Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርከንቲባ ታከለ ኡማ የተበዝባዥ ሠራተኞች አቤቱታችን ይድረስዎ

ከንቲባ ታከለ ኡማ የተበዝባዥ ሠራተኞች አቤቱታችን ይድረስዎ

ቀን:

ለክቡር ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አቤቱታ የሚያቀርቡት ቁጥራቸው ከ300 ሺሕ በላይ የሆኑ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቢሮዎችና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች፣ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የሹፍርና፣ የእንግዳ ተቀባይነት፣ የጥበቃ፣ የፅዳት፣ የአትክልት ክብካቤ ሥራ ላይ ተሠማርተው የቆዩ የቀድሞ ሠራተኛ ማኅበራት አመራሮች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይል ቀጥረው ከሚንቀሳቀሱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እንዲሁም በውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሥር የሚንቀሳቀሱ የውኃ ልማትና ሌሎች ተጠሪ ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎችም የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት ፋብሪካዎች ማለትም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ሥር ያሉ ፋብሪካዎች፣ የመንግሥት ሆስፒታሎችና ሆቴሎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩሊቲን ጨምሮ እንደ ቦሌ ክፍለ ከተማ የመሳሰሉ የከተማው መሥሪያ ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮን ጨምሮ ሌሎችም የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በዘመቻ የጥበቃ፣ የሹፌር፣ የፅዳት፣ የእንግዳ ተቀባይ ሠራተኞችን ለቁጥጥር አላመቸም በሚል ሰንካላ ሰበብ የሠራተኛ ማኅበራትን በማፈራረስ ከ300 ሺሕ በላይ ሠራተኛ በጡረታ አሰናብተዋል፡፡

የፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩ ግለሰቦችም ሌሎች ከኮሚሽነርነት ያነሰ ማዕረግ ያላቸው የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ ከፍተኛ የወታደር ማዕረግተኞች የነበሩ፣ ከአዲስ አበባ  ሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ፈቃድ በመውሰድ፤ የተወሰኑትም ያለፈቃድ ለጥበቃ፣ ለፅዳት፣ ለሹፌርና ለሌላውም የሥራ ዘርፍ የሰው ኃይል አቅራቢ የሆኑ ኤጀንሲዎችን በመክፈት ግልጽነት በጎደለው ጨረታ ከ300 ሺሕ በላይ ሠራተኛ በግፍ እንዲከፋፈሉ ተደርገዋል፡፡

ሠራተኛው የሚያገለግለው መንግሥትን ቢሆንም፣  በመንግሥትና በሠራተኛ መካከል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች ጣልቃ እንዲገቡ በመደረጉ፣ ከሠራተኛው ደመወዙ ላይ የማይቋረጥ ቋሚ ኮሚሽን እያፈሱ ኪሳቸውን ይሞላሉ፡፡ አሁንም ድረስ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ቀጣሪዎቹ ድርጅቶች ሲያተርፉ ይሰጡ የነበረውን ቦነስና ጥቅማ ጥቅም ‹‹ድርጅቱን አታገለግሉም፤ እናንተ በሰው ኃይል አቅራቢ ድርጅት በኩል የመጣችሁ በመሆናችሁ አይመለከታችሁም፤›› እየተባልን ጥቅማ ጥቅሞቹ ወደነዚህ ከበርቴ መኮንንዎች ኪስ እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ መሠረት የደንብ ልብስ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰጥ የነበረው በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ተደርጓል፡፡ በአንፃሩ ድርጅቶቹ ለዚህ የሥራ መደብና የሰው ኃይል ያወጡት የነበረው በጀት በሁለትና በሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡  ገንዘቡ ግን ወደ አስቀጣሪ ኤጀንሲዎቹ ይገባል፡፡ ሥራው ለኤጀንሲዎች ለምን ተሰጠ ቢባል ወጪ ለመቀነስ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን ቀረና ወጪው በእጥፍ አደገ፡፡ ዓላማው ያልሠሩበትን ሀብት ማጋበስ ለሚፈልጉ ሰዎች ሕገወጥ የመበልፀጊያ መንገድ በመሆኑ፣ ሀብቱን ወደሚቀራመቱ ሰዎች እየተዘዋወረ ነው፡፡ በአንድ ሠራተኛ በወር እስከ 2000 ብር ትርፍ ያገኛሉ፡፡ ሳይወጡ ሳይወርዱ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠረው ሠራተኛ በወር ምን ያህል ሚሊዮን ብር እንደሚያጋብሱ ማሰብ ነው፡፡ ሕጋዊ የዘርፋ መንገድ ተመቻችቷል ማለቱ ይቀላል፡፡

 ለኤጀንሲዎቹ ፈቃድ ሰጥቶ ያዘረፈን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የችግሩ አካል እንደመሆኑ መፍትሔ ስላልሰጠን እንዴት በአገራችን ቅኝ እንገዛለን፣ ጉልበታችን ይበዘበዛል በማለት ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ አመልክተናል፡፡ ከጅምሩ ጉዳያችንን በጥሩ ሁኔታ ይዘው ሥራው የግድ ለውጭ ቀጣሪና አስቀጣሪ ድርጅቶች ይሰጥ ከተባለ እንኳ የሠራተኛውን ጥቅም ባስከበረ መንገድ መሆን አለበት የሚሉ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡ በመንግሥት ፖሊሲ መሠረትም ሠራተኛው ተደራጅቶ ሥራውን ሊይዘው ይገባል የሚል ሐሳብ በመያዝ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ደብዳቤዎችንም ልከውልን ነበር፡፡

ጉዳያችን እስከ ቀደምቷ ሚኒስትር ቢደርስም፣ በሒደት ግን እኛን ገሸሽ የሚያደርጉና ከኤጀንሲዎቹ ጋር ግንኙነት የፈጠሩ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ግን አልጠፉም፡፡ ይህን የተመለከቱና ጉዳያችን ያሳዘናቸው አንድ ቅን የተቋሙ ባልደረባ፣ ‹‹ዝምብላችሁ ነው የምትለፉት›› ብለው ጉዳያችን እንዴት እንደተጻፈ አረዱን፡፡ ለሕይወታችንም እንደሚያሠጋን አስጠነቀቁን፡፡ እንደተባለውም የፖሊስና የመከላከያ ኔትወርካቸውን በመጠቀም የኤጀንሲዎቹ ባለቤቶች ለመቀጣጫ የሠራተኛውን አስተባባሪዎች በከባድ ድብደባ አካል ማጉደልን ጨምሮ እሥራትና አፈና አመጡብን፡፡ ይህ ድርጊት እየባሰ ሲመጣ የከፋውን እንዳይደርስብን በመፍራት ጉዳዩን ተውነው፡፡

ይኼው ለዓመታት ዓይናችን እያየ፣ እንደባሪያ ጉልበታችን እየተበዘበዘ ደመወዛችንን የኮሚሽን ድርጅቶች እየተካፈሉን እኛ ስንደኸይ እነሱ በሕንፃ ላይ ሕንፃ እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ ሠራተኛው ስንት ዓመት ካገለገለበት መሥሪያ ቤት ከቋሚ ሥራው ተነስቶ ወደ ኤጀንሲ ግባና ሥራ እየተባለ፣ መሥሪያ ቤትህ ለኤጀንሲ አስረክቦሃል፣ አገልግሎትህን ለእኛ ትሰጣለህ እየተባለ፣ ደመወዝና ማንኛውንም ነገር ከኤጀንሲው ጋር ጨርስ እየተባለ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ በፊት ከሚያገኛትም አነስተኛ ደመወዙ ላይ እየተቀነሰበትና ለኤጀንሲው እየተከፈለው መኖሩ በደም ብዛት፣ በስኳር በሽታና በኑሮ ጉስቁልና ጨርሶታል፡፡ የቀረውም አቅም አጥቶ የግፍና የዘረፋ ቀንበር ተሸክሞ ኑሮውን እየተፍገመገመ ቀጥሏል፡፡

ዘርፉ በአብዛኛው የተማረውን የሰው ኃይል ስለማያሳትፍ በደሉ ሰሚ አጥቶ ተድበስብሶ ቆይቷል፡፡ በሒደት የዩንቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶች ሥራም አማራጭም በማጣት በጥበቃም በሌላውም ሙያ ሲቀጠሩ ከሚሠሩበት የመንግሥት ተቋም በስማቸው የሚወጣውን የገንዘብ መጠንና የሚከፈላቸውን ገንዘብ በማነፃፀር ለሚሠሩበት የመንግሥት ተቋም ኃላፊዎች የመብት ጥያቄዎችን ማንሳታቸው አልቀረም፡፡ ሆኖም ኤጀንሲውን ጠይቁ ይባላሉ፡፡ ኤጀንሲውን ሲጠይቁም በቀጥታ ከሥራ ይባረራሉ፡፡ ከባሰም የፖሊስና የመከላከያ ኔትወርካቸውን በመጠቀም የሠራተኛውን ጥያቄ በጉልበት ያዳፍናሉ፡፡ የጉልበት ብዝበዛው ባርነት ሆኗል፡፡

ጥቂቶች እንዲከብሩበት ከአንድ ሚሊዮን በላይ በላባችን የምንኖር ዜጎችና ቤተሰቦቻችን ደኅይተናል፡፡ ተርበናል፡፡ ተሰቃይተናል፡፡ የኦሮሚያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በክልሉ ተነስቶ በነበረውና ለለውጡ መሠረት በጣለው የሕዝብ አመፅ የወጣቶች ጥያቄ አንዱ ምክንያት እንደሆነ በማጤን የኤጀንሲዎችን ተግባርም ብዝበዛ እንደሆነ፣ በተቃውሞ ወቅትም ለፋብሪካዎች መቃጠልና መውደም ሠራተኛው የነበረው ብሶት አስተዋጽኦ ማድረጉን በማጥናትና በማጣራት ለሜታ አቦና ለሌሎች ድርጅቶች የሰው ኃይል ያቀርቡ የነበሩ ኤጀንሲዎችን ፈቃድ በመሰረዝ የሠራተኛውን ጥቅም አስከብሯል፡፡ ዛሬ በኦሮሚያ በሚገኙ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኛው በቀጥታ ከአሠሪው ጋር እየተገናኘ በመካከላቸው በተፈጠረ መግባባት ከሠራተኛው ደመወዝ ቋሚ ኮሚሽን የሚወስዱ በዝባዦች ተወግደው ሠራተኛው የላቡን እያገኘ የሚኖርበት የኢንዱስትሪ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በአዲስ አበባ የምንገኝ ሠራተኞች ግን ጉልበታችን እየተበዘበዘ ተመልካች አጥተን በስቃይ ላይ እንገኛለን፡፡

ክቡር ከንቲባ እንዲሰጡን ምንፈልገው መፍትሔ

በከንቲባነት በሚያስተዳድሯት አዲስ አበባ ከተማ ለምንኖር ዜጎች የመጨረሻው ውሳኔ ሰጭ እንደመሆንዎ፣ በደሉም እየተፈጸመ የሚገኘው በአስተዳደሩ ሥር እንደመሆኑ የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የእነዚህን በዝባዥ ድርጅቶች ፈቃድ ከማደስ እንዲቆጠብና እንዲሰርዝ ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጡልን በመላው ሠራተኛና በሚያስተዳድረው ቤተሰብ ስም እንጠይቃለን፡፡ 20 የማይሞሉ ሰዎች እንዲበለፅጉ ሲባል ከነቤተሰባችን ለችግር መጋለጣችንን ዓይተው አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡን እንጠይቃለን፡፡

የኦሮሚያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተሞክሮ እንዲወስድና ተደጋጋሚ አቤቱታ በአካል፣ በሚዲያና በሠልፍ ጭምር ቀርቦለት መፍትሔ ያልሰጠው የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጭራሹኑ አቤቱታ አቅራቢ የሠራተኛው ተወካዮችን ተስፋ ለማስቆረጥ ፒያሳ ካቴድራል በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ውስጥ በራሱ የሰው ኃይል ያከናውናቸው የነበሩትን የሥራ መደቦች የራሱን ሠራተኞች የትም በትኖ ሥራውን ከኃላፊዎቹ ጋር በጥቅም ለተሳሰረው ኤጀንሲ በመስጠት የሠራተኞችን መብት በማስጠበቅ ለሌሎች አርዓያ መሆን ሲገባው የብዝበዛው ተባባሪ በመሆኑ ዕርምጃ እንዲወስድበትና አሠራሩ እንዲፈተሽ በመላው ሠራተኛና በሚያስተዳድረው ቤተሰብ ስም እንጠይቃለን፡፡

(ከአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኞች አስተባባሪዎች)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ