በገለታ ገብረ ወልድ
የገናን በዓል ምክንያት አድርጌ ወደ አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች፣ በመቀጠልም የጥምቀትን በዓል ከዘመድ ወገኖቼ ጋር ለማክበር ወደ ደቡብ ክልል ወላይታና አርባ ምንጭ አካባቢ ተጉዤ ነበር፡፡ በእውነቱ ጉዞዬ ማኅበራዊ፣ ወቅቱም ሃይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩበት ይሁን እንጂ፣ ትልቅ ፖለቲካዊ ንፅፅርና ትርጉም የሰጠሁበት የጥሞናና የምልከታ ጉዞ ነበር ያካሄድኩት፡፡ በሚገርም ሁኔታ በሁለት የተለያዩ አካባቢዎች በአሥር ቀናት መሀል በተደረገ ጉዞ የሕዝቡ የለውጥ ስሜት የከፋፈለህ ግዛው ሥልትን የመናቅ ፍላጎቱ እጅግ የበረታ ሆኖብኛል፡፡ አሁን ያለውን የለውጥ ኃይል አረረም፣ መረረም በተስፋና በአጋርነት መንፈስ የሚጠብቀው ዜጋ በተለይ አዲስ ትውልድ በእጅጉ በዝቶ የሚታየውም ለዚሁ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ በአርባ ምንጭ ከተማ ያገኘናቸው አንድ የቀድሞ ፖሊስ አዛዥ፣ አንባቢና የታሪክ አዋቂ አንጋፋ ግለሰብ ያሉኝ፣ ‹‹በመሠረቱ ለውጥ የሚመጣው በሕዝብ ነው፡፡ መሪም ቢሆን ሕዝብና የለውጥ አየር ይፈጥረዋል እንጂ ድንገትና በአጋጣሚ አይበቅልም፡፡ ፈቃደ ፈጣሪም አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ ተፈጥሯዊ የሆነውን ለውጥ ለመቀልበስ ወይም የለውጡን መሪ ከዚህ ቀደም በሚታወቅበት ቁመና ወይም በመጣበት ኅብረተሰብና ባልተገባ ዳራ በመመዘን ለማጣጣል መሞከር የዋህነት ነው፡፡ ይልቁንም ለውጥን ከመገዳደርና ከማደናቀፍ በለውጥ ውስጥ ለመታቀፍ መሰናዳት እንደ ሕዝብ የሚበጅ ይሆናል፡፡›› የሚለውን አባባል ደጋግሜ እንዳጤነው ሆኛለሁ፡፡ የኖርንበት ታሪክም ሲነግረን የኖረው ይኼንኑ ነውና፡፡
በእውነቱ ምንም ያህል ወቅታዊ ፈተናዎች ቢበረቱ ከልምድም ሆነ ካልታሰቡ ቀውሶች በተነሳ የአገሪቱ መሪ ሊደነቃቀፍ ቢችል እንኳን፣ ሕዝቡ አንዴ “ሆ!” ብሎ ደግፎልናል የሚቀየር ነገር አይኖርም፣ ቢቀየርም በሕዝብ ምርጫ እንጂ በግርግር ሊሳካ አይችልም፣ የፖለቲካ እስረኞች በገፍ በመፍታት፣ መላውን ተገዳዳሪ ኃይል በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በፖለቲካው እንዲሳተፍ በማነሳሳት፣ ሚዲያው ቀስ በቀስ የተጫነበትን እግረ ሙቅ በማላቀቅ. . . የብርሃን ተስፋ ፈንጥቋል፡፡ ከዚህም በላይ ለዓመታት የአገር ሀብት በመመዝበርና የንፁኃንን ዕንባ በማፍሰስ ሲንፈላሰሱ የነበሩ “አይነኬዎችንም” (በእነ አቶ በረከት በቁጥጥር ሥር መዋል ክሱ ምንም ሆነ ምን ሕዝቡ ምን እያለ መሆኑን እያየን ነው)፣ ቀስ በቀስ መጨምደድና ሕግ ፊት ማቅረብ መጀመሩ የለውጥ ኃይሉን ትልቅነት ወለል አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ቲም ለማና አጋሮቹ፣ አገራዊ አንድነትን ለመመለስ ብሎም መለያየትና ዘረኝነትን ለማስቀረት ያሳዩትን ኢትዮጵያዊ አንድነትና መደመር፣ አክብሮትና ሃልዮት ማጣጣም ይዟልና ለውጡን አለመቀበል አይሻም፡፡ ይኼንን እውነታ ሲያጣጥሉ የሚያይ ዜጋም የራሱን ጥቅም እንደ ማስወሰድ እየቆጠረው ይመስላል፡፡ ለፖለቲካ ተገዳዳሪዎችም ቢሆን፣ በዚህ መሸጋገሪያ ወቅት የሚታዩ አንዳንድ አፍራሽ አካሄዶችን መምረጥ የሚያስከትለው የፖለቲካ ኪሳራ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ ተነስቼም ኢሕአዴግን ከውስጥ እንደሚያውቀው ሰው ብቻ ሳይሆን፣ በየጊዜው ሲወላከፍበት የቆየውን አካሄድ እየተገነዘበ፣ በዚህም ገና ከዓመታት በፊት “በቃኝ!!” ብሎ ገለል እንዳለ ዜጋ ለውጡን መጎተት ይሆን እንጂ፣ ለመቀልበስ አይቻልምና “አትሞክሩት!!” ማለትን መርጫለሁ፡፡ መፍትሔውም ለውጡን ማጠናከርና ማፍጠን ብቻ መሆኑን እንደ ብዙኃኑ እኔም ላወሳ እወዳለሁ፡፡
እዚህ ላይ በስንት መከራና ለቅሶ ምሕረት ተሰጥቷቸው ከነበሩበት የገቡ ፖለቲከኞችና ሽምቅ ታዋጊዎች፣ በየአካባቢው ሁከትን እንደ ወቅታዊ የፖለቲካ መታገያ ሲያደርጉ የቆዩ ወገኖች (የሰሞኑ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዕርቅ በጎ ዕርምጃ ቢሆንም)፣ እንዲሁም በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ ባሉ ብሔራዊ ድርጅቶች የተንሰራፋው በለውጡ ያልተደሰተ ኃይል ሁሉ ቢችል በመደማመጥ ወደ ለውጡ መቅረብ ካልሆነ አርፎ መቀመጥ ነው የሚበጀው፡፡ ከዚህ አንፃር ለሁሉም ተዋናይና በተለመደው መንገድ እየፋነኑ ለመኖር የሚሹ ጥገኞችም ቢሆኑ ሊነገራቸው የሚገባው፣ ለውጡ ላይቀለበስ ነገር አጉል መንገታገት አይበጅም የሚለውን መልዕክት መሆን አለበት፡፡ ይልቁንም አሁን ወደ መሪነት የመጡ ኃይሎች ከጀርባቸው ካላቸው ሰፊና ትኩስ ኃይል ድጋፍ አንፃር አጋርነትን እያጠናከሩ፣ ለውጡን ሁሉ አቀፍና አሳታፊ እንዲሆን ማድረግ የተሻለ ዕድል ይፈጥራል ባይ ነኝ፡፡
በመሠረቱ በአገሪቱ ለተጀመረው እመርታዊ የፖለቲካ ለውጥ የሕዝቡ የመረረ ግፊት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግም በውስጡ ጥልቅ ተሃድሶ ማድረጉ አላገዘም ሊባል አይችልም፡፡ እንዲያውም የማይደፈረውን ውስጣዊ አምባገነንነትና ኢፍትሐዊነት ብሎም ዘግናኝ ዘረፋ ለማስቆም ዕንቁላሉን ከውስጥ የሰበረው ኃይል ሚናው ከፍ ያለ እንደነበር መርሳት ወይም ማንኳሰስ ለውጡን እንደ መካድ ነው የሚቆጠረው፡፡ በእውነቱ የሕዝቡ ግፊትና የተገዳዳሪው ኃይል ልዩ ልዩ ትግል ባይሰወርም፣ የውስጥ ትግሉ ያውም ኢሕአዴግ ቀስ በቀስ እየገነባው ከመጣው አያፈናፍኔነት (ወጥመዱንና አድርባይነቱን ውስጡ የነበረውን በሚገባ ስለምናውቀው) አንፃር ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነበር፡፡ ስለዚህ የለውጡ ደጋፊ ትግሉን ሲያግዝም ሆነ፣ ሊገዳደር የሚሻውም ከመቀላቀሉ በፊት መስዋዕትነቱንና አስተዋጽኦውን ወደ ኋላ ካለመመለስ ጋር ሊያገናዝበው ይገባል ባይ ነኝ፡፡
በነገራችን ላይ እኔ በግሌ ከሦስት ዓመታት በፊት በቅርበት በማውቀው አዲስ አበባ ብአዴን በሚባለው ኮሜቴ ውስጥ አደረጃጀት ውስጥ ቢያንስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማሮችን ወክለው፣ የሰሜን ወሎ የአንድ አካባቢ ልጆች ብዙዎቹ በቀጥታ በእነ አቶ በረከት ትዕዛዝ የሚተነፍሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ተጠሪነታቸውም ለሕወሓት ነባር አመራር ስለነበር፣ ይፈጽሙት የነባረውን ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊትና የኔትወርክ ተግባር በሚዲያ ለማጋለጥ ሞክሬያለሁ፡፡ በእርግጥ ይኼ ባህሪና አካሄድ የነባሩ ኢሕአዴግ ተፈጥሯዊ ባህሪ ስለሆነ፣ በእንዲህ ያለው ጎጠኛ አስተሳሰብ ላይ ደጋግሞ ማሰብም ራሳቸውን የመሆንን ያህል አድካሚ ቢሆንም ታግያቸዋለሁ፡፡
በሒደቱ በፓርቲው ውስጥ ቀስ በቀስ እያቆጠቆጠ የመጣው ዞናዊነትና የወረዳ አስተሳሰብንም ለመታገል የሞከሩትን ያስከፈለን ዋጋ ለማሳየት ስሞክር፣ እስከ ክልል ድረስ ያለውን ገመድና ማዕከላዊ ኮሜቴ (በነገራችን ላይ ከቀድሞው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሜቴ ምርጫ ከተገለሉት 17 በዚህ ውስጥ ነበሩ) ድረስ የተዋቀረውን ትስስር ጠቅሻለሁ፡፡ በዚያ ጊዜ በተለይ የተሻለ ለመታገል የሚሞክሩትንና ብቃትም ያላቸውን የአዲስ አበባ ካድሬዎችና የብአዴን አባላትን ወይም “የዓይኑ ቀለም” ያላማራቸውን የአማራ ተወላጅ ሁሉ (እኛን ጨምሮ) በመዋቅሩ ውስጥ ሲያሳድዱ መክረማቸውንም ነበር በድፍረት ያነሳሁት፡፡ በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ መስከረም 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕትም ላይ “ኢሕአዴግ ሆይ ውስጥህን አጥራ ወይም ተለወጥ ካልሆነ ግን. . . በሚል ርዕስ ሞግቻለሁ፡፡
በተመሳሳይ በደኢሕዴንና በኦህዴድ ውስጥም ቢሆን በጥቂት አምባገነን ከፍተኛ አመራሮች ኔትወርክ ተሳስቦ ያልመጣ የበታች ካድሬ አድርባይና አጎንባሽ እንዲሆን ይካሄድ የነበረውን (መንደርተኝነቱ እዚህም የተባባሰ ነበር) ተንኮል ጽሑፉ ዳስሶት ነበር፡፡ ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን፣ ካድሬውንና አባል ተብዬውን የሚያማርረው ድርጊትም በአብዛኛው ከሕወሓት ውጪ ባለው ኃይል ይፈጸም እንደነበር በይፋ የሚታወቅ እንደሆነ በማሳያዎች ተዳሷል፡፡ በዚህም እየተቀጣጠለ በነበረው ትግል ላይ ዛሬ ሳይሆን፣ ትናንት አንድ ጠጠር እንደወረወርኩ ይሰማኛል፡፡
በመሠረቱ ፍላጎቱ የሕወሓት ይሁንም አይሁንም፣ በኢሕአዴግ ስም ይፈጸም የነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊነትና የተደራጀ የቡድን ጥቅም የማስከበር ጥድፊያ በየአካባቢው የተጀመረውን ትግል ክፉኛ በማዳከም፣ ሥርዓቱን ወደ ቀውስ እንደገፋው የሚታወቅ ነበር፡፡ እነዚህም ኃይሎች ቢሆኑ አይደለም የአገሪቱን ጥቅም ሊያስከብሩ፣ የበቀሉበትን ሕዝብም የሚያስደስትና የሚያረካ ተግባር መፈጸም አይሆንላትውም፡፡ እንደ አብዮታዊ ዴሞክራት የሌላውንም ጥቅም ሊያስከብሩ ከመቻል ይልቅ፣ እንዲያውም በተቃራኒው እንደተሠለፉ ይፋ እየሆነ መጥቶ ነበር፡፡ ይህ አካሄድም ተያይዞ ገደል እንደሚጥል ብቻ ሳይሆን፣ ለውጡ ባይደርስበት ደግሞ አገርም የሚበትን ነበር፡፡ እኛ ዘወር ብንልም በውስጥ አምርረው ይኼን አሳሳቢ አካሄድ ፊት ለፊት የታገሉት ጀግኖች ናቸው የዛሬዋን የለውጥ አየር እንድትነፍስ ያደረጉት ብሎ አለማሰብ ደግሞ ድንቁርና ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ቀደም ሲል የእኛ ቢጤ ተንገሽግሾና ተሰላችቶ ከመዋቅሩ የወጣውም ሆነ አሁንም ቢሆን በውስጥ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ያለው ግን የሥርዓቱ ብልሽትና ኢፍትሐዊነት ብቻ ሳይሆን፣ የዘረፋና የዘረኝነት አካሄድ የማያስደስተው በርካታ ካድሬና አመራር አለ፡፡ በጥልቀታዊው ተሃድሶ ዋጋ ከፍሎና ጎምርቶ በየብሔራዊ ድርጅቱ (በተለይ በያኔዎቹ ብአዴንና ኦህዴድ) የተፈጠረው የለውጥ አመራር ግን በአገሪቱ ገንግኖ የነበረውን የጥላቻና የፍረጃ ፖለቲካ በማስቀረት ለዕርቅ፣ ለፍቅርና ለመደመር የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝና አገርን የሚያኮራ ነው፡፡ ይኼን ሕወሓትም ሆነ ደኢሕአዴን ከልብ ተቀብለው በጋራ ወደ ፊት መምራት ነው የሚጠቅማቸው፣ የሚበጀውም፡፡
በዚህ ረገድ አገሪቱ ከጎረቤት አገሮች ጋር ጭምር የጀመረችው ለውጥም የሚናቅ ሳይሆን፣ ሳንካዎቹ እየታረሙ መጠናከር ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ቢሆን ለውጥን በማድነቅና በመደገፍ ብቻ ሳይታጠር አጋር ሆኖ ሥር እንዲሰድና ካለፉት የኢሕአዴግ ዘመናት ድክመትና ጥንካሬ ተምሮ እንዲስተካካል የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው ያለበት፡፡ ያሳይሆን ቀርቶ በተራ አሉባልታና ማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚካሄደው ውኃ የማይቋጥር ማንቋሸሽና ማናናቅ ግን ታሪክን ካለመገንዘብና የለውጥን ተፈጥሮ ካለመረዳት የሚመነጭ አጉል ስህተት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ፈጥኖ መስተካከል ያለበትም ሀቅ ይኼው ነው፡፡
በመሠረቱ በውስጥ ካለው ድርጅታዊ መቆራቆስ ባሻገር፣ የለውጥ ኃይሉ በተቃዋሚው ወገንና በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ድጋፍና የኃይል ሚዛን ከፍታ መለካት ለማንም የሚበጅ ይሆናል፡፡ ከተሃድሶው በኋላ የለውጥ ኃይሉ በጠራቸው የሕዝባዊ ንቅናቄ መድረኮች ደጋፊና ተቃዋሚ ሳይባል መላው ሕዝብ ገደብና ድንበር በሌለው ነፃነት የተሞላበት ንግግርና አጋርነት ስሜቱን መግለጹ ለአባባሉ ማሳያ ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ ሞቅ ቀዝቀዝ እንዳለ ባይካድም የሕዝብ ድጋፉ ከፍተኛ እንደሆነ በተግባር መታዘብ የሚቻል ነው፡፡
ከላይ በገለጽኩት የሰሞኑ የክልሎች ምልከታዬ የተገነዘብኩትም አብዛኛው ሕዝብ “ኢሕአዴግ” የሚለውን ነባር ስም ጭራሽ ለመጥራት እንደማይፈልግ፣ “ቲም ለማ” የሚባለው የእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኃይልም “አገር ለማዳን ከፈጣሪ እንደተላከ መሲህ” ሁሉ በተጋነነ ደረጃ መታየት እንደጀመረ ነው የተረዳሁት፡፡ ይህን የለውጥ መንፈስ ለማደናቀፍ መሞከር ደግሞ “አገርም ብትሆን ትፍረስ!!” እንደሚባለው ተስፋ ቆራጭነት እንጂ፣ ማንም ሊቀበለው የሚችል አይደለም የሚል ድምዳሜ እንድንይዝ የሚያደርግ ነው፡፡
በዚህም የተነሳ በለውጡ ላይ ዕንቅፋቶች እየተጋረጡም ቢሆን፣ የሕዝቡ በተለይ የአዲሱ ትውልድ ድጋፍ እየጋመና እልህ የማስጨረስ በሚመስል መንገድ እየሰፋ እንጂ (ብዙ የተባለለት “ባለ ትልቅ የሕዝብ አጋሩን” ኦነግን እንኳን ራቁቱን ያስቀረው ቄሮና ራሱ የኦሮሞ ሕዝብ “እረፍ ባይነት!!” መሆኑን ልብ ይሏል) የተቀዛቀዘ ነገር አልተስተዋለም፡፡ በአንዳንድ አካባቢም ቢሆን ሕዝቡ የከፋ ሁከትና ነውጥ ሳይቀሰቀስ (አፋርን ያስታውሷል) ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም አሉ ያሏቸውን ችግሮች በማቅረብ፣ አሠራሮችንም በመተቸት ላይ መሆኑም ይታወቃል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ እርምት መደረግ ያለበትን በመጠቆም ለመንግሥታዊ አሠራሮች መስተካከልና ለራሱም አመቺ ሁኔታ የሚፈጠርበትን መንገድ በማበርከት ተሳትፎውን እያሳደገ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በየአካባቢው የሚመራው ካገኘ የድርሻውንም ለመወጣት ወደ ኋላ ሊል አይችልም፡፡
በእርግጥ አብዛኛው ነባሩ የቀድሞው የኢሕአዴግ አመራር (ይህ ኃይል ምናልባት ከኦዴፓና ከደኢሕዴን በስተቀር በሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች የተወሸቀ የ1960ዎቹ ፖለቲከኞች አሻራ ያረፈበት ነው)፣ እንዲሁም በሥር ነቀል ትግሉ ጥቅማቸው የተነካባቸው አንዳንድ ጥገኞችንም ያቀፈ ነው፡፡ ይህም ኃይል ለውጡ ወደ ኋላ ተመልሶ በቀደመው በሬ ለማረስ እንደቋመጠ ታይቷል፡፡ ፍላጎቱም በተለያዩ አፍራሽ ተግባራት እስከመታጀብ ሲደርስ ተመልክተናል፡፡ ይሁንና ከዕድሜ ብዛት ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ድረ ገጾች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረት ትግል ያልገባው፣ የዘመኑ ትውልድ ፍላጎትና ዓለም አቀፋዊ ተናባቢነትንም ያላጤነ በመሆኑ መለስተኛ ሊባል የሚችል አብዮት ከመድረኩ ገፍትሮታል፡፡ ከዚህ በኋላም ቢሆን የፖለቲካ ሕይወቱ ለዚህ ትውልድ የማይመጥንና እያከተመ ያለ ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ ሕልሙን ዕውን ለማድረግ ኃፍረቱን ሸጦ ማንኛውንም የውንብድና የጥፋት ዕርምጃ ለመለኮስ ቢጣጣርም፣ ሊሳካለት የማይችለው ከዚሁ እውነታ አንፃር ነው፡፡
ይህ በጥላቻ ፖለቲካ ተፈጭቶና ተቦክቶ የተጋገረ ግራ ዘመም ኃይል፣ በአንድ ወገን የበላይነት የራሱን ጥቅም ማደለብ የሚሻ ነው፡፡ በተመሳሳይ መደብ ላይ የሚገኝን የራሱን ወገን አጋጭቶና አጫርሶ ለመቀጠል ግን ወደ ኋላ የማይል መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የአገርንም ገጽታ አበለሻሽቶ ተመልሶ ሥልጣን ላይ ለመንጠልጠል መሞከሩ ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም በፖለቲካ ስካር ውስጥ የሚገኝና ቅጥ አንባሩ የጠፋው አንዳንድ ቀለብተኛ ጦማሪና ደጋፊ ስለማያጣም ትንፋሹ ገና እንዳልቆመ ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገርና ሕዝብ ወደ ጨለማና ሌላ ውድቀት ለመግባት እንደ መንደርደር የሚቆጠር አደገኛ መንገድ ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለምም ሊቀበለው እንደማይችል መታመን አለበት፡፡
በመሠረቱ ለአሁንም ሆነ ለወደፊቱ የለውጡና የተሃድሶው ንቅናቄ ዋና መሪና ተዋናይ ሕዝብና ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ውስጥ ፈልቅቆ እንደ ንስር የወጣው የለውጥ ኃይል ከፍ ያለ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት የቻለውም፣ የሕዝብን ጥያቄና ፍላጎት የትግሉ መልህቅ ማድረግ ስለቻለ ብቻ ነው፡፡ እንደ በፊቱ አጀማመር “የፉገራ” የውስጥ ማሻሻያና የቀባ ቀባ ለውጥ ላድርግማ ቢል ኖሮ ተጨማሪ የሕዝብ ማዕበል ግንባሩን ሙሉ በሙሉ ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓተ መንግሥቱንም ቢሆን በጅምላ ከመጠራረግ አይመለስም ነበር፡፡
አሁንም ግን ድሉ ገና ነው የሚያስብሉና ያፈጠጡ ቀሪ ተግባራት አሉ፡፡ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፉ፣ ብሎም በሰላምና በአገራዊ ደኅንነት ረገድ ከፍ ያለ ሥራ ከፊት ለፊት አለ፡፡ ምርጫና የፖለቲካ ውድድርን በተቃና መንገድ ለማካሄድም እነዚህ ወሳኝ ተግባራት ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡም ሙሉ ትኩረቱን በእነዚህ ላይ ማስቀደም ይኖርበታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአገሪቱ ከመልካም አስተዳደር ጥሰት፣ ከሰብዓዊ መብት መጓደል፣ ከፍትሕ ዕጦት፣ ከሙስናና የተደራጀ ዘረፋ ብሎም በመንግሥት ሥልጣን ያላግባብ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ በየአካባቢው በሕዝብ በደረሰ በደል ላይ ተጠያቂነት መጀመሩ ለለውጡ ሌላ ማርሽ እንደሚቀይር የታመነ ነው፡፡ ተጠናክሮ መቀጠሉ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ፊትም እንዳያገረሽ ሥርዓታዊ ዋስትና እየሰጡ መሄድም ግድ ይላል፡፡
በአጠቃላይ ለማንም ቢሆን “ለውጡ ይጎተት እንደሆነ እንጂ አይቀለበስም” ብሎ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ግን ይህ ዕውን እንዲሆን የተለያዩ የዴሞክራሲ ኃይሎችና ሕዝቡ ሚናቸው አሁን ከሚታየውም በላይ መጠናከር አለበት፡፡ በእርግጥ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት የተለያዩ ጉልህ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑ በጎ ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል አጥፊ አመራር፣ ፈጻሚና ባለሀብት ካለ በመረጃ ላይ ተመሥርቶ የሚጠየቅበት ሥርዓት መዘርጋቱ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም አካባቢና በየደረጃው መከናወን አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊ ትግሉ መፈርጠምም ይኖርበታል፡፡ የሕግና የመዋቅር ማሻሻያ ሥራውም በጅምሩ ቢያኮራም፣ በተግባር መታገዝ ግድ ይለዋል፡፡
በሌላ በኩል በየደረጃው የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል የሚችሉ፣ የአገር ፍቅር ስሜትና የሕዝብ ተቆርቋሪነት ያላቸው ምሁራንና አመራሮችን ከሁሉም አከባቢ ሕዝቡን በማስተቸት ጭምር ወደ ኃላፊነት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም በመዋቅሩ ውስጥ ተወሽቆ በየደረጃው ለውጥ እያደናቀፈ፣ በተለመደው አሠራር እየተንገታገተና እያስመሰለ መቀጠል የሚሻውንም መጥረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህም በመዋቅርና በአሠራር እየታጀበ መቀጠል አለበት፣ ይኖርበታልም፡፡
በመሠረቱ የተጀመረው ለውጥ ለሕዝቡም ቢሆን የተዛቡና የተሳሳቱ አመለካከቶችን አውልቆ በመጣል የተስተካከለ ዕይታ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ የተጭበረበረ ምርጫን፣ አስመሳይነትን፣ ነፃነት ማጣትና በፖለቲካ እምነት ምክንያት መዋከብ፣ መታሰርና ያልተገባ ስደትን እንዳይቀበል ያደርገዋል፡፡ ትውልዱ ሞጋችና ለመብቱ የማይዘናጋ በማድረግ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈትም ያስችላል፡፡ ከሁሉ በላይ ጥቂቶች ያሻቸውን እየዘረፉና እየፈጸሙ፣ ሌላው ደግሞ በድህነትና ችግር ሲላጋ የሚኖርበትን የዘረፋና የውንብድና ምዕራፍ ለመቋጨት የሚረዳ ብቻ ሳይሆን፣ ይበልጥ የሚያጋልጥ የታሪክ ምዕራፍ ላይ አድርሶናል፡፡
ለሁሉም የለውጡ ስኬት መለኪያ የሕዝብ ንቁ ተሳታፊነት ሲሆን፣ ይህም በተጨባጭ በተዘረጉት ሰፊ የዴሞክራሲ መድረኮች እየተረጋገጠ እንዲሄድ ማድረግ ተገቢ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ለውጡ እንኳን ከመቀልበስ ከመዘግየትም የሚወጣው እነዚህ ሥራዎች ሲጠናከሩ ብቻ ናቸው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡