Saturday, April 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በሐሳብ ልዩነት ውስጥ መኖር መቻል ሥልጣኔ ነው!

ዴሞክራሲ ማለት የተለያዩ ሐሳቦች የሚቀርቡበት ገበያ ማለት ነው፡፡ በዚህ የሐሳቦች ገበያ ውስጥ በግልጽነት፣ በነፃነትና በተፎካካሪነት ስሜት የሚቀርቡ የፖለቲካ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን በጥንቃቄና በሰላማዊ መንገድ ይወጣሉ፡፡ ዴሞክራሲ ማለት በሐሳብ ልዩነት ውስጥ መኖር ማለት ሲሆን፣ የተለያዩ ሐሳቦች ጠብና ግጭት ሳያስፈልጋቸው በነፃነት የሚፎካከሩበት ነው፡፡ እዚህ ገበያ ውስጥ የሚቀርቡ ሐሳቦች በሙሉ ለሕዝብ የህሊና ዳኝነት የሚቀርቡ በመሆናቸው፣ ተፎካካሪ ኃይሎች በሰላማዊና ጨዋነት በተሞላበት መንገድ የሕዝብ ብያኔ መጠበቅ ግዴታቸው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የጨዋታ ሕጉን ጠንቅቀው በሚያውቁ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ሲሆን፣ እነዚህ ኃይሎች የእያንዳንዱ ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን ደግሞ ለሕግ የበላይነት መከበር በአንድነት ይቆማሉ፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ ደኅንነትና የተለያዩ የፀጥታ ኃይሎች በገለልተኝነት ሥራቸውን የሚያከናውኑበት በሕግ የተደገፈ አሠራር እንዲኖር በጋራ ይሠራሉ፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ እንዲያዝ ቁርጠኛ ይሆናሉ፡፡ በልዩነት ውስጥ በመኖር የጋራ ዓላማን ያሳካሉ፡፡

ዴሞክራሲን ስሙን ስለጠሩት፣ የፓርቲ ስያሜ ማዳመቂያ ስላደረጉት፣ በፕሮግራማቸውና በደንባቸው ውስጥ ደጋግመው ስላወሱት ወይም በአስመሳይነት ስለሚታበዩበት ሳይሆን፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ተረድተውት ተግባራዊ ሲያደርጉት ነው ሥርዓት መሆን የሚችለው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ስንቶች ለሐሳብ ነፃነት ዕውቅና ይሰጣሉ? ስንቶች የዴሞክራሲን ጽንሰ ሐሳብ ተረድተዋል? ስንቶች ለተፎካካሪዎቻቸው ዕውቅና ይሰጣሉ? ስንቶች ልዩነቶችን ለማክበር ዝግጁ ናቸው? ስንቶች ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የጨዋታ ሕግ ራሳቸውን አስገዝተዋል? ስንቶች ለሕግ የበላይነት ክብደት ይሰጣሉ? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች ቢቀርቡ ምላሹ አሳዛኝ ነው፡፡ ትልቁ ችግር የሚጀምረው የሐሳብ ልዩነትን ካለማክበር ነው፡፡ ‹እኔ ያልሆንኩት ካልሆነ ገደል ይግባ› የሚል አጉል ጀብደኝነት የተፀናወታቸው ኃይሎች በስፋት ይታያሉ፡፡ የሐሳብ ልዩነትን እንደ ፀጋ ተቀብሎ ለመወያየት፣ ለመከራከር፣ ለመደራደርና ለመስማማት ከመሞከር ይልቅ፣ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እናንተ›› በሚል ፍረጃ ውስጥ ልዩነትን ማስፋትና ቅራኔን ማክረር የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ዴሞክራት ነን ለማለት እንዴት ይቻላል? በሐሳብ ልዩነት ውስጥ መኖር አለመቻል የኋላቀርነት እንጂ የመሠልጠን ምልክት አይደለም፡፡

‹‹የሐሳብ ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› የሚባለው ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብ በነፃነት የማስተላለፍ ተፈጥሯዊ ነፃነት እንዳለው ለማመላከት ነው፡፡ ይህንን ነፃነት ለአንዱ ሰጥቶ ለሌላው መንፈግ ከቶውንም አይቻልም፡፡ ለጊዜው ጉልበተኞች ይህንን ማድረግ ቢችሉም መዘዙ የከፋ እንደሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን አንድ ጤነኛ የሆነ ሰው የሚፈልገውን አስተሳሰብ በነፃነት ሲያንፀባርቅ ኃላፊነት እንዳለበት አይዘነጋም፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች በነፃነት ሲነጋገሩ ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይግባባሉ፡፡ እነዚህ መግባባቶች በተለይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ለመፎካከር የሚያግዙ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ለማበጀት፣ የመጫወቻ ሜዳውን ለማመቻቸት፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ዓውድ ለመፍጠር ይጠቅማሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ መግባባት ሲቻል የሲቪልና የዴሞክራሲ ተቋማት እያበቡ የሕዝቡን ንቃተ ህሊና ከማጎልበት በተጨማሪ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ያቀርባሉ፡፡ የመገናኛ ብዙኃን በገለልተኝነት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤቶች በነፃነት ይሠራሉ፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዳችም ልዩነት ሳይኖር ሕግ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ለጠብና ለግጭት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይወገዳሉ፡፡ በልዩነት ውስጥ መኖር ባህል ይሆናል፡፡

ሰባተኛው የአገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ሰሞኑን ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተቋሙን በጅምላ በመፈረጅ ስሙን ማጥፋት እንደማይገባና ስህተቱን እንዲያርም በመጠቆም ማገዝ ይገባል ብለዋል፡፡ ከለውጡ ወዲህ እየተገነባ ያለው የመከላከያ ሠራዊት የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጠብቅ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ነገ እናንተ በምርጫ አሸንፋችሁ ሥልጣን ስትረከቡም ተግባሩን የሚቀጥል ነው፤›› ብለዋል፡፡  የመከላከያ ኃይሉ በየጊዜው ከሚወጣውና ከሚወርደው ጋር እንዳይወርድ በገለልተኝነት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡት ቃል በተግባር የሚከበር ከሆነ ታላቅ የምሥራች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት መዋቅሮች፣ የፀጥታ ተቋማትና ሌሎችም ከፓርቲ ፖለቲካ ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ ተላቀው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚመረጥ መንግሥትን ብቻ እንዲያገለግሉ ከተደረገ፣ ለአገሪቱ አንድ ትልቅ ዕርምጃ ይሆናል፡፡ የፓርቲና የመንግሥት ሚና እየተደበላለቁ የደረሰው ሥቃይና መከራ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ በመውጣት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት፣ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ለጨዋታው ሕግ መገዛት አለባቸው፡፡ ከጉልበተኛ አካሄድ ራስን ሙሉ በሙሉ ማስወጣት፣ ጠመንጃን ከፖለቲካው ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ፣ ለሐሳብ ነፃነት ትልቅ ሥፍራ መስጠት፣ ከተለመደው የጥላቻና የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ በፍጥነት መውጣት፣ ለሠለጠነ ፖለቲካ ቦታውን መልቀቅና የመሳሰሉትን ማሰብ ይገባል፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት ስላልሆነ ደፈር ማለት ይገባል፡፡

አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተስፋ እየታየ ነው፡፡ ይህ  ተስፋ እያበበና እየጎመራ የሚሄደው ግን ዴሞክራሲያዊ ጽንሰ ሐሳብን በሚገባ በመገንዘብ ለተግባራዊነታቸው በመትጋት ብቻ ነው፡፡ ይህ ጽንሰ ሐሳብ እኩልነት፣ ተጠያቂነት፣ የሕዝብ ተሳትፎ፣ የሕግ የበላይነት፣ የፖለቲካ መቻቻል፣ ግልጽነት፣ የኢኮኖሚ ነፃነትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች ማከናወን የሚቻለው ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ለሐሳብ ነፃነት ትልቅ ሥፍራ ሲሰጡ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ማለት በሐሳብ ልዩነት ውስጥ መኖር መቻል ነው ሲባል፣ እየመረረንም ቢሆን የማንቀበለው ሐሳብ በነፃነት እንዲስተናገድ ጠበቃ እንድንሆን ግዴታም ይጥልብናል ማለት ነው፡፡ በአፍ ዴሞክራት በድርጊት ደግሞ ጉልበተኛ እየሆኑ እዚህና እዚያ መርገጥ ሸፍጠኝነት ነው፡፡ በዚህ ሸፍጠኝነት የተካኑ አስመሳዮች ሕዝብን አንዴ ማታለል ቢችሉ እንኳ፣ እየደጋገሙ ማታለል አይችሉም፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ የመጨረሻው ዳኛ እሱ ስለሆነ፣ ለሕዝብ ፍላጎት መገዛት ይገባል፡፡ የፖለቲከኞች ጥበብ የሚጀምረው ደግሞ ሕዝብን ከማክበር ነው፡፡ ሕዝብን በልብ እየናቁ በአፍ መደለል አይቻልም፡፡ ሕዝብ ብዙ ነገሮችን ያውቃል፡፡ ይልቁንም በሐሳብ ልዩነቶች ውስጥ ሆኖ የተሻለ ሐሳብ በማመንጨት የሕዝብን ልብ መግዛት ያስከብራል፡፡ ስለዚህ በሐሳብ ልዩነቶች ውስጥ መኖር መቻል ሥልጣኔ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት የእያንዳንዱ ፖለቲከኛ ግዴታ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት 27.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 ሂሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 27.5...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...