Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አመኔታ እየጨመረ ስለሆነ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ሲመጡ እያየን ነው››

ሚስተር አዳሙ ላባራ፣ የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) የኢትዮጵያና የአካባቢው አገሮች ኃላፊ

ሚስተር አዳሙ ላባራ የዓለም ባንክ የግሉ ዘርፍ ቀኝ እጅ እንደሆነ በሚነገርለት የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የጂቡቲ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የሶማሊያና የሱዳን ኃላፊ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ኢትዮጵያ ተመድበው እነዚህን አገሮች በኃላፊነት የሚመሩት ሚስተር ላባራ፣ የገንዘብ ተቋሙን የተቀላቀሉት እ.ኤ.አ. በ1998 ነበር፡፡ በወቅቱም ለመካከለኛው አፍሪካ ቀጣና የኢንቨስትመንት ኦፊሰር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ወደ ኮትዲቯር በማቅናት በኮርፖሬሽኑ የአቢጃን ከተማ መሥሪያ ቤት ሲያገለግሉ ቆይተው፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከዚያም ወደ ሴኔጋል በመዛወር በተለያዩ የኃላፊነት ምድቦች ሠርተዋል፡፡ በገንዘብ ገበያው፣ በአምራች ኢንዱስትሪውና በአገልግሎት መስክ ለተሠማሩ የግል ኩባንያዎች ኮርፖሬሽኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች መርተዋል፡፡ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአይኤፍሲ ዋና ተወካይ በመሆን በኪንሻሳ የነበረውን ተቋም ሲመሩ ቆይተው፣ በአሁኑ ወቅት የሚገኙበትን ኃላፊነት በመረከብ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁንም እዚህ ሆነው የዴሞክራቲክ ኮንጎን የኮርፖሬሽኑን ሥራዎች ይመራሉ፡፡ በቢዝነስ አስተዳደር ከዩናይትድ ኪንግደም ሐንሌይ ማኔጅመንት ኮሌጅ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚክስ ከካሜሮን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ያውንዴ ሁለት የማስትሬት ዲግሪዎችን ሠርተዋል፡፡ አይኤፍሲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተነቃቃ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረባቸውና የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍባቸው መስኮችን፣ በቅርቡ በኮርፖሬሽኑና በመንግሥት መካከል የተፈረሙ ስምምነቶችና አይኤፍሲ ስለሚሰጣቸው ሌሎችም አገልግሎቶች ብርሃኑ ፈቃደ ከሚስተር አዳሙ ላባራ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ይፋ ያደረጋቸውን ዕቅዶች ተከትሎ፣ አይኤፍሲ ከሌላው ጊዜ ይልቅ በሰፊው የመምጣቱ ምክንያት ምንድነው?

ሚስተር ላባራ፡- ከዚህ ቀደም በመንግሥት የበላይነት ይመራ ከነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ አሁን ወደ ግሉ መር ያደላ መሠረታዊ ለውጥ አለ፡፡ አይኤፍሲ የግሉን ዘርፍ ለመደገፍና ለማልማት እንዲችል ተብሎ ነው የተቋቋመው፡፡ የኋሊት ጥቂት መለስ ብለን ብናይ አይኤፍሲ የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1956 ሲሆን፣ በርካቶች ኢትዮጵያ መሥራች መሆኗን አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያ ተቋሙን ከመሠረቱት አገሮች አንዷ ነች፡፡ አይኤፍሲን በመመሥረትም ከአፍሪካ ብቸኛዋ አገር ነች፡፡ ከምሥረታው ጀምሮ ለተቋሙ የተሰጠው ኃላፊነት ግልጽ ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ ልማት ላይ እንዲያተኩርና ዓለም አቀፍ የመልሶ ግንባታና የልማት ባንክ (ኢንተርናሽናል ባንክ ፎር ሪኮንስትራክሽን ኤንድ ዲቨሎፕመንት)፣ ወይም የዓለም ባንክ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት መደገፍና ከሥራዎቻቸው ጋር የሚጣጣሙ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ ላይ ነው ትኩረቱ፡፡

ሪፖርተር፡- ምንም እንኳ ኢኮኖሚው አሁንም ቢሆን በመንግሥት የበላይነት የተያዘ ቢሆንም፣ የቀድሞው አስተዳደር ይል የነበረው ኢኮኖሚው በግሉ ዘርፍ መመራት አለበት ነው፡፡ ታዲያ አይኤፍሲ በአሁኑ አስተዳደር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ማረጋገጫ የሰጠው ምንድነው?

ሚስተር ላባራ፡- ኢትዮጵያ አሁንም የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ በመተግበር ላይ ነች፡፡ በዕቅዱ መሠረት የግሉ ዘርፍ ዋናው የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተዋናይ ይሆናል ይላል፡፡ አይኤፍሲም የዚህ ደጋፊ ነው፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳሉትም፣ አይኤፍሲ የግሉን ዘርፍ በሚያሳድጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በጉልህ ይሳተፋል፣ ያግዛል፡፡ ይህም እስካሁን ስናከናውን ከቆየነው ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ እንዳደረጉት፣ የተወሰኑ የኢኮኖሚው መስኮች ለግሉ ዘርፍ ክፍት ይደረጋሉ፡፡ አይኤፍሲም ለእነዚህ መስኮች ጠንካራ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከመንግሥት ጋር በመሥራትም ዘርፎቹ ስትራቴጂካዊ በሆነ አኳኋን ክፍት እንዲደረጉ እናግዛለን፡፡ ይህም አይኤፍሲ በሰፊው ጎልቶ እንዲመጣና እንዲያግዝ ምክንያት ከሆኑት መካከል የሚመደብ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ከአጭር ጊዜ ቆይታውና ልምዱ አኳያ ይፋ ያደረጋቸው የፕራይቬታይዜሽን ዕርምጃዎች ትልልቅ በመሆናቸው፣ አይኤፍሲን ሊያሳስበው ወይም ሥጋት ሊፈጥርበት የሚችል ነገር የለም ማለት ነው?

ሚስተር ላባራ፡- አንዲት አገርን ወደ ለውጥ ጎዳና የሚመራ አካል ራዕይ ያስፈልገዋል፡፡ እንደማስበው ይህ አስተዳደርም ጠንካራ ራዕይ አስቀምጧል፡፡ ይህ ሲሟላ በማስከተል ስለሰው ሀብትም ሆነ ስለገንዘብ ሀብት መነጋገር እንችላለን፡፡ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ግን ራዕይ መኖሩ ነው፡፡ ራዕይ ነው ሌሎቹን ዓላማዎች ሁሉ አብሮ የሚያስኬዳቸው፡፡ ራዕይ ኢኮኖሚው ወዴት አቅጣጫ መመራት እንዳለበት ለማስቀመጥ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሕግ መውጣቱ፣ መንግሥት በመሠረተ ልማት አውታሮች ልማት ሒደት ላይ ምን ዓይነት አካሄድ እንደሚከተል አመላካች ዕርምጃ ነው፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ማዕቀፍ በአብዛኛው በመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍና የመሠረተ ልማት እንዲያለማ ተጋብዟል፣ ተፈቅዶለታል፡፡ እንዲህ ያሉት ጉዳዮች ለአይኤፍሲ በሰፊው መምጣትና በሰፊው መፈለግ ጠቋሚ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡-  ከበፊት ጀምሮ የሚነገሩ ወይም እንደ ሥጋት የሚታዩ አመለካቶች በዓለም ባንክና በሥሩ ባሉ እንደ አይኤፍሲ ወይም እንደ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ያሉት ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት ለአገሮች ፖሊሲ ከማውጣት የዘለለ ሚና የላቸውም የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማስተካከያ ፕሮግራም ፖሊሲ ጀምሮ ሌሎችም ተቋማት ሰፊ አመኔታን እንዳጡ ስለሚታመን፣ ኢትዮጵያ በሯን ለውጭ ዓለም ክፍት ማድረጓ ተጋላጭ እንዳያደርጋት በማለት መንግሥትን የሚያስጠነቅቁ አሉ፡፡ ለምንድነው እንዲህ ያሉ ሥጋቶች አሁንም ድረስ ጎልተው የሚደመጡት?

ሚስተር ላባራ፡- እኔ በሌላ መንገድ ላስቀምጠው እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በአይኤፍሲ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ቀላል ነው፡፡ በአይኤፍሲ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለው ድርሻ አነስተኛ ነው፡፡ ወይም መንግሥት መቶ በመቶ ድርሻ አልያዘም፡፡ በምንሠራቸው ማንኛውም ሥራዎች ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠውም ለግሉ ዘርፍ ነው፡፡ የፕሮጀክት ፋይናንስ በማቅረብ የግሉን ዘርፍ እንቅስቃሴዎች እናግዛለን፡፡ የግሉን ዘርፍ ልማት ለማገዝ የሚውሉ ሁለት የድጋፍ መስኮቶች አሉን፡፡ አንደኛው የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን፣ ሁለተኛው የማማከር አገልግሎት ነው፡፡ በማማከሩ በኩል በሁለት ደረጃ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በመጀመሪያው ረድፍ የሚጠቀሰው ከመንግሥታትና ከአስተዳደሮች ጋር አብረን የምንሠራበት መስክ ነው፡፡ የተወሰኑ ዘርፎችን ወይም በጥቅሉ ኢኮኖሚውን በመመልከት ኢኮኖሚው ወይም ዘርፎቹ ለቢዝነስ ያላቸውን ተስማሚነት እንለያለን፡፡ ከዚያም ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በመሆን እንደ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረኮችን በመጠቀም የሚተገበሩ ሪፎርሞች ላይ ምክክር በማድረግ ስምምነት እንዲፈጠር በማድረግ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው እናግዛለን፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና ከመንግሥት ጋር በመሆን ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ያስጀመርነው የምክክር መድረክ፣ በኢትዮጵያ የሚያስፈልጉ የሪፎርም ዕርምጃዎች ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲፈጠር አግዞ ነበር፡፡ ከሪፎርም ዕምርጃዎቹ መካከል ለአብነት በንግድ ምዝገባ ሒደት ወቅት፣ ለምዘገባ የሚወስደው ጊዜና ለምዝገባው የሚያስፈልጉ የአፈጻጸም ሒደቶችና መሟላት የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን በተመለከተ ትኩረት ካገኙት መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ እነዚህ ዕርምጃዎች በአገር ውስጥ ባሉ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ በኢንቨስትመንት ከባቢው ላይ ከምናካሂዳቸው የማማከር አገልግሎቶች ውስጥ እንዲህ ያሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሌላው የማማከር ሥራችን ለኩባንያዎች የምናቀርባቸው አገልግለቶችን ይመለከታል፡፡ ለምሳሌ የበቆሎ ወይም የሌላ የግብርና ምርቶች የሚፈልግ አንድ ኩባንያ አለ እንበል፡፡ እነዚህን ጥሬ ዕቃዎች ከሚፈልገው ኩባንያ ጋር በመሥራት አርሶ አደሮች ለዘለቄታው ሳያቋርጡ ምርት ማቅረብ የሚችሉበትን ሰንሰለት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሥራዎችን እናግዛለን፡፡ አርሶ አደሮች በዚህ ሒደት ውስጥ በምርት ሰንሰለቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

በጠቅላላው ሲታይ በአንድ ጎን ከመንግሥት ጋር በሌላ ጎንም ከኩባንያዎች ጋር የምንሠራባቸው የአገልግሎት መስኮች አሉን ማለት ነው፡፡ የገንዘብ አቅርቦትም እናደርጋለን፡፡ አንድን ፕሮጀክት በገንዘብ በምንደግፍበት ወቅት የመንግሥት ዋስትና እንዲቀርብልን አንጠይቅም፡፡ የተቋቋምንበት ዓላማም አይደለም፡፡ አንድ የግል ኩባንያ የፕሮጀክት ሐሳቡን ሲያቀርብልን አዋጭነቱን፣ ሊተገበር ይችል እንደሆነና ለሥራ የሚያውለውን ገንዘብ እንዴት እንደሚጠቀምበት አጣርተን፣ ከአካባቢና ከማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ከገበያ አኳያ የሚኖሩትን ተጨባጭ ተፅዕኖዎች እንገመግማለን፡፡ ፕሮጀክቱ ስላሉበት ሥጋቶች በማጥናትና በመገምገም በስተመጨረሻ ድጋፍ ልናደርግለት እንችላለን፡፡ እነዚህን ሳያሟላ ከቀረም ውድቅ ልናደርገው እንችላለን፡፡ የፋይናንስ ድጋፋችን ወደ መንግሥት ቋት አይሄድም፡፡ በመንግሥት ዕዳ ላይም አምስት ሳንቲም አይጨምርበትም፡፡ ገንዘቡ በቀጥታ ወደ ኩባንያው የሚተላለፍና ሥራ ላይ የሚውል ነው፡፡ ከልማት ባንክ ጋር ያለንን ልዩነት በድጋሚ ካየነው፣ መንግሥት በልማት ባንክ ውስጥ መቶ በመቶ ባለድርሻ ነው፡፡ በአይኤፍሲ ውስጥ ግን ከዚያ ያነሰ ድርሻ ነው ያለው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንደ ልማት ባንክ ያሉትን ጨምሮ የልማት ገንዘብ የሚያበድሩ ተቋማት ዋናው ትኩረታቸው በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ያደላ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ደካማ ስለሆነ፣ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ስለማያነጭና ዕጥረቱም ከፍተኛ በመሆኑ ሳቢያ የውጭ ምንዛሪ ለሚያስገኙ ዘርፎች ትኩረት መሰጠቱ ብዙም ላያነጋግር ይችላል፡፡ የእርስዎ ምልከታ ምንድነው?

ሚስተር ላባራ፡- ስናበድር በውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ እንዲከፈለን የምንጠብቀውም በውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ይህንን ሊያሟላና ከሌሎች ቀድሞ ሊጠቀስ የሚችለው፣ የወጪ ንግድ ዘርፉ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የወጪ ንግድ ዘርፉ ብቻውን ተነጥሎ አይሠራም፡፡ የአገር ውስጥ የአቅርቦት ሰንሰለት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ ከማስመጣት ጣጣ ይታደጋል፡፡ ነገር ግን ጥሬ ዕቃው እዚህ መገኘት መቻል አለበት፡፡ እንደምታስታውሰው የአይኤፍሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ወቅት ከተፈረሙት ስምምነቶች አንደኛው በብር የሚከፈል ብድር ለማቅረብ የሚያስችለው ስምምነት ነበር፡፡ ይህ ስምምነት ጥሬ ዕቃ ከአገር ውስጥ ለማግኘት እንዲቻል የሚያግዝ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ገቢ ሸቀጦችን ለመተካትም የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ከውጭ ታስገባለች፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከምታስገባው በላይ ወደ ውጭ መላክ የምትችልበት አቅም አላት፡፡ አይኤፍሲ በአገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብ ማበደር የሚችልበት አሠራር ባይኖረውም፣ በውጭ መገበያያ ገንዘብ አበድረን በአገር ውስጥ ገንዘብ ብድሩን የምናስመልስበት አሠራር ወደፊት ሊኖር ይችላል፡፡ እስከዚያው ግን በውጭ መገበያያ ገንዘብ ብድር የምንሰጣቸው ኩባንያዎች የተወሰነውን ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የአገር ውስጥ የምርት ፍላጎት ከፍተኛም ቢሆን የግድ ወደ ውጭ መላክ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ፣ ከእኛ መደበር የሚፈልጉ ኩባንያዎች ይህንን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በፈጠረው ጫና ነው፡፡ በመሆኑም ለዕዳ ክፍያ ከሚያውሉት ባሻገር፣ ለመለዋወጫና ለልዩ ልዩ መሣሪዎች ግዥ የሚያውሉት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የግድ ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ በጠቅላላው ግን ምርት ወደ ውጭ የሚልኩትንም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ኩባንያዎችን እናግዛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለማክሮ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እናንሳ፡፡ ሰፊ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቷል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ለፖለቲካዊ ቀውስ የከተተ ሰፊ የሥራ አጥነት ችግርም አለ፡፡ በየጊዜው እየሰፋ የመጣ የክፍያ ሚዛን ጉድለትና በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ባሉበት አገር ውስጥ የቀደመውም የአሁኑም አስተዳደር አብዛኛው ትኩረት ፖለቲካው ላይ ነው፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚው ትኩረት አልተሰጠውም የሚሉ ትችቶች አሉ፡፡ አይኤፍሲ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፎችን ለማድረግ በሰፊው መምጣቱ ትልቅ ጉዳይ ቢሆንም፣ በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ ሊጫወት የሚችለው ሚና ግን እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

ሚስተር ላባራ፡- በኢኮኖሚው ውስጥ ትልልቅ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ራሳችንን አጋር አድርገን ከምናይባቸው ዘርፎች አንዱ ይኸው የማክሮ ኢኮኖሚው መስክ ነው፡፡ ለአብነት የምግብ ዘይት  ከውጭ ከማምጣት ይልቅ መቶ በመቶ በአገር ውስጥ ለሚያመርተውና ወደ ውጭ ለሚልከው ኩባንያ ገንዘብ ማቅረብ መቻል፣ አገሪቱ ለገቢ ንግድ የምታውለውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት የክፍያ ሚዛኗ እንዲሻሻልና ያለባት ጫናም እንዲቀንስ ማድረግ ይቻላል፡፡ የውጭ መጠባበቂያ ክምችቷን በማሻሻል የገቢ ንግዷን ለመቀነስ እንዲህ ያሉትን ኩባንያዎች ማበራከት ወሳኝ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ ልናበረክት የምንችለው አንደኛው አስተዋጽኦ ነው፡፡ አይኤፍሲ ድጋፍ የሚሰጣቸው ኩባንያዎች ከውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሻገር፣ ለበርካቶች ሥራ ያስገኛሉ፡፡ በእንቅስቃሴያቸውም ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችንም ይፈጥራሉ፡፡ ታክስ ይከፍላሉ፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለቱንና የምርት ሥርጭት መስመሮችን ካየኻቸውም፣ አኃዞቹ ምን ያህል እነዚህ ኩባንያዎች ለኢኮኖሚው መረጋጋት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ያስገነዝቡሃል፡፡ በዚህ መሠረት ያለውን ሒደት ስናይ፣ አስተዋጽኦዋችን ከአንድ ኩባንያ እስከ አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚው ክፍል የሚደርስ ሚና እንደምንጫወት እንገነዘባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በውጭ ምንዛሪ ለሚቀርበው ብድር በአገር ውስጥ መገበያያ ብድሩ ስለሚከለፍበት ጉዳይ ጠቅሰው ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ለአገሪቱ የገቢ ንግድ ዋስትና የሚሰጥ ስምምነትም መፈረሙ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙና የስምምነቱ ተጠቃሚ ባንኮችስ እንዴት እንደተቀበሉት ቢገልጹልን?

ሚስተር ላባራ፡- የገቢ ንግዱን ለመደገፍ የተዘረጋው ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍም የማማከር አገልግሎቶችንም ያካተተ ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ባንኮች የንግድ ገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ድጋፍ እንደጣለን፡፡ ለመጀመር ቀላል ከሆነው የዋስትና ሽፋን አሰጣጥ መጀመር እንፈልጋለን፡፡ ባንኮች ለአስመጪዎች ለሚከፍቱት የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ዋስትና እንሰጣለን፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የኢትዮጵያ ባንኮች ሌተር ኦፍ ክሬዲት ሲከፍቱ፣ አብረዋቸው ከሚሠሩ የውጭ ባንኮች ማረጋገጫ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የውጭዎቹ ባንኮች ለተከፈተው የዋስትና ሰነድ ማረጋገጫ ከመስጠታቸው በፊት፣ የሰነድ ማረጋገጫው ተራውን እንዲጠብቅ፣ ወይም በተከፈተው ዋስትና ሰነድ መጠን መቶ በመቶ ክፍያ ወዲያውኑ እንዲፈጸም፣ ወይም ገንዘቡ እንዲገባላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ወቅት አይኤፍሲ በተለይም ገንዘቡ በሙሉ ገቢ እንዲደረግ በሚጠየቁበት ጊዜ ድጋፍ ለመስጠት ይገባል ማለት ነው፡፡ የተጠየቀው ገንዘብ በሙሉ በአንድ ጊዜ ከሚከፈል ይልቅ፣ ሌላ ድጋፍ የሚሰጥበት አሠራር ስላለው ይገባበታል ማለት ነው፡፡ ይኸውም እንበልና አንድ በውጭ ያለ በአንድ አገር ውስጥ ካለ ባንክ ለተላኩለት የዋስትና ሰነድ ጥያቄዎች ማረጋገጫ ከመስጠቱ በፊት ተጠባባቂ ሊያደርገው ይችላል፡፡ የውጭው ባንክ ለአሥር ዋስትና ሰነዶች ብቻ ሊሆን ይችላል ማረጋገጫ ሊሰጥ የሚችለው፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ ባንኩ የሚፈልገው የ15 ሌተር ኦፍ ክሬዲት ማረጋገጫዎች እንዲሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም የውጭው ባንክ ማረጋገጫ በማያሰጥባቸው የሌተር ኦፍ ክሬዲት ጥያቄዎች ላይ አይኤፍሲ ዋስትና በመስጠት፣ የአገር ውስጥ ባንኩ የሚያስፈልገውን እንዲያገኝ ያግዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ሌተር ኦፍ ክሬዲትን ብቻ እንደ ንግድ መሣሪያ ይጠቁሙበታል፡፡ ነገር ግን በርካታ ዓለም አቀፍ ንግድን ለማቀላጠፍ የሚረዱ የክፍያ መሣሪያዎች አሉ፡፡ ይሁንና የአገር ውስጥ ባንኮች እነዚህን መሣሪያዎች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉት ተገቢው ሥልጠናና ግንዛቤ ሲኖራቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌተር ኦፍ ክሬዲት ባሻገር ያሉት የዓለም አቀፍ የንግድ ማስኬጃ መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

ሚስተር ላባራ፡- ‹‹ዶክመንተሪ ክሬዲትስ›› የሚባሉና ሰነድን እንደ ብድር አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችሉ አሉ፡፡ በሌተር ኦፍ ክሬዲት ውስጥም የተለያዩ ዘዴዎች አሉ፡፡  ለምሳሌ ግሪን ክሎዝ ኤልሲ፣ ሬድ ክሎዝ ኤልሲ የሚባሉና ሌሎችም የተለመዱ  ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አንድ ዓይነት የኤልሲ ሥርዓትን ብቻ ነው የምናየው፡፡ ለባንኮች የሚሰጠው ሥልጠና እንደ የንግድ ሥጋት ሥራ አመራር፣ የንግድ እንቅስቃሴን፣ የገንዘብ አቅርቦት ሥራ አመራር፣ ወዘተ የሚባሉትን የሚያካትት ነው፡፡ አንድ ባንክ ኤልሲ በሚከፍትበት ወቅት ሊከተላቸው የሚገቡ የሥጋት ሥራ አመራር ደረጃዎች የትኞቹ እንደሆኑና የተከፈተው መተማመኛ ሰነድ ወይም ኤልሲው የሚቆይበት ጊዜ በሚያበቃበት ወቅት፣ ባንኩ የሚጠበቅበትን ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችለው የገንዘብ አቅርቦት እንዳለው የማረጋገጥ ሥራዎችም ይካተታሉ፡፡ ለባንኮች የኤልሲ ዋስትና በምንሰጥበት ወቅት፣ ባንኮቹ አስተማማኝ የገንዘብ አቅርቦት ሥራ አመራር ክህሎትና ሒደት ስለመፍጠራቸው ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ በነገራችን ላይ የአይኤፍሲ የዓለም አቀፍ የንግድ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2008 ነበር፡፡ በመሆኑም የ65 ቢሊዮን ዶላር የኤልሲ ልውውጦችንም ያለ ምንም ችግር አጠናቀናል፡፡ ከሰሃራ በታች አፍሪካም ዋናዎቹ የእኛ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ናይጄሪያና ኬንያ ናቸው፡፡ በምሥራቅ እስያ ባንግላዴሽና ቬትናም ዋናዎቹ የፕሮግራማችን ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ባንኮች ለከፈቱት ኤልሲ ወቅቱን ጠብቀው መክፈል ሲያቅታቸው እንደነበር ይሰማል፡፡ ለብራዚል ባንኮች ያልተከፈለ ውዝፍ በባንኮቹ ላይ እንደሚገኝባቸውም ይነገራል፡፡ በዚህ ሳቢያም የአገር ውስጥ ባንኮች ደንበኞች ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት ሲቸገሩና ተቀባይ ባንኮችም ኤልሲ እንዳይልኩ ይልቁንም በጥሬው እንዲከፍሉ ሲጠይቋቸው ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ የሩቅ ጉዳዮች በተባራሪ ይሰማሉ፡፡ እናንተስ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ትከታተላላችሁ? ተመሳሳይ ጉዳዮችን እንዳጠናችሁ መናገር ይችላል?

ሚስተር ላባራ፡- ለአንድ ዓመት ያህል ለገቢ ንግዱ ዋስትና የምንሰጥበትን ፕሮግራም ለማስጀመር ምክክር ስናደርግና ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በፕሮግራሙ 200 ማረጋገጫ ሊሰጡ የሚችሉ የውጭ ባንኮችን አካተናል፡፡ አንድ ኢኮኖሚ ሲያድግ ፍላጎቶቹም አብረው ማደጋቸው አይቀሬና የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከአሥር በላይ የውጭ ባንኮች በአንድ አገር ላይ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ያላቸው የኤልሲ መስመር ግን አገሪቱ እንደሚያስፈልጋት ብዛት ላይሆን ይችላል፡፡ የውጮቹ ባንኮች መስጠት የሚችሉት ገደብ ላይ ሲደርሱ፣ ሌላ ተጨማሪ ብትሰጣቸው እንኳ ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡ በተለይ አንዳንድ አገሮች ላይ ይህ ይታያል፡፡ ስለዚህ አንዲት አገር እያደገች በሄደች ቁጥር ለገቢ ንግዱ የኤልሲ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ የውጭ ባንኮች ያስፈልጓታል፡፡ አንተ ስለገለጽከው ችግር እኛ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ልነግርህ የምችለው ነገር ግን አንዳንድ መዘግየቶች እንደነበሩ ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ባንኮች ሁልጊዜም ክፍያቸውን ይፈጽማሉ፡፡ ሳይከፍል የቀረ ወይም ያስቀረ የኢትዮጵያ ባንክ የለም፡፡ 

ሪፖርተር፡- እዚህ ያሉ የውጭ ኩባንያዎች ከንግድ ዋስትና ፕሮግራሙ እንዴት ነው ተጠቃሚ የሚሆኑት?

ሚስተር ላባራ፡- የዓለም ንግድ ፋይናንስ ወይም የገቢ ንግድ ፋይናንስ ፕሮግራሙ ለባንኮች የተዘረጋ ቢሆንም፣ በዚህ ማዕቀፍ የሚስተናገዱ የንግድ ዘርፎች ግን ምናልባት ጥሬ ዕቃ፣ መሣሪያዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ማዳበሪያና ሌሎችም ሊካተቱበት ይችላሉ፡፡ የንግድ ልውውጡ በመሥፈርቱ መሠረት እስከተከናወነ ድረስ የውጭ ወይም የአገር ውስጥ ኩባንያ መሆኑ ላይ ልዩነት አይደረግበትም፡፡ ሁሉንም ያሳትፋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የንግድ ፋይናንስ ዋስትና ፕሮግራሙ ምን ያህሉን የአገሪቱን የገቢ ንግድ መጠን ሊሸፍን ይችላል? በገንዘብ ሲገለጽ ቁጥሩ ምን ያህል ነው? የመንግሥት ባለሥልጣናት የገቢ ንግዱን በሙሉ የሚሸፍን ዋስትና ይጠብቃሉ፡፡

ሚስተር ላባራ፡- ገና እየገመገምን ነው፡፡ በኢትዮጵያ በዓመት ለማዳበሪያ ግዥ የሚያስፈልገው ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የነዳጅ ግዥውን ካየህም በጣም ትልቅ መጠን ነው፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን እያደገ ካለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ፍላጎት አኳያ ስታየው የገቢ ንግዱ ወጪ በጣም ትልቅ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የውጭ ባንኮች እንደነገሩን ከሆነ በአንዱ የኢትዮጵያ ባንክ ላይ ብቻ በዓመት ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ያልተዘጋ ሒሳብ አላቸው፡፡ በመሆኑም ግምገማውን እየሠራን ነው፡፡ የሚያስፈልገው ብዛት ግን ትልቅ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከፀሐይ ኃይል አኳያም አይኤፍሲ 500 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ሁለት ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ግማሹ እንደሚለማ ይጠበቃል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ሒደት ወደ ግንባታ ጨረታ ግዥ መቃረቡም ይታወቃል፡፡ ምን አዲስ ጉዳይ ይነግሩናል?

ሚስተር ላባራ፡- አዎ ፕሮጀክቶቹ ወደ ጨረታ ግዥ ሒደቱ ተቃርበዋል፡፡ እንደማስበው ‹‹ስኬሊንግ ሶላር›› የተኙት ፕሮጀክቶች የመጀመሪያ ምዕራፍ የልማት ሥራው በጨረታ ግዥ ወደሚፈጸምበት ደረጃ ተቃርቧል፡፡ ይህ በጣም ጠቃሚው ምዕራፍ ነው፡፡ በጠቅላላው 500 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ስለሚቻልበት መንገድ የማማከር አገልግሎት ለማበርከት ስምምነት ፈጽመናል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ 250 ሜጋ ዋት ኃይል ይመነጫል፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ሒደቱን እየተከታተለው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለኢትዮጵያ አስፈላጊዋ የሆኑ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎች እየመጡ ነው፡፡ ይሁንና ለእነዚህ ድጋፎች ኢትዮጵያ የሚጠበቅባት ወጪ ምንድነው? ምንድነው የምትከፍለው?

ሚስተር ላባራ፡- ቀደም ብዬ ወዳነሳሁት ጉዳይ መመለስ አለብኝ፡፡ በልማት ባንክና በአይኤፍሲ መካከል ያለውን ልዩነት በተመለከተ ገልጫለሁ፡፡ አዎ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እናደርጋለን፡፡ ፕሮጀክቱ የሚያስገኘው ጥቅም ከሥጋቱ ጋር ተመጣጣኝ ወይም አቻ ሊሆን መቻል አለበት፡፡ ከውጭ ሚዲያ በምንሰማው ዘገባ ላይ ተመሥርተን አንሠራም፡፡ መሬት ላይ ያለውን እውነታ እናውቀዋለን፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ያለውን የሥጋት መጠን በተመለከተ የተለየና የተሻለ ግንዛቤው አለን፡፡ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ስንደግፍም ያለውን ሥጋት በሚገባ መዝነን ነው፡፡ ሌሎች እዚህ አገር እንቅስቃሴ የሌላቸው ሲመጡ ስለ አገሪቱ ስታንዳርድ መነሻ የሚሆን ነገር እናዘጋጅላቸዋለን፡፡ እኛ ከሠራነው ግምገማ በመነሳት ያቀረብነውን መነሻ ሐሳብ ከተቀበሉት፣ ሥራዎቻቸውን ለመሥራት እኛ ከምንሰጣቸው ስታትስቲካዊ መረጃዎች በመነሳት የተሻለ ውሳኔ ለመወሰን የሚችሉበት ዕድል ያገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በርካታ ኩነቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ በእርስዎ ምልከታ በዚህ አስተዳደር ወቅት በመጪዎቹ ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ውስጥ ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ ሊታይ የሚችልበት መስክ የቱ ነው?

ሚስተር ላባራ፡- የቀጣናው ትስስር ለሁሉም አገሮች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ ይህም እየመጣና ወደ ተግባርም እየተለወጠ መምጣት በመጀመሩ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ የአካባቢያዊ መረጋጋቱ ሲኖርና ትክክለኛው የኢንቨስትመት ማዕቀፍ ሲቀመጥ፣ የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ብዙ ለመሥራት መምጣታቸው አይቀርም፡፡ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አመኔታ እየጨመረ ስለሆነ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ሲመጡ እያየን ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ስካት ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...