-ክለቡ የ49 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቦ 44 ሚሊዮን አውጥቷል
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ባካሔደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ እንዳስታወቀው አጠቃላይ ሀብቱ ከ97 ሚሊዮን ብር በላይ እንደደረሰና በዓምናው እንቅስቃሴው ካሰባበሰበው ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ውስጥ ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ክለቡ እሑድ፣ የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ለታደሙ የጉባዔው አባላት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን አስደምጧል፡፡ የክለቡ አመራሮች ይፋ ባደረጉት መሠረት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በአክሲዮን ደረጃ ለማቋቋም በአማካሪ ኩባንያ በኩል ጥናት ተካሒዷል፡፡ ይህም የክለቡን አደረጃጀትና ባለቤትነት ይበልጥ ሕዝባዊ በማድረግ የገቢ ምንጩን ለማስፋት እንደሚረዳው የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ባቀረቡት ሪፖርት መግለጻቸው ታውቋል፡፡ ቀደምቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተመሠረተበትን 83ኛ ዓመት እያከበረ ይገኛል፡፡
የጉባዔው ታዳሚዎች የክለቡን እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ የቀረበውን ሪፖርት ካደመጡ በኋላ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን ለቦርድ አመራሩ አቅርበዋል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም ክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር ሊያቋቁም እንደሚገባው የቀረበው ይገኝበታል፡፡ በ83 ዓመታት ቆይታው ክለቡ እስካሁን ድረስ የደጋፊ ማኅበር አለመመሥረቱ በደጋፊዎቹ ዘንድ ጥያቄ ፈጥሯል፡፡
ከዚህ ባሻገር የማሊያ አቅርቦቱ የደጋፊውን ፍላጎት ያገናዘበ እንዳልሆነ፣ የውጪ አገር ተጨዋቾች የዝውውር ሒደትና ተጨዋቾቹ የሚመጡበት መንገድ ግልጽ ሊሆን እንደሚገባ፣ የስፖንሰርሺፕ ገቢው አነስተኛ መሆን በጥያቄ ተነስተዋል፡፡ ካሉት ስፖንሰር አድራጊዎች በተጨማሪ ሌሎችንም ማሳተፍ ለምን እንዳልቻለ፣ ክለቡ የራሱ የቴሌቭዥን ሥርጭት ይኖረዋል ቢባልም፣ እስካሁን አለመጀመሩና በቅርቡ ይፋ የተደረገው የክለቡ አክሲዮን ሽያጭ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያወሱ ጥያቄቆችም ለቦርዱ ቀርበዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረመስቀልና የቦርዱ ጸሐፊ አቶ ነዋይ በየነ፣ በተለይ የደጋፊ ማኅበርን በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ነዋይ እንዳሉት ‹‹በማኅበር ላይ ማኅበር ማቋቋም አይቻልም ምክንያቱም ክለቡ አስቀድሞ ሲቋቋም ደጋፊዎች ያሉበት ማኅበር ሆኖ ነው የተቋቋመው፤ ማኅበሩ መቋቋም አለበት ከተባለ፣ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ክለቡን ማፍረስ ይጠይቃል፡፡ በአማራጭነት ግን ደጋፊዎች በየአካባቢያችሁ በፈለጋችሁት መንገድ ተደራጅታችሁ ክለቡን ለማገዝም ሆነ ማኅበራዊ ድጋፍ ማድረግ ይቻል ዘንድ ማኅበራትን መቋቋም ትችላላችሁ፤›› ብለዋል፡፡
የማሊያ አቅርቦት እጥረትን በተመለከተ የቀረበው የደጋፊዎች ቅሬታ ትክክል እንደሆነ ተናግረው ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ ወደፈት ግን ክለቡ የደጋፊውን ፍላጎትና ስሜት በሚያረካ መልኩ ማልያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡
የውጪ ተጨዋቾችን በሚመለከት መልስ የሰጡት አቶ አብነት፣ ‹‹ምልመላው የሚከናወነው በብቁ ሙያተኞች ሆኖ የመጡት ተጨዋቾች በአሠልጣኞች ሲታመንባቸው ካልሆነ በቀር የቅዱስ ጊዮርጊስን ማሊያ አይለብሱም፡፡ አሁንም በአሠልጣኙ ምርጫና ፍላጎት ተጨማሪ ተጨዋቾችን አስመጥተናል፡፡ ውጤታማነታቸውን ግን ወደፊት የምናየው ነው፤›› ካሉ በኋላ ስፖንሰር አድራጊዎችን በሚመለከት ሲናገሩም፣ ክለቡን ለሚደግፉ በሩ ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከስፖንሰሮች በየዓመቱ እስከ 35 ሚሊዮን ብር እየተሰበሰበ እንደሚገኝና ወደፊትም ከደርባ ሲሚንቶና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ስምምነት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን በሚመለከት አመራሩ ጉዳዩን እየተከታተለው እንደሚግኝም አስታውቀዋል፡፡ ጥናቱ እንደተጠናቀቀና ወደ ተከታዩ ምዕራፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የክለቡ ስታዲየም ግንባታም ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡ የግንባታው ደረጃ 20 በመቶ ላይ እንደሚገኝና በፋይናንስ እጥረት የተነሳ መቋረጡን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡
ክለቡ አክሲዮን በመሸጥ ስለሚያካሒደው እንስቃሴም የቀረበው ጥያቄም ይጠቀሳል፡፡ በባለሙያ ጥናት ተካሒዶ ውጤቱም ይፋ ተደርጎ እንደነበር የሚያስታውስ ሲሆን፣ በዚህ አደረጃጀት ‹‹የቅዱስ ጊዮርጊስ አክሲዮን ማኅበር›› የሚል ጊዜያዊ ስያሜ በመያዝ ወደፊት 244 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ክለቡ አስታውቋል፡፡ የአንድ አክሲዮን የመነሻ ዋጋው 1,000 ብር እንደሚሆንና ከመጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ወራት ሽያጩ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡