- እነሱም ስኩል ባስ ሆነዋል፡፡
- ተማሪ ማመላለሻ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት እነዚያን መኪኖች የተማሪዎች ማመላለሻ ታደርጋቸዋለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ተማሪዎች እኮ የወደፊቱ ተስፋ ናቸው፡፡
- ዲስኩርህን እዚያው፡፡
- ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
- መኪኖቹን ለተሰብሳቢዎቹ ባለማከራየትህ እኮ ዶላር ነው ያስመለጥከኝ?
- ክቡር ሚኒስትር አልተደመሩም እንዴ?
- የምን መደመር ነው?
- አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው እኮ ለዜጋ ነው፡፡
- በዶላር ቀልድ የለም ስልህ?
- ካሉ እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለማንኛውም በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ገብቶኛል፡፡
- ምን ሊያደርጉ?
- ማለቴ የስብሰባ ተሳታፊዎቹ መኪና እንዳይከራዩ ማድረግ አለብኝ፡፡
- ታዲያ ከተማ ውስጥ በምን ይንቀሳቀሱ?
- በታክሲ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ የታሰሩ ጓደኛቸውን ሊጠይቁ እስር ቤት ሄዱ]
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሰላም ነህ?
- ምን ሰላም አለ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆንክ?
- መድኃኒት የለ፣ መጽሐፍ የለ፣ ሰው እንደ ልቡ መጥቶ አይጠይቀኝ፡፡
- ይኸው እየመጣሁ እጠይቅሃለሁ አይደል እንዴ?
- በፊት እየመጣ የሚሰግድልኝ ሁሉ አሁን የታለ?
- የሚሰግደው ተገዶ እንጂ ወዶ መሰለህ?
- በቃ በጣም መሮኛል፡፡
- ምን ሆነህ?
- እኔ እኮ ትልቅ ነገር ፈልጌ አይደለም፡፡
- እኮ ምንድነው የፈለግከው?
- ያው እስር ቤት ያለው ምግብ አልተመቸኝም፡፡
- ምን ሆነብህ?
- ደም ግፊቱ፣ ስኳሩም ስላለብኝ ጨው የሌለበት ምግብ መመገብ አልችልም፡፡
- ታዲያ እንዲስተካከልልህ አትነግራቸውም?
- ማን ይሰማኛል ብለው ነው? በዚያ ላይ እኔ የለመድኩት ዓይነት ምግብ ነው፡፡
- ታዲያ እዚህ ሼፍ እንዲቀጠርልህ ፈልገህ ነው?
- ለአገር ካበረከትኩት አንፃር እሱ ሲያንሰኝ ነው፡፡
- ቀልደኛ ነህ እባክህ?
- በዚያ ላይ መጽሐፍ ማንበብ እንደምወድ ያውቃሉ አይደል?
- ታዲያ መጽሐፍ እየገባልህ አይደል እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ከዘመኑ ጋር መራመድ አለብን፡፡
- እንዴት?
- አሁን እኮ ብዙ ነገር የሚነበበው ኢንተርኔት ላይ ነው፡፡
- እ. . .
- ኦንላይን እኮ ነው ማንበብ የምፈልገው፡፡
- ኦንላይን?
- አዎን ምነው?
- እውነትም ብሶብሃል፡፡
- ምኑ?
- ዕብደቱ፡፡
- በዚያ ላይ እኔ ስፖርት መሥራት የለመድኩት ጂም ነው፡፡
- እሺ ሌላስ?
- በየሳምንቱ ስቲምና ሳውና መጠቀምም እወዳለሁ፡፡
- በጣም ተቸግረሃልና?
- ታዲያስ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ይሻላል ታዲያ?
- እኔማ ከሌሎችም አገሮች ቢሆን ልምድ ብትወስዱ ባይ ነኝ፡፡
- የምን ልምድ?
- ማለቴ እስር ቤቴን ብትቀይሩልኝ፡፡
- የት መታሰር አማረህ?
- ሆቴል!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ከሥልጣን የወረዱ ሚኒስትር ደወሉላቸው]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሄሎ ማን ልበል?
- ማን ልበል?
- አዎን ማን ልበል?
- እርስዎም ማን ልበል ማለት ጀመሩ?
- ይቅርታ ከየት ነው የተደወለው?
- ያኔ በቀን አሥሬ እንዳልደወሉልኝ አሁን ማን ልበል ይሉኛል ክቡር ሚኒስትር?
- እስካሁን አላወቅኩህም፡፡
- ለማንኛውም የቀድሞ ወዳጅዎ ነኝ፡፡
- ውይ ቁጥርህ እኮ ተቀይሮብኝ ነው፡፡
- እርስዎም ረሱኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ኧረ ሁሌ ልደውል አስባለሁ፡፡
- ቢያስቡኝማ ይደውሉ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሁሌ ነው የማስብህ ስልህ?
- ይኸው ድምፄን ራሱ መቼ ለዩት?
- ከሥልጣን ስትወርድ የአንተም ድምፅ ተቀይሯል መሰለኝ፡፡
- እንደዚህ የእርስዎም መቀለጃ ሆንኩ፡፡
- ኧረ እየቀለድኩብህ አይደለም፡፡
- ትዝብት ነው ትርፉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ኧረ ሁሌ ከሚስቴ ጋር ስለእናንተ ነው የምናስበው፡፡
- ቢያስቡማ ኖሮ ይደውሉልኝ ነበር፡፡
- ያው እናንተ ጋ መደወል ችግር ነው ብዬ ነው፡፡
- ይኸው እኔ እየደወልኩ አይደል እንዴ?
- የሚገርምህ አሁን አንተ መሆንህን ሳውቅ መፍራት ጀመርኩ፡፡
- ለማንኛውም በፊት እንደዚያ ጠብ እርግፍ እንዳላሉልኝ በአንዴ ይዝጉኝ?
- ለመሆኑ ሌሎቹስ እንዴት ናቸው?
- ኧረ ሌሎቹም ተቀይሞዎታል፡፡
- ምን አጠፋሁ?
- መቼ ዞር ብለው ዓይተውን ያውቃሉ?
- ይቅርታ በሉልኝ፡፡
- ይቅርታ ኪስ አይገባም ሲባል አልሰሙም፡፡
- ምን ልቀጣ ታዲያ?
- እዚህ ያረፍነው ሆቴል መሆኑን ያውቃሉ አይደል?
- አዎን ሰምቻለሁ፡፡
- የሆቴል ወጪያችን ከፍተኛ እየሆነ ነው፡፡
- ምን ይደረጋል ታዲያ?
- ስለዚህ ሰሞኑን እንልክልዎታለን፡፡
- ምኑን?
- ቢሉን!