Tuesday, December 5, 2023

ሕጎችን የማሻሻል ተስፋና ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ዘንድ በተደጋጋሚ ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች ዋነኛውና አንዱ፣ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በአገሪቱ እየተሠራባቸው የሚገኙ በርካታ ሕጎች እንዲሻሩ አልያም እንዲሻሻሉ የሚለው ይገኝበታል፡፡

የፖለቲካ ልሂቃኑና የተቃውሞ ጎራው ፖለቲከኞች ሕጎች እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሻሩ የመወትወትና የመታገል ጉዳይ በበርካታ የዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም አገሮች ጭምር ሲስተገባና ከመንግሥት ጋር ሲያወዛግብ የነበረ ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም የሕግ መሻርን አልያም ማሻሻልን ጉዳይ በተመለከተ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ከመንግሥት በኩል ሲሰጡ የነበሩት ምላሾች ተመሳሳይ የነበሩ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ አብዛኞቹ ሕጎች ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው የዓለም አገሮች መቀዳታቸውን፣ የኢትዮጵያ ሕጎችም በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ምርጥ ሕጎች መካከል የሚመደቡ መሆኑን በመጥቀስ፣ የሚቀርቡትን ጥያቄዎችንም ሆነ ወቀሳዎችን ጆሮ ዳባ ልበስ ይላቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን የመንግሥት ምላሽ ተመሳሳይ የነበረ ቢሆንም፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃንና የተቃውሞ ጎራው ፖለቲከኞች ግን የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ፣ የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት አዋጆችን በመንቀስ መሻሻልና መሻር እንዳላባቸው ከመሞገት አልቦዘኑም ነበር፡፡

እነዚህ ሕጎች እንዲሻሩ አልያም እንዲሻሻሉ የሚወተውቱበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ፣ ሕጎቹ አፋኝ በመሆናቸው የተነሳ የፖለቲካ ሥራን ለማከናወን እንቅፋት ናቸው ከሚል መከራከሪያ ነጥብ አኳያ ነበር፡፡

በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅን በመጥቀስ የሚሟገቱ ፖለቲከኞች አዋጁ ለቦርዱ በሰጠው ሥልጣን፣ በቦርዱ አወቃቀርና አባላት ምክንያት በገለልተኝነት ምርጫዎችን ማስፈጸም አይችልም ይሉ ነበር፡፡ እንዲሁም ቦርዱ ለገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ያደላል የሚለው የሚጠቀስ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ለመከወን ስለሚቸገሩ ገዥውን ፓርቲ መፎካከርም ሆነ አማራጭ ሆኖ ለመውጣት ዕድል ይነፍጋል የሚለው ክርክርም በተደጋጋሚ ሲደመጥ የነበረ ሙግት ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት የዘለቁት እነዚህ ጥያቄዎችና ውትወታዎች በከፊልም ቢሆን የይሁንታ ምላሽ ያገኙት ላለፉት ሦስት ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ አገሪቱ ያጋጠማትን አለመረጋጋት ተከትሎ፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሕጎችን ለማሻሻልና  ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ፈቃደኝነቱን ከገለጸ ወዲህ ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሲጀመር 22 በሒደት ግን ቁጥሩ ዝቅ ብሎ 15 ከሚደርሱ አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች ጋር፣ ከሁለት ዓመት በፊት ድርድር ጀምሮ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በወቅቱ 13 ያህል የድርድር አጀንዳዎች ተለይተው ድርድሩ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፣ አምስተኛ አጀንዳ ሆኖ በተያዘው ብሔራዊ መግባባት ላይ ድርድር ተጀምሮም ነበር፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ባደረገው የአመራር ለውጥ ምክንያት ድርድሩ ተቋርጦ እስካሁንም በእንጥልጥል ላይ ነው፡፡

በመቀጠል ግን የገዥው ፓርቲ አመራርን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር እንደሚያሰፉና አፋኝ ሕጎችን እንደሚያሻሽሉ ቃል ገብተው የተለያዩ ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ሆኑ የተቃውሞ ጎራው አባላት በተፈጻሚነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ቢገልጹም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔና የገቡትን ቃል አወድሰውት ነበር፡፡ በተለይ የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎችንና ምሁራንን በመጋበዝ የአገሪቱን ሕጎች ለማሻሻል ምክር ቤት ማቋቋማቸው ሙገሳን አትርፎላቸዋል፡፡

ሕጎችን ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ እየተገለጸ ሲሆን፣ ከገለልተኝነት ጋር ጥያቄ የሚቀርብበትን የምርጫ ቦርድን መልሶ ለማቋቋም ያለመው ረቂቂ አዋጅ ባለፈው ሳምንት  ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቀርቧል፡፡

ረቂቂ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ የተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየትን እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን፣ ከቦርዱ አባላት ስብጥር አንፃር መልካም ጅማሮ እንደሆነ የሚገልጹ እንዳሉ ሁሉ ሕጉ አብዛኛው የአደረጃጀት ጉዳይ እንጂ፣ የምርጫ ሥርዓቱን አልተመለከተም የሚሉ ትችቶችም እየቀረቡበት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው የቦርድ አባላት ቁጥር ዘጠኝ ሲሆን፣ አሁን ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ የቦርዱ ማሻሻያ አዋጅ የአባላቱን ቁጥር ወደ አምስት ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርዱን አባላት የሚመለምል ኮሚቴ እንደሚያዋቅሩም ረቂቂ አዋጁ ያትታል፡፡

በዚህ መሠረት የቦርዱን አባላት የሚመለምለው ገለልተኛ ኮሚቴ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ላይ ከሚሠራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንዲሁም ከሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚመረጡ አንዳንድ አባላት የሚኖሩት ሲሆን፣ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ደግሞ አራት ሰዎች እንደሚወከሉ ረቂቅ አዋጁ ያትታል፡፡

የቦርዱ አባላት ሆነው የሚመረጡት ደግሞ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟሉ እንደሆኑ ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ በረቂቅ አዋጁ የተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎችም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው፣ በሚሾምበት ጊዜ የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነና ላለፉት አምስት ዓመታት የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ከፍተኛ አመራር ያልነበረ፣ ከምርጫ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ባላቸው በተለይም በሕግ፣ በፖለቲካ ሳይንስ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በስታትስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያለው፣ መልካም ሥነ ምግባርና ሰብዕና ያለው፣ ዕድሜው ከ30 ዓመት በላይ የሆነ፣ እንዲሁም ሆነ ተብሎ በተፈጸመ ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የማያውቅ የሚሉት ናቸው፡፡

እነዚህንና መሰል ከቦርዱ አደረጃጀት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ለዓመታት የዘለቀውን የፖለቲካ ልሂቃን፣ እንዲሁም የተቃውሞ ጎራው አባላት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት መጀመሩን የሚያሳይ ነው ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ፣ ረቂቅ አዋጁ ግማሽ ቁንጮ ግማሽ ልጩ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡

ረቂቅ አዋጁ የሚጠበቅበትን ያህል የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥያቄና ፍላጎት እንዳላሟላ የሚገልጹት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ፣ ‹‹ነገር ግን ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ማለት አይቻልም፤›› በማለት ለሪፖርተር ሐሳባቸው አጋርተዋል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም አዋጁ ችግር እንዳለበት በማንሳት በፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር መድረክ ጉዳዩን አቅርበን ድርድር ስናደርግበት የነበረ ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ አሁን በረቂቅ አዋጁ ለመሻሻል የቀረበው የቦርዱን አደረጃጀት የተመለከተው ክፍል ብቻ ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 532/99 ላይ የነበረው ችግር ግን ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የምርጫ ሥርዓቱንም የተመለከተ ነገር ጭምር እንጂ፤›› በማለት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ የቦርዱን አደረጃጀት ብቻ ሳይሆን፣ የምርጫ ሥርዓቱም መስተካከል እንዳለበት ይከራከራሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ራሱን ያከሰመው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ የመንግሥትን የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚያሳይና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡

‹‹ዋናው ነገር ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ መሻሻል እንደሚያስፈልገው መታመኑ ላይ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ስንጮህለት የነበረው ጉዳይ በመንግሥት ዕውቅና አግኝቶ እዚህ ደረጃ መድረሱ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላው አሠራሩን ተቋማዊ ማድረግ ነው፤›› በማለት፣ መንግሥት አፋኝ የተባሉትን ሕጎች ለማሻሻል ፍላጎት ማሳየቱ መልካም ጅማሮና አበረታች መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ ዋስይሁን ገለጻ አዋጁን ለማሻሻል የተሄደበት መንገድ በራሱ ችግር አለበት፡፡ ‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዋጅ በዋናነት የሚገዛው ፓርቲዎችን በአጠቃላይ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አዋጅ ላይ ዋና ባለድርሻ አካላት ነን ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በዚህ አዋጅ ላይ እኛ ግብዓት ሰጪ ሳይሆን ተደራዳሪ ነው መሆን የነበረብን፡፡ ነገር ግን አሁንም ይህንን አዋጅ ለማሻሻል ተነሳሽነቱን የወሰደው መንግሥት ነው፡፡ ፓርቲዎች በአዋጁ ይዘት ላይ መደራደር ይገባቸው ነበር፡፡ ያ አልተደረገም፡፡ በአስፈጻሚው አካል የቀረበውን አዋጅ እንደ ማንኛውም አካል ተችተናል፡፡ ነገር ግን አሁን አለ ከሚባለው ለውጥ አንፃር በሚገባው ደረጃ የተደረገ ድርድርም ሆነ ውይይት አልነበረም፤›› በማለት ሙግታቸውን ያቀርባሉ፡፡

ከፖለቲካ ቁርጠኝነት አንፃር አዋጁን የተመለከቱት አቶ የሺዋስ በበኩላቸው፣ ይህ ክስተት መንግሥት አሠራሩን ለማሻሻል የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳለው አመላካች እንደሆነ በመሞገት፣ ቀሪዎቹ የአሠራር ጉዳዮች በሰከነና ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ መቀጠል እንደሚችሉ እምነታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡  

‹‹የመንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ዋናው ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ወ/ሪት ብርቱካንን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መሾም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመኖሩ የተነሳ ሊሆን ችሏል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ተነሳሽነቶች ቁርጠኝነትን የሚያሳዩ ናቸው፤›› በማለት፣ የአዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ከፍተኛ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

ቦርድ ወይስ ኮሚሽን?

ከሁለት ዓመታት በፊት በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል ሲካሄድ በነበረው ድርድር ወቅት፣ ሁለቱንም ወገን ያጨቃጨቀው አንደኛው ጉዳይ ተቋሙ ቦርድ ወይስ ኮሚሽን ተብሎ ይሰየም የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡

በወቅቱ በርካታ የተቃውሞ ፓርቲ አመራሮች ተቋሙ በኮሚሽን ደረጃ እንዲዋቀር ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ኢሕአዴግን በመወከል ሲደራደሩ የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ ‹‹ቦርድ ይሁን የሚለው ጉዳይ አጠቃላይ ምርጫ ከማስፈጸም ጋር ምን ግንኙነት አለው?›› በማለት ተቃውመው ተቋሙ ኮሚሽን ሳይሆን፣ ቦርድ የሚለውን ስያሜ ይዞ መቀጠል እንዳለበት ሞግተው ነበር፡፡

በወቅቱ ተቋሙ ወደ ኮሚሽን እንዲለወጥ ሲሟገቱ ከነበሩት መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ ምንም እንኳን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ እንዳልተመለከቱት ለሪፖርተር ገልጸው፣ ረቂቅ አዋጁ አሁንም ቦርድ በሚለው ስያሜ መውጣቱን መስማታቸውን በመግለጽ ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ በዚህ ረቂቅ አለመካተቱን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ ዋስይሁን ኮሚሽን እንዲሆን የቀረበው የፓርቲዎች ጥያቄ በረቂቁ ተግባራዊ አልሆነም በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ኮሚሽን ወይም ቦርድ የሚለው ጥያቄ ከስያሜው ጋር የተያያዘ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኮሚሽን ሲሆን ገለልተኝነቱ፣ ሥልጣኑ፣ እንዲሁም በጀቱ ከቦርድ የተሻለ ይሆናል ከሚል አተያይ ነው፤›› በማለት ኮሚሽን ቢሆን የሚመርጡበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዋዜማ ላይ የምትገኘው አገር ከምርጫው ጋር ተያይዘው ያሉ ሕጎችን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሯን የሚያወድሱ እንዳሉ ሁሉ፣ አሁንም የሕግ ማሻሻያዎቹ በቂ ውይይትና ድርድር አልተካሄደባቸውም በማለት ተቃውሞ የሚያሰሙ አካላት በሌላኛው ፅንፍ አሉ፡፡ መጪውን ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ አሁንም የሚሻሻሉና የሚወጡ ሕጎች በአሳታፊነት ቢከወኑ የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -