ያላለሙ ይነጠቃሉ ተብሏል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ውስጥ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች የመሬት ሊዝ ውላቸውን እንዲያድሱ፣ የቤቶች ግንባታ በማካሄድ ላይ ያልሆኑት ደግሞ የሊዝ ውላቸው ተቋርጦ የወሰዱት ይዞታ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ወሰነ።
የከተማ አስተዳደሩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሪል ስቴት ዘርፍ ላይ የዳሰሳ ጥናት እንዲያካሄድ ያቋቋመው ግብረ ኃይል፣ ተልዕኮውን ፈጽሞ የዳሰሰ ጥናት ግኝቱን ረቡዕ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ለአስተዳደሩ ካቢኔ ካቀረበ በኋላ ነው።
የተቋቋመው ግብረ ኃይል የዳሰሳ ጥናቱን ያከናወነው የሪል ስቴት ኩባንያዎችን ፋይል በመገምገም፣ በሳይቶች ላይ ምልከታ በማድረግና መጠይቆችን በመጠቀም፣ እንዲሁም የሪል ስቴቶቹን የሕግ አግባብነት፣ የሊዝ ውልና የግንባታ ደረጃ በማጣራት መሆኑ ተገልጿል።
በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ከተፈቀደላቸው ይዞታ በላይ አስፋፍተው መሬት የያዙ ኩባንያዎች መኖራቸው፣ የሊዝና የቤት ግብር ያልከፈሉ እንደሚገኙ፣ ግንባታ ጀምረው ያቋረጡ፣ የተፈቀደላቸውን መሬት ከሪል ስቴት ልማት ውጪ ለሆነ ዓላማ የተጠቀሙ፣ ለሪል ስቴት ልማት ተብሎ የተፈቀደላቸውን መሬት ለሦስተኛ ወገን ያስተላለፉና የሸጡ መገኘታቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የከተማ አስተዳደሩ ግብረ ኃይሉን ያቋቋመው፣ ከሪል ስቴት አልሚዎች ጋር ከተወያየ በኋላና በግብረ ኃይሉ ውስጥም ኩባንያዎቹ በአባልነት ተወክለው እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም የቀረበው የዳሰሳ ጥናት በዘርፉ ያለውን ችግር ያመለካተ እንደሆነና የከተማ አስተዳደሩም በቀረበው ግኝት ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ አስረድተዋል።
ውሳኔዎቹ ዘርፉን ከመደገፍ አንፃር የተቃኙና ሕግን የማስከበር ኃላፊነትንም ያልዘነጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ግንባታ ጀምረው ለረጅም ዓመታት ማጠናቀቅ ያልቻሉትን መደገፍ እንደሚገባ በማመን፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መወሰኑን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ መሬት ወስደው ግንባታ ያልጀመሩና መሠረት ብቻ አውጥተው ወደ ግንባታ ያልገቡ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ይዞታ ተነጥቆ ወደ መሬት ልማት ባንክ ገቢ እንዲደረግ፣ ተመላሽ የተደረገውም መሬት የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ላይ እንዲውል መወሰኑን ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አልሚዎቹ ለተባለው ዓላማ ከወሰዱት የመሬት ይዞታ ጋር በተገናኘ በርከት ያሉ የሕገወጥነት ድርጊቶች በመስተዋላቸው፣ ይኼንን ለማስተካከል የመሬት ሊዝ ውላቸውን እንዲያድሱ መወሰኑን አስረድተዋል።
የመሬት ሊዝ ውላቸውን እንዲያድሱ የሚጠበቅባቸው በሪል ስቴት ልማቱ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙትና ድጋፍ ተደርጎላቸው መቀጠል የሚችሉ መሆናቸው ታምኖ የሚለዩት እንደሚሆኑ ምክትል ከንቲባ ታከለ አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 139 ሪል ስቴት ኩባንያዎች በአጠቃላይ ከአሥር እስከ 50 ሔክታር የሚደርስ መሬት ወስደዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በአጠቃላይ 560 ሔክታር መሬት የተረከቡ ሲሆን፣ እስካሁን 9,963 ቤቶችን ለደንበኞቻቸው አስረክበዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም. በተደረገ ማጣራት 19 ኩባንያዎች ችግር እንዳለባቸው በመረጋገጡ የሊዝ ውላቸው የመከነ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በከተማው 120 ሪል ስቴት ኩባንያዎች በሥራ ላይ ናቸው፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ዕቅድ መሠረት የሪል ስቴት አልሚዎች እስካሁን ማስተላለፍ የነበረባቸው 27 ሺሕ ቤቶችን ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ያስተላለፉት አሥር ሺሕ የማይሞሉ ቤቶችን ብቻ እንደሆነና በአሁኑ ወቅት 16 ሺሕ የሪል ስቴት ቤቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ያመለክታል፡፡