Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት አንድ ጉዳይ ገጥሞኝ ወደ ሱልልታ ሄጄ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሥጋና የጠጅ መናኸሪያ የሆነችውን ሱልልታ የፆም ቀን (ረቡዕ) ብሄድባትም፣ ጉዳዬን ከጨራረስኩ በኋላ ደስ የሚል መስተንግዶ አግኝቼባታለሁ፡፡ በተለይ በሥራ አጋጣሚ የተገናኘሁዋቸው የአካባቢው ሰዎች ትህትናና በጨዋነት የታጀበ አቀራረብ በጣም ነው ያስደሰተኝ፡፡ ለገጠመኜ መነሻ የሆኑት ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ሚዛን የሚባለው ሥፍራ ያገኘኋቸው አዛውንት ግን መቼም ቢሆን ከልቤ አይጠፉም፡፡ ሚዛን ስደርስ አዛውንቱ እጃቸውን እያርገበገቡ እንድጭናቸው ጠይቀውኝ ነው የተዋወቅነው፡፡ እኔም መኪናዬን አቁሜ በሩን ከፈትኩላቸው፡፡ አዛውንት ማክበር ባህላችን ስለነበረ ነው እኚህን ትልቅ ሰው የጫንኩት፡፡ ህሊናዬም ቢሆን ይኼንን እንዳደርግ ያስገድደኛል፡፡ ሰው የመሆናችን ሚዛን የሚለካው ታላላቆችን በማክበር ነውና፡፡ 

አዛውንቱ አቶ ሞቱማ ጉዲሳ እንደነገሩኝ ተወልደው ያደጉት ሰላሌ ጎርፉ የሚባል አካባቢ ሲሆን፣ ሱልልታ መኖር ከጀመሩ ከ40 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ባለትዳርና የሰባት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ሞቱማ ሁሉንም ልጆቻቸውን ድረው ከባለቤታቸው ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ ከእርሻ በተጨማሪ የአናፂነት ችሎታ ስላላቸው በከተማም ሥራ አላቸው፡፡ ዕድሜያቸው 67 ሲሆን፣ ጠንካራ ቁመና አላቸው፡፡ አነጋገራቸው በብስለት የተሞላና የማስታወስ ችሎታቸው አስገራሚ ስለሆነ ሲናገሩ አፍ ያስከፍታሉ፡፡ ከሚዛን አዲስ አበባ ፍልውኃ አካባቢ እስክንደርስ ድረስ፣ እሳቸው እየተናገሩ እኔ እያዳመጥኩ ያደረግነው ጉዞ በጣም ደስ የሚል ነበር፡፡ ማን ነበር፣ ‘ከአገራችን ምሁር ተብዬዎች የገጠሩ አርሶ አደር ይግደለኝ’ ያለው?

አቶ ሞቱማን ሥራ፣ ቤተሰብ፣ አገር፣ ወዘተ. በተመለከተ ርዕስ እያነሳሁ ስጠያይቃቸው ከወቅቱ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ላይ ወግ ጀመሩ፡፡ ‹‹ወንድሜ ያገናኘን አጋጣሚ ነው፡፡ እኔና አንተ ባንተዋወቅም፣ በአንድ አካባቢ ተወልደን ባናድግም፣ ምን እንደሆንን ባይታወቅም፣ የፈጣሪ ልጆች መሆናችን በቂ ነው፡፡ እንኳን ኢትዮጵያዊ ወገኔ የገዛ አገሬ ልጅ ሆነህ፣ ባህር ተሻግረህ የመጣህ ባዕድ ብትሆን እንኳ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርክ ሰው መሆንህ ብቻ ይበቃኛል፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ ኬንያ፣. . .  ብትሆን፣ ነጭ፣ ጥቁር ወይም ሌላ ብትሆን ዋናው ሰው መሆንህ በቂ ነው፡፡ ይኼው የእኛ አገር ሰው አሜሪካ ውስጥ እንደ ጉንዳን ይተራመስ የለ? አሜሪካኖቹ በሰውነቱ ባይቀበሉት ኖሮ በሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሰው እዚያ አገር ንብረት አፍርቶ ይኖር ነበር?›› እያሉ ትውውቃችንን በአስገራሚ አገባብ ጀመሩት፡፡

‹‹የእኔ አባት ትውልዱ ወለጋ ነው፡፡ ከነቀምት ወጣ ብሎ ሳሲጋ የሚባል ሥፍራ፡፡ እናቴ ደግሞ እዚሁ ሰላሌ ናት፡፡ አባቴ አጎቱን ፍለጋ መጥቶ እዚሁ ቀረ፡፡ የሰላሌ ሰው ሆኖ አደገ፡፡ አባቴና እናቴ ሁለት ልጆች ብቻ ነው የወለዱት፡፡ ታላቅ ወንድሜ በልጅነቱ ወታደር ሆኖ በንጉሡ ዘመን ከሶማሌ ጋር ሲዋጋ ሞተ፡፡ እኔን በ15 ዓመት ይበልጠኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ግብርናን ከአናፂነት ጋር አጣምሬ ልጆቼን አሳደግኩ፡፡ ልጆቼ በሙሉ አዲስ አበባ ነው የሚኖሩት፡፡ ሦስቱ ዲግሪ አላቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ዲፕሎማ አላቸው፡፡ ሁሉም ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው፡፡ ጋብቻቸው ደግሞ ይገርምሃል፡፡ የመጀመሪያዋ ባሏ ጉራጌ ነው፡፡ ሁለተኛዋ የአገሯ ልጅ ነው፡፡ ሦስተኛው የሰሜን ሸዋ ልጅ ነው ያገባው፡፡ ምን አለፋህ ብሔር ብሔረሰብ ሆነዋል. . . እያሉ ሳቁ፡፡

አቶ ሞቱማ ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ወንድሜ በልጆቼ ደስተኛ ነኝ፡፡ ግን የበለጠ ደስ የሚለኝ አገሬ ደስ ሲላት ነው፡፡ ሲከፋት ይከፋኛል፡፡ ታላቅ ወንድሜ ለአባቴ ይልካቸው የነበሩትን የጦር ሜዳ ደብዳቤዎች ሳነብ ስላደግኩ የአገር ፍቅር ውስጤ የገባው ያኔ ነው፡፡ በጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ይመራ በነበረው የኦጋዴን አንበሳ ክፍለ ጦር ውስጥ ስለአገር ፍቅር ስሜት፣ ጀግንነት፣ መስዋዕትነት፣ ቆራጥነት፣ ወዘተ. የሚተርኩት የዚያ ጀግና ወንድሜ ደብዳቤዎች አሁን ድረስ አሉ፡፡ እሱ የሞተ ጊዜ ድፍን ሰላሌ ነው ያለቀሰው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የሠራው ጀብዱ በሚገባ ተጽፎ ተልኮ ነበር መርዶ የተነገረው፡፡ የአካባቢያችን ሕዝብ በጀግንነቱ እየፎከረ ነበር ያለቀሰው፡፡ እኔም አገሬን የወደድኩት፣ የሰውን ልጅ በሙሉ የወደድኩት በዚያን ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በወቅቱ በነበረ የወታደር ጋዜጣ ላይ ስለወንድሜ የተጻፈውን ታሪክ ደጋግሜ ሳነብ አለቅስ ነበር፡፡ ይኼ ሁሉ የአገር ፍቅር የመጣው ከዚያ ነው፤›› ብለው ትዝታ ውስጥ ሰጠሙ፡፡

ከአፍታ ቆይታ በኋላ፣ ‹‹አየህ ወንድሜ አገራችን መኖሪያችን፣ መኩሪያችን፣ ገመና ከታቻችን፣ መቀበሪያችን፣ ብቻ ምን ልበልህ ሁሉም ነገራችን ናት፡፡ ይኼንን አለመረዳት ማለት ጥሩ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች የሚስቱት አንድ ነገር አለ፡፡ አገርና ፖለቲካን አደባልቀው የቱን እንደሚይዙ፣ የቱን እንደሚለቁ አያውቁም፡፡ መንግሥት በለው ሕዝብ በለው አላፊ ነው፡፡ አገር ግን ለመጪው ትውልድ እየተላለፈች የምትቀጥል ቋሚ እናት ናት፡፡ እናት ሲከፋት ዝም አይባልም፡፡ ሲያማት ዝም ተብሎ አይታይም፡፡ መከፋቷን በደስታ፣ ሕመሟን በፈውስ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ግን በተለይ ተምረናል የሚሉ ሰዎች በቡና ረከቦት ዙሪያም ሆነ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚናገሩት አጓጉል ነገር ግራ ይገባኛል፡፡ የቤትህን ትኋን ለማጥፋት ፀረ ተባይ ትጠቀማለህ እንጂ ቤትህ ላይ እሳት ትለኩሳለህ? አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ሳይ የአዕምሮ ሁከት ያለባቸው ሰዎች ሥራ እንጂ የጤነኞች አይደለም. . .›› እያሉኝ ሲነግሩኝ አዲስ አበባ ገባን፡፡

የከተማውን ትራፊክ እያቆራረጥን ስንጓዝ፣ ‹‹ወዳጄ አዲስ አበባ ከተቆረቆረች ከ130 ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ ይህች ከተማ የሁላችንም ናት፡፡ ማንም ተነስቶ የእኔ ናት ቢልህ አትስማው፡፡ የአፍሪካውያን ከተማም እንደሆነች መዘንጋት የለብንም፡፡ ከተማ እየመሰለች ያለችው ግን አሁን ነው፡፡ በእርግጥ መለወጧ የግድ ቢሆንም፣ ነዋሪዎቿ እየተጎሳቆሉና እየተፈናቀሉ የትም እየተጣሉ መሆን የለበትም፡፡ ልማቱ የሰውን ልጅ ሲያቅፍ ይደምቃል፡፡ ጥቂቱ ጠግቦ እያገሳ ብዙው እየተራበ አይሆንም፡፡ ግን ለማደግ ደግሞ መስዋዕትነት መከፈል አለበት፡፡ መስዋዕትነቱና ባለቤትነቱ ግን የጋራ እንደሆነ ሁሉንም ሊያግባባ ይገባል፡፡ ለማንኛውም አገራችን የእኛ፣ እኛም የአገራችን የምንሆንበትን አስታራቂ መፍትሔ ማፍለቅ ከቻልን ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፤›› ብለውኝ እንደ ዘመድ ተቃቅፈን ከተሰነባበትን በኋላ ተለያየን፡፡ የሱልልታውን አርሶ አደር አዛውንት ዓይነት ዕድሜ የጠገቡና ምራቃቸውን የዋጡ ሰዎችን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ተብዬዎቹ ምናለበት ቢያፈላልጉልን? ግራ ተጋብተው ግራ ከሚያጋቡን ምሁር ተብዬዎች እነሱ ይሻላሉ፡፡ ተማርን የሚሉትንማ እያየናቸው ነው፡፡ በጎራ እየከፋፈሉን ሊያፋጁን ነገር እየተፈላለጉ አገር ያምሳሉ፡፡ የሚያምስ ያምሳቸውና፡፡

(ዘሪሁን ወረደ፣ ከቄራ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...