Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክያልተሟላው የሕዝብ ቆጠራ የሕግ ማዕቀፍ

ያልተሟላው የሕዝብ ቆጠራ የሕግ ማዕቀፍ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

መግቢያ

ከተለያዩ አገሮች የሕዝብ ቆጠራ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ቆጠራን ተከትሎ የሚመጡ አለመግባባትና ሙግቶች አሉ፡፡ የቆጠራው ውጤት መንግሥታዊ ውሳኔዎች ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንደሚኖርም የታወቀ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከበጀት፣ ከማኅበራዊ አገልግሎት ማቅረብ፣ በየደረጃው በሚኖሩ ምክር ቤቶችና አጠቃላይ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ከመወከልና ከመሳተፍ ጋር ተያይዞ አለመግባባት ተከስቷል፡፡ በተወሰኑ አገሮች ካለመግባባት አልፎም ግጭትም ደም አፋሳሽ ግጭት የተፈጠረባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡ ይባስ ብሎም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም ቀውስ ውስጥ የገባባቸው አገሮችም ነበሩ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን የሕዝብ ቆጠራ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታ፣ እነዚህ አንድምታዎች አሉታዊ ውጤት እንዳያስከትሉ አስቀድሞ ጥንቃቄ የማድረግን አስፈላጊነት ለማሳየት ነው፡፡ ስለሆነም ቆጣሪው ስለሚቆጠረው ሰውና ጉዳይ ለምን እንደሚቆጠር፣ የት እንደሚቆጠር በማንሳት በጥቂት ነጥቦች ላይ ምጥን አስተያየት ይቀርባል፡፡ በዋናነት ሕገ መንግሥቱንና የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተንጠለጠለ ትንተና ይቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ ነገራችንን የበለጠ ለማብራራትም ሆነ ለመኮነን የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ጥናቶችን፣ እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን ሕግጋትና ሰነዶችንም በዋቢነት እንጠቀማለን፡፡

ያልጠሩ ሐሳቦች

ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 በአማርኛ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን በእንግሊዝኛው (Population Census Commission) የሚል ርዕስ ይዟል፡፡ ይሁን እንጂ ለርዕስነት የተመረጡት ቃላት ከጅምሩ መስተካከል ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ በአንድ በኩል (Census) የሚለው ቃል ቆጠራ ብቻ የሚል ትርጉም ይዟል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹Census›› የሚለው ቃል ‹‹Population›› (ሕዝብ) የሚል ገላጭ ጨምሮ ሕዝብ ቆጠራ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ቆጠራ የሚደረገው ቢያንስ ሕዝብና ቤትን በመሆኑ አንድን ብቻ ነጥሎ ርዕስ ማድረግ ተገቢ አልነበረም፡፡ በተጨማሪም ይህ አንቀጽ ብሔራዊ ሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ስለሆነና የእንግሊዝኛው ላይ ‹‹National Census Commission›› ወረድ ብሎም በተመሳሳይ ሁኔታ ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ላይ ‹‹There shall be established a National Census Commission. . . ›› እንዲሁም ‹‹Members of the National Census Commission . . .›› በሚል ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ በአማርኛው ላይ ግን ‹‹National›› የሚለውን የተካ ቃል አልገባም፡፡

አማርኛ አገላለጽ ቢያንስ ሁለት ነጥቦች ስቷል፡፡ አንዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው፣ ዩኤንኤፒኤ ተብሎ በአህጽሮተ ስሙ የሚታወቀው ‹‹United Nations Fund for Population Activities›› (UNFPA) የሰጠው ብያኔ ጋር አለመግጠሙን እንረዳለን፡፡ ይህ ደግሞ ትኩረቱ ሕዝብን ብቻ ወደ መቁጠር ያሳንሰዋል፡፡

ሁለተኛው በእንግሊዝኛው የሚለው ቃል የአገራችን ኢትዮጵያን የአንድነቷ መገለጫ፣ አንድ ተቋም ብቻ መኖርን፣ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለ ምንም መነጣጠል የጋራቸው መሆኑን የሚያይ ሲሆን፣ በአማርኛው ላይ ብሔራዊ ሳይባል መዘለሉ ቃሉ የቆመለትን ዓላማና ትርጉም በሐሳብም በተግባርም እንዲያጣ ወይም እንዳይዝ መንደርደሪያ ይሆናል፡፡ ብሔራዊ ባንክ፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ ወዘተ እንደሚባለው፣ ‹‹ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ጥናት ኮሚሽን›› አልተባለም፡፡ ስለሆነም የዚህ ተቋም ፋይዳና ገለልተኛነት የፖለቲካና ሕዝባዊ አጀንዳ ሳይሆን የአንቀጽ 103 ይዘት ወደ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ይዘት እንመለስ፡፡ አንቀጹ ሙሉ በሙሉ የሕዝብ ቆጠራን ብቻ ይመለከታል፡፡ ስድስት ንዑሳን አንቀጾችም አሉት፡፡ ይህን ያህል ንዑሳን አንቀጾች ያለው ድንጋጌ መኖሩ በራሱ የተሰጠውን ትኩረት ያመለክታል፡፡ ይዘቱን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ የመጀመርያ የቆጠራውን አካል አወቃቀር፣ ተጠሪነትና ኃላፊነት የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቆጠራን አስፈላጊነትና ግብ ይመለከታል፡፡

ሀ. የኮሚሽኑ አቋምና ተጠሪነት

የሕዝብ ቆጠራና ጥናት የማከናወን ኃላፊነት ብቻ ያለው ኮሚሽን መቋቋም እንዳለበት አንቀጽ 103 (1) ላይ ተገልጿል፡፡ የኮሚሽኑ አባላትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡ የኮሚሽኑ ተጠሪነትም ለምክር ቤቱ ነው፡፡ ኮሚሽኑም ዋና ጸሐፊና አስፈላጊ ሙያተኞችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም ይኖሩታል፡፡ ዓመታዊ በጀቱንም በቀጥታ ለምክር ቤቱ አቅርቦ ያስፀድቃል፡፡

ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ሥር ሙሉ በሙሉ እንዳወድቅ፣ ብሎም ገለልተኛ እንዲሆን ታሳቢ ያደረገ ይመስላል፡፡ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጀቱንም በቀጥታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያስፀድቅ ማለት በአስፈጻሚው ወይም በገንዘብና ኢኮኖሚ ብሎም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል አያቀርብም፡፡ ስለሥራ አፈጻጸሙም በየጊዜው እንዲሁ ለምክር ቤቱ ነው ሪፖርት የሚያቀርበው፡፡

ለ. የኮሚሽኑ ተግባራት

ወደ ኮሚሽኑ ተግባራት ስንሻገር በዋናነት የአገሪቱን ሕዝብ መቁጠርና ማጥናት ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ቆጠራውን ደግሞ በየአሥር ዓመቱ የማከናወን ግዴታ አለበት፡፡ የጥናቱ/የቆጠራው ውጤት ደግሞ ለተለያዩ ጥቅሞች ሊውል ቢችልም የምርጫ ወረዳዎችን ለማካለል ይውላል፡፡ የምርጫ ወረዳዎችን የሚያካልሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የምርጫ ቦርድ ናቸው፡፡ ስለሆነም በየአሥር ዓመት አንድ ጊዜ አገር አቀፍ ቆጠራና ጥናት ማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት ቢሆንም፣ በአጠቃላይ በየጊዜው የናሙና ቆጠራና ጥናት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ዓመታዊ በጀት መጠየቅና በየጊዜው ሪፖርት ማቅረብ የተጠበቀበት በቋሚነት የሚኖር ተቋም ስለሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም እንዲኖሩት የተፈለገው ሕዝብን መቁጠርና ማጥናት የዚህ ተቋም ኃላፊነት ስለሆነ ነው፡፡

በድጋሚ የቀረው ኮሚሽን

ኢሕአዴግ የመንግሥትነት ሥልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ እንኳን ቅኝት ብናደርግ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አራት አዋጆችን አውጥቷል፡፡ የመጀመርያው በሽግግር ወቅቱ ጊዜ ሲሆን፣ የአዋጁ ቁጥርም 32/1985 ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱን መፅደቅ ተከትሎ የቀድሞውን አዋጅ ያሻሻለው ደግሞ በ1989 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ቁጥር 84/1989 ነው፡፡

ከዚያም በ1991 ዓ.ም. ኮሚሽኑ እንደገና ለማቋቋም ሌላ አዋጅ ወጣ፡፡ አዋጅ ቁጥር 180/1991፡፡ በእነዚህ በሦስት አዋጆች መልሶ ቀልሶ ሲቋቋም የነበረው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ በ1987 ዓ.ም.፣ ሁለተኛውን አገር አቀፍ ሕዝብና ቤት ቆጠራና ጥናት ብቻ ነው ያከናወነው፡፡ ለነገሩ ሦስተኛውም ሳይከናውን ከእንደገና በአዋጅ ቁጥር 449/1997፣ ኢትዮጵያ ምርጫ 97ን ተከትሎ በግጭት እየታመሰች በነበረችበት ወቅት ግንቦት 18 ላይ የቀድሞው አዋጅ ተሽሮ ኮሚሽኑ ከእንደገና በሌላ ሕግ ተቋቋመ፡፡   

በዚህ አዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽን የ1999ኙን ሕዝብና ቤት ቆጣራና ጥናት በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን አማካይነት አከናወነ፡፡ በ1960 ዓ.ም. የተቋቋመው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን በሌላ አዋጅ ከኮሚሽኑ አንድ ወር ቀደም ብሎ ሚያዝያ 12 ቀን በቁጥር 442/1997 ሌሎች ሥልጣንና ተግባር ተጨምረውለት በድጋሚ ተቋቋመ፡፡ አሁንም በሥራ ላይ ያለው ሕግ ይኼው ነው፡፡

አዋጅ ቁጥር 449/1997 የመጣውም የኮሚሽኑን ሥልጣን ለመቀነስና አንዳንድ የአሠራር ለውጦችን ይዞ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 442/1997 የኮሚሽኑ ሥልጣን ኃላፊነት ወደ ስታትስቲክስ ባለሥልጣኑ ስለተዛወረ ይኼንኑ ለማስተካከል ሲባል የመጣ ነው፡፡ ከአዋጅ ቁጥር ላይ ምን ምን እንደተቀነሰ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ከአዋጅ ቁጥር 180/1991 ጋር በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ንፅፅር እናድርግ፡፡

የኮሚሽኑ በባለሥልጣኑ መተካት

በአዋጅ ቁጥር 180/1991 ገና ከመግቢያው የጀምሮ የምናገኘው ሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚል ሐረግ አለ፡፡ በትርጓሜ ክፍሉ በአንቀጽ 2 የሕዝብ ቆጠራንም የቤት ቆጠራንም የብቻቸው ትርጓሜ ተሰጠቷቸዋል፡፡ እንደ ዓላማም ያስቀመጠው የሕዝብ ቆጠራ ብቻ ሳይሆን የቤትንም ጭምር ነው፡፡ የናሙና ቆጠራዎችን ማድረግም በአንቀጽ 7 (7) መሠረት እንዲሁ የኮሚሽኑ ሥልጣን ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረትም ኮሚሽኑ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ስብሰባ ማድረግ አለበት፡፡ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤትም እንዴት መዋቀር እንዳለበት ስለሠራተኞች አስተዳደርና ወዘተ በግልጽ ሠፍሮ እናገኘዋለን፡፡

የኮሚሽኑ ሰብሳቢን የሚሰይመው ከአባላቱ መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ (ዋና ጸሐፊ) የኮሚሽኑ አባልና ጸሐፊ ሆኖ፣ ነገር ግን ድምፅ የመስጠት መብት አይኖረውም፡፡ ምንም እንኳን የኮሚሽኑን አባላት የማቅረብ ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሰጥም፣ ይህ አዋጅ ደግሞ አንቀጽ ስድስት ላይ አባላቱ ከዘጠኙ ክልሎች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ እንደሚሆኑ ደንግጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ያጣበበው ይመስላል፡፡

አዋጅ ቁጥር 449/1997 የቤት ቆጠራ የሚለውን እርግፍ አድርጎ ትቶታል፡፡ እየለቀመ አውጥቶታል፡፡ ከትርጓሜ አንቀጹም ላይ ፍቆታል፡፡ እንዲያውም አዋጁ እንዲወጣ ምክንያቱን ‹‹አዋጅ ቁጥር 180/1991 በተግባር ሲታይ ሥራ ድግግሞሽ የሚፈጥር ሆኖ በመገኘቱ›› በማለት ሥራውን በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ከአንድ ወር በፊት መነጠቁን አሜን ብሎ በመቀበል ሕጋዊ ዋስትና ሰጠው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በእሱ ቁጥጥርና ክትትል ሥር የነበረን ተቋም ሥልጣንና ኃላፊነቱን ቀንሶ አሽቀንጥሮ በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሥር ለሚገኝ መሥሪያ ቤት ሰጠ፡፡ የኮሚሽኑ ተግባር ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ጋር ቢደራረብና ቢደጋገም ወደ ኮሚሽኑ ማጠቃለል እንጂ ወደ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ አይሰጥም፡፡ ምክንያቱም ኮሚሽኑ በሕገ መንግሥቱ የታወቀና ተግባርና ኃላፊነቱም ከሞላ ጎደል የተለየ በመሆኑ ነው፡፡

የኮሚሽኑ አባላትና አመራረጣቸው

የኮሚሽኑ ሰብሳቢንም በቀድሞው አዋጅ ምክር ቤቱ ከአባላቱ መካከል የሚሾም ሲሆን፣ በዚህኛው ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀራቢነት ሚኒስትር ወይም ከዚያ በላይ ሥልጣን ያለው እንደሚሆን ደንግጓል፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤትም በተደራቢነት የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት እንዲሆን አንቀጽ 5(3) ላይ ተደነገገ፡፡ ለሕዝብ ቆጠራ ጉዳይ ብቻ ሲሆን፣ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለኮሚሽኑ እንደሚሆን አዋጁ ገለጸ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ የኮሚሽኑ አባልና ጸሐፊም ይሆናል፡፡ በቀድሞው አዋጅ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የኮሚሽኑ አባልና ጸሐፊ ሆኖ ድምፅ የመስጠት መብት ያልነበረው ቢሆንም፣ በዚህኛው ግን በዝምታ ስላለፈው ድምፅ የመስጠት መብት አለው ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ሌላው ትዝብት አለ፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሚሾመው በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር አቅራቢነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የኮሚሽኑ አባላት ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡

በዚህ አዋጅ መሠረት ግን የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሹመት ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምንም ዓይነት ሚና ሳይኖረው የኮሚሽኑ አባልና ጸሐፊ እንዲሆን አዋጁ ፈቅዷል፡፡ የኮሚሽኑ አባላትን በሚመለከት ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ ከምርጫ ቦርድና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ እንዲሁም ከፌዴራል ሚኒስትር ሚኒስትሮች እንደሚሆን አንቀጽ 7 ይናገራል፡፡ በዚህ ዓመት ኅዳር ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የኮሚሽኑ ብዛት 20 ሲሆን፣ በሕጉ ላይ ከተገለጸው ባፈነገጠ መልኩ የባለሥልጣኑን ዋና ሥራ አስኪያጅ የምርጫ ቦርድ ኃላፊን፣ የአዲስ አበባና የአፋር ክልል ተወካዮችን አልያዘም፡፡

ከቆጠራ ፋይዳዎች አንዱ

ከኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው የቆጠራው ግብ የሕዝብ ኑሮ ለማሻሻልና ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው መሠረት ፖለቲካዊ ሥርዓትን ለማከናወን ነው፡፡ በአገር አቀፍም ይሁን በሌሎች ከዚያ በታች ባሉ ዕርከኖች ላይ ለሚደረጉ ምርጫዎችን ለማከናወን አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ይሰጠዋል፡፡ ለተለያዩ ዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል፣ ትንተና፣ ጥናትና ምርምር የማድረግ ዓላማዎችንም ያካትታል፡፡

በየአሥር ዓመቱ በሚደረገው ቆጠራ መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወከሉት ከእንደገና ይሰላል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤትም ይወሰናል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 (3) ላይም እንደተገለጸው፣ በዚህ ምክር ቤት ተወካይ ሆነው የሚመሩት ሰዎች መሠረቱ የሕዝብ ቁጥር ነው፡፡ የሚወክሉት በተቻለ መጠን እኩል (ተቀራራቢ) ብዛት ያለውን ሕዝብ ነው፡፡ ልዩ ውክልና ከሚያስፈልጋቸው በስተቀር፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የፓርላማ መቀመጫ በየክልሉ፣ በ1999 ዓ.ም. የቆጠራ ውጤትና የ2011 ዓ.ም. ግምት በማስቀመጥ ለ550 የምክር ቤት መቀመጫ ምን መሆን እንዳለበት ነው ምሳሌው የሚያሳየው፡፡

በየክልሉም ሆነ የመላው አገሪቱን የሕዝብ ቁጥር ግምት የተወሰደው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ያሰላውን ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 111/1989 መሠረት በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሚኖረው ሰው ግምት 100,000 ነበር፡፡ በ1999 ዓ.ም. የቆጠራው ውጤትን ብንጠቀም አንድ የምርጫ ወረዳ በአማካይ 134 ሺሕ ሕዝብ መያዝ ሲኖርበት፣ በ2011 ዓ.ም. ግምት ደግሞ አጠቃላይ ሕዝቡ 98 ሚሊዮን 665 ሺሕ ስለደረሰ አንድ የምርጫ ወረዳ ወደ 18 ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ እንዲይዝ ሆኖ መካለል ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በየክልሉ የሚኖረው ተወካዮች ላይ ለውጥ ስለመኖሩ የየክልሎቹን ሕዝብ ብዛት ለ134 ሺሕና ለ180 ሺሕ በማካፈል ማረጋገጥ ይቻላል፡፡  

ይህ አጠቃላይ ሕዝቡን ለየምርጫ ወረዳዎች እኩል በእኩል በማካፈልና እኩል ውልክልና እንዲኖር የማድረግ ዘዴን (Equal Proportion aka the Hill or Huntington Method) በመጠቀም የሚገኝ ውጤት ነው፡፡ የምርጫ ወረዳን በድጋሚ ማካለያ ዘዴዎች (Reapportionment Methods) መካከል ከላይ የተጠቀሰውን አንዱ ብቻ ቢሆንም፣ ሌሎች ዘዴዎችም ስላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው በመቀየርም ይሁን ቀድሞ በነበረው የየክልሎቹ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና ጭማሬን መሠረት ስለሚያደርግ ውጤቱ ላይ ለውጥ ሊኖር የመቻል ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

ባለ አንድ ራስ ሁለት ምላሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

የብሔሮቹ ስም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሰጣል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ከተመለከቱት ጋር እንዲዛመድ በማድረግ ይቆጠራል፡፡ ወይም ከዝርዝሩ ውጪ ከሆነም የብሔሩ ስም ይገለጻል፡፡ ካልሆነም ‹‹ሌሎች›› በሚል ጥቅል ምድብ ውስጥ ይካተታል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ውክልና ያላቸውን በዝርዝሩ ውስጥ እንደሚካተቱ ይጠበቃል፡፡ ምክር ቤቱ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን 77 ብሔሮች ላይ ደርሷል፡፡ በ1987 ዓ.ም. የቤት ቆጠራ ወቅት በኢትዮጵያ 84 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በ1999 ዓ.ም. ደግሞ 85 ሲሆኑ፣ በ1987 ዓ.ም. ከነበሩት አምስቱ ይቀሩና ሌሎች ስድስት ተጨምረዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ አቆጣጠር ግጭት የማስነሳት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለኮሚሽኑ 84 ወይም 85 የብሔር ዝርዝር ይልካል፡፡ በራሱ ምክር ቤት ግን እስካሁን ከ67 ተነስቶ 77 ላይ ነው የደረሰው፡፡ የትኛውም ብሔር በፌዴሬሽን ምክር ቤት መቀመጫ ይኖረው ዘንድ ሕገ መንግሥቱ ያስገድዳል፡፡ በቆጠራ ደግሞ የብሔርን ዝርዝር እንዲልክ በአዋጅ ቁጥር 449/1997 በተደነገገው መሠረት ስለሚልክ ለኮሚሽኑ የሚልከውና በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ተመሳሳይ መሆን ሲገባው ሁለት ዓይነት መረጃ በመያዝና በማቅረብ ተጠምዷል፡፡ እንዲቆጠሩ ስማቸውን እየላከ፣ መቀመጫ እንዳያገኙ መግፋት ምን የሚሉት የኃላፊነት ማጣት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ እንዲያውም አንዴ ዝርዝራቸውን ለኮሚሽኑ በመላክ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በመተው ግጭት ፈጣሪም ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

የዊሊያምና ሜሪይ የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ካሬ ፒክስለር ስለአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ሕግና አተገባበር በጻፉበት አንድ ሀተታቸው ላይ ‹‹የአዶልፍ ሒትለር፣ የጄኔራል ዊሊያም ሸርማንና የፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት የሕይወት ታሪክ መጽሐፍት አንድ የሚጋሩት ጭብጥ አለ፡፡ ይኼውም ሦስቱም የሕዝብ ቆጠራ መረጃን እኩይ ለሆነ መንግሥታዊ ግብ መጠቀማቸው ነው፡፡ ሒትለር የመላው አውሮፓን የሕዝብ ቆጠራ መረጃ አይሁዶችን ለመለየትና የጭፍጨፋ ዒላማው ለማድረግ ተጠቀመበት፡፡ ሸርማን የአሜሪካን የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ለጆርጂያ ዘመቻው ተጠቀመበት፡፡ ሩዝቬልት የሕዝብ ቆጠራ ውጤትን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጊዜ ጃፓኖችን በማቆያ ካምፕ ለማሥፈርና በዚያው ለማቆየት ተጠቀመበት፡፡

ይኼ የሕዝብ ቆጠራ ውጤትን ለበጎ እንደሚውለው ሁሉ እኩይ ለሆነ ግብም እንደሚውል ማሳያዎች ናቸው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ጃፓን ፒርል ሐርበርን ከደበደበች በኋላ ሩዝቬልት በአሜሪካ የሚገኙ ጃፓኖችን (ጃፓናዊ ተወላጆችን) ለይቶ ማወቅና አንድ ካምፕ ውስጥ ማሥፈር ፈለገ፡፡ ይኼኔ ማን ጃፓናዊ ተወላጅ እንደሆነና የት እንደሚገኝ ማወቅ ግድ ሆነ፡፡ የሕዝብ ቤት ቆጠራ ቢሮ ሙሉ መረጃ ስለሰጠ 112,000 ጃፓኖች ማቆያ ካምፕ ውስጥ ከየቦታው እየተለቀሙ ገቡ፡፡ በ2004 ዓ.ም. ይኼው ቢሮ አሜሪካ የሚገኙ (አሜሪካዊ ዓረቦችን) ዓረቦችን የአገር ውስጥ ፀጥታ (ደኅንነት) ዲፓርትመንት መረጃ ሲጠይቅ ዝርዝር ይሰጠዋል፡፡ መነሻው የአሜሪካን የፀጥታ ሥጋት ለመቀነስ ቢሆንም፣ የተነሳው የሕግ ጉዳይ ቢሮው የግለሰቦችን መረጃ ለማን መስጠትና አለመስጠት እንዳለበት አለመታወቁ ነው፡፡

የቆጠራ ጥሬ መረጃን መቼና ለማን መስጠት እንዳለበት በግልጽ ባይደነገግም ሁለቱም አዋጆች ማለትም 442/1997 እና 449/1997 ያልተጠቃለሉ ወይም ያልተተነተኑ፣ ለቀረበ ጥያቄ የተሰጡ መልሶችንና ምላሾችን ፍርድ ቤት ሳያዝ መስጠት ክልክል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕጎቹ ክልከላውን ተላልፈው መረጃ የሰጡ ሰዎች የሚኖርባቸውን የወንጀል ኃላፊነት አይገልጽም፡፡ አስተዳደራዊ ቅጣትም አልተደነገገም፡፡ ይባስ ብሎም ሁለተኛው አዋጅ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ያልተጠቃለሉ መረጃዎች እንዳይሰጥ ከለከለ እንጂ መረጃ ሰብሳቢዎች ወይም ሠራተኞች መረጃ ቢሰጡ የሚለውንም አይመልስም፡፡

ማጠቃለያ

ለማጠቃለል የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ለብዙ ውሳኔዎች በግብዓትነት እንደሚውል የታወቀ ነው፡፡ ቆጠራው በአግባቡና በጥንቃቄ፣ እንዲሁም በገለልተኛነት መመራት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ ሕገ መንግሥቱ ስለኮሚሽኑ ገለልተኝነት ዝምታን መርጧል፡፡ በተግባርም የኮሚሽኑ አባላት ጥንቅርም ገለልተኝነቱን አይመሰክርም፡፡ የሆነው ሆኖ በርካታ ብሔሮችና ሃይማኖት በሚገኝባት አገራችን የሕዝብ ቆጠራ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ አሳሳቢነቱ ደግሞ የቅማንት ማኅበረሰብም ሆነ የአማራ ሕዝብ ላይ የተሠራው ሻጥር ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የቆጠራው ውጤት ተዓማኒነት ያለው መሆኑ ወሳኝ ነው፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች ከሕዝብ ቆጠራ ጋር የሚያያዙ አለመግባቶች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ግልጽ አሠራር ካለመኖሩ አኳያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡

ስለዚህ ኮሚሽኑ በድጋሚ ቀርቷል፡፡ እንደ ተቋም ራሱን ችሎ ገለልተኛ ሆኖ አልተደራጀም፡፡ ከ1985 እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ በአንፃራዊነት በተሻለ ሁኔታ እየተዋቀረ ሄዶ ነበር፡፡ ከዚያ እንደ አዲስ ሲዋቀር የ1999ኙን ዓይነት ቆጠራ አከናወነ፡፡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አማራ ያጠፋውን፡፡ እያደር ገለልተኝነቱ እየጠፋ ሄደ ማለት ይቻላል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

      

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...