አካዴሚዎችና ፌዴሬሽኖች የገንዘብ ድጎማ አገኙ
ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና የሥልጠና አካዴሚዎች የታደሙበትና በመጪው ዓመት በጃፓን ለሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅትና የዕቅድ ግምገማ ተካደ፡፡
መድረኩን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ ማኅበራትና ማሠልጠኛ አካዴሚዎች በታዳጊ ወጣቶች ላይ እንዲሠሩ የሚያግዛቸው የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ማኅበራትና የሥልጠና አካዴሚዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የስፖርት ማኅበራት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የዕቅድ፣ ግምገማና ውይይት የተካሄደው ሐሙስ፣ የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመድረኩ ከተነሱት ዓብይ ነጥቦች መካከል ኦሊምፒክን ጨምሮ አኅጉራዊ ውድድሮች ከመቃረባቸው አስቀድሞ አስፈላጊና መሠረታዊ ቅድመ ዝግጅቶች ሊከወኑ ይገባል የሚለው ይገኝበታል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለሁሉም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች የ100 ሺሕ ብርና ለብሔራዊ ስፖርት አካዴሚዎች ደግሞ የ200 ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ በቋሚነት ማበርከቱ ተነግሯል፡፡ ለተቋማቱ የተበረከተው የገንዘብ ድጋፍ በዋናነት በታዳጊ ወጣቶች ላይ አተኩረው እንዲሠሩ ለማበረታታት ተፈልጎ እንደሆነ በመግለጫው ተካቷል፡፡ ተቋማቱ የገንዘብ ክፍያው የሚፈጸምላቸው የፕሮጀክት ትልመ ሐሳባቸው ወደ ተግባር ተቀይሮ በሚያበረክተውና በሚመዘገበው ውጤት መሠረት ግምገማና ክትትል ተደርጎበት ነው፡፡
የዕቅድ ግምገማውንና ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የውይይት መድረኩ፣ ከዚህ በፊት ከስፖርት ማኅበራቱ ጋር ሲደረግ ከነበረው የተከተለ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የውይይቱ ዋና ዓላማም ኢትዮጵያ ከፊት ለፊቷ ለሚጠብቋት አኅጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ብሎም በጃፓን ለሚዘጋጀው 32ኛው ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት ብሎም በቅርቡ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ዕቅድና ዝግጅት ላይ ለመወያየት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቀደም ሲል በተገለጸው መሠረት፣ ለስፖርት ማኅበራቱ የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ብሔራዊ ተቋማቱ የሚያቀርቡትን የአፈጻጸም ሪፖርት ለማድመጥና በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች ካሉም በጋራ ለመፍታት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሐፊ አቶ ታምራት በቀለ በበኩላቸው፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፉት ስድስት ወራት ስላካሄዳቸው የስፖርት ልማት ሥራዎችና እ.ኤ.አ. ለ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ የዝግጅት ጉዳዮች ላይ ብሎም የባለድርሻ አካላት ስለሚጠበቅባቸው ሚናና ኃላፊነት ላይ ያተኮረ የጥናት ጹሑፍ ቀርቦ ከመድረኩ ውይይት የተካሄደበት ነበር፡፡