Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ትዕግሥት የሚባል ነገር ሁሌ ስለማይሠራ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል›› ...

‹‹ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ትዕግሥት የሚባል ነገር ሁሌ ስለማይሠራ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል›› ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

ቀን:

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት አጭር አስተያየት፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ትዕግሥት የሚባል ነገር ሁሌ አይሠራም፣ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፤›› አሉ።

በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን የመጣስና በትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች የሚሰነዘሩበት እንደሆነ ገልጸው፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ የጋራ እንደ መሆኑ መጠን ሁሉም ሊጠብቀው እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አንዱ የሚጠብቀው አንዱ የሚጥሰው መሆን እንደሌለበትም ተናግረዋል።

ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ትዕግሥት የሚባል ነገር ሁሌ ስለማይሠራ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለው፣ እሱ እንዳይሆን (ወደ ዕርምጃ እንዳንገባ) ግን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ገዥው ፓርቲ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ የካቲት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተከበረውን 44ኛ የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫም፣ ድርጅቱና ደጋፊዎቹ የምሥረታ በዓሉን የሚያከብሩት በኢትዮጵያ የተጀመረውና መላው ዓለም የመሰከረለት የለውጥና የዕድገት ጉዞ ወደ ኋላ እየተቀለበሰ፣ ብርሃን ማየት የተቻለበት የብልፅግና ጉዞ ወደ ሥጋትና ጭንቀት እየተቀየረ ባለበት ወቅት እንደሆነ አስታውቋል።

ለተጠቀሰው ችግርም የኢሕአዴግ አመራር ውስጥ የተፈጠረ አለመግባባትና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደሆኑ ያመለክታል።

‹‹የዚህ ሁሉ ችግር መሠረታዊ ምክንያት፣ በኢሕአዴግ አመራር ውስጥ እየተንከባለሉ የመጡ የጥገኝነት አስተሳሰብና ተግባር ወደ ከፋ ደረጃ በመድረሱ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ከዚህ ቀደም በኢሕአዴግ አመራር የተጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ሒደት በጋራ በተቀመጠው አቅጣጫ ባለመሄዱና በመኰላሸቱ፣ እንዲሁም የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ጭምር ነው፤›› ሲል መግለጫው ያትታል።

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ መሆኑን፣ የሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎቶች የሆኑትን ልማትና ዴሞክራሲ ወደ ጎን በመባላቸው የተጀመረው ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሐዊ የልማት ዕድገት ችግር ውስጥ በመውደቅ ላይ ነውም ብሏል።

‹‹በስመ ለውጥ ለአገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት መረጋገጥ ዕድሜ ልካቸውን የደከሙና የለፉ የሚረገሙበትና የሚብጠለጠሉበት፣ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዜጎች ላይ የተለያዩ በደሎችና ግፍ የፈጸሙ፣ እንዲሁም የአገራቸውን ሉዓላዊነት አሳልፈው የሰጡ ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አብረው አገርና ሕዝብ የወጉ የሚመሠገኑበትና ክብር የሚሰጥበት የክህደት ዘመን ላይ ደርሰናል፤›› በማለት ሕወሓት በመግለጫው ትችቱን ሰንዝሯል።

ይሁን እንጂ የአገሪቱ ሁኔታ ሕወሓት ካወጣው መግለጫ በተቃራኒ እንደሆነ በርካቶች ይገልጻሉ።

ከምንጊዜውም የተሻለ ዴሞክራሲ የሰፈነበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የቆሙበትና ቀደም ሲል ለተፈጸሙ ጥሰቶችም ፍትሕ የተሰጠበት መሆኑን የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ በይፋ እየተናገሩ ናቸው።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀል መኖር እርግጥ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ሽግግር ከዚህ የፀዳ ሊሆን እንደማይችል ነገር ግን ይህ ችግር እየደበዘዘ መሄድ እንዳለበትና በአሁኑ ወቅትም መረጋጋት መኖሩን ያስረዳሉ።

ሕወሓት በፖለቲካ ማዕከሉ ላይ የነበረው ተፅዕኖ በመቀነሱ የመገፋት ስሜት ሊጫነው እንደሚችል፣ ይኼንንም የሚያባብሱ የፖለቲካ ትግሎች በኢሕአዴግ ውስጥ መቀጠላቸው በግልጽ የሚታይ ቢሆንም፣ ጉዳዩን ከሕዝብ ጋር ማገናኘት ስህተት እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ሐሳብ ነው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...