Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮንስትራክሽን መተግበሪያ ሶፍትዌር ወጣኞች

የኮንስትራክሽን መተግበሪያ ሶፍትዌር ወጣኞች

ቀን:

የአዲስ አበባ የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ላይ ያተኮረ አዲስ አሠራር ነበር ለመጀመርያ ጊዜ ይዘው ብቅ ያሉት፡፡ አሠራሩ የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች እንደ ሞባይል ካርድ ያለ ትኬት እየቆረጡ እንዲገለገሉ የሚያስችል ነው፡፡ አንዴ የገዙት ካርድ እንዳለው ቀሪ ሒሳብ በተለያዩ ጊዜያት አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡ ገንዘብ ሳይከፍሉ አታለው መውረድም ሆነ ወደ መጠበቂያ ተርሚናሉ መግባት የማይታሰብ ነው፡፡

ወደ ተርሚናሉ የሚያስገባውን የብረት ፍርግርግ ማለፍ የሚቻለውም የገዙትን ሕጋዊ የባቡር ካርድ መግቢያ ላይ በሚገኘው ሴንሰር ካሳዩ በኋላ ነው፡፡ ሴንሰሩ በትኬቱ ላይ በቂ ገንዘብ ያላቸውን መርጦ ሲያስገባ የሌላቸውን ደግሞ እንዳይገቡ መንገድ ይዘጋባቸዋል፡፡ አሠራሩ መንገደኞችን በትኬት ለሚያስተናግደው፣ ትኬት የቆረጡና ያልቆረጡ መንገደኞችን የሚለይ አሠራር በማይከተለው የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አዲስና ሥራንም ቀላል የሚያደረግ ነው፡፡ አቤል ገብረአናንያ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ለመመረቂያ በቡድን የሠሩት ፕሮጀክት ነው፡፡

በዚህ ፕሮጀክት ‹‹ኤ›› አግኝተው ሲመረቁ፣ አቤል 3.7 ውጤት አስመዝግቦ ነበር፡፡ በተመረቀበት የኮምፒዩተር ሳይንስ ሙያ መስክ ለመቀጠር የትምህርት ማስረጃውን ቀምሞ በየቢሮው መዞር አላስፈለገውም፡፡ እንዲያውም ተቀጥሮ የመሥራት ሐሳብ ፈፅሞ አልነበረውም፡፡ አቤል እንደ ተመረቀ ኢዩኤል ሙሉነህና አሞን ኢሳያስ ከተባሉ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ሀበን ሶፍትዌር ዲይዛን የተባለ ድርጅት አቋቋመ፡፡ ድርጅቱ በተመሠረተ በወራት ዕድሜ ውስጥም አንድ ነገር ሠሩ፡፡

የሠሩት በስልክ ላይ የሚጫን አፕሊኬሽን ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸውን ለአድማጮች የሚያቀርቡበት መድረክ ነው፡፡ እንደ ዩትዩብ ካሉ አፕሊኬሽኖች የሚለየውም የሚጫኑት ሙዚቃዎችን በቀላሉ አድማጮች በስልካቸው አውርደው ማድመጥ እንዲችሉ ማድረጉ ነው፡፡ በዚህ አፕሊኬሽን ላይ የሚጫኑት ሙዚቃዎች የቪዲዮ ክሊፕ ስለሌላቸው ለማውረድ ወደ ኤምፒ3 መቀየር ሳያስፈልግ ቀጥታ ማውረድ ይቻላል፡፡ ሥራው ለአድማጭ እንዲደርስለት የሚፈልግ ድምፃዊ ክፍያ ሳያስፈልገው ሥራዎቹን ለአድማጭ በነፃ ያቀርባል፡፡ የድምፃውያኑ የባለቤትነት መብት ሳይጋፉ ድምፃዊያንን ከአድማጭ የሚያገናኙበት አፕሊኬሽን በዚህ ወር መጨረሻ ለሕዝቡ እንደሚደርስ የሚናገረው አቤል እኛ ሌሎች የተሻሉ ሥራዎችንም ሠርተን ጨርሰናል ይላል፡፡

የአገርን ሀብት ከብክነት ሕዝቡን ከምሬት ይታደጋል የሚለው ሶፍትዌር በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚውል እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዘርፉ ያለውን የሀብትና የጊዜ መባከን ያስቀራል ያለውን ሶፍትዌር ለመገንባት ያነሳሳቸውን ጉዳይም እንደሚቀጥለው አብራርቷል፡፡ ‹‹ሁሉም ቦታ ኮንስትራክሽን አለ፡፡ ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች እዚህም እዚያ ይገነባሉ፡፡ በአጠቃላይ አገራችንን እየገነባን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የኮንስትራክሽን ሁኔታም በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡›› በአቤል አገላለጽ፣ ዘርፉ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖም ለማሳየት በሦስት ዓመታት ውስጥ የነበረውን የኮንስትራክሽን ሁኔታ በማስረጃነት ያነሳል፡፡ ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ለምሳሌ ይጠናቀቃሉ ከተባለበት ጊዜ በእጅጉ የዘገዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የህዳሴው ግድብ፣ እንዲሁም የተለያዩ የመስኖና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ መጓተት በአገር ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ፣ መንግሥትም በማኅበረሰቡ ዘንድ አመኔታ እንዲያጣ ማድረጉን ይጠቅሳል፡፡ እንዲህ ላሉ ብልሹ አሠራሮች መኖር ዋነኛው ምክንያትም የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚፈጸሙበት አሠራር አስፈላጊው ክትትል የጎደለው፣ ግልጽነት የማያውቁ በመሆናቸው ነው ይላል፡፡

የፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት ከሚፈጥረው የጊዜ ብክነት ባሻገር የሚያስከትላቸው እንደየወቅቱ የሚለዋወጠው የገበያ ሁኔታ የግንባታውን አጠቃላይ ወጪ በከፍተኛ መጠን ሊቀይረው ይችላል፡፡ መጠናቀቅ ካለበት ጊዜ ሲዘገይ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ሊንርና በተያዘው በጀት መጨረስ የማይታሰብ ይሆናል፡፡ ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት ዋጋ እንዲጨምሩ የተጠየቁ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎችን ሁኔታ ማንሳት በቂ ነው ይላል፡፡

ግንባታውን በተባለው የጥራት ደረጃ ገንብቶ ከማስረከብ ጋር የተያያዙ ችግሮችም እንዲሁ ግልጽ የሆነ አሠራርን ባለመከተል የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ከዚህ የባሰው ትልቁ ችግር ደግሞ አሉ የተባሉት የአሠራር ክፍተቶች ድምር ተፅዕኖ የሚታየው ጊዜ ካለፈ ከዓመታት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዴ የፈሰሰ ውኃ አይታፈስም በሚል የሚታለፉ ሲሆን፣ ኪሳራውን በኮንትራክተሩ ወይም በደንበኛው ላይ ይሆናል፡፡ ችግሮቹም በግልም ሆነ በመንግሥት የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ ናቸው፡፡ ችግሮቹን መቅረፍ ይቻላል የሚሉት አቤልና ጓደኞቹ የሠሩት ሶፍትዌር ኮን ዲጂታል ይባላል፡፡ ሶፍትዌሩ አንድ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው የሚኖረውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለባለድርሻዎች በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡

ፕሮጀክቱን የተመለከቱ ማንኛቸውም እንቅስቃሴዎች በቁጥር፣ በፎቶና በተለያዩ ዶክመንቶች አስደግፎ ለሚመለከተው አካል በሙሉ በግልጽ እንዲታይ ሆኖ የሚቀርብበት ነው፡፡ የተገዙ ዕቃዎች ደረጃ፣ ዋጋ፣ የምርት ስም ሳይቀር በደረሰኝ የሚቀርብበት፣ ግንባታው የሚገኝበት የግንባታ ደረጃንም እንዲሁ ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች ጭምር እንዲረዱት ሆኖ በፎቶ የሚጫንበትም ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በቁፋሮ፣ በኮንክሪት ሙሌትም ይሁን በሌላ የግንባታ ደረጀ ላይ የግንባታ ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉበት መንገድ በምሥል ይጫናል፡፡ አቤል እንደሚለው፣ አጠቃላይ መረጃው በየጊዜው የሚጫን በመሆኑ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጊዜ መለየት ያስችላል፡፡ ይህም በግንባታ መጓተት ምክንያት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን፣ እንዲሁም ሌሎች የአሠራር ችግሮችን በጊዜ ለመለየት ዕድል ይሰጣል፡፡ ስለዚህም ደንበኛውም ሆነ ኮንትራክተሩ ሊደርስበት ከሚችል ችግር ቀድሞ ራሱን ይከላከል፡፡ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ያለበትን ሁኔታና የሚጓዝበትን ፍጥነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ከሥር ከሥር ተከታትሎ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ነው፡፡

ሶፍትዌሩን ሠርቶ ለመጨረስ ወራት የፈጀ ሲሆን፣ በተለያዩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በነፃ ተግባራዊ እንዲሆን ፍላጎት አለን ይላሉ፡፡ በገንዘብ የሚያቀርቡት ለግል የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች እንደሆነም አቤል ይናገራል፡፡ ከሳምንታት በኋላም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ያስረዳል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...