የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ በሁለት ዋና ጉዳዮች ሲብጠለጠል ሰንብቷል፡፡ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ስም ሲነሳና ሲጣል የሰነበተባቸው ጉዳዮች ከሕንፃ ግዥና ከትጥቅ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በተለይ ከትጥቅ አቅርቦት ጋር ተያይዞ እንደ ክፍተት ሲነገሩ ከነበሩት ጉድለቶች በዋናነት ከተቋሙ የመደራደር አቅም ውስንነት የመነጨ እንደሆነ ሲነገር፣ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ አሁንም ጊዜ እንዳለው ተከራክሯል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በሦስት ዓበይት ጉዳዮች ማለትም የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በሰጠው ሦስት ሚሊዮን ዶላር ስለገዛው የቢሮ ሕንፃ፣ የብሔራዊ ቡድን አልባሳትን በሚመለከት ከትጥቅ አቅራቢው ኢራ ከተሰኘው የጣሊያን ትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር የአራት ዓመት ውል ከተዋዋለ በኋላ ኮንትራቱ የሁለት ዓመት ጊዜ እየቀረው፣ አምብሮ ከተሰኘ ሌላ ትጥቅ አቅራቢ ድርጅት ጋር አዲስ ኮንትራት የተፈራረመበትን ሒደትና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለስፖርት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ለፌዴሬሽኑ የቢሮ አገልግሎት የሚውለውን የሕንፃ ግዥ አስመልክቶ ፊፋ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ድርድሩ የተጀመረው በአቶ ጁነዲን ባሻ የአገልግሎት ጊዜ ማለትም እ.ኤ.አ በ2015 እና 2016 በጀት ዓመት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ እንዲያውም አቶ ጁነዲንና ካቢኔያቸው ፌዴሬሽኑን ለሁለተኛ ጊዜ ለማገልገል ለምርጫው ራሳቸውን ያቀረቡበት አንዱ ምክንያት ይህ የሕንፃ ግዥ ፕሮጀክት መሆኑን በመጥቀስ ነበር፡፡
በአመራር ላይ የሚገኘው የአቶ ኢሳያስ ጅራ ካቢኔ፣ ቀደም ሲል ባለመዋዋሉ የተነሳ ፊፋ በጀቱን አጥፎት የነበረ በመሆኑ አቶ ኢሳያስ ደብዳቤዎችን ከመጻጻፍ ጀምሮ በአካል በመገኘት ተቋሙ ጉዳዩን ሊያጤነው እንደሚገባ በማሳመን ገንዘቡ እንዲፈቀድ ማድረጋቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ፊፋ በፈቀደው ሦስት ሚሊዮን ዶላር የሕንፃ ግዥው መፈጸሙ በመግለጫው ይፋ ሆኗል፡፡
ይሁንና ሕንፃ ግዥው ተፈጽሟል ተብሎ መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ እንዲያውም የሕንፃ ግዥ መፈጸሙ መነጋገሪያነቱ ሳያከትም፣ ባናቱ የመጣው፣ ፌዴሬሽኑ ከትጥቅ አቅራቢዎች ጋር በውል ላይ ውል ፈጽሟል መባሉ ሌላ ትኩስ የውዝግብ ርዕስ ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ከጣሊያኑ ትጥቅ አምራች ድርጅት ኢራ ጋር የነበረውን የውል ስምምነት በማቋረጥ፣ አምብሮ ከተሰኘው የእንግሊዝ ትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር ስምምነት ማድረጉ ጥያቄዎችን ማጫሩ አልቀረም፡፡
ከኢራ ጋር የነበረው ቀሪ የውል ስምምነት የተቋረጠበት መንገድ ፌዴሬሽኑን ተጨማሪ የገንዘብ ኪሳራ ያስከትልበታል በሚል በተለይም በመግለጫው ዕለት ከስፖርት መገናኛ ብዙኃኑ ለተነሱት ጥያቄዎች የፌዴሬሽኑ ምላሽ ተቋሙ ውል ሲቋረጥና በውል ላይ ውል በሚፈጸምበት ወቅት ሊያስከትል የሚችለውን ትርፍና ኪሳራ ያገናዘበ የመደራደር አቅም ውስንነት ያለበት መሆኑን ያመላከተ እንደነበር ማረጋገጫ ሆኗል፡፡ ትጥቅ ለማቅረብ ውል የነበረው ድርጅት ቀሪ የሁለት ዓመት ጊዜ ያለው መሆኑ በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ምናልባም ጉዳዩ ወደ ሕግ የሚሄድ ከሆነ ፌዴሬሽኑን እስከ መቶ ሺሕ ዩሮ ለኪሳራ እንደሚዳርገው አምነዋል፡፡
እንደ አቶ ኢሳያስ ከሆነ ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን በሰላም ለመጨረስ የሚያስችል የመደራደሪያ ጊዜ እንዳለው፣ የማይሆን ከሆነ ግን ተቋሙ ኪሳራውን ቢከፍልም አትራፊ ነው፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ከኢራ ጋር የተደረሰው ስምምነት ድርጅቱ የ90 ሺሕ ዩሮ ትጥቅ ካቀረበ፣ ፌዴሬሽኑ 50 ሺሕ ዩሮ ተጨማሪ ትጥቅ እንዲገዛ የሚያስገድድ ነበር፡፡ ከአምብሮ ጋር የተደረገው ስምምነት ግን የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖች አልባሳትን ጨምሮ በየደረጃው ሊሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች በነፃ እንደሚያቀርብ፣ በዚያ ላይ በጥራትም ሆነ በብዛት ልዩነቱ ከፍተኛ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡
አምብሮ ቀደም ሲል ከነበረው ቁጥር በዕጥፍ የሚጨምር ከመሆኑ ባሻገር ሁሉም በነፃ መሆኑ፣ ከጥራት ጋር በተያያዘ ከፌዴሬሽኑ አመራሮች በተጨማሪ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችና በዘርፉ የጠለቀ እውቀት ያላቸው ሙያተኞች ሐሳብና አስተያየት ታክሎበት የተፈጸመ ውል ስለመሆኑ ጭምር አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል፣ ይህንኑ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብርሃቱም ተናግረዋል፡፡
ከትጥቁ ጎን ለጎን ሰፋ ያለ ጥያቄና ክርክር የተስተዋለበት ፊፋ በሰጠው ሦስት ሚሊዮን ዶላር ግዥ መፈጸሙ የተነገረለት የፌዴሬሽኑ ሕንፃ ነበር፡፡ ምክንያቱም መግለጫው ከመሰጠቱ አስቀድሞ ለሕንፃው የሚወጣው ገንዘብ ከመብዛቱ የተነሳ ተቋሙ የቢሮ ሕንፃ እንዲገነባበት በብሔራዊ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ ግቢ የተረከበው ቦታ ላይ በአነስተኛ ገንዘብ መገንባት የሚችልበት ዕድል እያለው ሮጦ ወደ ግዥ መግባት አልነበረበትም የሚሉ ክርክሮችና አስተያየቶች ሲቀርቡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይሁንና ፌዴሬሽኑ ለፊፋ ባቀረበው ትልመ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) መሠረት በተፈቀደለት ሦስት ሚሊዮን ዶላር ሕንፃ ለመግዛት የሕንፃ ግዥ ኮሚቴ ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በማዋቀር ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ስብሰባ አድርጎ መሠረታዊ በሚባሉ የጨረታ ደንብና መመሪያዎችን የተመለከቱ ውይይቶችን ማድረጉን የኮሚቴው ሰብሳቢ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ተናግረዋል፡፡
ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በሪፖርተርና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የመጀመሪያው ጨረታ እንዲወጣ ተደርጎ አራት ተጫራቾች ቀርበው የሁሉም ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደገና ሌላ ጨረታ እንዲወጣ ተድርጎ ሁለት ተጫራቾች በመቅረባቸው እንዲሰረዝ ስለመደረጉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በሦስተኛው ግን ከቀረቡት ሰባት ተጫራቾች ተፈላጊው ሕንፃ ተገኝቶ ከቫት ውጪ 83 ሚሊዮን ብር ግዥ ስለመፈጸሙም አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ መግለጫ ሦስተኛው ጉዳይ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታን የተመለከተ ነበር፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም ቡድናቸው አጣዳፊ የሆነ ዝግጅት እያደረገ ባይሆንም የዋናው ቡድን ተተኪ ላይ በትኩረት እየሠሩ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡ ከ23 ዓመት በታች ለኦሊምፒክ ቡድን 33 ተጨዋቾች መርጠው የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ከማሊ ጋር መጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ፣ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ከሦስት ቀን በኋላ ባማኮ ላይ እንደሚያደርጉ፣ ፕሮግራሙ የተጣበበ በመሆኑ በጉዳዩ ከካፍ ጋር እንደሚገናኙም ተናግረዋል፡፡
ዋና አሠልጣኙ የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖችን ጨምሮ ዋናው ብሔራዊ ቡድን በፊፋ የወዳጅነት ጨዋታ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር እንዲፈጠር ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ በተለይ በስፖርት ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አሠራር መፍጠር ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት በመሠረታዊነት ሊታይ እንደሚገባ ጭምር አስረድተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአካል ብቃት አሠልጣኝ ከመቅጠር ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኑ የሚጠናከርበት የአሠልጣኞች ስብስብ አስፈላጊነት ላይም አብራርተዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ሁሉም ለብሔራዊ ቡድኑ ጥንካሬ የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የፕሪሚየር ሊግ አሠልጣኞች የካቲት 23፣ ለቀድሞ ተጨዋቾች ደግሞ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ተገናኝተው ውይይት እንዲደረግ ፕሮግራም ስለመያዙም አስረድተዋል፡፡