Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዕድል የማበላሸት ልማዳቸውን አበላሽተው አያውቁም እንዳንባል

ዕድል የማበላሸት ልማዳቸውን አበላሽተው አያውቁም እንዳንባል

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ከጥላቻ ፖለቲካ ውስጥ እንውጣ፣ በዕርቅ እንተቃቀፍ፣ ወገንተኛ ባልሆኑ አውታራት ላይ ዴሞክራሲን እንገንባ፣ ማንነትን፣ በተለይም ብሔራዊ ማንነትን ከኢትጵያዊነት ጋር እናግባባ፣ እንደ አገር ህልውናን በሚወስኑ የቀጣናችንና የአኅጉራችን አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ እናተኩር፣ በአጠቃላይ በውስጧ ሰላም የሆነች፣ ከሌሎችም ጋር በሰላም የምትኖር እውነተኛ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብክ ኢትዮጵያን እንገንባ ብሎ የተነሳውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩት ለውጥ እነሆ መጋቢት 24 ሲመጣ አንድ ዓመት ይሞላዋል፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአብዛኛውም በመጀመርያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ የሚፈለጉ ግን ያልተጠበቁ ዓለምንም፣ አኅጉርንም፣ አገርንም ያስደነቁ ብዙ አዳዲስ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

‹‹የፖለቲካ እስረኞች ብሎ ነገር አላውቅም››፣ ‹‹የጠላት ወሬ ነው›› ይል የነበረ ፓርቲና መንግሥት ራሱ መንግሥት ሳይገረሰስ፣ የፖለቲካ እስረኞችን በስማቸው ጠርቶ ከእስር ቤት ለቋል፡፡ የአሸባሪነትን ትርጉም በገዛ ራሱ ፓርላማ ውስጥ፣ ‹‹ማነው አሸባሪ?›› ብሎ የጠየቀው የለውጡ የመንግሥት አመራር አሸባሪ በማለት የፈረጃቸውን የተቃዋሚዎች ስያሜ ሽሮ ወደ አገር ለሰላማዊ ትግል ጋብዟል፡፡ ፓርቲዎች፣ ስደተኞችና ተቃዋሚዎች አበባና ባንዲራ በያዙና በተሸለሙ ደጋፊዎቻቸው እየታጀቡና በሆታና በዕልልታ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው፣ ለዓለም ገላጋይና ሽማግሌ አስቸግሮ የኖረው ከ20 በላይ ዓመታት ደመኛ ግንኙነት ባልተገመተ ፍጥነትና ብዙ ውጣ ውረድ ባልታየበት ጥሪና ጥረት ቀጣናዊና አኅጉራዊ ሰላም ፈጥሯል፡፡ ከአገር ውስጥ ተቃውሞ ጋር ተሸራርቦ የነበረው የኤርትራ ጠላትነት በመለወጡ ደግሞ፣ ለአገር ውስጥ ሰላም የማይናቅ ተጨማሪ ጉልበትና ብርታት ሰጥቷል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ገጽታ ታይቶ የማይታወቅ አዎንታዊ ስምና ዝና አግኝቷል፡፡ ስም ያላቸው የዓለም መገናኛ ብዙኃን በየፊናቸው ‹‹በልዩ ዝግጅት›› ለውጡን አጅበውታል፡፡ ሌላው ሌላው ቀርቶ መኖሩ አለመኖሩ፣ መምጣቱ አለመምጣቱ፣ በተለይም አለመኖሩና አለመምጣቱ (መቅረቱ) ልዩነት ባያመጣም፣ ኢትዮጵያ ለዚህ ዓመት የኖቤል ሽልማት ታጨች ማለት በቁም ነገር የተነሳው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የአዲሱ ለውጥ ማስረጃ ግን የውጭ ‹‹ምሥጋና›› እና ‹‹ውዳሴ›› ብቻ አይደለም፡፡ ተጨባጭና መሬት ላይ የሚታዩ የለውጥ ጅምር ዕርምጃዎች አሉ፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር እንዲጣላ ያደረገው፣ የኢትዮጵያን ‹‹ዴሞክራሲያዊነት›› እና ‹‹ሪፐብሊክ››ነት የውሸት የውሸት ያደረገው፣ ገዥው በሕዝብ ድምፅ የሚወጣበትና የሚወርድበት ሥርዓት እንዳይኖር ያደረገው ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ ኢወገናዊ ተቋማት አለመኖራቸው ነው፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ እንደ ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤትና ሌሎችም የዴሞክራሲና የመብት ተቋማት ገለልተኛ ሆነው ባለመቀረፃቸው፣ ይልቁንም ፖለቲካኛ ሆነው ተጠፍጥፈው በመሠራታቸው ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ገለልተኝነትን ለመመሰል ዓይኗን በጨርቅ እንደ ተጋረደችው ሴት ለፓርቲያዊም ሆነ ለብሔርተኛ ወይም ለሌላ አድልኦ ዓይናቸው የተጋረደ ሆኖ የሁሉም፣ የሁላችንም የጋራ አለኝታ ተደርገው ለመታየት የሚችሉበት ታሪክ በወሬ ብቻ ሳይሆን በዕቅድ በመንግሥት ፖሊሲ ደረጃ መጀመሩ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡

ዛሬ ዓብይ አህመድና መንግሥታቸው ስለገለልተኛ ፍርድ ቤት ስለገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ማንንም ስለማይወግን መከላከያ፣ ስለገለልተኛ ‹‹ኮሚሽን››፣ ስለገለልተኛ ‹‹ሰብሳቢ›› ጮኾ ሲናገር እየሰማን ነው፡፡ የለውጡ ተጠናዋቾች ብቻ ሳይሆኑ የለውጡ ደጋፊዎች ጭምር ሳያውቁት ተረባርበው ካላደናቀፉት በስተቀር፣ ጅምሩና ዕርምጃው የጩኸትና የንግግር ብቻ አይደለም፡፡ ለዘመናት የተከመረ፣ የተከማቸ፣ የተጫነ ከሰማይ ከምድር የከበደ ድብርትና ‹‹ቆሼ›› ቢኖርም፣ በየተቋማቱ የማይናቅ አንዳንዴም ይደፈራል ተብሎ የማይታሰብ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ ‹‹ቢፒአር›› ብቻ እንኳን ሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ዘጠኝ ውስጥ የማይደፈር ምሽግ ሠርቶ ተቋቁሟል የሚባለውን ፍርድ ቤትን፣ ምን ያህል የፓርቲና የካድሬ መጫወቻ እንዳደረገው ጫፍ ጫፉን ሰምተናል (ሪፖርተር የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ቁጥር 1960 ቆይታ)፡፡ የምርጫ አስፈጻሚው አካል ውስጥና ላይ እየታየ ያለው እንቅስቃሴ ትርጉምና አንድምታ የሚታወቀውና የሚረጋገጠው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትልቅ ድልም የሚሆነው ይህ ወይም ያ አማራጭ፣ አማራጭ ፓርቲ፣ አማራጭ ሐሳብ፣ (የ2012 ምርጫ በተቆረጠለት ቀን ይካሄድ? ወይስ ይራዘም ማለት አማራጮች ጭምር) ማሸነፉ አይደለም፡፡ አማራጮች በነፃነት ጎልተው፣ አፍጥጠው መቅረባቸው፣ በእርጋታ ታይተው፣ ተገላብጠው፣ ተመክሮባቸው ሕዝባዊ በሆነ አወሳሰን ዕልባት ማግኘታቸው ነው፡፡

እነዚህ የጠቃቀስኳቸው ጅምሮች የሚያመላክቷቸው ጥሩና ማለፊያ አዳዲስ ሥራዎች ቢኖሩም፣ ሁኔታው ዛሬም ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሰየሙበት ዕለት ወዲያውኑ እንደተናገሩት፣ ‹‹ዓለም በአንድ በኩል በጥሞና፣ በአግራሞትና በጉጉት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሥጋት እየተመለከተው ያለ ለውጥ ላይ እንገኛለን፡፡›› ከሥጋቱ አኳያ ከዚህ ፈቀቅ ያለ የተሻለና አስተማማኝ፣ ለውጡ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ገና አልተቆናጠጥንም፡፡ የዚህ ምክንያት ‹‹ጨዋታው›› በዋናው የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ አለማተኮሩ፣ በጨዋታው ሕግ ላይ የጋራ መግባባት አለመፈጠሩ ነው፡፡

ዓብይ በመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ንግግራቸው፣ ‹‹በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር ዕድሎችን አግኝተን ብዙዎቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል . . . ›› ብለው አሁንም ይህ ሌላ ታሪካዊ ዕድል እንዳያመልጠን ሲሉ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ዕድላቸውን የማስመለጥ ዕድላቸውን አስመልጠው የማያውቁ የሚባሉቱ፣ ከለውጡ ተቃዋሚዎች ይልቅ የለውጥ ደጋፊዎች የሚባሉት ናቸው፡፡ የለውጡ ደጋፊዎች አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡ ችግሩ አንድ ዓይነት አለመሆናቸው አይደለም፡፡ እንኳንስ ‹‹መላው›› የለውጡ ደጋፊ ይቅርና ‹‹ፌዴራሊስቱ›› ራሱ የተለያየ ነው፡፡ ባለ ብዙ አቅጣጫ ነው፡፡ የአሁኑ ማለትም ያለው ሕገ መንግሥትና የፌዴራል አከፋፈሉ እንዳለ ሆኖ፣ ዴሞክራሲ ብቻ ቢታከል ይበቃል የሚል አለ፡፡ ዴሞክራሲ ቢቋቋምም የብሔር ብሔረሰብነት መነጽር ያለው አከፋፈል ካልተቀየረ፣ የሕዝብ መንጓለልና መፈናቀል አይወገድም የሚል አለ፡፡ ያለው የፌዴራል አካላት/አባላት አከፋፈል የአገረ ብሔር ድርሻ ሆኖ እንዲታወቅለትና የአገረ ብሔሩን ሀብትና ምድር የብሔሩ ልጆች የብቻ መጠቀሚያ እንዲሆን የሚፈልግ አለ፡፡

ተደጋግሞ እንደተነገረው መንግሥት ግርሰሳ ውስጥ ሳይገባ የተገኘውን ለስላሳ የለውጥ መንገድና አካሄድ በዓለም ኅብረተሰብ ፊት ጭምር ተደናቂ ያደረገው፣ ያለውን ሕገ መንግሥት እወደዋለሁ ብሎ የመፈጠም ጉዳይ አይደለም፡፡ ያለውን ሕገ መንግሥት የሚወደውም የሚጠላውም በእሱ መሠረት ጨዋታውን መጫወቱ ነው፡፡ የጨዋታው ሕግ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ሕገ መንግሥቱን እስከ መለወጥ የሰፋና የደራ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡

በአገራችን ታሪክ ውስጥ በተለይም ከኤርትራ መመለስ በኋላ የፀደቁት ሕገ መንግሥቶች መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን በመደርደርና በመሰደር፣ እንዲሁም የሕግ ሥርዓቶችን በመዘርዘር ረገድ ብዙ የሚነቀፍ ነገር የነበራቸው አይደሉም፡፡ ዴሞክራሲ ከእነ ስሙ እንኳን የጠፋው እነዚያ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ መኗኗርን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ማቋቋም ባለመቻላችን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊነት እየተለመደና እየተረጋገጠ የሚመጣው ያሰብነውን፣ የፈለግነውን፣ የፈቀድነውን ስንገልጽና ለፍላጎታችን፣ ለፈቃዳችንና ለጥቅማችን ድጋፍ ማሰባሰብ የሚያስችል እንቅስቃሴ ስናደርግ፣ ለእንቅስቃሴያችንም ስምና ዓርማ ሰጥተን፣ ወዘተ እስከ መታገል ድረስ በመብትና በነፃነታችን ውስጥ ስንኖር ነው፡፡ አንድ ሐሳብ ላይ ስለመደረስ ሳንጨናነቅ ተከባብሮ የተለያየ ሐሳብ መለዋወጥን እየተለማመድን፣ የሌሎችን ማለትም የተከታዮቻችንን የገረሩና የጠጠሩ ስሜቶችን መበተንና እንዳይጠራቀሙ መከልከል ስንችል ነው፡፡ እነዚህ መብቶች ውስጥ መኖርን መሠረት ለማስያዝ መረባረብና ችግሮች ሲመጡ ደግሞ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች ለመፍታት፣ ውጤቱንም ለመቀበል የሚያስችል ግትርነትና ባህርይ ይዘን ጨዋታው ውስጥ ነን ማለት በጭራሽ አይቻልም፡፡ ዴሞክራሲ በእውነተኛ ኑሮ ውስጥ በገሃዱ ዓለም ውስጥ የሚለፋበት፣ የአቋመ ብዙነትና ጥል የለሽ ውድድር የሚኖርበት፣ መብቶችና ኃላፊነቶች የተግባቡበት ‹‹ጨዋታ›› ነው፡፡

በዚህ የጨዋታ ሕግ ማዕቀፍና ቅጥር ግቢ ውስጥ እስከሆንን ድረስ፣ በእሱ ከተገዛን ሕገ መንግሥቱን እንዳለ ሳይነካ እንዲቆይ መፈለግ ወይም በቃ ይቀየር ማለት፣ ፌዴራሊዝም ጥሩ ነው ወይም አሃዳዊ ነው ብሎ ለለውጥ መነሳት፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስሟ ፊንፊኔ ነው የለም አዲስ አበባ ነው ከማለት ጀምሮ፣ ከዚያም በላይ ፊንፊኔ የኦሮሚያ ነው ማለት በጭራሽ አያጣላም፡፡ ምክንያቱም ለሁሉም ከላይ ለተጠቀሱት ሁለቱም የጨዋታው ሕግ አክባሪዎች፣ የትኞቹም ፍላጎቶች በሕዝቦች እውነተኛ ድምፅ መወሰናቸውና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ገለልተኛ ሥርዓት መዘርጋቱ የጋራ ጥያቄ ስለሚሆን ነው፡፡ የዚህ ምክንያት የሁሉም የለውጥ ኃይሎች ወይም ደጋፊዎች የመጀመርያው ደረጃ አብሮ የመሥራት ተልዕኮ አስቀድሞ የታወቀ፣ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ በመሆኑ ነው፡፡ መሆንም ያለበት ይኼው ነው፡፡

ይህ የተጀማመረው ዴሞክራሲን ፅኑ መሠረት በማስያዝ ተግባር ውስጥ መከላከያን፣ ደኅንነትን፣ ፖሊሲንና የፍትሕ ተቋማትንና ምርጫ አስፈጻሚ አካላትን በአጠቃላይ መንግሥታዊ አውታራትን ከማንኛውምና ከየትኛውም ፓርቲና ብሔር ወገናዊነት የፀዱ አድርጎ የማነፁ ጅምር ሥራ ግን በቅድመ ሁኔታ እየተጨናገፈ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ ተነስቶ፣ ‹‹አዲስ አበባን ፊንፊኔ ማለት ወይም በአዲስ አበባ ላይ የግዛት ወይም የልዩ ጥቅም ጥያቄ ማቅረብ ከፕሪሚየር ሊጉ ያስወግዳል ሲል››፣ ሌላው ‹‹ፊንፊኔ የኦሮሚያ ከተማ መሆኗን የማይቀበል ፓርቲ ኦሮሚያ ውስጥ እናቱ እንኳን አትመርጠውም›› ይላል፡፡ ምንም ነገር ከንግግር በላይ ባለመሆኑ ጉዳዩ የመናገር መብት ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ ንግግሩ ሐሳብን ከመግለጽ በላይ አፈጻጸሙን ለተለመደውና በቅድመ ለውጥ ተቃውሞ ወቅት በጥቃትና በውድመት ለተበላሸው ትግልና ታጋይ አፈጻጸሙን መስጠት መሆኑ ነው፡፡ ፈትዋ መሆኑ ነው፡፡  

እንዲህ ያለ ‹‹ንግግር›› ከንግግር በላይ ነው የምንለው በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ንግግሩ የሚረባ ተጨማሪ እሴት ስለሌለው ብቻ አይደለም፡፡ መናገርን፣ ለመብት መቆምን፣ ለመሰለው ነገር መከራከርን ጭምር የሚያሸማቅቅ ማስፈራሪያ ነው፡፡ ፈርተን ፈርተን እጅ የሰጠንባቸውን አንድ ሁለት ሌላ ምሳሌዎች እግረ መንገዴን ላንሳ፡፡ ለምሳሌ በአማርኛ ስለኦሮሚኛ ቋንቋ ለመናገር ስንፈልግ፣ ‹‹አፋን ኦሮሞ›› ወይም ‹‹ኦሮሚፋ›› እስከማለት እንጠነቀቃለን፣ እንሠጋለን፣ እንፈራለን፡፡ ቁጣ አለዚያም ቅሬታ ይነሳ እንደሆነ ብለን እንጠነቀቃለን፡፡ ሌላም ሌላም ነበር፡፡ ግን ደግሞ ‹‹ብሔር ብሔረሰብ›› ያስቀይማል ብዬ እፈራለሁ፡፡

ዴሞክራሲ ማለት በሐሳብ ልዩነት ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች ጥል የለሽ ውድድርና ፉክክር የሚያደርጉበት፣ በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት ያሸፈነው ሐሳብ ገዥ የሚሆንበት፣ ገዥውን ሐሳብ እንደገና መመርመር መመልከት ሲያስፈልግ ይህንንም ለሕጉ ተገዥ ሆኖ የሚወስኑበት ሥርዓት ነው፡፡ ተቃራኒ ወይም የማይጥምና የማይገጥም ሐሳብን በወንጀላና በዱላ (በሌላም ሌላም ጭምር) ከማጥቃት ድርጊት ሳይወጡ፣ ተደማምጦ ለመወያየት ሳይጣጣሩ እኔ ብቻ ልክ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ እያሉ ዴሞክራሲንና ነፃነትን ለማግኘት እጥራለሁ ማለት የማይቻል ሥራ ነው፡፡

ዓብይ በመጋቢት 24 ቀን ንግግራቸው ያሉትንና ከላይ የጠቀስኩትን ልድገመው፡፡ ‹‹በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር ዕድሎችን አግኝተን ብዙዎቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል፡፡›› ከቅርቦቹ እንኳን ብንጀምር የ1966 ዓ.ም. አብዮት በደርግ ሥልጣን መያዝ መጨናገፉ አንድ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም.፣ በ1997 ዓ.ም. ሌሎች ዕድሎች አምልጠዋል፡፡

የጥያቄዎቻችንና የዕይታዎቻችን አለመገናኘት በተለይም በጥርጣሬ  ከመከፋፈል ጋር እየተጋገዘ ውጤታማ ትግል ከማድረግ እንደገታን አስተውለን፣ አዲስ የተፈጠረውን ዕድል ከእጃችን እንዳይወጣ ባለ በሌለ ኃይላችን መከላከል አለብን፡፡

ይህንን ለማድረግ በዚህ የሽግግር ወቅት የሚነሳ የትኛውም ዓይነት ግርግር የቅልበሳን ቀዳዳ ስለሚከፍትና የለውጥ ዕድልን የሚያስቀጭ መሆኑን ተገንዝቦ፣ የዴሞክራሲ ጅምራችን በጥያቄና በጫጫታ ጋጋታ እንዳይቀጭ ዕድል ላለመስጠት ትኩረታችንን በአዛላቂ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ አለብን፡፡ በመንግሥት በኩልም ለውጥና ማሻሻያዎችን ማካሄድና ማሳለጥ ማለት ከየአቅጣጫው ለሚመጡ (እንዲያውም በለውጡ ምክንያት ለሚዘረገፉ) ጥያቄዎች እየተዋከቡ መገበር ማለት አይደለም፡፡ ዋናው ሥራ ተቀዳሚ በሆኑ በሁለት የዴሞክራሲ ተግባራት ላይ ማተኮር ነው፡፡

የመጀመርያው ሁሉም ቡድኖች ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገር መገንባትን ሥራችንና ጉዳያችን ብለው የተሰባሰቡበት፣ እንዲሁም ነፃ የብዙኃን ማኅበራትና ነፃ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎዎች የሚፍለቀለቁበት የፖለቲካ አየር መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ፍርኃት መሸማቀቅ በሌለበት አየር ውስጥ ደግሞ ደጋግመን እንዳልነው የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው የዴሞክራሲ ተቋማትንና አውታራትን ማሰናዳት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ከቡድኖች የፖለቲካና የድምፅ ትርፍ ይልቅ፣ ለጤናማ የምርጫ እንቅስቃሴና ዘመቻ ላልተጭበረበረ፣ ምርጫና የሕዝብ ፈቃድን ላገናኘ የድምፅ አሰጣጥ ሥር መያዝ መጨነቅን ያበለጠ የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊናን የማጎልበት ሥራ ማከናወን፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ላይ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ነው፡፡

ሁለተኛው ተግባር መልስና መፍትሔ አሁኑኑ አምጡ እየተባለ ማዋከብ በሌለበት አኳኃን፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ የሰከኑ ውይይቶችን እያካሄዱ ለተዋጣለት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለሁሉም አቀፍ የአገር የሶሲዮ ኢኮኖሚ ልማት የሚበጁ ሁነኛ ጉዳዮችን እየመረመሩ እያብላሉ ወደ መፍትሔ መሄድ ነው፡፡ ሁለተኛው ተግባር ውስጥ የሚካተተው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ካቢኔ ሐሳብ አፍላቂነት በአዋጅ የተቋቋመው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ገና ከጅምሩ ያጋጠመው ተቃውሞና ርብርብ አሳዛኝ ዕድል ቢሆንም፣ ተቃውሞውንም ሆነ ምላሹን በተነጋገርነውና መነሻና መድረሻችን በሆነው በዚያው ዴሞክራሲያዊ ግቢና የጨዋታ ሕግ ውስጥ መመከትና መቅረፅ ያስፈልጋል፡፡ ዋነኛውና ትልቁ ግብ የተባለውና ተቃውሞ የቀረበበት ኮሚሽን እውነት ኢሕገ መንግሥታዊ ነው? አይደለም? የሚለው ባይሆንም መሆን አለመሆኑ ግን መወሰን ያለበት አሁንም በሕግ መሠረት ነው፡፡ ሕግም የዘረጋው ሥርዓት የታወቀ ነው፡፡

አንደኛው በምክር ቤቱ በራሱ የሥነ ሥርዓት ደንብ ‹‹ውሳኔ  የተሰጠበትን ጉዳይ እንደገና ስለማየት›› በሚደነግገው መሠረት መረማመድ ይቻል እንደሆነ ማየት ነው፡፡ ሌላውና የታወቀው መንገድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ኢሕገ መንግሥታዊ ነው ብሎ ማመልከት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በኮሚሽኑ አቋቋም፣ አቋምና ሥራ ላይ በአቋም መግለጫ፣ ወዘተ ‹‹ጫና›› መፍጠር ሕጋዊ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ሕጋዊ አለመሆኑ አይደለም፡፡ በዚህ የተለየ ጉዳይ ላይ በተለይ አቋም የወሰዱ ወገኖች የመወጋገዝ ፖለቲካቸውን አቁመው በሕግ ውስጥ እየተረማመዱ፣ ሁሉም ወገኖች ለአገሪቱ ፖለቲካ ሰላምና ግስጋሴ አስፈላጊነታቸውን በግልጽ ማውጣት ካልቻሉ ኅብረተሰቡ ውስጥ የተሸጋገረውን የጠላትና የወዳጅነት ፍረጃ መበተን አይጀምርም፡፡ ይልቁንም ይደድራል፡፡

የዴሞክራሲን መደላድል የማዘጋጀቱና የማንጠፉን ሥራ ገና ከመጀመሩ፣ ዴሞክራሲን የማደላደልና የማፅናት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ከመድረሳችን በፊት ዋና ዋና ራሱን ዴሞክራሲን የሚፈልጉ ሥራዎችን ዛሬ ካልፈጸምን፣ የሚፈጸሙትም በእኔ መንገድና አማራጭ ብቻ ነው ማለት ቅደም ተከተል ማዛነቅ ብቻ ሳይሆን ዋናውን ተልዕኮ መክዳት ነው፡፡ ‹‹አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር›› እንደገና እና መቼ እንደሚገኝ ፈጽሞ የማናውቀውን ዕድላችንን ማበላሸት ነው፡፡ ዕድላቸውን ከማበላሸት ልማዳቸው ዛሬም አልተላቀቁም፣ ዕድል የማበላሸት ልማዳቸውን አበላሽተው አያውቁም ተብሎ ከሚተረትብን በላይ፣ ሁሉም የግራውም የቀኙም፣ ነባሩም አዲሱም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው የሚሉትን ዴሞክራሲን እንቢ ማለት ነው፡፡

መጀመርያ የዴሞክራሲ መብቶች ይበልጥ ተግባራዊና ተጨባጭነት የሚያገኙበት ሁኔታ እንፍጠር፣ የብዙኃን ማኅበራት ነፃና ንቁ ሕይወት ያግኙ፣ ከፖለቲካ ወገናዊነት ገለልተኛ መሆን በሚገባቸው የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለው ሲወርድ ሲዋርድ የመጣ ወገንተኝነት መጀመርያ ትዝብት ውስጥ ገብቶ ይፈር፣ የፍትሕ አካላት ያለ አድልኦ ለመሥራት (አፍ ያለውንም፣ ጉልበት ያለውንም፣ ባለ ጭፍራውንም፣ ባለ መሣሪያውንም እየሰሙ ከመገበር ወጥተው) ያለ አድልኦና ያለ ፍርኃት ለመሥራት የሚመች ነፃ ደመና ውስጥ ይግቡ፡፡ የፀጥታ ኃይሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣  ታጥቀውም ሆነ ፈትተው ወደ አገር የተመለሱ ኃይሎች፣ አክቲቪስቶች ሊይዙት ስለሚገባ ባህሪይ፣ ባህሪውም የግድ ስለሚጠይቀው ጨዋነት፣ በሚዲያም ሆነ በሌላ መድረክ ሊያራምዱ ስለሚችሉት አቋም በነፃ መነጋገር እንጀምር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ጨዋታዎችን የማወዳደር መሰናዶ ሳናደርግ ቀጥታና አሁኑኑ ስለከተማ ባለቤትነት፣ ስለክልልነት ውሳኔ፣ ወዘተ. እንነጋገር ብንል ይህ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ሱሪ በአንገት ማውጣት ይሆንበታል፡፡ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር ዕድላችንን ያስመልጠናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...