Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊሲቪል ማኅበራትን ያነቃቃ አዋጅ

ሲቪል ማኅበራትን ያነቃቃ አዋጅ

ቀን:

የተሻሻለው የሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ 1113/2011 ዓለም አቀፍና አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመተጋገዝ ልምድና ተሞክሮ የሚለዋወጡበትን፤ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከልና የአካል ጉዳተኞች ድርጅቶች፣ የአድቮከሲና የግንዛቤ ማስረጽ ተግባራትን በስፋት ለማከናወን የሚያስችላቸውን ጥሩ መደላደል መፍጠሩን አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሙያ ማኅበራት ተወካዮች ይገልጻሉ፡፡

ተወካዮቹ ይህንን ያስታወቁት ‹‹የማኅበራዊ ድርጅቶች ተወካዮች ለአዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብና ማኅበራት አዋጅ መተግበር፣ ለዘርፉ መነቃቃት የሚጫወቱት አዎንታዊ ጎንና የሲቪክ ማኅበራት ሚና›› በሚል ርዕስ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

አስተያየታቸውን ካንፀባረቁት ተወካዮች መካከል የቮለንቲር ሰርቪስ ኦቨርሲስ ካንትሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ ራሔል ገብረማርያም እንደገለጹት፣ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለየ አቅምና ልምድ ሲኖራቸው አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ኅብረሰቡን ጠጋ ብለው ከማወቅና ከመረዳት አኳያ የተሻሉ ናቸው፡፡

- Advertisement -

የተሻሻለው አዋጅ በሰጠው የሥራ ነፃነት መሠረት ሁለቱም ድርጅቶች በመቀናጀት ጠያቂ ኅብረተሰብ ከመፍጠር በተለይም ዝቅተኛው ኅብረተሰብ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስኮች የጎላ ተሳትፎ እንዲያደርግና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አስረድተዋል፡፡ ዝቅተኛው ኅብረተሰብ ደግሞ በተጠቀሱት መስኮች ተጠቃሚነቱ ከተረጋገጠ በአገሪቱ የተሻለ የሰላም ሁኔታ እንደሚሰፍን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ አዋጅ፣ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶች ገንዘብ ከመለገስና በቀጥታ ትግበራ ውስጥ ከመሳተፍ ውጪ ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር ተቀናጅተው የመሥራትን ሁኔታን እንደማያበረታታ፣ በዚህም የተነሳ አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተዳክመው ቆይተዋል፡፡

‹‹በቀድሞው አዋጅ ያልተካተተው፣ በተሻሻለው አዋጅ የተቀመጠውና ትልቅ ቦታ የተሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራን የማበረታታት ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ራሔል፣ በጎ ፈቃደኝነት በዓለም ላይ ትልቅ ኃይል እንዳለው፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን ከማሳካት አኳያ ሚናው ትልቅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ይህንን የበጎ ፈቃደኝነትን ሥራ ከማስፋፋት አኳያ የተሻሻለው አዋጅ ጥሩ ትኩረት እንዲሰጠው፣ በአጠቃላይ ዴሞክራሲን ከመፍጠርና ከማጎልበት አኳያ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው መታወቅ እንደሚኖርበት ካንትሪ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ኦክስፋም ዓለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ከበደ ናቸው፡፡ አቶ ገዛኸኝ የተሻሻለው ሕግ ከቁጥጥር ወደ ክትትል በሚል መንፈስ ላይ የተቃኘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህም ሊወደስ እንደሚገባ ጠቁመው፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ከሦስቱ ምሰሶዎች ማለትም ከመንግሥት፣ ከግሉ ዘረፍና ከመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ አራተኛው ምሰሶ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ዘርትሁን ተፈራ የሲቄ ውመንስ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ተወካይ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ዘርትሁን ‹‹በሴት ጥቃቶች ዙሪያ ለመሥራት ብንፈልግም ተጠቂዎችን መርዳት እንጂ ጥቃቶቹ እንዳይፈጸሙ የመከላከል ዕድል አልነበረንም፣ የተገደበ ከፍተኛ ችግር ነበረብን፡፡ አሁን ግን ይህ ዓይነቱ ዕድል በመገኘቱ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

ሴቶችን በኢኮኖሚ የማጎልበት ሥራ ቢከናወንም፣ አቅማቸው ሲጎለብት ግን ባላቸው ንብረት ላይ መብታቸውን እንዴት ማስጠበቅ እንዳለባቸው አይነገራቸውም ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ሥራው በአግባቡ ይከናወን ነበር ለማለት እንደማይቻል ገልጸው፣ የቀድሞው ሕግ የዚህ ዓይነቱን ችግር ዕልባት መስጠት በሚቻልበት መልኩ በመሻሻሉ እንደ ትልቅ ድል የሚቆጥሩት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚሠራና ኖቪድ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ሙላቱ፣ የቀድሞው አዋጅ የሰብዓዊ መብቶችን በመገደቡ የተነሳ የመንግሥት ገጽታ እንዳበላሸ፣ በተቃራኒው ደግሞ የተሻሻለው አዋጅ 1113/2011 የመንግሥትን ገጽታ እንዳደሰው አስረድተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካል ጉዳተኛ መብት ኮንቬንሽንን (ኮንቬንሽን ዘ ራይትስ ኦፍ ፐርሰንስ ዊዝ ዲዝኤቢሊቲ) ኢትዮጵያ ተቀብላ ከስምንት ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማፀደቅ የአገሪቱ የሕግ አካል ማድረጓን፣ በጊዜውም ይኼ አዎንታዊ ዕርምጃ ተብሎ ከፍተኛ የሆነ አድናቆት ተችሮት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን እስከዛሬ ድረስ ሥራ ላይ እንዳልዋለ አዋጁ ከመፅደቁ በዘለለ አካል ጉዳተኞችን እንዳልጠቀመ፣ የአካል ጉዳትኛ ድርጅቶችንም እንዳላጠናከረ፣ አመልክተው፣ የተሻሻለው ሕግ በዚህ በኩል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ እንደታመነበት ገልጸዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች የተሻሻለውን ሕግ በመጠቀም በመብቶችና በአድቮኬሲ ላይ ጠንክረው መሥራት ከቻሉ የፖሊሲ ለውጥና የሕግ የበላይነት ሊያመጡ እንዲሁም የአገርን ገጽታ ሊገነቡ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) ‹‹አዋጅ ቁጥር 621/2011 የሙያ ማኅበራት ለአባላት ጥቅም ብቻ ነበር እንድንሠራ የፈቀደልን፡፡ ይኼ ደግሞ ከእኛ የሙያ ሥነ ምግባር አንጻር ትክክል አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የተጠቀሰው አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ችግሮችን አሳልፈናል፡፡ የተሻሻለው አዋጅ ግን የሙያ ማኅበራት የአባሎቻቸውን መብት ከማስጠበቅ ባሻገር የሙያውን ሥነ ምግባር ማሳደግና ለሦስተኛ ወገንም በቅን ልቦና ለማገልገል የሚመያስችል አካሄድ አስቀምጧል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል የግል አማካሪና የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ አርቃቂ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ ዙሪያ ባደረጉት ገለጻ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ በውስጡ የውጭና አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የሙያ፣ የወጣትና የሴቶች ማኅበራትን፣ ኅብረቶችንና ኔትወርክ፣ የተባሉትን በሙሉ ያጠቃልላል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ የሕግ ተፈጻሚነት ወሰን ከበፊቱ የተለየ እንደሆነ፣ በዚህም መሠረት አንድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀት በሁለትና ከዛ በላይ ባሉ ክልሎች ውስጥ የሚሠራ ወይም የሚንቀሳቀስ ከሆነ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ሕግ፣ በአንድ ክልል ብቻ ከተንቀሳቀሰ ክልሉ በሚያወጣው ሕግ መሠረት ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶትና ማኅበራት ኤጀንሲ በተሻሻለው አዋጅ አጠራር ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ›› ተብሏል፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲሆን በፊት ግን በሰላም ሚኒስቴር ስር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ኤጀንሲው ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ 11 የቦርድ አባላት እንዳሉት፣ የቀድሞው ቦርድ በአብዛኛው ትኩረቱ ቁጥጥር ላይ እንደነበር፣ የአሁኑ ቦርድ ግን አብዛኛው ትኩረቱ የዘርፉን አቅም በመገንባት፣ በማስተባበርና ለአገር ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኣ በመርዳት መልኩ እንዲሆን መደረጉንና ዝርዝር የሆኑ ሰፊ ሥልጣኖችም እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡

ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ነገሮች ከባድ ሳይሆን በጣም ግልፅና ቀላል መለኪያዎች እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ አንድ ድርጅት በ30 ቀናት ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት፣ ኤጀንሲው በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ መጠየቅና ለቦርድ ማቅረብ፣ ከቦርዱም አልፎ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንደሚቻል ታውቋል፡፡

መሠረታዊ ለውጥ የተደረገበት ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሥራ ነፃነትን በሚመለከት ነው፡፡ የከዚህ ቀደሙ ሕግ በሚያገኙት የገቢ ወይም የገንዘብ ምንጭ መሠረት በዚህ ሥራ መሥራት ትችላላችሁ፣ በዚህ ሥራ መሥራት አትችሉም የሚል ገደብ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ዓይነቱ ገደብ እንደተነሳ፣ በምትኩ የተቀመጠው አንድ መለኪያ ብቻ እንደሆነና እሱም የሚሠራው ሥራ ሕጋዊ ነው? አይደለም? የሚለውን ብቻ ማየትና ይህንንም የሚያየው ኤጀንሲው ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ልምዶችን መሠረት በማድረግ ሊሠራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የመጠየቅ፣ የመቀበልና የመጠቀም መብት እንዳላቸው በተሻሻለው አዋጅ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠ ከዚህ ቀደም 70/30 የነበረው 20/80 ሆኖ መውጣቱን ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡

አንድ ድርጅት ለተወሰነ ጊዜም ላልተወሰነ ጊዜም አንድ ጊዜ ከተቋቋመ ወይም ከተመዘገበ እንደ ከዚህ በፊቱ በየሦስት ዓመቱ እየጠሩ እንደገና ፈቃድህን አድስ፣ ቃልም እንግባ ይባል የነበረው አካሄድ ቀርቷል፡፡ አንዴ ከተመዘገበ የሚጠበቅበት ቢኖር በየዓመቱ ሪፖርት ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ተጠያቂነቱም እስከ መዘጋትና እስከ ማፍረስ ሊደርስ ይችላል፡፡

አንድን ድርጅት ማገድ የሚቻለው የኤጀንሲው ዳይሬክተር ሲሆን፣ ዕገዳው ያረፈበት ድርጅት ለቦርዱ ይግባኝ ማለት ይችላል፡፡ ከዚህም ሌላ የአንድን ድርጅት መፍረስ የሚወስነው ቦርዱ ነው፡፡ በውሳኔው ቅሬታ ያደረበት ድርጅት ፍርድ ቤት ይግባኝ የመጠየቅ መብት አለው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የሚመዘገብ ድርጅት የምክር ቤቱ አባል መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሕግ የተካተተውና በፊት ያልነበረው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ ነው፡፡ ዋና ዓላማውም ለሦስተኛ ወገንና ለአገር ጥቅም፣ ጥሩ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው ለሚታሰቡ ድርጅቶች ድጋፍ ለማድረግ የበኩሉን እገዛ የሚያደርግ ነው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ሕግና ሥርዓትን አክብረው በመንቀሳቀስ የሕዝቡን የላቀ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት መድረክ ሊቀመንበር አቶ ነጋሽ ተክሉ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ጉዳዩ በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ለፀደቀው ለዚሁ የተሻሻለው አዋጅ የመድረኩ አባል ድርጅቶች አማራጭና ጥሩ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦቻቸው የተካተቱበት 46 ገጽ ሰነድ በማቅረብና ከሕግ አርቃቂው ምክር ቤት ጋር በመወያየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...