የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ለመንገድ ጥገናና ደኅንነት ማስጠበቂያ በነዳጅ ላይ የተጣለውን ታሪፍ ጨምሮ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች በሰባት ወራት ውስጥ 1.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በሰባት ወራት ከአምስት የገቢ ምንጮች ማለትም ከነዳጅ ታሪፍ፣ ከተሽከርካሪ ቅባትና ዘይት፣ ከመንገድ ተጠቃሚነት ክፍያ፣ ከግምጃ ቤት ሰነድ ግዥ ወለድ፣ በክብደት ላይ ከተመሠረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ዕድሳት ክፍያ ከሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የያዘው በነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ ያገኘው ገቢ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በሕግ በተፈቀደለት መሠረት ገቢ እያሰባሰበ ለመንገድ ጥገና ያውላል፡፡ ባለፉት በሰባት ወራትም በነዚህ የገቢ ምንጮች በኩል ካሰባሰበው ገንዘብ ውስጥ በነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ ለጽሕፈት ቤቱ የገባው ገቢ 1.3 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ከዚህ ከነዳጅ ታሪፍ ባሻገር በክብደት ላይ የተመሠረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ዕድሳት ላይ ከሚጣል ክፍያ የተሰበሰውም በርከት ያለ ገንዘብ ነው፡፡ ከዚህ የገቢ ምንጭ ጽሕፈት ቤቱ ማሰባሰብ የቻለው 96.2 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከግምጃ ቤት ሰነድ የግዥ ወለድ 7.5 ሚሊዮን ብር፣ ከመንገድ መጠቀሚያ ክፍያ 3.8 ሚሊዮን ብር ማግኘት ችሏል፡፡ ከመንገድ መጠቀሚያ ክፍያ የሚሰበሰበው ገቢ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ከሚጠየቅ የኮቴ ክፍያ እንደሆነም ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከተሽከርካሪ ዘይትና ቅባት 1.8 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ከተሽከርካሪ ዘይትና ቅባት የሚሰበሰበው ገቢ በእያንዳንዱ ሽያጭ ላይ የአሥር ሳንቲም ጭማሪ በማስላት ለመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ገቢ የሚደረግበት ሥርዓት አለው፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በ2011 በሰባት ወራት በጠቅላላው ማሰባሰብ የቻለው ገቢ ከዕቅዱ 92 በመቶውን እንደሆነ የሚያመላክት አፈጻጸም አስተናግዷል፡፡ ዕቅዱ የ1.53 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ቢሆንም፣ በውጤቱ ግን 1.4 ቢሊዮን ብር ሊያሰባስብ ችሏል፡፡
በአንዳንዶቹ የገቢ መደቦች ከዕቅዱ በላይ አከናውኗል፡፡ በተለይ ከግምጃ ቤት ሰነድ ግዥ ወለድ በሰባት ወራት ውስጥ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 4.8 ሚሊዮን ብር ገቢ ቢሆንም፣ ክንውኑ ግን 7.5 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የዕቅዱን 156 በመቶ ለማሳካት እንዳስቻለው ይጠቁማል፡፡
ከመንገድ ተጠቃሚነት ክፍያም የዕቅዱን 132 በመቶ እንዳሳካ ጽሕፈት ቤቱ ይጠቅሳል፡፡ ይሁን እንጂ በፈንዱ ለተደገፉ የመንገድ ጥገና ፕሮጀክቶች በሚቀርቡ የክፍያ ሰርተፍኬቶች መሠረት ለመንገድ ኤጀንሲዎች እከፍላለሁ ብሎ በዕቅዱ የያዘውን ያህል መክፈል አልቻለም፡፡
ከዚህ ፈንድ ለመንገድ ኤጀንሲዎች እከፍላለሁ ብሎ ለመክፈል አስቦ የነበረው 1.41 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ እስካሁን ግን የፈጸመው 655.5 ሚሊዮን ብር ወይም 46 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ክፍያው የሚፈጸመው የክፍያ ሰርተፍኬት ሲያቀርቡ በመሆኑ ኤጀንሲዎች ሰርተፍኬቱን ባለመቅረባቸው ክፍያው ሊፈጸምላቸው አልቻለም፡፡
ከመረጃው መረዳት እንደሚቻለውም ከዚህ ፈንድ ውስጥ ለመንገድ ጥገና ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን 876.7 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የወሰደው ግን 470.24 ሚሊዮን ብር ወይም 54 በመቶውን ብቻ ነው፡፡
ዘጠኙ ክልሎችም 341.19 ሚሊዮን ብር በጀት የተፈቀደላቸው ቢሆንም በሰባት ወራት ውስጥ የወሰዱት 37 በመቶ ሲሆን ከተሞች ደግሞ ከተፈቀደላቸው 169.1 ሚሊዮን ብር 30 በመቶውን ወይም 49.6 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሐመድ እንደገለጹት፣ በእኛ አሠራር የተመደበው ገንዘብ ለተባለው ዓላማ መዋሉን ከአማካሪ ድርጅቶች የክፍያ ሰርተፍኬት ሲቀርብ የሚከፈል በመሆኑ ነው፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት ኤጀንሲዎች የተመደበላቸውን ክፍያ ያልወሰዱት በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን የገለጹት አቶ ረሺድ፣ አሁን ግን ሁሉም የክፍያ ሰርተፍኬት እያቀረቡ ክፍያቸውን እየወሰዱ በመሆኑ ከበጀት አጋማሽ ወዲህ ያለው አፈጻጸም ጥሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በጽሕፈት ቤቱ መረጃ መሠረት በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ጥገናና ለወቅታዊ ጥገና ከሚመደበው በጀት በመደበኛ ጥገና 5.735 ኪሎ ሜትር ጥገና ሲከናወን፣ 1.481 ኪሎ ሜትር ደግሞ ወቅታዊ ጥገናዎች ተካሂደዋል፡፡ ይህ የጥገና አፈጻጸም የዕቅዱን 78 በመቶ የሸፈነ ነው ተብሏል፡፡