Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኢትዮጵያውያን አትሌቶች ክብረወሰን የሰበሩበትን ድል በበርሚንግሐም ተቀዳጁ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ክብረወሰን የሰበሩበትን ድል በበርሚንግሐም ተቀዳጁ

ቀን:

በመካከለኛ ርቀት የሩጫ ውድድር ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደናቂ ድል በተመዘገበበት ሳምንት፣ አንዱና የመጀመሪያው ድል፣ ከሁለት አሠርታት በላይ በሞሮኳዊው ሒሻም ኤል ጉሩዥ ተይዞ የቆየው የ1,500 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ክብረ ወሰን በ14 ማይክሮ ሰኮንድ በወጣቱ ሳሙኤል ተፈራ የተሻሻለበት ነው፡፡

በ3,000 ሜትር ሴቶች ምድብም ኢትዮጵያውያኑ ያለተቀናቃኝ በበላይነት በድል አጠናቀው ብቃታቸውን ያስመሰከሩባት የእንግሊዟ በርሚንግሐም ከተማ በኢትዮጵያ አትሌቶች ድል ተሟሙቃ ነበር፡፡ አምስተኛውን ደረጃ ለኔዘርላንዳዊቷ ሯጭ ከመልቀቃቸው በቀር፣ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ባለው ረድፍ በመደዳ የገቡት የኢትዮጵያ እንስት አትሌቶች ነበሩ፡፡

የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በአውሮፓ ታላላቅ ከተሞች በዙር ከሚያከናውናቸው የቤት ውስጥ ውድድሮች አንዱ የሆነው የ1,500 ሜትር የሩጫ ውድድር ሰፊ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ካተረፉት ውስጥ ይመደባል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 በሞሮኳዊው አትሌት ሒሻም ኤል ጉሩዥ አሸናፊነት የርቀቱ ክብረ ወሰን ተይዞ ላለፉት 22 ዓመታት ቢቆይም፣ በወጣቱ ሳሙኤል ተፈራ ተሰብሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የናይኪ አካዴሚ ሥልጠናውን እየተከታተለ ከሚገኘው ዮሚፍ ቀጀልቻ ጋር ተፎካክሮ ክብረ ወሰኑን በእጁ አስገብቷል፡፡ በኤል ጉሩዥ ተይዞ የኖረው ክብረ ወሰን 3፡ 31.08  ሲሆን፣  አትሌት ሳሙኤል ያስመዘገበው አዲሱ ክብረ ወሰን 3፡ 31.05 ሆኗል፡፡ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ በ3፡31.58 ሠዓት ሳሙኤልን በመከተል በሁለተኛነት አጠናቋል፡፡

‹‹ሚውለር ኢንዶር ግራንድ ፕሪክስ›› የሚል ሥያሜ በተሰጠውና በእንግሊዟ በርሚንግሐም ከተማ ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የቤት ውስጥ ውድድር ለአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ዮሚፍ ቀጀልቻ ነበር፡፡ ዮሚፍ ከበርሚንግሐሙ ውድድር በፊት ክብረ መወሰን ሊሰብር ጫፍ የደረሰበት ውድድር ለአናፊነት ዕጩ አድርጎት ነበር፡፡ በአሜሪካ ሜልሮስ በተካሄደው የቤት ውስጥ ውድድር ለክብረ ወሰን ተወዳድሮ ባይሳካለትም አሸናፊ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በበርሚንግሐም ከተማም ክብረወሰን ለመስበር እንደሚወዳደር ቀደም ብሎ አስታውቆም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በናይኪ አካዴሚ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ከሚከታተሉ አትሌቶች ውስጥ ዮሚፍ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ልማት ኤጀንሲ አትሌቲክስ ክለብ ውስጥ በኢትዮጵያውያን የሚሠለጥነው ሳሙኤል ተፈራ፣ ርቀቱ ሊጠናቀቅ 300 ሜትር እስኪቀረው ድረስ ከዮሚፍ ቀጀልቻ ጋር አንገት ለአንገት ተያይዞ በመዝለቅ፣ ሳይጠበቅ አፈትልኮ በመወጣት ለአሸናፊነት ስለመብቃቱ አይኤኤኤፍ በድረገጹ አስነብቧል፡፡

ከውድድሩ በኋላ አስተያየት የሰጠው ሳሙኤል፣ ‹‹እኔ አላምንም›› ማለቱ ታውቋል፡፡ ማሸነፉ ብቻም ሳይሆን፣ ለሁለት አሠርታት ሳይነካ የዘለቀውን የ1,500 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ክብረ ወሰን በእጁ ማስገባቱ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡ ለዚህ ደስታው ምክንያት የሆነውም፤ ‹‹ሁሉም እንደሚያውቀው የርቀቱ ክብረ ወሰን በሞሮኳዊው ሒሻም ኤል ጉሩዥ የተያዘው እኔ ከመወለዴ በፊት ነው፤›› በማለት የ19 ዓመቱ ወጣቱ ተስፈኛ አትሌት ተናግሯል፡፡ ሁለቱን ኢትዮጵያውያን ተከትሎ ሦስተኛ የወጣው ደግሞ አውስትራሊያዊ ስቴዋርት ማክሰዌን ሲሆን፣ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ 3፡35.10 ነበር፡፡ ከሁለቱ አትሌቶች የዘገየ ሰዓት ያስመዘገበው አትሌት፣ በሳሙኤልና በዮሚፍ መካከል የነበረውን እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅና ፈጣን ሩጫ መቋቋም እንደተሳነው ያመላክታል፡፡

በክብረ ወሰን ከታጀበው የወንዶቹ ድል ጎን ለጎን፣ በሴቶች መካከል የተደረገው የ3,000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ይጠቀሳል፡፡ እንደ አይኤኤኤፍ መረጃ፣ በኢትዮጵያውያን እንስቶች መካከል የነበረው የእርስ በርስ ፉክክር ልዩ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ርቀቱን 8፡54.60 በሆነ ሰዓት አጠናቃ አንደኛ የወጣችው አልማዝ ሳሙኤል ስትሆን፣ አክሱማዊት አምባየ በ8፡54.90 ሁለተኛ፣ መስከረም ማሞ 8፡55.94 ሰዓት ሦስተኛ ወጥታለች፡፡ እጅጋየሁ ታዬ፣ በ8፡55.28 ሰዓት በመግባት አራተኛ ስትወጣ፣ ሐዊ ፈይሳ፣ በ8፡57.10 ስድስተኛውን ደረጃ አግኝታለች፡፡ ማውሪን ኮስተር የተባለች የኔዘርላንድስ አትሌት በ8፡56.44 አምስተኛውን ደረጃ ወስዳለች፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...