Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአርሶ አደሩን የቀደመ ዕውቀትና ሳይንሱን አጣምረን ነው ወደ ሥራ የምንገባው›› አቶ ፋሲል መኳንንት፣ የፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር ማርኬቲንግ ባለሙያ

ስድስተኛው አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም ከየካቲት 1 እስከ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል ተካሂዷል፡፡ በሲምፖዚየሙ ከየክልሉ የተውጣጡ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የየክልል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲዎች ተካፍለዋል፡፡ በአገሪቱ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ዓይነተኛ ሚና አላቸው የሚባሉት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቶቻቸውን ይዘው በመግባትም በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ አቅርበዋል፡፡ በኤግዚቢሽኑ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከደቡብ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከድሬዳዋና ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቢሮዎች አገልግሎቶቻቸውን አስተዋውቀዋል፡፡ የኤክዚቢሽኑ ተካፋይ ከሆኑት ማኅበራት መካከል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ አዘዞ ቀበሌ 20 አካባቢ የሚገኘው የፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር አንዱ ነው፡፡ አቶ ፋሲል መኳንንት የማኅበሩ ማርኬቲንግ ባለሙያ ናቸው፡፡ ማኅበሩ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር በጎንደር አዘዞ ታዋቂ ነው፡፡ ይህን ያደረገው የትኛው አገልግሎታችሁ ነው?

አቶ ፋሲል፡- ፀሐይ ዩኒየን ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ በአገሪቱ አሉ ከሚባሉት ዩኒየኖችም አንዱ ያደረገው ሰሊጥ፣ አረንጓዴ ማሾና ሽምብራ ወደ ውጭ መላኩ ነው፡፡ ማኅበሩ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ባለፈም አባላቱ እንዲጠቀሙ ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በአገራችን ገበያን በማረጋጋትና የገበያ ንረትን ለማስተካከል ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በተለይ ጤፍ ላይ ከፍተኛ ሥራ እንሠራለን፡፡ ጤፍ ከመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሰብስበን በምንሠራው ሥራ ኅብረተሰቡንም አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከምን ያህል መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ነው የምትሠሩት?

አቶ ፋሲል፡- በ12 ወረዳ ውስጥ 135 መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አሉን፡፡ ከእነዚህ ምርት በመሰብሰብና በአንድ ማዕከል በማምጣት ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆነውን ለአገር ውስጥ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ለውጭ እየላክን አባላት የሚጠቀሙበትን አግባብ እየፈጠርን ነው፡፡ ለከተሜውም ከሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ጎንደር አካባቢ ካሉና በአማራ ክልል ከሚገኙ አቻ ማኅበራት ጋር ትስስር እየፈጠርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዋጋ ውድነት የኅብረተሰቡ ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርገናል ትላላችሁ?

አቶ ፋሲል፡- ፀሐይ ዩኒየን የተመሠረተው በ1992 ዓ.ም. በ2500 ብር ካፒታል በሁለት ወረዳዎች ነው፡፡ አሁን ላይ 12 ወረዳዎችን በማቀፍ ወደ 61 ሚሊዮን ብር ካፒታል አለው፡፡ ማኅበሩ ምርትን አምርቶ በመሸጥ ብቻ አልተወሰነም፡፡ በምርቶች ላይ እሴት በመጨመር፣ በተለይ የዘይት ምርት ላይ እንሠራለን፡፡ ዘይትን በተመለከተ የኑግ፣ የሱፍና የአኩሪ አተር ዘይት በቀን አሥር ሺሕ ሊትር ለማምረት የቅድመ ዝግጅት ሥራ ጨርሰናል፡፡ ምርትን አምርቶ መላክ፣ አገር ውስጥ ማከፋፈል ብቻ ሳይሆን የዘይትን እጥረት ለመሙላትም እየሠራን ነው፡፡ እንደሚታወቀው አርሶ አደራችንም የከተማው ኅብረተሰብም የኮሌስትሮል ችግር እየገጠመው መሆኑን እንሰማለን፡፡ ከጤንነት፣ ከጥራትና ከመጠን አንጻር የዘይት ፋብሪካው ችግር ይፈታል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ በተሻለ እንዲያመርት ምን ድጋፍ ታደርጋላችሁ?

አቶ ፋሲል፡- ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያመርት ግብዓት እናቀርባለን፣ የአቅም ማሳደጊያ ሥልጠና፣ የትራንስፖርት፣ የመጋዘን አገልግሎቶች እንሰጣለን፡፡ የሙያ ድጋፍና ባመረቱት ልክ የትርፍ ክፍፍል ለአርሶ አደሩ እናመቻቻለን፡፡ በዚህም አርሶ አደሩ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ጥራትን የምናረጋግጠው ታች ካለው መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡ በጥራት የተሻለውን ነው የምንገዛው፡፡ ወደ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራትም የጥራት መስፈርቶችን እናወርዳለን፡፡ ሻጋታ (አፍላቶክሲን) እና ሌሎች ችግሮችም እንዳይከሰቱ እናሰለጥናለን፡፡ አፍላቶክሲንን የምንከላከለው ኦርጋኒክ ሰሊጥ በማምረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአርሶ አደሩ ሕይወት መሻሻል ሲነሳ ብዙውን ጊዜ የሚነሳው ቤት ስለመሥራቱ፣ ልጆች ትምህርት ቤት ስለመላኩ በበቂ በልቶ ስለማደሩ ነው፡፡ ሆኖም ጉልበቱን ከጨረሰበት ከብት ጠምዶ ከማረስ አልወጣም፡፡ በከብት ከማረስ ባለፈም በዕድሜ የገፉ አርሶ አደሮች በከብት ሲያርሱ ይስተዋላል፡፡ ልጆቻቸው ወደ ከተማ እየፈለሱም ነው፡፡ የሻሻለ ግብርና እንዲኖር፣ ልጆችም በአካባቢያቸው ተምረው ለዕድገቱ አጋዥ እንዲሆኑ ምን ትሠራላችሁ?

አቶ ፋሲል፡- ፀሐይ ዩኒየን በዕቅድ የያዘው የእርሻ ሜካናይዜሽን ነው፡፡ አርሶ አደሩ በበሬ ሲያርስ በኖረበት ጊዜ ሰዓቱንም ጉልበቱንም ሲጨርስ ቆይቷል፡፡ በባህላዊ አስተራረስ መቀጠል ጥራቱን የጠበቀ ምርት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ በመሆኑም በትራክተር ማረስን ለናሙና በሦስት ወረዳዎች ማለትም በደምቢያ፣ በጎንደር ዙሪያና በአለፋ አስጀምረናል፡፡ ከወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ እንደ ማኅበር ብዙ ባንሠራም ጅምር አካሄዶች አሉ፡፡ በአካባቢው የሚገኙ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በቅጥር ሠራተኛ እንዲመሩ እያደረግን ነው፡፡ አርሶ አደሩ የራሱ አመራር፣ የራሱ ንብረት፣ የራሱ ገንዘብ ያዥ ስለነበረው 10ኛ ወይም 12ኛ ክፍልን በጨረሱ የአርሶ አደሩ ልጆች እንዲሠራ እየጣርን ነው፡፡ በአካባቢው ላይ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ እንረዳለን፡፡ መሠረታዊ ማኅበራት ቅጥር ሠራተኞችን እንዲጠቀሙ በማድረግ ሥራ አጥነትን ለማስቀረት እየሠራን ነው፡፡ ከ135ቱ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አብዛኞቹ በቅጥር ሠራተኛ እየተመሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሮች ባመረቱትና በለፉት ልክ ተጠቃሚ አለመሆናቸው፣ ከምርቶቻቸው ተጠቃሚ የሚሆኑት በንግድ ሰንሰለቱ የገቡ መሆናቸው ይነገራል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት መምጣት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ፀሐይ ዩኒየን በአካባቢው ያሉትን አርሶ አደሮች ምን ያህል ተጠቃሚ አድርጓል? ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃርስ?

አቶ ፋሲል፡- ሰፊ ሥራ የምንሠራው አርሶ አደሩ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርት ነው፡፡ በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፉ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ከመደገፍ በተጨማ ብዙም አልሠራንም፡፡ ሥራዎቹ እንዲሠሩ ግን ግፊት እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ወደውጭ ከምንልክላቸው ተቋማት ጋር የመጠጥ ውኃ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች እንዲረዱና እንዲያግዙ እየሠራን ነው፡፡ ምሥራቅ በለሳ በሚባል ቦታ ላይ ያለውን የውኃ ችግር ለመቅረፍ የገበያችን መዳረሻ ከሆኑ የውጭ ገዢዎች ጋር ሰፊ ሥራ ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአካባቢው ላይ በብዛት የሚመረተው ምንድነው?

አቶ ፋሲል፡- በማኅበራችን ዋና ሰብል የምንለው ጤፍ ነው፡፡ ከቅባት እህል ሰሊጥ፣ ከጥራጥሬ ሽምብራ ከቅመማ ቅመም ደግሞ ነጭ አዝሙድና ጥቁር አዝሙድ ናቸው፡፡ ማሾና ሰሊጥ ለውጭ ገበያ እንልካለን፡፡ ውጭ በመላካችን አርሶ አደሩም ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. ሁለት ሚሊዮን ብር ያህል የውጭ ምንዛሪ አስገኝተናል፡፡፡

ሪፖርተር፡- ከአቻ ማኅበራት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? የልምድ ልውውጥስ ታደርጋላችሁ?

አቶ ፋሲል፡- የዘይት ፋብሪካውን ከመትከላችን በፊት ከደቡብ ክልል ተሞክሮ ወስደናል፡፡ ፀሐይ ዩኒየንም በክልሉ ካሉ ማኅበራት ጋር በሒሳብ አያያዝ፣ በግብይት እንቅስቃሴው፣ በማበጠሪያ ማሽንና በሌሎችም የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ካነሷቸው ምርቶች በተጨማሪ በቆሎና ሩዝ ላይ አትሠሩም? አትክልትና ፍራፍሬስ?

አቶ ፋሲል፡- በቆሎ ገዝተን መኖ በማቀነባበር ለአርሶ አደሩና ለከተማው ኅብረተሰብ እናቀርባለን፡፡ ማቀነባበሪያ ፋብሪካም አለን፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ግን አንሠራም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምርት መትረፍረፍና ብክነት አንዱ መንስዔው ማቀነባበር አለመቻሉም ነው፡፡ ማቀነባበር ላይ የምትሠሩት ሥራ አለ?

አቶ ፋሲል፡- ጤፍን አበጥረን እንሸጣለን፡፡ በቆሎ አቀነባብረን ነው የምናቀርበው፡፡ ክምችት ላይ ችግር የለብንም፡፡ ገበያ ተኮር ሆነን ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም ላይ ያለው ተሞክሮ ምን ይመስላል፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩት ላይ ብዙውን ጊዜ የተፈጥሮ (ኦርጋኒክ) የሚባል ቅድመ ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ እዚህ ላይ አስተያየት ቢሰጡን?

አቶ ፋሲል፡- በአብዛኛው ወደ ውጭ የምንልከው መደበኛውን ሰሊጥ ነው፡፡ ያልተነካካ፣ ከኬሚካልና ከዘመናዊ ማዳበሪያ የፀዳ ነው፡፡ በመሆኑም ሰሊጡ በውጭው ዓለም ተፈላጊ ነው፡፡ ኦርጋኒክ በብዛት የተለመደው በቡና ላይ ቢሆንም ጎንደር ዞን በኦርጋኒክ ሰሊጥ እየታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም በአውሮፓ ተፈላጊ ነው፡፡ ዘንድሮ በያዝነው ወር 1900 ኩንታል ሰሊጥ ሸጠናል፡፡ በተሻሻሉ ሰብሎች ዙሪያ ሽምብራ ላይ እንሠራለን፡፡ ሀርሙ የሚባለውን ሽምብራ እያለማመድን ሲሆን አርሶ አደሩም ጥሩ ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን የዘር እጥረት አለ፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን የመቀበል አዝማሚያው ምን ይመስላል?

አቶ ፋሲል፡- ጎንደር ዙሪያ ላይ በአብዛኛው ቁንጮ ጤፍን ተቀብሏል፡፡ ደምቢያና ጎንደር ዙሪያ ቴክኖሎጂውንም ተቀብሎ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ የራሱ የቀደመ ዕውቀት አለው፡፡ ዕውቀቱን ጠብቆ ለማቆየት ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ፋሲል፡- አርሶ አደሩ ጋር ያለው ዕውቀት አይናቅም፡፡ ከልምድ የመጣም ነው፡፡ የአስተራረስ፣ የአስተራረም፣ የአዘራር፣ የአስተጫጨድ፣ ተባይ ለመከላከልና መሬቱ አልሰጥ ሲል የሚጠቀሙትን ዘዴ እናያለን፡፡ ይህንን ዕውቀት ከሳይንሱ አጣምረንና መርጠን ነው ወደሥራ የምንገባው፡፡ አርሶ አደሩን በሙያ የምንደግፈውም ያለውን የቀደመ ዕውቀት መሠረት አድርገን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደማኅበር ችግር ብላችሁ የምታነሱት ምንድነው?

አቶ ፋሲል፡- የገንዘብ እጥረት አለብን፡፡ ለግብይት ሰፊ ዕቅድ ቢኖረንም ዕቅዱን ለማሳካት ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም የገንዘብ እጥረት አለብን፡፡ ከዓባይ ባንክ፣ ንግድ ባንክና ሌሎችም ጋር ግንኙነት በመፍጠር ብድር ብናመቻችም በቂ አይደለም፡፡ ከአርሶ አደሩ ምርት ለመሰብሰብ የገንዘብ እጥረት ስላለብን ለኅብረት ሥራ ማኅበራት የተሰጠውን ትኩረት ያህል የገንዘብ እጥረት ችግርን ለመፍታት መንግሥት ቢያግዝ እንላለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...