Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመምህራኑ 70ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ

የመምህራኑ 70ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ

ቀን:

በዓለም ላይ ጥንታዊ ከሆኑ ነገሮች የምትመደበው ኢትዮጵያ የጥንታዊነቷን ያህል ዘመናዊ ትምህርትን በመቀበል ከቀዳሚዎቹ አይደለችም፡፡ የብዙ አገሮች የዘመናዊ ትምህርት ታሪክ ከ200 ዓመታት በላይ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያው የ100 ዓመት ዕድሜ ያህል ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) እንደሚሉትም፣ ትምህርት በዘመናዊ መልኩ የተደራጀው ደግሞ ከ1933 ዓ.ም. የጣሊያን ጦርነት ማክተም በኋላ ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው እየተሻሻለና እያደገ ቢመጣም፣ ከበፊትም ጀምሮ ዘርፉ ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር፡፡

በተለይ ተማሪ ባለበት ቤት ውስጥ ሁሉ የሚነበቡት መምህራን፤ በመማር ማስተማሩ ውጣ ውረድ ያለፉ፣ ክፉና ደጉን የቀመሱ፣ በየዘመኑ በነበሩ ፖለቲካዊ ኩነቶች የሚታወሱ፣ ለትምህር ጥራት መሻሻልም ሆነ መውደቅ የሚነሱ ናቸው፡፡ በአገሪቱ የትምህርት ሽፋን ማደጉ ሲነሳም መምህሩ ግንባር ቀደም ተጠሪ ነው፡፡

የትምህርት ጥራት ዛሬም ድረስ ችግር ያለበት በመሆኑ አዲስ የትምህርትና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ያሉ አካላት እየተወያዩበት ቢሆንም፣ መምህሩ ባለው አቅምና አገሪቷ በሰጠችው የተጓደለ የመማር ማስተማር ግብዓትም ቢሆን በሸለቆው፣ በበረሃው፣ በጋራው፣ በደጋው፣ በቆላማ አካባቢው የአየር ንብረቱ ቀዘቀዘ ሞቀ ሳይል ትምህርት በገባበት ሁሉ ትምህርት እንዲስፋፋ የተወጣውና የሚወጣው ኃላፊነትም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ቢሆን፣ መምህራን ከንጉሡ አንስቶ አሁን እስካለንበት የኢሕአዴግ ሥርዓት የፈጠሩት ተፅዕኖ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ በመታገላቸው፣ በመጠየቃቸው፣ ትክክል አይደለም በማለታቸው መምህራን ተገርፈዋል፣ ተሰደዋል፣ ተገለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ጥላዬ፣ በአገሪቱ ሴክተር ሪቪው ሲጠና የዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አልተሻሻለም ብለው ለውጥ እንዲመጣና ድህነት እንዲወገድ መምህራን ያልሠሩበት፣ ያልወጡበት፣ ያልወረዱበትና ያልታገሉበት የፖለቲካ ቅንጣት አልነበረም፡፡ አገሪቷ አሁን ለደረሰችበት ለውጥም ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረጉት መምህራን ናቸው፡፡

እነዚህ መምህራን ግን በአገሪቷ ዘመናዊ ትምህርት ተጀምሯል ከሚባልበት ጊዜ አንስቶ እንኳን ቢታይ በመልካም መደላድል ላይ አልነበሩም፡፡ በወቅቱ ይህንን የተረዱ መምህራን፣ ለመምህራኑ ብሎም በአገሪቱ ላለው የመማር ማስተማር ሒደት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ኅብረት የፈጠሩት ከ70 ዓመታት በፊት የካቲት 14 ቀን 1941 ዓ.ም. ነበር፡፡

መምህራንን ሊያሰባስብ የሚችል ኅብረት ሲመሠረት ስለነበረው አነሳስ የሚገልጽ የተደራጀ መረጃ ባይገኝም፣ በቀድሞው ስሙ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የ1ኛ ደረጃ መምህራን ያሉበትና 32 መምህራንን ያቀፈ ‹‹የመምህራን ኅብረት›› እንደተመሠረተ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ በንቲ ተናግረዋል፡፡

በ32 መምህራን የተመሠረተው ‹‹የመምህራን ኅብረት›› ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የተባለ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ አባላቱ 508 ሺሕ ደርሰዋል፡፡ በአገሪቱ በአጠቃላይ ያሉት መምህራን 700 ሺሕ የህል መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ጥላዬ፣ ማኅበሩ ቀሪዎቹ መምህራን ለምን እንዳልተካተቱ እንዲታይ ለማኅበሩ የቤት ሥራ ሰጥተዋል፡፡

የአባላት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉትን የሙያ ማኅበር ይዞ በኢትዮጵያ በነበሩት የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ማለፍ ግን ቀላል አልነበረም፡፡

የመምህራንን መብት ለማስከበርና በአገሪቱ ጥራት ያለው ትምህርት ለማስፈን የተመሠረተው ማኅበሩ፣ በሚያነሳቸው አጀንዳዎች በጉልህ መጋጨት የጀመረው በንጉሡ ዘመን ነው፡፡

በንጉሡ ጊዜ የትምህርት ዘርፉ ፍተሻ (Education Sector Review) አሳታፊ ካለመሆኑም በላይ በርካታ መምህራንን ለመቅጠር ከሚል እሳቤ፣ የመምህራን የትምህርት ደረጃና የደመወዝ ክፍያ ዝቅተኛ መደረጉን ማኅበሩ ተቃውሞ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት ‹‹እኔ የመምህራኖቼ ውጤት ነኝ›› በሚል መሪ ቃል የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲያከብር ያገኘናቸው አንዳንድ መምህራን እንደነገሩን፣ ይህ ወቅት ለትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት ከሆኑ ቀዳሚ ምክንያቶች ይጠቀሳል፡፡ ምናልባትም ከዚህ ጊዜ አንስቶ የተደራረቡ የመማር ማስተማሩ ችግሮች፣ በቅርቡ ፍኖተ ካርታው ሲተገበር ይፈታቸዋል ቢባልም፤ እስካሁንም ድረስ ዘርፉን እየፈተኑት ነው፡፡

ይህ ከመሠረቱ እንዲስተካከል መምህራን ማኅበር በንጉሡ ጊዜ ማሳወቁ፣ በኋላም መቃወሙና ለንጉሡ ሥርዓት መውደቅም ቀዳሚ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ በደርግ ጊዜ በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ የማኅበሩ ተሳትፎ የጎላ የነበረ ቢሆንም፣ ሥርዓቱ የማያወላዳ ስለነበር እንደዘመኑ ሆኖ ማሳለፉ ይነገራል፡፡ በኢሕአዴግ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ፖለቲካውና ቢሮክራሲው ባያሠራም፣ የመምህራንና የትምህርት ጉዳዮችን ያካተቱ ጥያቄዎች በማንሳትና መልካም ምላሽ በማግኘት ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመምህራን የደመወዝ ደረጃ ዕድገትና የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይገኙባቸዋል፡፡

በ1998 ዓ.ም. በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጥራት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች፣ በተማሪ ዲሲፕሊን፣ በፈተና ኩረጃ፣ በአጠቃላይ ትምህርት፣ በመምህራን ደመወዝ ጥናት፣ የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ስታፍ የደመወዝ ስኬል ጥናት፣ መሠረቱን ትምህርት ቤት ባደረገ የፆታ ትንኮሳ በ1ኛ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል የሴት ተማሪዎች የሳይንስ ትምህርት አቀባበል ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ጉዳዮች፣ በ2010 ዓ.ም. የ1ኛ ደረጃ 1ኛ ሳይክል የመምህራን ምልመላ ቅጥርና የመማር ሁኔታ፣ ዘንድሮ ደግሞ ጥናቱ የተጠናቀቀውና ለሚመለከታቸው የተላከውን ስለ መምህራን አገልግሎት ኮሚሽንና ከዚሁ ጋር በማያያዝ የመምህራን ማኅበር የመደራደር አቅም ጉዳይ በተለይም ወደ ተሟላ ሠራተኛ ማኅበር መለወጥን የተመለከቱ በርካታ ጥናቶች ማኅበሩ ካከናወናቸው ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ማኅበሩ በራሱ በኩል ከአሥር ዓመት በፊት ጀምሮ ጥናት ሲያስጠና ለመምህራን መብት ሲታገል ቢቆይም፣ በተለይ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ላይ ጆሮ የሰጠው አልነበረም፡፡

የመምህርነት ሥልጠና ለመውሰድ ኮሌጅ የሚገቡ ተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆን፣ 12ኛ ሳይጨርሱና በዕድሜ ሳይጎለብቱ ወደ ሥልጠና መግባታቸውና ከዚህ ባለፈም ወደ መምህራን ኮሌጅ የሚገቡ ተማሪዎች እንደየኮሌጆቹ ቢለያይም እስከ 400 ብር በወር እየተሰጣቸው ከጊቢ ውጪ እንዲያድሩ መደረጉ፣ መምህራን ግብዓት ባልተሟላበት እያስተማሩ መሆኑንና ተያያዥ ችግሮችን በመቃወምም ችግሩ እንዲቀረፍ ጥሯል፡፡ እነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች የትምህርቱን ጥራት ያስጠብቃል፣ የአገሪቱንም ለውጥ ያፋጥናል በተባለው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ መልስ ያገኛሉ ቢባልም፣ የቀደሙት መምህራን ግን በፖለቲካ ተፅዕኖ ውስጥ በወደቀውና ለመምህራን አመቺ ድባብ ባልነበረበት ማለፍ ግዴታቸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም እንዳሉት፣ መምህርነት የሚወደድ ሙያ ቢሆንም፣ መምህርነት አንገፍግፏቸውና አንድ ዓመት እንኳን ማስተማር ተስኗቸው ሙያ የሚቀይሩ ቀላል አይደሉም፡፡

ትምህርት ቤቶች በዓመት ውስጥ አሥር የሚደርሱ መምህራንን ያጡበት ወቅትም ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ውጣ ውረድ ችለው ደግሞ መምህርነትን የሙጥኝ ያሉ አሉ፡፡ 20 ዓመት፣ 25 ዓመት፣ 30 ዓመትና ብሎም 40 ዓመት ድረስ በመምህርነት ሙያ ያገለገሉ የማኅበሩ አባላትም አሉ፡፡ ‹‹የመምህራን ኅብረት›› ከተመሠረተ ከ23 ዓመት በኋላ በ1964 ዓ.ም. የመምህርነትን ሙያ የተቀላቀሉት አንጋፋው መምህር አቶ ገብረፃዲቅ ወልደመድህን፣ ‹‹መምህርነትን እወደዋለሁ›› ይላሉ፡፡

መምህርነት ቆንጆ ሙያ ቢሆንም፣ ከበፊትም ጀምሮ መምህራን ይጨቆኑ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ከ10ኛ ክፍል አቋርጠው መምህር እንደሆኑና በኋላ በተለያዩ ሥልጠናዎች ራሳቸውን ማብቃታቸውን የሚናገሩት አቶ ገብረፃዲቅ፣ መምህርነት ከበፊትም ጀምሮ የቀዘቀዘና ብዙም ክብር የማይሰጠው ነበር ይላሉ፡፡ ባል ማግባት እንደ መስፈርት በሚቆጠርበት በዛ ዘመንም ‹‹ብታጪ ብታጪ አስተማሪ አታጪ›› ይባል ነበር ይላሉ፡፡

ከትምህርት የወደቀ ሁሉ ወደ መምህርነት ይገባ እንደበር፣ መምህሩ ብቁ ሳይሆን ቢያስተምርም በተማሪው በኩል የነበረ ግብረገብ ግን ግሩም እንደነበርም ያክላሉ፡፡ ‹‹እንደአሁኑ መምህሩ ላይ የሚያፈጥና የሚቆጣ የለም፡፡ ተማሪው ለመምህሩ ካለው አክብሮት የተነሳ መምህሩ በገባበት አይገባም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የአገር ዕድገት ሲታሰብ መምህሩ ግንባር ቀደም ሚና አለው፡፡ ‹‹መምህርነት የሙያዎች ሁሉ ቁንጮ ነው›› የሚሉትና በአንጋፋ መምህርነት ከተሸለሙት አንዱ የሆኑት መምህር ቦርሳም ቦሎሎ ቦካ፣ መምህርነት ለአገር ልማት መሠረት ቢሆንም፣ በጃንሆይ ጊዜ የትምህርት ዘርፍ ፍተሻ፣ በደርግ ‹‹የተማረ ሁሉ ያስተምር›› የሚል አካሄድ የትምህርቱን ጥራት ለማወክ ዓይነተኛ ምክንያቶች ነበሩ ይላሉ፡፡

በ1972 ዓ.ም. ኮሎኔል ጐሹ ወልዴ (ዶ/ር) ትምህርት ሚኒስትር ሲሆኑ፣ ትምህርት ጥራት ላይ መሻሻሎች መታየታቸውን ያስታወሱት አቶ ቦርሳም፣ ያለፉት 27 ዓመታት ግን ጥራት የወደቀበት ትምህርት የተስፋፋበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እንደባለሙያ ሳየው ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ወድቋል›› የሚሉት አቶ ቦርሳም፣ ለመምህርነት የሚመደበው ራሱ ፈቅዶና ፈልጎ አለመሆኑም ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የትምህርትና ሥልጠናው ፍኖተ ካርታ የመማር ማስተማሩን ሒደት ለማሻሻልና አገሪቷን ለማሳደግ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን በዚሁ ጎን ለጎን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መምህራንን ያቀፈው የመምህራን ማኅበር ራሱን ከፖለቲካ ተለጣፊነት ነፃ አድርጎ ለአገሪቷ ልማት ጉልህ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል፡፡ የ70ኛ ዓመት ኢዮቤልዩውም ለወደፊት የዕድገት ተስፋን የሰነቀና ለመምህሩ አለኝታነቱን ያጠነከረበት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...