በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ዳንኤል በቀለ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር እንዲሆኑ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ በመስማማት እንደተቀበሉ ታወቀ።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት አሜሪካን የሚገኙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ዳንኤል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት እንዲመሩ መንግሥት ላቀረበላቸው ጥያቄ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዕጩዎችን የሚያቀርበው ኮሚቴ በዕጩ ኮሚሽነርነት እንደመዘገባቸው ገልጸዋል።
ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ኮሚሽነሮች የሚሾሙት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቋቁመው ኮሚቴ ዕጮዎችን ተቀብሎና መዝኖ ከመረጠ በኋላ ለምክር ቤቱ በማቅረብ ሲፀድቅ ነው።
በዚሁ መሠረትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ወር እረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነር አቅራቢ ኮሚቴ አቋቁሟል። በዚህም መሠረት 11 አባላት የያዘ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን፣ ኮሚቴውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በሰብሳቢነት ይመሩታል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካይ ለኮሚቴው በአባልነት ከተመረጡት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። የተቀሩት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል የተመረጡ ናቸው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ዳንኤል በዕጩነት ለኮሚቴው እንደቀረቡ ለማወቅ ተችሏል።
አቶ ዳንኤል በቀለ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ማግሥት መንግሥት ባቀረበባቸው ክስ ከዓመት በላይ ታስረው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ አክሽን ኤድ ተብሎ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማኅበር ባልደረባ ነበሩ።
ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከአገር በመውጣትና መቀመጫቸውንም በኬንያ በማድረግ፣ አምነስቲ ለተባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ በመሆን የኢትዮጵያንም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ይከታተሉ ነበር።
በመቀጠልም ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ላደረገው ታዋቂው ‹‹ሂውማን ራይትስ ዋች›› የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር በመሆን፣ ለረዥም ዓመታት ኒውዮርክ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤቱ ሲያገለግሉ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።