Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያው በስድስት ወራት ያገበያየው ምርት በመጠንና በገቢ ቀንሷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ያገበያየው ምርት በመጠንና በገቢ ቅናሽ አሳየ፡፡ ምርት ገበያው ባለፉት ስድስት ወራት 255,763 ቶን ምርት አገበያይቶ 14 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገባቱ ታውቋል፡፡ ሆኖም ምርት ገበያው ያገበያየው ምርት በመጠንም ሆነ በገቢ ካለፈው ዓመት ሲነፃፀር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በመላክ በርከት ላይ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝባቸው ቡናና ሰሊጥ በተያዘው በጀት ዓመትም የሚጠበቀውን ያህል ግብይት እንዳልተፈጸመባቸው፣ የወጪ ንግዱ በጠቅላላ ከሌላው ጊዜ ብዙም የተሻሻለ አፈጻጸም አለማሳየቱን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ወደ ምርት ገበያው ለግብይት የሚቀርበው ምርትና ግብይት የተፈጸመበት ዋጋ መጠን ማሽቆልቆሉ፣ ኢትዮጵያ ከግብርና ወጪ ንግድ ለማግኘት ያስቀመጠችውን ገቢ እያሽቆለቆለ እንዲሄድ አስገድዶታል፡፡ የዓለም የሸቀጦች የገበያና የዋጋ ሁኔታ ሲታከልበትም የወጪ ንግዱን አፈጻጸም ደካማ እንዲሆን ጫና አሳርፎበታል፡፡

ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው በስድስት ወራት የተገበየው የምርት መጠን ከዕቅዱ አንፃር ሲታይ አፈጻጸሙ 88 በመቶው ነው፡፡ ከግብይት ዋጋ አንፃር ደግሞ ከዕቅዱ በላይ 111 በመቶ ማሳካቱን ያመለክታል፡፡ በመጀመርያው ግማሽ በጀት ዓመት ቡና 129,933 ቶን፣ ሰሊጥ 99,147 ቶንና ቦሎቄ 26,623 ቶን በድምሩ 255,763 ቶን ምርት ማገበያየት ችሏል፡፡

የምርት ገበያው መረጃ የሚያሳየው ግብይቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ፣ ዘንድሮ በታሰበው ልክ እንዳልተከናወነ ነው፡፡ ዘንድሮ የተገበያየው የምርት መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ17 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ይህ ማለት ዓምና በግማሽ ዓመቱ ለምርት ገበያው ከቀረበው የምርት መጠን የዘንድሮው ከ61,600 ቶን በላይ ቀንሷል ማለት ነው፡፡ በ2010 ግማሽ ዓመት ምርት ገበያው ለግብይት ያዋለው የምርት መጠን 317,607 ቶን እንደነበር ይታወሳል፡፡

ዓምና በመጀመርያው ግማሽ ዓመት ለግብይት የቀረበው የምርት መጠን ከ2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት አኳያ በ42 በመቶ ዕድገት የታየበት ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ዕድገቱ ወደ ኋላ ሄዶ ጭራሹን በ17 በመቶ ቀንሷል፡፡ ከወጪ ንግዱ የሚመነጨውን ገቢ ለማሳደግ ዓይነተኛ መፍትሔም አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ምርት መጨመርና የምርት ዓይነቶቿን ማስፋፋት እንደሚጠበቅባት  በተደጋጋሚ ሲገለጽ የመቆየቱን ያህል፣ በዋነኞቹ የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ የአቅርቦት ቅናሽና መዋዠቅ የሚከሰተው ለምንድን ነው? ዘንድሮስ በምርት ገበያው መገበያየት የነበረባቸው የቡናና የሰሊጥ ምርቶች መጠን ካለፈው ዓመት አኳያ ለምን ቀነሰ? ለሚለው ጥያቄ ምርት ገበያው የራሱን ምላሽ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡

ወደ ግብይቱ መድረኮች የተላኩት ምርቶች መጠን መቀነስና በታቀደው ልክ አለመሆን ዋነኛ ምክንያት ተብለው ከተጠቀሱት አንደኛው የምርት ቅበላ መቀነስ ነው፡፡ ሌላው የዋጋ ጭማሪ ይኖራል በሚል ግምት በመጋዘን ያሉ ምርቶችን ወደ ገበያ በሚፈለገው ጊዜ አለማቅረብና በየአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ምርት ሊወጣ አለመቻሉ ለግብይቱ መቀነስ ምክንያቶች ቢባሉም፣ በዋጋ ደረጃ ግን ከዓምናው ጋር ተቀራራቢነት የታየበት ግብይት ተፈጽሟል፡፡

ዋጋው ተቀራራቢ ነው ይባል እንጂ ከዓምናው አንፃር ሲታይ፣ አሁንም ቅናሽ ማሳየቱ ግልጽ ነው፡፡ በ2010 ግማሽ በጀት ዓመት ወደ ማዕከል ቀርቦ ግብይት የተፈጸመበት የምርት ዋጋ 14.47 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ዘንድሮ በግማሽ ዓመቱ በምርት ገበያው ያገበያየበት ዋጋ 14 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በዚህ ዓመት መገበያየት የነበረበትን ያህል ምርት ሊቀርብ ካልቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ የቡናና የሰሊጥ ምርቶች አቅርቦት መቀነስ አንዱ ነው፡፡

ምርት ገበያው በ2010 ግማሽ ዓመት አገበያይቷቸው ከነበሩት 317,607 ቶን  ምርቶች ውስጥ 133,818 ቶን ለምርት ገበያው የቀረበ ቡና ነበር፡፡ ቡናው መገበያየት የቻለበት የገንዘብ መጠንም ዘጠኝ ቢሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ2011 ግማሽ ዓመት ግን ለምርት ገበያው የቀረበው የቡና መጠን 129,933 ቶን ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ለምርት ገበያው ከቀረበው የቡና ምርት መጠንም በ3,885 ቶን መቀነሱን ያሳያል፡፡

በዘንድሮው ግማሽ ዓመት የተለየ ክስተት ሆኖ የተመዘገበው የሰሊጥ ግብይት ማሽቆልቆሉ ነው፡፡ የሰሊጥ ግብይት መቀነስም ለአጠቃላይ የግብይት አፈጻጸሙ መቀዛቀዝ ከፍተኛውን ድርሻ እንዳበረከተ የሚጠቁም አፈጻጸም ነበረው፡፡

የምርት ገበያው ሪፖርት የቀደሙ ዓመታት የሰሊጥ ግብይት ውጤቶችን አመሳክሮ በማቅረብ፣ በ2011 አጋማሽ የሰሊጥ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ምርት ገበያው እንዳልቀረበ አመላክቷል፡፡  

ምርት ገበያው ማገበያየት የቻለው 99,147 ቶን ሰሊጥ ነው፡፡ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ተገበያይቶ የነበረው የሰሊጥ ምርት መጠን ግን 166,691 ቶን ነበር፡፡ ዘንድሮ የተገበያየው የሰሊጥ ምርት ከዓምናው በ67,544 ቶን ቀንሷል፡፡ ወደ ምርት ገበያው የቀረበው የሰሊጥ ምርት በዚህ መጠን መቀነሱ ያልተጠበቀ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በተለይ የሰሊጥ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ምርት ገበያው የሚገባበት ወቅት ስለነበርም፣ ጉዳዩን በተለየ መንገድ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ ከዋጋ አንፃርም፣ ባለው ዓመት የመጀመርያው አጋማሽ 5.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያወጣ የሰሊጥ ምርት ተገበያይቶ ነበር፡፡ ዘንድሮ የተገበያየበት ዋጋ ግን ከአራት ቢሊዮን ብር በታች በመሆኑ፣ የዘንድሮው የሰሊጥ የግብይት ዋጋ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ቀንሷል፡፡

ይህም ሰሊጥ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን አጠቃላይ የግማሽ ዓመቱ የግብይት አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳየ የሚያሳይ ሆኗል፡፡

በ2010 ግማሽ ዓመት የነበረው ክንውን በ2009 ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አኳያ ሲታይም፣ የሰሊጥ ግብይት በመጠን 42 በመቶ ከፍ ብሎ ነበር፡፡ ከተገበያየበት ዋጋ አንፃርም የ107 በመቶ ብልጫ ነበረው፡፡ በ2011 ግማሽ ዓመት ግን ግብይቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰ ታይቷል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ከተከናወነው አጠቃላይ ግብይት ውስጥ የ127 የግብይት ቀናት ባስተናገዱት ስድስት ወራት ውስጥ በምርት መጠን ሲታይ ቡና 76 በመቶ፣ ሰሊጥ 16 በመቶ እንዲሁም ነጭ ቦሎቄ ስምንት በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡ በዋጋ ደረጃም ቡና 87 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚ ሲሆን፣ ሰሊጥ በ12 በመቶ ሁለተኛውን  ደረጃ እንደያዘ የምርት ገበያው መረጃ ይጠቁማል፡፡  

በ2011 በጀት ዓመት ምርት ገበያው በአስገዳጅነት አኩሪ አተርና ሽምብራን ወደ ግብይት መድረኩ ማስገባት ችሏል፡፡ ባቄላና ኑግም ለግብይቱ የሚበቁበት የሁለተኛ ደረጃ ጥናት ተጠናቆ የግብይት ውል እየተሰናዳ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ ግብይት መድረክ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል፡፡ የማሾ ምርትን በአስገዳጅነት በምርት ገበያው መገበያየት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍም ተዘጋጅቶ ፀድቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በምርት ገበያው መጋዘኖች በማከማቸት ከባንኮች ብድር የሚያገኙበት አሠራር ለመዘርጋት ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝም ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡ ምርት ገበያው የዘንድሮው የግብይት እንቅስቃሴ ባሰበው ልክ ባይሆንም፣ በክፍያና ርክክብ ሥርዓት በኩል በስድስት ወራት ውስጥ 14.7 ቢሊዮን ብር ለምርት መግዣ የተንቀሳቀሰ ገንዘብ ነበር፡፡ በመሆኑም በአማካይ 116 ሚሊዮን ብር በስድስት ወራት ውስጥ ተንቀሳቅሷል፡፡ የሽያጭ ገንዘብን በተመለከተ ባለፉስት ስድስት ወራት 14.3 ቢሊዮን ብር ተመዝግቦበታል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ለመግዣ የገባው ገንዘብ በ24 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በ2011 ግማሽ በጀት ዓመት ከመግዣ ገንዘብ ማስገቢያ ሒሳብ የተቀነሰና ወደ ሽያጭ ገንዘብ መቀበያ የባንክ ሒሳብ ገቢ የተደረገ ገንዘብ በክፍያ ፈጻሚ ባንኮች ድርሻ በተመለከተ በጠቅላላ ብር 14.8 ቢሊዮን ብር ከአባላትና ደንበኞች የመግዣ ሒሳብ ላይ ተቀናሽ ተደርጓል፡፡ በክፍያ ፈጻሚ ባንኮች ከተደረጉት ተቀናሾች ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል፡፡ ይህም ከመግዣ ገንዘብ ማስገቢያ ሒሳብ በተቀናሽ ሒሳብ በ24 በመቶ መሪነቱን ሲይዝ አዋሽ ባንክ 16 በመቶ፣ አቢሲኒያ ባንክና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በ11 በመቶ ተከታታይ ድርሻ ስለመያዛቸው የምርት ገበያው መረጃ ያስረዳል፡፡

የምርት ገበያው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን የሚጠቁመው መግለጫ በተጨማሪነት ባካተተው መረጃ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ሥራ ሒደቱን በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት እየሠራ ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡  በአዲስ አበባ ብቻ ከሚደረገው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የግብይት ማዕከላትን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱንም በማስታወስ፣ የሐዋሳ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ የግብይት ሥራውን መጀመሩን ገልጿል፡፡ ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው የነቀምትና የሁመራ ግብይት ሲሆን፣ በቀጣይ ወራት ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ አገልግሎትን ለአርሶ አደሩ፣ ለአቅራቢዎች፣ ለላኪዎችና ለሌሎችም የግብይት ተዋንያን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግም በክልል ከተሞች የተለያዩ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም፣ የመቱ ቅርንጫፍ በያዝነው ወር ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምርም አረጋግጧል፡፡

እነዚህ እንቅስቃሴዎች ወደ ተግባር ሲለወጡ ግብይቱን ከፍ ያደርጋሉ ቢባልም፣ አሁን ወደ ምርት ገበያው የሚመጣው ምርት ሊጨምር የሚችልበት ሥልት ሊቀየስ እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች