Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዓለምየናይጄሪያ ምርጫ መራዘም

  የናይጄሪያ ምርጫ መራዘም

  ቀን:

  አብዛኛው ናይጄሪያውያን ባለፈው ቅዳሜ የሚካሄደውን የአገሪቱን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ ከምርጫው አምስት ሰዓት ያህል ቀድሞ የተነገረውን ‹‹የምርጫው ተላልፏል›› ዜና ‹‹የውሸት ዜና ነው›› በሚል ነበር ያለፉት፡፡ ሆኖም ይህ ዜና እውነት ነበር፡፡ ናይጄሪያውያን በጉጉት ሲጠብቁት ነበር የተባለው ምርጫ ለአንድ ሳምንት ያህል ተራዝሟል፡፡

  በመሐሙድ ያኩቡ የሚመራው የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን፣ ገጥሞኛል ባለው የቁሳቁስ አቅርቦት ችግር ምክንያት ምርጫውን ለሳምንት አራዝሜያለሁ ብሏል፡፡ ይህም ቀድሞውንም ምርጫው ተሰርዟል መባሉን ላላመነው መራጭ ተጨማሪ ብስጭትና ብሶትን ወልዷል፡፡ አንዳንዶችም ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡

  በምርጫው ለመሳተፍ 550 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ከናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ በሰሜናዊ ናይጄሪያ ወደምትገኘው ዳውራ ያቀናው ሙሳ አቡበከር፣ ‹‹ምርጫው ተሰርዟል መባሉን ማመን አልችልም›› ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡

  ብዙዎቹ ናይጄሪያውያንም ምርጫውን በትውልድ ቀያቸው ለማከናወን አቅንተው ነበር፡፡ ምርጫው በመራዘሙ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ለምርጫው የሄዱ ዜጎችም ምን መወሰን እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል፡፡

  የምርጫ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በሰጠው መግለጫ፣ ምንም ዓይነት የምርጫ መራዘም እንደማይኖር አሳውቆ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ አለመሆኑ በኮሚሽኑ ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬን አጭሯል፡፡

  ​​​​የናይጄሪያ ምርጫ መራዘም

   

  የምርጫው መራዘም የፈጠራቸው ሥጋቶች

  በምርጫው ለመሳተፍ ወደየአካባቢያቸው የተጓዙ መራጮች ለሳምንት ያህል ባሉበት ለመቀመጥ ወይም ትተው ወደቀደመ መኖሪያቸው ለመመለስ ለመወሰን መቸገራቸው ቢገለጽም፣ በመላ አገሪቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ገደብ መጣሉ በምርጫው ላለመሳተፍ ዕድል አይሰጥም ተብሏል፡፡

  በርካቶች በሁኔታው በመበሳጨታቸው የመራጮችን ቁጥር ሊቀንሰው ይችላል የሚል ግምት ከወዲሁ እየተሰነዘረ ነው፡፡ ቢቢሲ እንደሚለውም፣ የምርጫው መራዘም የመራጮች ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት ይሆናል፡፡ አንዳንዶችም ‹‹ናይጄሪያ በሙስና ውስጥ ናት፣ በቀጣዩ ሳምንት ለምርጫ አንወጣም›› ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹ምርጫው በሳምንት የተራዘመው የተሳካ እንዲሆን ለማስቻል ነው›› የሚል አመለካከት አንፀባርቀዋል፡፡

  ምርጫው በመራዘሙ ምክንያት ሕዝቡ በነቂስ ይወጣል? አይወጣም? ከሚለው በከፋ ግን በአማኞች መካከል የተፈጠረ ግጭት አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ከምርጫው አስቀድሞ በሃይማኖታዊ ግጭት ምክንያት 66 ሰዎች መሞታቸው ምርጫውን ያደናቀፋል የተባለ ቁልፍ ሥጋት ነው፡፡

  የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት በምርጫ አጭበርባሪዎች ላይ ዕርምጃ እንደወሰዱ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውም ሌላው ሥጋት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የምርጫው ሰዓት ሲቃረብ ‹‹ምርጫው ተራዝሟል›› መባሉን አስመልክቶ የሰጡት ትዕዛዝ ለቀጣዩ ሳምንት ለታቀደው ምርጫም ሌላ ችግር ይዞ እንዳይመጣ ተሰግቷል፡፡ ተንታኞችም የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ ‹‹የጫካ ፍትሕ›› ብለውታል፡፡

  የፕሬዚዳንት ቡሃሪ ተቀናቃኝ አቲኩ አቡበከር በበኩላቸው፣ ምርጫ ኮሚሽኑ አቅም እንደሌለውና ምርጫው ለምን እንደተራዘመ ምርመራ እንደሚያስፈልግ አሳውቀዋል፡፡

  የምርጫውን መራዘም አስመልክቶ አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጡት ፕሬዚዳንት ቡሃሪ፣ ‹‹ማንም ይሁን ማን የምርጫ ሳጥኑን የሚመዘብር ወይም ለመረበሽ የሚጥር ላይ የሚያዳግም ዕርምጃ እወስዳለሁ›› ብለዋል፡፡ በምርጫው ጣልቃ የሚገባም ‹‹በሕይወቱ ላይ የፈረደ ነው›› ሲሉ አክለዋል፡፡

  ‹‹ይህ የግድያ ፈቃድ›› ነው ሲል የፕሬዚዳንቱን ንግግር የኮነነው ዋና ተፎካካሪ ፓርቲው ፒፕልስ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ፒዲፒ) ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱን ዛቻም ‹‹ለጫካ ፍትሕ ቀጥተኛ ጥሪ›› ብሎታል፡፡

  ምርጫው በመራዘሙ ላይ የፕሬዚዳንቱ ቡሃሪ ተቀናቃኝም ሆኑ ፕሬዚዳንቱ ቅሬታ ቢያሰሙም፣ የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል የተባለው ምርጫም ተዓማኒነት አጥቷል፡፡ ምርጫው በተባለው ቀን ይካሄዳል ብሎ ለመናገር እንደማይቻል የምርጫ ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡

  ይህ ደግሞ በቦኮ ሃራም የተለያዩ ጥቃቶችን ለምታስተናግደው ናይጄሪያ ሌላ ሥጋት ነው፡፡ የምርጫው ውጣ ውረድ ናይጄሪያን የቀውስ አውድማ ሊያደርጋት ይችላል የሚል ሥጋትም አለ፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img