የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለይ ለግብርና የሰጠው ብድር ሊመለስ የማይችልበት ደረጃ ስለመድረሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ፡፡
ገዥው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ዛሬ የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ባንኩ ለግብርና ከሰጠው ብድር ውስጥ 6.3 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ሊመለስ የማይችል ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ ይህም የሆነው በተደራጀና በተቀነባበረ መንገድ ብድሩ በመሰጠቱ ነው ብለዋል፡፡
ይህም የባንኩን የተበላሸ የብድር መጠን ከፍ ያደርገዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፈው ዓመት የተበላሸ የብድር መጠኑ 40 በመቶ መድረሱ ይታወሳል፡፡ ‹‹የልማት ባንክ ከፍተኛ ችግር አለበት፡፡ ያልተመለሰ ብድር ምጣኔው በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡ በተለይ ደግሞ ለእርሻ ያበደረው ብድር መመለስ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ወደ 6.3 ቢሊዮን ብር ለእርሻ ሥራ በሚል ለባለሀብቶች የተሰጠ ብድር አለ፤›› ያሉት ገዥው፣ ይኼ ብድር የሚመለስበት ሁኔታ በጣም ጠባብ ሆኗል፤›› በማለት አክለዋል፡፡ በተቻለ መጠን እነዚህ የተበደሩ ሰዎች ወደ ሕግ የሚቀርቡበት ሁኔታ ግን እንዲጀመር ብሔራዊ ባንክ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡
ከዚህ ሌላ ልማት ባንክ በአጠቃላይ ውጤታማነቱ ምን ያህል ነው የሚል ጥናት እየተጠና ነው፡፡ በዚህ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ልማት ባንክ ትልቅ የሚባል የሪፎርም ሥራ ካልሠራ ካለበት ችግር ሊወጣ እንደማይችል ተጠቁሟል፡፡ ስለዚህ ልማት ባንክ የሪፎርም ሥራ እንዲሠራ ቢታቀድም፣ እስካሁን ባለው አሠራር ግን ያላግባብ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለግለሰቦች መጠቀሚያ እንዲሆን ማድረጉ ተገልጿል፡፡
‹‹የብድር አወሳሰኑ ሕጋዊ ነው፣ ነገር ግን በጣም በተደራጀና ሕገወጥ በሆነ ኔትዎርክ ገንዘቡ እንዴት እንደማይመለስ ተቀነባብሮ የተወሰደ ብድር ነው፤›› በማለት ገዥው ተናግረዋል፡፡