Friday, January 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ ተስፋ በልጆቿ እጅ ላይ ነው!

የታላላቅ ታሪኮች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ፈተናዎች የተሻገረችው በልጆቿ ነው፡፡ የወራሪዎችንና የተስፋፊዎችን ምኞት ከማክሰም ጀምሮ፣ በውስጥ ለሥልጣን የተደረጉ ሽኩቻዎችንና ጦርነቶችን ጭምር ያካሄደችው በልጆቿ ነው፡፡ አንዱ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ሌላው ሲወርድ ሥርዓቶች እየተቀያየሩ እዚህ ዘመን የተደረሰው፣ ባዕዳን በቀጥታ ጣልቃ ሳይገቡ በልጆቿ መካከል በተከናወኑ ድርጊቶች ነው፡፡ ጨቋኝነትም ሆነ ተጨቋኝነት የነበረው በኢትዮጵያዊያን የእርስ በርስ መስተጋብር ነው፡፡ ምንም እንኳ በዚህ መስተጋብር ውስጥ ውስጥ ከፍተኛ ቅራኔዎች እንደነበሩ ግልጽ ቢሆንም፣ በአገር ጉዳይ ተቃርኖ ያላቸው ወገኖች ጭምር አቋማቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ጭቆናው የመደብም ይባል የብሔር ‹‹ዞሮ ዞሮ መዝጊያው ጭራሮ›› እንደሚባለው በአገር ጉዳይ ግን ቀልድ አልነበረም፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድ በእጅጉ ሊረዳው የሚገባው ጉዳይ፣ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ሲደራደሩ አይታወቅምና የአገራቸው ዋልታና ማገር ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው ናቸው፡፡ የአገራቸው ተስፋም በእጃቸው ላይ ነውና፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብን ለድህነት፣ ለኋላቀርነትና ለጉስቁልና እየዳረጉ በገዛ አገሩ ነፃነት አልባ ሆኖ እንዲባዝን ያደረጉት፣ ለዘመናት በገዥዎች መካከል ሥልጣን ለመያዝ ይከናወኑ የነበሩ ግጭቶች እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ ስንመረምር፣ ሥልጣን ከአንደኛው ወደ ሌላኛው የተላለፈበት ሁኔታ እጅግ ከባድ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ጠንካራ መንግሥታት ብታገኝም፣ የአገረ መንግሥት ምሥረታ ሒደቱ እጅግ በጣም ደካማ ስለነበር በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በየካቲት 1966 ዓ.ም. በፈነዳው አብዮት ምክንያት ከሥልጣን ከተወገደው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት እስከ ኢሕአዴግ ድረስ የተከናወኑት የመንግሥት ለውጦች በደም የጨቀዩ ነበሩ፡፡ የዛሬ 11 ወራት አካባቢ በኢሕአዴግ ውስጥ የተካሄደው ከፍተኛ ውስጣዊ ሹኩቻ አስፈሪ የነበረ ቢሆንም፣ ከውስጡ አዲስ ኃይል ወጥቶ አገሪቱ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይህም ሆኖ ግን በተለያዩ ሥፍራዎች በተከሰቱ ግጭቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ ድርጊት በፍጥነት መቋጫ እንዲያገኝ የኢትዮጵያዊያን ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ የአገር ተስፋ በኢትዮጵያዊያን እጅ ላይ ነውና፡፡

በኦሮሚያ ክልል አጋጥመው የነበሩ አደገኛ ግጭቶችንና የንፁኃንን ዋይታ ለማስቆም በአባ ገዳዎች ኅብረት የተደረገው ጥረት፣ መልካም ፍሬ እያሳየ መሆኑ እየተነረ ነው፡፡ ከዕልቂትና ከውድመት ማንም እንደማያተርፍ የታወቀ በመሆኑ፣ ይህ ጥረት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በአማራ ክልል በንፁኃን ላይ እየደረሰ ያለው ሞትና መፈናቀልም በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ በተለይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግጭቱን ለማባባስ ተሳትፎ ያላቸውን በማጋለጥ ለሕግ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ እግረ መንገዱንም የአካባቢው የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ከማኅበረሰቦች ጋር በመሆን፣ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲመጣ በቁርጠኝነት ሠርተው ውጤት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የግጭት ነጋዴዎች ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚጠቀሙባቸውን የዋሆች በመምከርና በመገሰፅ ጭምር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት ዕልቂት በሚደግሱ ሴረኞች ላይ የሚመለከታቸው የመንግሥትና የፍትሕ አካላት፣ ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ግዴታቸው መሆኑን ሊያውቁ ይገባል፡፡ በተለይ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥታት ዳተኝነት ምክንያት እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች መገታት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር ተፅዕኖ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንዱ ክልል ጉዳት ሲደርስበት ሕመሙ የመላ ኢትዮጵያዊያን እንደሆነ ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ደግሞ በዋዛ አይታለፍም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዘመን በርካታ ዕድሎች አሉ፡፡ እነዚህን ዕድሎች በከንቱ ማስመለጥ አይገባም፡፡ የመጀመርያው ተግባር ከምንም ነገር በፊት የኢትዮጵያን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የተሟላ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ሲጠፋ የመንግሥት ሥልጣን ገደብ አልባ ይሆንና ችግር ይፈጠራል፡፡ ከመንግሥት በተጨማሪ ራሳቸውን እንደ መንግሥት ማየት የሚቃጣቸው ጉልበተኛ ቡድኖች ክፍተቱን እየተጠቀሙ ትርምስ ይፈጥራሉ፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይነቱን ይዞ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ሁለተኛው በአሁኑ ጊዜ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ትልቅ ትኩረት ካልተሰጠ አገር የሁከት መናኸሪያ ትሆናለች፡፡ የተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ በፍጥነት አገግሞ ንግድና ኢንቨስትመንት ካሸለቡበት መነሳት አለባቸው፡፡ በየቦታው ታስሮ የተቀመጠ ገንዘብና የፈጠራ ሐሳብ ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውን ከመቻላቸው በላይ፣ ለአገር ተጨማሪ ካፒታል መፍጥር ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ችግሩን ቆሞ ማየት በአገር ላይ አደጋ መጋበዝ ነው፡፡ ሦስተኛው የፍትሕ ሥርዓቱ እስካሁን ከቆየበት ድብርት ወስጥ መውጣት አለበት፡፡ በተለይ የፍርድ ቤቶች ነፃነት በአስቸኳይ ተከብሮ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ መሆን ካልቻለ አደጋ ነው፡፡ የፍትሕ ጉዳይ አሁንም አጠያያቂ እንደሆነ ነው ያለው፡፡ ዜጎች የፍትሕ ያለህ እያሉ አሁንም እየጮሁ ነው፡፡ አራተኛው የዴሞክራሲና የሲቪክ ተቋማት በነፃነት ተደራጅተው ሥራቸውን በፍጥነት እንዲጀምሩ መደረግ አለበት፡፡ መጪው ምርጫ አፍጥጦ እየተቃረበ ነውና፡፡ ምርጫው እውነተኛ ምርጫ መሆን የሚችለው እነዚህ ተቋማት በነፃነት ተደራጅተው፣ በገለልተኝነት ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ አምስተኛው የፀጥታ ኃይሎች ገለልተኝነት በሚገባ ተረጋግጦ፣ የሕዝብና የአገር ጠባቂ መሆናቸው በተግባር እንዲታይ ማድረግ ነው፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ገለልተኝነት ሳይረጋገጥ ስለሕግ የበላይነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የኢትዮጵያ ተስፋ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ልጆችም እነዚህን ተስፋዎች መጠበቅ አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ተስፋ በልጆቿ እጅ በመሆኑ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ለአገራቸው ሰላም፣ ዕድገት፣ ዴሞክራሲና ተሰሚነት በአንድነት መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ወይም ፍላጎቶች ቢኖሩ እንኳ በአቋራጭ ሥልጣን ለማግኘት ሲባል ብቻ፣ የአገር ሰላም ማደፍረስ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ሕገወጥ ነው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው የአገሪቱ ምድር የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩም ሆኑ፣ በባዕዳን አገሮች ያሉ ኢትዮጵያዊያን ከልዩነቶቻቸው ይልቅ የጋራ ጉዳዮቻቸው ይበዛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከጉስቁልናና ከኋላቀርነት በመላቀቅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገነባ በጋራ መመካከር አለባቸው፡፡ ታላቅና ለአፍሪካውያን ጭምር ዋስ ጠበቃ መሆን የቻለች አገር እያለቻቸው፣ በስስትና በፍርኃት ስሜት ውስጥ በመሆን ‹‹የእኛ›› እና ‹‹የእነሱ›› ከሚባል አዙሪት ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ የማይረቡ ፖለቲከኞች የሚፈጥሩትን አሉባልታና አፍራሽ ጭቅጭቅ በማስወገድ፣ የአገራቸውን ፀጋና በረከት አልምተው በጋራ መጠቀም ከተቻለ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ዕድሎቿን በሙሉ መጠቀም ከቻለች የአፍሪካ አንፀባራቂ አገር ትሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ ተስፋ ያለው በልጆቿ እጅ ላይ ነው የሚባለው ለዚህ ነው!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

ቁልፍ የተረከቡ የ40/60 ዕድለኞች በአስተዳደሩ ችግር ምክንያት ቤቶቹን መረከብ አልቻልንም አሉ

በተወሰኑ ቤቶች ላይ ባንክ ማስጠንቀቂያ ለጥፏል ‹‹ያጋጠመን ችግር አገራዊ በመሆኑ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ቀጥሎ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት  አቅም ግንባታ እንቅስቃሴ

በኢትዮጵያ የተቋማት ግንባታ ታሪክ ረዥም ዘመናትን ማስቆጠሩ የሚነገርለት መከላከያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...

የመንግሥት አንዱ ኃላፊነት ዜጎችን ማዳመጥ ነው!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ድጋፍ የሚሰጠውን ወገን ብቻ ሳይሆን፣ በተቃውሞ ጎራ ያለውን ጭምር በአንክሮ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ የዕለት ኑሮዋቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና ከሚሉ ዜጎች...