የጀርመን መንግሥትና በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በሶማሌና በአፋር ክልሎች ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ 30 ተሽከርከሪዎችን ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሃሪያ አብዱላሂ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አስረከቡ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ የተረከቧቸው እነዚህ ተሽከርካሪዎች በሁለቱም ክልሎች ለሚንቀሳቀሱ የጤና አጠባበቅና የተመጣጠነ ምግብ አገልግሎት አቅራቢ ቡድኖች መገልገያ እንደሚውል በጀርመን ኤምባሲ የልማትና የሰብዓዊ ቢሮ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጊላን ሚልሳን በሁለቱም ክልሎች የሕፃናት ጤና አጠባበቅና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከክልሎች አጋሮች ጋር በመተባበር ሕፃናቱ የሕይወት አድን ሕክምናና የተመጣጠነ ምግብ ዘለቄታዊ ባለው መልኩ የሚያገኙትን ሁኔታ እንደሚያጠናክር አስረድተዋል፡፡
በጀርመን ኤምባሲ የጀርመን ዴቨሎፕመንት ኮኦፕሬሽን ኃላፊ ሚስተር ሀንሰፒተር ሸዋር፣ ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በሁለቱም ክልሎች ለሚገኙ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች የሚውል የጤና አገልግሎት ለማቅረብ በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ላይ ዩኒሴፍ ከጎኑ መቆሙን ገልጸዋል፡፡
በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ የተመጣጠነ የምግብና የጤና አገልግሎት አቅራቢ ቡድኖች የተቋቋሙት እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. መሆኑን ቢሮው አመልክቶ ለሕፃናቱና በአጠቃላይ ለችግር ተጋላጭ ለሆነ ማኅበረሰቦች ጤና፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ የውኃና የሳኒቴሽን አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አስረድተዋል፡፡