Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቤተሰብ ዕቅድ የተጠቃሚዎችን መብት እንዳይጥስ ማሳሰቢያ ተሰጠ

የቤተሰብ ዕቅድ የተጠቃሚዎችን መብት እንዳይጥስ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

የቤተሰብ ዕቅድ ለሥነ ሕዝብ ልማት ዕቅዶች ስኬት ወሳኝ ቢሆንም የተጠቃሚዎችን መብት ሳይጥስ መተግበር እንዳለበት ተገለጸ፡፡

የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የውይይት መድረክ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የሥነ ተዋልዶና ጤና ረዳት ፕሮፌሰርና ከፍተኛ ባለሙያ እውነት ገብረሃና (ዶ/ር)፣ ‹‹የቤተሰብ ዕቅድና የሥነ ተዋልዶ ጤና በሥነ ሕዝብና ልማት ማዕቀፍ ሥር›› በሚለው ጽሑፋቸው እንደገለጹት፣ የቤተሰብ ዕቅድ ከሥነ ሕዝብና ልማት ጋር ተያይዞ ሲታሰብ/ሲታቀድ ጥራቱን የጠበቀ፣ ተጠያቂነት ያለው፣ ፍትሐዊ፣ የተጠቃሚ ግለሰቦችን መብት የማይጥስና በሙሉ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡

የቤተሰብ ዕቅድ ተቀዳሚ ዓላማው የኅብረተሰቡን በተለይም የእናቶችን ጤና፣ ሰብዓዊና ሥነ ተዋልዶ መብቶቻቸውን ማስከበር ነው፡፡ ለዚህም አገሪቱ በጤናው ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥታ ከምትሠራባቸው ዘርፎች አንዱ ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴርም ብሔራዊ የቤተሰብ ዕቅድ መመርያ አውጥቶ እየተጠቀመበት ይገኛል ብለዋል፡፡

የቤተሰብ ዕቅድን አስመልክቶ የወጣውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ኢትዮጵያ ተስማምታ እንደተቀበለችው፣ በድንጋጌውም መሠረት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የሚሰጠው በተጠቃሚው ሙሉ ፈቃድና ስምምነት መሆን እንዳለበት፣ ይህንንም ሁኔታ ለመተግበር የሚያስችል መመርያ እንዳወጣች፣ በባለሙያዎች ሥልጠና ላይም እንዳካተተችውና ከፖሊሲ ባሻገር በየደረጃው ለመተግበር እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች በፈቃደኝተን ላይ የተመሠረተ የቤተሰብ ዕቅድ እንዲተገበር አቋም መያዝና ለአተገባበሩም ድጋፍ ለመስጠት በሚያስችላቸው ዝግጁነት ላይ መሆናቸውን ዶ/ር እውነት ገልጸዋል፡፡

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም ባለሙያ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት አሰጣጥ መርሆዎችንና አተገባበራቸውን ጥንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሥነ ምግባር የታነፃና የተገልጋዮችን ፍላጎት ለመረዳትና ለማስተናገድ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡ የፈቃደኝነት መርሆዎችን እንዳይጥስ የተጠያቂነትን መስመሮች መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ዶ/ር እውነት፣ በቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ ከአገልግሎት ሰጪው አካል በተጨማሪ የግለሰብ መብቶችን የሚጥሱ (የቤተሰብ ዕቅድ እንዲጠቀሙ በተለያየ መልክ የሚያስገድዱ ወይም እንዳይጠቀሙ የሚከለክሉ) አካላት የሚለዩበትንና አስፈላጊ ከሆነ በሕግ አግባብ የሚስተናገዱበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ያሉትና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የምርምር አካል በሆነው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ምርመር ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ሰኢድ ኑሩ (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ልማት ቁርኝት›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ አገሮች ከከፍተኛ ወሊድና ከፍተኛ የሞት ምጣኔ ወደ ዝቅተኛ የወሊድና የሞት ምጣኔ ሽግግር ሲያደርጉ እናቶች በዕድሜያቸው የሚወልዷቸው ልጆች መጠን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ የሥነ ሕዝብ ስብጥሩ ወጣቶች ወደ በዙበት አወቃቀር እንደሚቀየር፣ ይህ ክስተት እንደ አገሪቱ ዝግጅት ዕድል ወይም ፈተና ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ይህም በአንድ ወቅት ብቻ የሚከሰት፣ ከአዘቦት የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ከሚገኝ የበለጠ የወጣትን የሥራ ዕድል መሠረት ያደረገ የኢኮኖሚ ጥቅም፣ የሥነ ሕዝብ ለውጥ ትሩፋት እንደሚባል ገልጸዋል፡፡

‹‹በትምህርት፣ በክህሎት፣ በጤና፣ በሥራ ተነሳሽነት፣ በሥነ ምግባር፣ በአገራዊ ስምምነትና በዛላቂ የሥራ መስኮች የተቃኘ ዝግጁነት ትሩፋቱ ዕውን እንዲሆን ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አገሮች ነባራዊ ሁኔታ የሕዝብ ብዛት ሀብት ወይም ሸክም ሊሆን እንደሚችል፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ዝቅተኛ የመሬት ይዘትና ከፍተኛ የገጠር ድብቅ ሥራ አጥነት፣ ከፍተኛ የከተማ [የወጣት] ሥራ አጥነት፣ የሕዝብ ብዛት ወደ ሸክምነት እንዳጋደለ (ዶ/ር) ሰኢድ ኑር ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕዝብ ጥናት ማዕከል የሥነ ሕዝብና ልማት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተረፈ ደገፋ (ዶ/ር) ‹‹ሥነ ሕዝብን ከግንዛቤ ያስገቡ የልማት ፖሊሲዎች፤›› በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በጽሑፉም፣ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ፣ ከዓለም 12ኛ ናት፡፡ የወጣቱ ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አገሪቱ የወጣት ወይም ወጣት በብዛት የሚገኝበት አገር ተብላ ትጠራለች፡፡

ነገር ግን የወሊድ ምጣኔውና ዕድሜያቸው ከዜሮ እስከ 14 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በአንፃሩ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 64 ዓመት የሆኑና መሥራት የሚችሉ ሰዎችና የአረጋውያን ቁጥር ከፍ እያለ እንደመጣ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ በሥነ ሕዝብ ላይ ያመዘነ በርካታ የልማት ተግዳሮቶች እንደተጋረጡባት፣ ከተግዳሮቱቹም መካከል ድህነት፣ ጠኔ፣ ረሃብ፣ የአካባቢ መጎሳቆል፣ የደን መመናመን፣ የአፈር መከላት፣ የብዝኃነት መሳሳት ወይም መቀነስ እንደሚገኝበትም፣ እነዚህም ተግዳሮቶች ከሕዝብ ቁጥር ወይም ብዛት፣ ከምርት ሥርዓቱና ከአኗኗሩ ስትራቴጂዎች ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የሥነ ሕዝብና ልማት ትስስርና የፖሊሲ አንድምታው በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ባካሄደው የውይይት መድረክ በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻነት ውይይትና ጥያቄና መልስ የተካሄደ ሲሆን፣ ‹‹ዘ ዲሞግራፊክ ዴቪደንድ›› በሚል ርዕስ በአካዴሚው የታትመው ‹‹ፖሊሲ ሜከርስ ቡክሌት›› እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቤተሰብ ዕቅድ እየተሻሻለ የመጣው ከ25 ዓመታት በፊት ነው፡፡

በዚህም መሠረት በ1982 ዓ.ም. ከ2.3 በታች ወይም 63 በመቶ የሚሆኑና በወሊድ ዕድሜ የሚገኙ ሴቶች ብቻ ዘመናዊ የቤተሰብ ዕቅድ መኖሩን ያውቁ እንደነበር፣ ይህም መጠን በ1992 ዓ.ም. በ82 በመቶ፣ በ1997 ዓ.ም. 86 በመቶ፣ በ2003 ዓ.ም. 97.2 በመቶ ማደጉን፣ በአጠቃላይ በ1982 ዓ.ም. እና በ2003 ዓ.ም. መካከል የቤተሰብ ዕቅድ ግንዛቤ በ54.3 በመቶ ጨምሯል፡፡  

ዘመናዊ የቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮ እያደገ እንደመጣ፣ በተጠቀሰውም ዓመት ብቻ 3.5 በመቶ የሚሆኑና በመውለድ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሁሉም ሴቶች የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንደሆኑ ጽሑፉ ያስረዳል፡፡ የተጠቃሚዎች ቁጥር በ1992 ዓ.ም. በስድስት በመቶ፣ በ1997 ዓ.ም. በአሥር በመቶ፣ በ2003 ዓ.ም. 19 በመቶ፣ በ2008 ዓ.ም. 35 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

ይህም ሆኖ ግን በወሊድ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ሴቶች አሁንም የዘመናዊ ቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ፣ ከአምስት ሴቶች መካከል አንዷ ተጨማሪ ልጅ እንዲኖራት ባትፈልግም ወይም አራርቆ መውለድ ብትፈልግም የቤተሰብ ዕቅድ ግን ተጠቃሚ እንዳልሆነች ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ መንግሥታዊ ያልሆነና ለትርፍ ያልቋቋመ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 783/2005 ከተመሠረተበት መጋቢት 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ሳይንስ፣ ፈጠራ፣ ሥነ ጥበብና ምርምር እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሙያዊና ሳይንሳዊ ምክረ ሐሳቦችን ለፖሊሲ አውጪዎች በማቅረብም ለኢትዮጵያ አንድነት የበኩሉን እያበረከተ ይገኛል፡፡

አካዴሚው ከተቋቋመበት ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በጤና፣ በግብርና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በምሕንድስናና ቴክኖሎጂ፣ በማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ እንዲሁም በሥነ ጥበባት ዘርፎች 33 መድረኮችን አካሂዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...