በተመስገን ተጋፋውና በሔለን ተስፋዬ
123ኛው ክብረ ዓድዋ ድግስ (ፌስቲቫል) በተለያዩ ዝግጅቶች ሊዘከር ነው፡፡ በክብረ በዓሉም ከሆሊውድ የመጡ ሦስት የተመረጡ አጫጭር ፊልሞችን ጨምሮ ስድስት ዋና ዋና ዝግጅቶች ይኖራሉ ተብሏል፡፡
የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ከምኒልክ አደባባይ እስከ ዓድዋ ድልድይ ድረስ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ጥንታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ የባዶ እግር ጉዞ መኖሩንም የሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይንመንት ባለቤት አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን ተናግሯል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከታሪኩ ለመጋራትና የጥንት አባቶቻችንን ለማስታወስ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዝክሩ፣ የአገር ውስጥ ፊልሞች ሂስ ይሰጥባቸዋል፣ በሌላ በኩል ከዲኤስቲቪ እና ከኬንያ የፊልም ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ከተለያዩ ቴሌቪዥን ተቋማትና ከማኅበራት ለተመረጡ 20 ፕሮዲውሰሮች ሥልጠና ይሰጣል፡፡
የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በጣይቱ ሆቴል የዋዜማ ዝግጅት ተካሂዷል፡፡ በዝግጅቱም ሙዚቃዊ ተውኔት አንጋፋና ታላላቅ እንዲሁም ወጣት አርቲስቶችና ከ300 በላይ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከደራሼ፣ ከጅንካ፣ ከጎንደርና ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በዝክረ በዓሉም ላይ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጥናታዊ ጽሑፍና የሊቃውንተ ጉባዔ (ኢመደበኛ ባልሆነ መልኩ) እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከየካቲት 16 እስከ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚቆይ ጥንታዊ አባቶችን የሚያስታውስ የሥዕል ኤግዚቢሽን ይካሄዳል፡፡
ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴመንት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ከየካቲት 8 እስከ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር መሰናዶውን አጠናቋል፡፡
ዝክሩም የታሪኩ ከፍታ የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችልና ለመጪውም ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያግዙ ይዘቶች ያሉት መሆኑ ተነግሯል፡፡