Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትእግር ኳስ ፌዴሬሽን በ90 ሚሊዮን ብር የሕንፃ ግዥ ውል መፈጸሙ ተነገረ

እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ90 ሚሊዮን ብር የሕንፃ ግዥ ውል መፈጸሙ ተነገረ

ቀን:

የለውጥ ዕርምጃው ሠራተኞችን አሥግቷል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከስድስት ዓመታት በፊት በብሔራዊ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ ግቢ ውስጥ ለቢሮ የሚጠቀምበት ቦታ ቢሰጠውም፣ በቦታው ግንባታ ሳያከናውንበት ቆይቷል፡፡

ይሁንና ከሰሞኑ ወሎ ሠፈር፣ አይቤክስ ሆቴል ፊት ለፊት የሚገኝ ሕንፃ በ90 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ድርድር መጀመሩ ተሰምቷል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሕንፃ ግዥ ውል ሒደቱን ስለመጀመሩም አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

በቀደምትነታቸው ከሚጠቀሱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አንዱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ይሁንና ዕድሜውን በሚመጥን ደረጃ ተቋሙ የራሱን የቢሮ መሠረተ ልማት ከማሟላት ጀምሮ ከፍተኛ በሆነ የአደረጃጀት ክፍተት ከሚታመሱ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ካዛችስ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል አጠገብ በእነ አቶ ሳህሉ ገብረ ወልድ የአመራር ዘመን የገዛው አፓርትመንት ካልሆነ እስካሁን የእኔ የሚለው ደረጃውን የጠበቀ ጽሕፈት ቤት ሳይኖረው መቆየቱ እያነጋገረ ይገኛል፡፡

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የእግር ኳስ ደረጃቸው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አባል አገሮች ከቢሮና ከሌሎች መሠረተ ልማት አውታሮች ባሻገር፣ ለእግር ኳስ ልማት የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ ዕገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሠረት ከአንድ ዓመት በፊት ኃላፊነቱን ያስረከበው የአቶ ጁነዲን ካቢኔ፣ ለፊፋ ባቀረበው ትልመ ሐሳብ መነሻነት ለቢሮ ግዥና ተያያዥ ጉዳዮች የሚውል የሦስት ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገለት  አይዘነጋም፡፡ 

በወቅቱ የነበረው የፌዴሬሽኑ አመራር ከፊፋ የተገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ለሚፈለገው አገልግሎት ሳያውለው የቆየው ከሕንፃ ግዥው ጋር ተያይዞ በአመራሩ መካከል በተፈጠረው የውስጥ ሽኩቻ እንደነበረም ሲነገር ነበር፡፡ አመራሩ የአራት ዓመታት የኃላፊነት ቆይታውን የሚያጠናቅቅበት ወቅት ስለነበር፣ በርካቶቹ ኃላፊዎች ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ ራሳቸውን ዕጩ በማድረግ ሲያቀርቡ ምክንያታቸው ‹‹ከፊፋ ጋር የተጀመረውን ጠንካራ ግንኙነትና የሕንፃ ግዥ ለማስፈጸም›› በሚል ለምረጡን ዘመቻ የተጠቀሙበት የቅስቀሳ ዘዴ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ምርጫው በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች መከናወን ከነበረበት ጊዜ ተላልፎ ከብዙ ውዝግብና ትርምስ በኋላ በአፋር ሰመራ መከናወኑ አይዘነጋም፡፡

በአቶ ኢሳያስ ጅራ የሚመራው አዲሱ ካቢኔ በፊፋ የገንዘብ ድጋፍ በ90 ሚሊዮን ብር የሕንፃ ግዥ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ከታወቀ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም፤ ‹‹ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሙሉ ክፍያ ፈጽሞበት የገዛው ሕንፃ የለም፡፡ ምክንያቱም ለሕንፃው ግዥ የሚውለውን ገንዘብ የሚፈቅደው የዓለም አቀፉ ተቋም ስለሆነና ይህንኑ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለፌዴሬሽኑ ገቢ ስላላደረገ፣ ቀደም ሲል ለዚሁ ተብሎ ከሰጠው ገንዘብ ውስጥ ለውል ማስከበሪያ 13 ሚሊዮን ወይም ሕንፃው በአጠቃላይ ከሚጠይቀው ክፍያ አምስት በመቶውን ካልሆነ በቀር የፈጸመው ሌላ ክፍያ የለም፡፡ እንደ አካሄድ ግን ሕንፃ ተገዛ የሚባለው የሚፈለገው ክፍያ ሲፈጸም ነው፡፡ ስለሆነ አሁን ባለው ሁኔታ የሕንፃው ባለቤት ከፈለገ ፌዴሬሽኑ ገዝቶታል ተብሎ የሚነገርለትን ሕንፃ የውሉን ማስከበሪያ በማፍረስ ለሌላ አካል መሸጥ የሚችልበት ሙሉ መብት እንዳለው ሊታወቅ ይገባል፤›› በማለት የድርድሩ ሒደት ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እያከናወነው ባለው የለውጥ ትግበራ ሳቢያ በተቋሙ ሠራተኞች መካከል መደናገጥ መፈጠሩ ተሰምቷል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ከለውጥ ትግበራው ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል እንደተናገሩት፣ ‹‹ተወደደም ተጠላ፣ ፌዴሬሽኑ ትክክለኛ አደረጃጀት ይኑረው ከተባለ በጥናት የተረጋገጠ ሪፎርም ማድረግ ይጠበቅበታል፤›› ብለዋል፡፡ ከሰሞኑ ከዚህ የፌዴሬሽኑ የለውጥ ዕርምጃ ጋር በተያያዘ የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች በአካዴሚክ ብቃታቸውና ዝግጅታቸው ደረጃ አዳዲስ ምደባዎች እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡  

በዚህም በተቋሙ በአንዳንድ ንዑስ ክፍሎች ማለትም ውድድር፣ ዳኝነት፣ ቴክኒክና ልማት፣ እንዲሁም በሌሎችም የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ የኃላፊነት ሽግሽግ የተደረገባቸው ሠራተኞች ቅሬታ ማሰማት እንደጀመሩ ታውቋል፡፡                                                                                                         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...