ለዓመታት በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዳይሳተፉ በሕግ ተከልክለው የቆዩት ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በዘርፉ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ዛሬ የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዳይሳተፉ የሚያግደውን ሕግ በማሻሻል ተሳታፊ የሚሆኑበት መንገድ መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የፋይናንስ ዘርፉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላላቸው ብቻ የተፈቀደ ሲሆን፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው ዳያስፖራዎች በዘርፉ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ተገድበው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ዳያስፖራው ተሳታፊ ይሆንበታል የተባለው አዲሱ ረቂቅ ዝርዝር ጉዳዩ ባይገለጽም፣ ማሻሻያው ዳያስፖራው በዘርፉ እንዲሰማራ ይፈቅዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹በእኛ በኩል በተለይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፋይናንስ ዘርፉ መሳተፍ የሚቻልበትን ዕድል እንዲኖር ጥናቶችን አጥንተናል፤›› ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ተደርጎ ከፀደቀ አንድ ትልቅ የለውጥ አካል ይሆናል የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡