Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለኮንትሮባንድ ከዛቻም ከዘመቻም የበለጠ ሥራ ያስፈልጋል

ኢኮኖሚው እንደሚፈለገው መጓዝ እንዳይችል፣ ለአገር ዕድገትና ለውጥ እንቅፋት መሆኑ እየታወቀም ከመቀነስ ይልቅ እየጦዘ የሚገኘው ሕገወጥ ንግድ፣ በኢትዮጵያ ያፈጀ ነባር ችግር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ብሶበት መታየቱ አሳሳቢነቱን አጉልቶታል፡፡  

ሕገወጥ ንግድ ሲታሰብ ጎልቶ የሚጠቀሰው የኮንትሮባንድ ተግባር ነው፡፡ ይቺን አገር በቁም የገፈፈ፣ የወደፊቱ ጉዞዋ ላይ ጋሬጣ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድ ማቆሚያ፣ መግቻ ሥርዓት ካልተበጀት የአገርን ዕድገት ማሰብ፣ ጤናው የተሟላና ተወዳዳሪ የግብዓት ሥርዓት ማስፈን ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ አይሆንምም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የኮንትሮባንድና የኮንትሮባንዲስቶችን አደገኛነት በተደጋጋሚ መግለጻቸው፣ ልዩ ኦፕሬሽኖች እየተካሄዱም ጆሮ የሚበጥሱ አስደንጋጭ የሕገወጥ ተግባራት መፈጸማቸው ሲታወቅ፣ ጉዳዩን ከሚነገረው በላይ የሚያስፈራ፣ ከሚታሰበው በላይ የሚያስበረግግ ያደርገዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት በሕገወጥ መንገድ ሊወጡም ሊገቡም ሲሉ ተያዙ እየተባሉ የሚለፈፍባቸው፣ የአገር ውስጥና የውጭ መገበያያ ገንዘቦች፣ የሚያዙ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ የጦር መሣሪዎችና ሌላውም ሁሉ እጀ ረጃጅም ኮንትሮባንዲስቶች የተንሰራፉበት የንግድ መስመር ምን ያህል ረዥም ሰንሰለት እንዳለው አሳባቂ ነው፡፡ ከውጭ ድንበር ጥሰው ወደ አገር የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ከዚህ በፊት ከሚሰማው በተለየ መንገድ ጦር መሣሪያ ያሸመቁ የሚመላለሱባቸው ሆነዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም በቅርቡ በመግለጫቸው እንዳሉት፣ ይህንን የአገር ነቀርሳና የሌብነት አውራ የሆነውን የኮንትሮባንድ ንግድ አደብ ማስገባት እስካልተቻለ ድረስ፣ ኢትዮጵያን ወደፊት ፈቅ ማድረግ እንደማይቻል በአፅንኦት መናገራቸው የችግሩን አሳሳቢነት አጉልተን እንድንረዳ የሚያደርግ ነው፡፡

 ችግሩ ከምናየውና ከሚወራውም በላይ ስለመሆሉ መገመት አይከብድም፡፡ ምክንያቱም ተያዘ የሚባለውን እንጂ በየአቅጣጫው የሾለከውን መጠንና ዓይነትና፣ ብዛትና ጭነት ስለማናውቀው ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ችግሩ ሥር ሰዶ የተንሰራፋ፣ አገር ሊያጠፋ የተቃረበ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ፣ ሲነገርና ሲዘከር ቢቆይም፣ ነገሬ ብሎ የሠራበት ባለመኖሩ ምክንያት ዛሬም ትልቅ ዘመቻ የሚያስፈልገው የአገር ብርቱ ጉዳይ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ሆን ተብሎ፣ በቸልተኝነት ወይም በጥቅም ተጋሪ የመንግሥት ኃላፊዎች ከለላ የኮንትሮባንድ ንግድ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ነግሦ ከመደበኛው የንግድና የኢኮኖሚ ሥርዓት እኩል ከፍተኛ ገንዘብ ሲንቀሳቀስበት የከረመ የ‹‹ጨለማ›› ወይም የሥውር ኢኮኖሚ መስክ ነው፡፡

 ኮንትሮባንዲስቶችን የማስቆም ኃላፊነት የተጣለባቸው ሳይቀሩ በሌብነቱና በዘረፋው ውስጥ ተሳትፈው፣ የስንቱን ደሃ ሕይወት ያቀና የነበረ ሀብትና ንብረት ለጥቂት በልቶ አደር ስግብግቦች ሲሳይ ሆነ፡፡ በልተው ላያድሩ አገር ፆም የሚሳድሩ ሆድ አምላካቸው በረከቱና ሥርዓት ጠፋ፡፡ ሕዝብ ይበደላል፣ አገር ይጎዳል የሚል ህሊናና አዕምሮ ሲጠፋ መሪም ተመሪም አንድ መሳ ሆነው ሌብነትን ያቀነቅናሉ፡፡ ‹‹ቢዝነስ ያልሠራው›› ሲነጣ የሠራው ፎቅ በፎቅ፣ የቅንጦት መኪና በላይ በላይ እየደራረበ፣ ዓለምን በደሃ ገንዘብ መነዘረ፡፡ ዘራፊ ሁሉ ይመስለዋል እንጂ በሄደበት ሁሉ ጥላው ውርደትን የሚያስታውሰው፣ ሥጋትና ጭንቀትን የሚያመጣበት በሽተኛ ነው፡፡ ኮንትሮባንድን የክፉዎች ተግባር ያደረገው እንዲህ ያለው ጥቅመኝነትና ራስ ወዳድነት በጊዜ ባለመኮርኮሙ ነው፡፡ በአደባባይ የጉዳዩን አሳሳቢነት ደጋግመን ማውራት ችግሩንም መናገር ጀመርን እንጂ ኮንትሮባንድ ከጠረፍ ከተሞች እስከመባል መርካቶ የተንሰራፋ የሌብነት ተዋናዮች መፈንጫ ከሆነ ስንት ዘመኑ፡፡

ስንሰማ በመንግሥት ባለሥልጣናት ስም፣ በከበርቴ ነጋዴዎች ታርጋ የማይፈተሸ፣ የማይነኩ ስንትና ስንት ኮንቴይነሮች፣ ስንቱ መድኃኒት፣ ስንቱ ሸቀጣ ሸቀጥ ተራገፈብን፡፡ ስንቱ ከአቅማችን በላይ በሚጫን ዋጋ ተቆለለብን፡፡ የማንም አገር ሸቀጥ ማራገፊያዎች ሆነን ኖርን፡፡

አገር በውጭ ምንዛሪ ችግር ስታነባ ከመላ አገሪቱ በየአቅጣጫው በሕገወጥ መንገድ የሚመጣው የውጭ ሸቀጥ ግን ማን ነው የማርያም መንገድ የሚሰጠው ያሰኛል፡፡ የቁም እንስሳት ከኢትዮጵያ በገፍ በጠራራ ፀሐይ እየተነዱ ድንበር የሚሻገሩት በኮንትሮባንድ አለቆች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከምታገኘው በላይ የኮንትሮባንድ መዳረሻዎቹ አገሮች ስንትና ስንት ሲመነዝሩ ያውም በኢትዮጵያ ሀብት መሆኑን ላየ፣ የአገር ያለህ ቢል ማን ሰምቶት፡፡ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ሆነና የድርሻ ድርሻውን የሚዘግንባት ምስኪን አገርና ጎስቋላ ሕዝብ በቁዘማ የሚኖሩበት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጸመው በደል ነው፣ ማቆሚያው ይናፍቃል፡፡ ባለቤት አልባ አድርጓት፣ እንድትሆን የተፈረደባት አገር ሆነች ወደሚያስብል ድምዳሜ እንድንገባ የሚያስገድድ ብዙ ጉድ አየን፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየአካባቢው ገንዘብ በጆንያ እዚህም እዚያም ሲዘዋወር ተያዘ ሲባል መስማቱ በራሱ የአገራችን ገንዘብ እንቅስቃሴ ሕግን በተከተለ አሠራር ያልተቃኘ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ነገሩን ወደኋላ መለስ ብለን ስንፈትሸው፣ ስለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በገፍ መሰማት የጀመርነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑ ደግሞ አንድ ጥያቄ እንድናነሳ ይጋብዘናል፡፡ ይኼውም በቀደመው ጊዜ ኮንትሮባንድ ተያዘ ሲባል በአብዛኛው የምንሰማው ሰልባጅና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ነበር፡፡ ከለውጡ ወዲህ በኮንትሮባንድ ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ያለ በሚመስል መንገድ በየጊዜው ከምንሰማቸው ዜናዎች ወርቅም የውጭ ገንዘቡም እየተያዘ ነው፡፡ ከችግሩ ጥልቀት አንፃር በሕገወጥ መንገድ አገርን የሚያራቁቱት የኮንትሮባንድና የሕገወጥ ንግድ ጉዳይ ግን ከዚህም በላይ ሊሠራበት ይገባል፡፡

የቀንድ ከብቶቻችን ለጎረቤት አገሮች የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሚሆኑት በርረው አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አገሪቱ የወጪ ንግድ ቁልቁል የተፈጠፈጠው ከወርቅ አምራች አካባቢዎች ወርቅ በመጥፋቱ ሳይሆን፣ በሕገወጥ ንግድ በመጧጧፉ ነው፡፡ የጦር መሣሪያዎች እዚህም ክፍያ ሲያዝ የተሸመተው በሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በተገኘ ገንዘብ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ የሰማነው ጉዳይ ነው፡፡

በየመደብሩ መደርደሪያ ላይ የሚገኙ መድኃኒቶች በሕገወጥ መንገድ ስላለመግባታቸው ይጣራ ቢባል አጀብ የምንሰኝበት ጉድ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ችግሩ እዚህም እዚያም የትዬለሌ ነው፡፡ ዝውውሩ በኮንትሮባንዲስቶች ብቻ ሳይወሰን ከላይም ከታችም ባሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ጭምር የሚታገዝ በመሆኑ፣ ይህንን ሰንሰለት ላያዳግም መበጠስ ያስፈልጋል፡፡ ሕጋዊ የግብዓት ሥርዓቱን የሚበርዝ፣ በሕግ የመሥራት ግዴታን የሚፈታተን በመሆኑም፣ የኮንትሮባንድ ዘርፍ ብዙ ችግሮች ያሉበትና  ጠጣር ጡንቻ ካላረፈበት በቀር ኢኮኖሚው መንገዳገዱ አይቀርም፡፡ በእርግጥ በኮንትሮባንድ ላይ ለመዝመት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ቢታመንም፣ ከሚታየውም ከሚሰማውም አኳያ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የገቢዎች ሚኒስትሯ ኮንትሮባንድን ተከታትሎ በማስያዝና በመያዝ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ሠራተኞች መሸለማቸው በጎ ጅምር ነው፡፡ ይህ መጠናከር አለበት፡፡ አገራዊ ስሜት፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነት እንዲፈጠር፣ ኃላፊም ሹመኛም ከገንዘብ በላይ ለአገር የሚያስብ ህሊና እንዲላበስ የማድረግ ሥራም ወሳኝ ነው፡፡ እጃቸውን መሰብሰብ ያልቻሉና ከኮንትሮባንዲስቱ ጋር የወገኑትንም በአደባባይ እንዲቀጡ ማድረግ ሊያግዝ ይችላል፡፡

በኮንትሮባንድ ንግዱ ውስጥ የተሳተፉትን በአደባባይ በማሳየት ጭምር እኔን ያየ ይቀጣ የሚያሰኝ ዕርምጃ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ዕርምጃ እንወስዳለን በሚል ዛቻና በወሬ ዘመቻ ብቻ የሚገታ ከሆነ አደጋው ከእስካሁኑም እንደሚከፋ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት