Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉየግል ባንኮች ጉዳይ ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ

  የግል ባንኮች ጉዳይ ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ

  ቀን:

  በመጥምቁ ዮሐንስ

  የንግድ፣ የማኅበራዊም ሆነ የመንግሥታዊ ተቋማትን መገንባት ለማንኛውም አገር ውስብስብና ፈታኝ ሥራ እንደሆነ ከልምድ ይታወቃል፡፡ ስለተቋማት ግንባታ ስናስብ እንቅፋት የሚሆንብን የተገነቡ ተቋማትን ዘለቄታ ባለው መንገድ አጠናክረን ቀጣይነታቸውን በማረጋገጥ ለመልካም አስተዳደር የበቁ፣ ለሙስናና ለመብት ጥሰት ያልተጋለጡ፣ ነፃና ፍትሐዊ አመለካከትና አሠራር ተመርኩዘው ያለ ተፅዕኖ የሚያገለግሉ ማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡

  ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ከሚፈታተኑን መሠረታዊ ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ይኼው ተቋማትን መፍጠር፣ ማሳደግና ማብቃት አለመቻላችን መሆኑ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ አገራችን በአቅማቸውም ሆነ በደረጃቸው አስተማማኝ የሆኑ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ባለመቻሏ ምክንያት፣ ዛሬ ለሚፈታተኑን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ውጣ ውረዶች መጋለጣችን አንዱ መንስዔ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ደግሞ የተቋማት ግንባታ ሒደቱን አሳዛኝ የሚያደርገው፣ በታሪክ አጋጣሚ በግለሰቦች ጥንካሬ ወይም በብቃታቸው ምክንያት የተገነቡ በጣት የሚቆጠሩ ተቋማትን ቀጣይነት ማረጋገጥ አለመቻላችን ነው፡፡

  ጠንካራ አቅምና ዘለቄታ ያላቸው የንግድም ሆነ የማኅበራዊ ወይም መንግሥታዊ ተቋማት የሌሏት አገር፣ በአገር በመሥራት ሒደት የምትከፍለው መስዋዕትነት እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ የንግድ ተቋማቶቿ ደካማ የሆኑባት አገር የአቅርቦት አቅሟም ሆነ የግብይት ሥርዓቷ ዕውቀትንና ብቃትን ከግምት ውስጥ አስገብቶና ሽግግር መሠረት አድርጎ ስለማይከናውን፣ ዜጎች የውጭ አገር ተቋማት ዝንባሌና አሠራር ጥገኛና የአስተሳሰብ ማራገፊያ ከመሆናቸውም በላይ ለሙስና የተጋለጡና አገራዊ የሆኑ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ቁሳዊ ሀብቶችን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የማይችሉ ደካማ ይሆናሉ፡፡

  ዛሬ የትኩረት አቅጣጫዬ ማኅበራዊና መንግሥታዊ ተቋማት አይደሉም፡፡ እንዳስፈላጊነቱ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ወደፊት እመለስበታለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይልቁንም ዛሬ የትኩረት አቅጣጫዬ በግል ኢኮኖሚው ዘርፍ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙትና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ገንቢም ሆነ አፍራሽ ሚና ለመጫወት ሰፊና ገንቢ ዕድል ካላቸው የንግድ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው በተለይ የባንኪግ ኢንዱስትሪው ላይ ሲሆን፣ በተናጠል ደግሞ አንጋፋ የሚባለውን አንድ የግል ባንክ የሚመለከት ይሆናል፡፡

  በመነሻነት ይኼንን ጽሑፍ እንድከትብ ያነሳሳኝ ጉዳይ በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ የረቡዕ ዕትም ላይ ‹‹የባንኪንግ ኢንዱስትሪው ከድጋፍ በተጨማሪ ቁንጥጫ ያስፈልገዋል›› በሚል ርዕስ፣ በአጠቃላይ በግል ባንኮች ላይ የተሰነዘረው እውነታንና ተቆርቋሪነትን ያማከለው የሰላ ትችት ነው፡፡ ነገር ግን በተለምዶ በጥቅል የሚሰጡ አስተያየቶች ምርትና ግርድ የመለየትና ተመክሮን በሚጋብዝ መንገድ ለእርምት አዘጋጅተው ስለማያውቁ፣ ጉዳዩን አንድ ደረጃ ወደ መሬት አውርዶ መተንተን አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

  የግል ባንክ ኢንዱስትሪው ካፈራቸው አንጋፋ ባንኮች መካከል ይህ የግል ባንክ በምሥረታው የመጀመርያ ከሚባሉት ባንኮች ውስጥ የሚቀመጥ ነው፡፡ ይህ የግል ባንክ ከጅምሩ በዘመናዊ የባንኪንግ አሠራር ራሱን ለማብቃት ውጥን ይዞ የተመሠረተና በባንኪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በስፋት በማስተዋወቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ ዛሬ ላይ ይህ ባንክ የከፈተውን በር በመከተል ግዙፉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ፣ ሁሉም የግል ባንኮች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተ ነበር፡፡

  ባንኩ በግል የንግድ ተቋም ግንባታ በተለይ በባንኪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያበረከተው ውለታ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ገና ከጅምሩ ሰፋ አድርጎ በማቀዱ እንደተለመደው ቅርንጫፎቹን አዲስ አበባ ላይ ብቻ ከማረባረብ ይልቅ፣ በክልል ከተሞች ቅርንጫፎችን በብዛትና በአንድ ጊዜ ከፍቶ መሠረተ ሰፊ ባንክ መሆኑ ያረጋገጠ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የብድር አሰጣጥ ሥርዓቱን ከማዘመን አኳያም ሆነ ከበርካታ አገሮች ጋር የዓለም አቀፍ የባንኪንግ አገልግሎትን በስፋት በመዘርጋት ረገድ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሐዋላ ግብይት (ዌስተርን ዩኒየን) ኤጀንት በመሆን ቀዳሚው የግል ባንክ ነው፡፡

  በዚሁ ጉዞው ባንኩ ኢንዱስትሪውን ከቴክኖሎጂ ጋር ከማግባባቱም በላይ፣ የመጀመርያውን ኤቲኤም በአገራችን ውስጥ ያስተዋወቀ ተጠቃሽና አንጋፋ ባንክ ነበር፡፡ የመጀመርያው ኮር ባንኪንግ ሥርዓትን በመዘርጋት፣ ጤናማ የሆነ የአሠሪና የሠራተኛ ግንኙነት ለመፍጠር ችሏል፡፡ ለሠራተኞች ሼር በመግዛትና በባንኩ ላይ ተመጣጣኝ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሰርፅ በማድረግ ኢንዱስትሪያዊ ሰላም እንዲሰፍን ፈር ቀዳጅ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ሠራተኛውን የትርፉ ተጋሪ በማድረግ በሠራተኛና በአሠሪ መካከል ሊኖር የሚገባውን ዘመናዊና ፍትሐዊ የሆነ የሥራና የጥቅም ግንኙነት ዕውን ለማድረግም የቻለ ተቋም ነበር፡፡

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የባንኩ ውጤት የቁልቁለት ጉዞውን ከጀመረ ከአምስት ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ቀደምት የባንኩ የቦርድ አመራር አባላት ሙሉ በሙሉ ኃላፊነታቸውን ለቀው የተኳቸው አዲሶቹ የቦርድ አመራሮች ወደ ኃላፊነት ከመጡ ጊዜ ጀምሮ፣ ባንኩ በአደጋ ቀጣና ውስጥ እንዲወድቅ ተገዷል፡፡ በወቅቱ በአዲስ አመራርነት የተተኩት መጀመርያውንም የቦርድ አባላት ዕቅዳቸው ባንኩ በብዙ ድካም ያፈራውን ሀብትና ከሕዝብ የሚሰበሰብውን ተቀማጭ፣ እንዲሁም በብዙ ድካም የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ለመቀራመት ዕቅድ በመዘርጋት ነበር፡፡ ለዚህም እንዲበጃቸው በመጀመርያ በየተመደቡበት ተቋማት ያከማቹትን ዘመናት ያስቆጠረና ሥር የሰደደ ሽኩቻ ከውጭ ጎተው በማምጣት በቀሰቀሱት ውጥረት ነባር የሆኑ፣ የተሻለ አቅምና ችሎታ ያላቸው የቦርድ አባላት እንዳይመረጡ አድርገዋል፡፡

  ይኼንን ተከትሎ የፈጸሙት ድርጊት ባንኩን እንደፈለጉት ለመዘወር እንዲመቻቸው በር እንዲከፍት ማድረግ ነበር፡፡ ወዲያው ተግባራዊ ያደረጉት ከፍተኛውንና መካከለኛውን በተለይ ደግሞ ነባሩን የባንኩ ሠራተኛ ስም በማጥፋት፣ በማሸማቀቅና ቅስሙን መስበር ነበር፡፡ በመቀጠልም አዲስ የአሠራር ሥልት እንዘረጋለን በሚል ባንኩ በትርፍ፣ በተቀማጭ ብዛትና በውጭ ምንዛሪ፣ እንዲሁም በብድር ከሁሉም የግል ባንኮች በርቀት ቀድሞ እንዲገኝ ያደረገውን ውጤታማ አሠራር በመቀልበስ  ከባንኩ ባህል፣ ዘይቤና አቅም ጋር የማይጣጣም ለዚያውም በተወነጋገረ ሁኔታ ከንግድ ባንክ የተቀዳና አወቃቀር አሠራር ተክለዋል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ መሠረታዊ አጀንዳቸው ሀበትን መቆጣጠር እንደመሆኑ መጠን፣ የብድርና የውጭ ምንዛሪ ውሳኔ አሰጣጡን ለተወሰ ቡድንና አካል እንዲተላለፍ በማድረግ የባንኩን አመራርና አሠራር ለግል ጥቅማቸው በሚመች መንገድ በራሳቸው አምሳያ ጠፍጥፈው መሥራት ችለዋል፡፡

  እነኚህ ተጠቃሽ ቦርዶች በቀጥታ ባለቤት ሳይሆኑ፣ በውክልና ባገኙት ድምፅና በራሳቸው አምሳያ የፈጠሩትን ደካማና የሞራልም ሆነ የሕግ ተጠያቂነት ስሜት የሌለው የባንኩን ከፍተኛ አመራር በመጠቀሚያነት በመያዝ፣ የባንኩንና የደንበኛውን ፍላጎት በማሟላት የተጣለባቸውን አደራ መወጣትና ቃል እንደገቡት ባንኩን ኃላፊነት በተሞላው መንገድ በሚያሳድግ አካሄድ ሳይሆን፣ ራሳቸውንና በዙርያቸው የተኮለኮሉትን ዘመድ አዝማድና ቤተሰቦች ጥቅም ማስከበርና ብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን እንደ ግል ሀብት በኮታ ማከፋፈል ነበር፡፡

  በዚህ ሁኔታ የባንኩን ሀብት ራሳቸውን፣ ዘመዶቻቸውንና አጋሮቻቸውን ቀጥሎም በተዋረድ የኮለኮሏቸውን የባንኩ አመራሮች ቀዳሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የፈጠሩት ግብግብ፣ በአንዳንድ የቦርዱ አመራር አባላትና በሠራተኛው አንዲሁም በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት የማኔጅመንት አባላት ዘንድ የአቋም ልዩነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ ባካሄዱት የማጥራት ንቅናቄ በባንኩ ውስጥ በሠራተኛው ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን አመራሮች ጨምሮ እስከ ታችኛው የባንኩ መዋቅር ድረስ ያሉ ሠራተኞችን በሐሜት፣ በሹም ሽርና በአሉባልታ በማመሰቃቀል ሠራተኛውን በመከፋፈል፣ ሪሶርስ በሚገኛባቸው ቦታዎች ላይ ሥጋት ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚገመቱ ሠራተኞችን በማስወገድ በምትካቸው በብቃት፣ በአቅም፣ በችሎታ፣ በሥነ ምግባር ጉድለትና በሙስና የሚታሙ በተለይ ደግሞ በታማኝነትት፣ በአቻ ጋብቻ፣ በወንዝ ልጅነት፣ እንዲሁም በጥቅም ተጋሪነት መሥፈርት ሊያገለግሏቸው የሚችሉ ደካማ ሠራተኞችን ወደ ኃላፊነት መሰላል በፍጥነት እንዲወጡ አደርገዋል፡፡

  ባንኩ ለዘመናት የገነባውን ከወንዝ ልጅነትና ከቤተሰባዊ ትስስር የፀዳና በሕግ የሚመራ ባህሪውን በማሳጣትና ከደረጃ በታች በማውረድ፣ ጠንካራ ሠራተኞች ከባንኩ እንዲሸሹና ቀሪው ሠራተኛም ተሸማቆ ሥራውን በአግባቡ መወጣት ወደማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ባንኩ ከትርፍ ጀምሮ በተቀማጭ ገንዘብ፣ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በጥቅሉ በሁሉም መሥፈርቶች ከግል ባንኮች ሁሉ የነበረው ግንባር ቀደም ተጠቃሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሟሽሽና በመጨረሻም  እንዲያጣው አድርገዋል፡፡ ዛሬም ባንኩ ከስህተቱ ለመማር ባለመቻሉ ውድቀቱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በከፍተኛ ርቀት ይከተሉት የነበሩት የግል ባንኮች ሳይቀሩ በሁሉም መለኪያ ጥለውት ለመገስገስ በሩን እያንኳኩ ይገኛሉ፡፡  

  የሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው በቅርቡ ከኃላፊነታቸው የተነሱት የቦርዱ አመራሮች የቀሰቀሱት አምሳያ የመፍጠር ግብግብ የከፈተውን በር በመጠቀም በባንኩ ውስጥ የተደራጁት ቡድኖችም በአገር ልጅነት፣ በጥቅም ተጋሪነትና በወገንተኝነት በመሰባሰብ የባንኩን ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ኃላፊነቶችን ጨምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የሚገኙ ሠራተኞች አሰላለፋቸውን እንዲያሳምሩ ለማድረግ ከማኔጅመንቱ ጋር በመመሳጠርና አሉባልታ በማሰራጨት ወደ መስመር አልገባ ያሉትን በማስባረር ባንኩን የግል መጠቀሚያቸው ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡

  እጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ ከጦርነት ባልተናነሰ ሁኔታ የሚካሄደው ግብግብ የሞት ሽረት ትግል ሆኖ በመቀጠሉና ሹም ሽረቱ፣ ከሥራ መሰናበቱና ከቦታ ቦታ መዛወሩ በጥቅሉ ውጣ ውረዱ በእነዚህ ሥውር ቡድኖች የሚመራ በመሆኑ ሠራተኛው ከዕለት ወደ ዕለት እጅግ የበረታ ሥጋት ላይ እንዲወድቅ አስገድዶታል፡፡ ከሥራ ይልቅ አሉባልታ በማሰራጨት ለእነዚህ ሥውር ቡድኖች ማደግደግ ያልቻለ ሠራተኛ ለጥቃት ከመጋለጡ በፊት፣ ባንኩን እየለቀቀ በመሄድ ባንኩን ሰው አልባ እያደረገው ሲሆን፣ የቀረው የሰው ኃይል ደግሞ እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከሥሩም እሳት የሚነድበት ሆኗል፡፡

  በሥውር የሚንቀሳቀሰው ቡድን የዘረጋው ኔትወርክ ሕጋዊ የባንኩን የአለቃና የምንዝር ግንኙነት ከማወኩና ከማዛባቱም በላይ፣ አዛዥና ታዛዥ ማን እንደሆነ እስኪጠፋ ድረስ ሥርዓተ አልበኝነት ነግሷል፡፡ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ገለልተኛ አለቃዎችም ኃላፊነታቸውን በአግባቡና በንቀት ለመወጣት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ደንበኛ አይከበርም፣ አዛዥና ታዛዥ አይታወቅም፣ ድለላ የባንኩ መደበኛ የአሠራር አካል ከመሆኑም በላይ ከደንበኛ እጅ መንሻ መቀበል ማስቀጣቱ ቢቀር ነውር መሆኑ ተዘንግቷል፡፡

  ከወራት በፊት አዲስ የተመረጠው ቦርድና ባለአክሲዮኖች የብድር አሰጣጥ ሥርዓቱን መፈተሸ አለበት በማለታቸው፣ ከዚህ ቀደም እንደ ልቡ ብድር ሲረጭ የነበረው አመራር ተፅዕኖ እየተደረገብኝ ነው በሚል ከሥራ እለቃለሁ ማለቱ ባንኩ ምን ያህል ሥርዓተ አልበኝነት ዓይን ባወጣ ደረጃ እንደተንሰራፋ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በቀጣዩ አወቃቀር በኔትወርክ የተሳሰሩት የብድር ደንበኞች አገልግሎት ማኔጀሮች በሠራተኛውና በደንበኛው በስፋት አቤትና እግዚኦ እየተባለባቸው ቢሆንም (መልስ ባይሰጥበትም፣ ሃሜቱ በገሃድ በባለ አክሲዮኖች ስብሰባ ላይ በከፍተኛ ባለአክሲዮኖች በተደጋጋሚ ተነስቷል፣ ዛሬም ለሹመት መዳረግ ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል፡፡

   በተለይ ከፍተኛ ስሞታ የሚሰማባቸው የቀድሞው የባንኩ የብድር መምርያ ኃላፊ ከጥቂት አሥር ሺዎች የማያልፍ ደመወዝተኛ ሆነው ሳለ በጥቅም ከተሳሰሯቸው ደንበኞችና ያለአግባብ ብድር ሲያመቻቹላቸው ከነበሩ ግለሰቦች (በተለይ ከፕሪ ሺፕመንት ጋር በተያያዘ ከ500 ሚለዮን ብር በላይ የተሰጡ ብድሮች እስካሁን በአግባቡ ተከፍለው ያልተጠናቀቁ ብድሮች ናቸው) ሕገወጥ ሥራቸው ባሳደረው ተፅዕኖ ከሥራ መልቀቃቸውን እንደ ሰበብ በመውሰድ፣ በማካካሻነት  ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ተሸከርካሪ ሸልመዋቸዋል፡፡ እስከ ዛሬ በባንኩ ታሪክ በብድርና በውጭ ምንዛሪ ላይ ከፍኛውን የመወሰን አቅም የነበራቸው ቀደምት የባንኩ ፕሬዚዳንቶችም ሆኑ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ይኼንን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጣ ዘመናዊ ተሸከርካሪ አይደለም ለመሸለም በአግባቡ ለመሸኘት አልበቁም፡፡ ከዚህ ምልከታ ተነስተን የሦስት ሚሊዮን ብር የተሸከርካሪ ሽልማትን ጉዳይ ስናጤነው ተሸላሚው ለሽልማት የበቁት ሥራን በኃላፊነት መንፈስና በአግባቡ፣ ከሙስና በፀዳ መንገድ በማከናወናቸው እንዳልሆነ ለመገመት ሳይንቲስት መሆን አያስፈልግም፡፡  

        የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ቀድሞውንም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ ሲታማ የነበረው እንደዚህ ዓይነት ፈር የለቀቀ የሥራና የደንበኛ ግንኙነት መንስዔው ምን እንደሆነ ለመረዳት አለመሞከራቸው ሳያንሳቸው፣ የድግሱ ተሳታፊ መሆናቸውና በዚህ ደረጃ አግባብ የሌለው ግንኙነት የፈጠረውን ችግር መሠረት አድርገው ባንኩ ያለበትን ሁኔታ መመርመር አለመፈለጋቸው አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከተሸላሚው ሥር የነበሩትንና ከፍተኛ ስሞታ የሚቀርብባቸውን ኃላፊዎች እንደገና መሾም ለምን እንዳስፈለገ የባንኩ መነጋገሪያ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ባንኩ ጤናማ በነበረበት ዘመን ባንኩን የመሩት ሦስተኛው ፕሬዚዳንት አንድ ቅርንጫፍ ላይ የሚሠሩ ሠራተኛ በዚሁ መንገድ በተፈጠረ የሥራና የደንበኛ ግንኙነት ተጠርጥረው ከፍተኛ ማጣራት እንደተደረገባቸው፣ በባንኩ ሠራተኞ ዘንድ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ዛሬ እንደዚህ ዓይነቱ ሙስናን መጠየፍ፣ ለፍትሕ መቆም፣ ለሕግ የበላይነት መትጋት ወዴት ደረሰ? ዛሬም አዲሱ ቦርድና የባንኩ ባለቤቶች ሊመልሱት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም በደሃው ሕዝብ ሀብት ጭምር እየሠሩ እንደመሆኑ መጠን፣ ተጠያቂነታቸው በዚያው ልክ መሆን እንዳለበት መዘንጋት አይገባም፡፡  

        ሌላው ቢቀር ፈር የሳተ ወገንተኝነት፣ ቡድንተኝነት፣ አድመኝነትና ጥቅመኝነት በሃይማኖታችንም ቢሆን መልካም የሥራ ግንኙነት ለመፍጠርም ሆነ ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ጠንቅ የሆኑ ፀያፍ ድርጊቶች ስለመሆናቸው መግባባት አለ፡፡ ቡድንተኝነትና አድመኝነት በሥራ ላይ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ መንገዱን በመሳት በሠራተኛው ዘንድ ተስፋ መቁረጥን ያስፋፋል፡፡ በትጋት፣ በሥራና  በውጤት ከማመን ይልቅ ብልሹ አሠራር ለሚፈለፍላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ ቡድኖች በመንበርከክና ወሬ በማቀባበል ዕድገትን መሻት ባህል ሆኖ እንደሚነግስ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ በሚዘዋወርባቸው እንደ ባንክ ባሉ ተቋማት ውስጥ ቡድንተኝነትና ቲፎዞ ሲሰፍን ሙስናን፣ ሥርዓተ አልበኝነትንና ጥቅመኝነትን እንደሚያስፋፋ በመረዳት ከፍተኛ ኃላፊዎች ለችግሩ መፍትሔ መስጠት አለመቻላቸው የቡድንተኝነት ሥጋት በመፍራት ወይም መጠቀሚያ ለማድረግ በማቀድ ራሳቸው አመራሮቹ ጭምር የቡድኖቹ ሰለባ ሆነዋል፡፡

        ሌላው የሚጠቀሰው ጉዳይ ባንኩ በማኔጅመንቱ አማካይነት ለሥራ ቀናና አመቺ የሆነ ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ የሥራ ድባብ መፍጠር የሚያስችል አቅምና ብቃት ማዳበር ባለመቻሉ ምክንያት፣ ሥራውን እያስፈጸመ ያለውና የሚፈልገውን የሚያስወስነው በቡድንተኝነት አደረጃጀት ውስጥ የሚገኘው ኃይል ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አመራሩ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ሕግ፣ መመርያና ደንብን የተከተሉ ባለመሆናቸው ውሳኔዎቹ የባንኩን ውጤት በተገቢው ደረጃ ከማሻሻል ይልቅ ሠራተኛው በእምቢተኝነት እንዲፈረጥም አድርገውታል፡፡ ማኔጅመንቱ የተፈጠረውን ክፍተት መርምሮ በብድር አሰጣጥ፣ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት፣ እንዲሁም በዕድገትና ዝውውር ላይ ያለውን ኢፍትሐዊ አሠራር በሕጋዊ የአሠራር ሥርዓቱ በመተካት ማስተካከያ ከማድረግ ይልቅ፣ ችግሩንና ተፅዕኖውን ቁልቁል ወደ ሠራተኛው በማውረድ በማስፈራራትና በዛቻ ለመቀልበስ መሞከሩ ይበልጥ ውጤት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ ውጤት ሲጠፋ ደግሞ ሠራተኛውን ወደ ማሸማቀቅ መገባቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሠራተኛው ላይ የተፈጠረው ያልተገባ ጫና የባንኩን ውጤት አዎንታዊ ሆኖ እንዲሻሻል አልረዳም፡፡ ይልቁንም በተቃራኒው በሠራተኛውም ዘንድ የተጠናከረ ውስጣዊ ቸልተኛነትና እምቢተኝነት እንዲነግሥ አድርጓል፡፡

         ዛሬም በጥቂት ውጫዊና ውስጣዊ አካላት ተፅዕኖ፣ ፍላጎትና አምሳያ በውኃ ልክ ተለክተው የተመደቡት የብድር ኃላፊዎች፣ የብድር መኰንኖችና የውጭ ምንዛሪ አከፋፋዮች በየደረጃቸው ቁልቁል መዋቅራቸውን ተከትለው የራሳቸውን አምሳያ በመትከሉ ሒደት ‹‹ሥራቸውን›› በተሳካ መንገድ በመወጣታቸው፣ የባንኩ ሠራተኞች ከላይ በግል ፍላጎታቸው በተጠመዱ የቦርድ አመራሮች ከታች ይኼንኑ ለማስፈጸም በሚተጋ፣ በቀሪው የባንኩ ሪሶርስ ላይ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የራሱንና ከሥር የኮለኮሏቸውን አስፈጻሚዎች የግል ጥቅም ለማጋራት በሚተጉ ኃላፊዎች መሀል የገና ዳቦ መሆኑ ሊገታ ያልቻለ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡     

          ከዚህ ቀደም ባንኩ በተለይ ይታወቅበት የነበረው የብሔራዊ ባንክ መመርያዎችንና ሕጋዊ አሠራሮችን ያለማዛነፍ በማስፈጸም፣ ጥብቅ የክትትልና የአፈጻጸም ሥርዓትንና አሠራርን በማስፈን፣ ጉቦኝነትን፣ ጥቅመኝነት፣ አድሏዊነትን፣ የአሠራር ጥራትና ብልሹነት አልፎ ተርፎም እበላ ባይነትና ጥቅመኝነት እንዳይሰፍን በፅኑ የታገለ ባንክ የነበረበት ምዕራፍ ተዘግቶ፣ ደንበኞችን ከማገልገል ይልቅ በቅድሚያ የጥቂት ቦርዱ አመራሮችንና የግል ወኪሎቻቸውን ፍላጎት ማሟላት፣ ቀጥሎ ደግሞ በተከፈተው ሕገወጥ በር በመሹለክ ተሿሚዎች ራሳቸውን ማበልፀግ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ውሎ ነው፡፡ በቅርብ የተካሄደው ሹም ሽረትም ይኼንኑ ይፈታል ተብሎ ቢጠበቅም፣ አሳዛኝ በሆነ ደረጃ በሙስና ተግባራቸው ደንበኛ ከፍተኛ ሮሮ የሚያሰማባቸው፣ ራሳቸውን በዚህ ሒደት ማበልፀግ በመቻላቸው በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አሜሪካና ካናዳ ለመዝናናት የበቁ፣ ቤተሰባቸውን በግማሽ ሚሊዮን ብር የማሳከም አቅም የፈጠሩ ሆነዋል፡፡ ሌላው ቢቀር ምንጩ ያልታወቀ ሀብትና ግብር ያልተከፈለበት ገንዘብ ለክስ የሚያበቃ መሆኑን፣ በተለይ ደግሞ በሕዝብ ሀብት ላይ ተንተርሶ የተፈጠረ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ለጥያቄ እንደሚጋብዝ ለመረዳት አለመቻሉ ሌላው አስደናቂ ጉዳይ ነው፡፡

        ከላይ እንደተገለጸው ባንኩ ውስጥ እንደ ወረርሽኝ እየተስፋፋና እየተለመደ የመጣው አስተማማኝ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ ከሙስና ነፃ የሆኑና ኃላፊነት የሚሰማቸውን ሠራተኞችን በተገቢው ቦታ ላይ በመሾም ሥራን በጥራትና በቅልጥፍና በማከናወን፣ ባንኩ የራሱንና የአስቀማጩን ሀብት መከላከልና ማሳደግ እንዳይችል በኔትወርክ መተብትቡንና ለከፍተኛና አላስፈላጊ ለሆነ ወጪ እየተደረገ መሆኑን ከማረም ይልቅ፣ ተጠያቂነትን በመድፈቅ አቅመ ደካሞችን በኔትወርክ በማቆላለፍ ጥቅመኝነትን ማራመድ መገለጫው መሆኑ ነው፡፡

        ዝንባሌው ምን ያህል ሥር የሰደደ መሆኑን ተጨማሪ መረጃ በማቅረብ እንመልከተው፡፡  ባንኩ በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ለወጪ ከተዳረገባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ከሥልጠና ጋር የተያያዘ ኪሳራ ነው፡፡ ባንኩ በብሔራዊ ባንክ በተመደበለት ለሠራተኛው ሥልጠና የመስጠት ግዴታ መሠረት ሥልጠናውን በወቅቱ ባለመስጠቱ ምክንያት፣ ሊወረስበት የነበረውን አሥራ አንድ ሚሊዮን ብር በልመናና በእግዚኦታ የተመለሰለት መሆኑ አንዱ ተጠቃሽ ጉዳይ ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪ የፈሰሰባቸውና ባንኩ በተለያዩ ጊዜያት በሙከራ መልክ ያስተዋወቃቸው ዛሬ የት እንደደረሱ የማይታወቁ የመዋቅር ለውጥ ጥናቶች፣ ባንኩን ለማዘመን በሚል አዲስ አመራር በመጣ ቁጥር የሚጠኑና ሳይተገበሩ የሚቀሩ የሞባይል ባንኪንግ፣ የኢንተርኔት ባንኪንግና የመሳሰሉት ፕሮጀክቶች እነዚሁኑ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ሲባል ለሚገዙት ሶፍትዌሮችና ሃርድዌሮች የሚወጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሮች ሌሎቹ ናቸው፡፡ በቅርቡ ከከፍተኛ ውዝግብ በኋላ በጨረታ ያሸነፈው ድርጅት ተሰርዞ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ ታክሎበት ግዥ እንዲፈጸምበት የተደረገው ሰርቨር ሌላው ባንኩ ባለቤት ያጣ መሆኑን ማሳያና መገለጫ ነው፡፡

        ከመዋቅር ለውጥ ጋር በተያያዘ  በገፍ የሚገዙ የቢሮ ዕቃዎች የትም ባክነው መቅረት፣ ከዚህ መዋቅራዊ ለውጥ ጋር የሚካሄዱ ውስጣዊ ወጪዎች፣ በቅርብ የተካሄደው የመወቅር ጥናት ውጤት ያምጣ አያምጣ ሳይታወቅና በቂ ጊዜ ሳይሰጠው እንደገና በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ ተደርጎ አዲስ የመዋቅር ጥናት መደረጉና ያንን ተከትሎም ባንኩ ካለው የመሸከም አቅም በላይ የተለጠጠና መጠነ ሰፊ መዋቅር መዘርጋት፣ ይኼንንም ተከትሎ ግልጽ በሆነ የመጠቃቀምና የቡድንተኝነት መንፈስ መሥራት፣ በሙስና የሚታሙ ግለሰቦችን ወደ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪነት ማሳደግ፣ የብድር ኃላፊው ከሥራ ለመልቀቅ ያስገደዳቸው የተቀናጀ የሙስና ተጠርጣሪነት ክስ በአግባቡ ሳይፈተሽና ብድሮቹ ያሉበት ሁኔታ ሳይረጋገጥ መልቀቂያ መስጠት፣ ከላይ ለተጠቀሰውና ባንኩን ለከፍተኛ ወጪ ሊዳርጉት የነበሩ የሥልጠና ኃላፊን ጨምሮ ሌሎችም በአቅም ማነስ መጠየቅ የነበረባቸውን ሠራተኞች ወደ ከፍተኛ ኃላፊነት ማሳደግ ያገኙበታል፡፡

        የኃላፊነት መንፈስ ለመዳከሙ በዋነኛ ምክንያትንት ከሚነሱት ውስጥ አንዱ፣ በሙስና የሚጠረጠሩ ሠራተኞች ጉዳይ በጠንካራ የቦርድና የኔትወርክ ደጋፊ ጉዳያቸው ‹የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ› ይሆናል እየተባለ ዕድገት እንጂ ክስና ወቀሳ የማይመለከታቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከላይ ለተዘረዘሩትና ባንኩ ላይ ለደረሱት ቁሳዊ ጉዳቶች እስካሁ ድረስ ተጠያቂነትንም ሆነ ኃላፊነትን የወሰደ አንድም ኃላፊና ግለሰብ አለመኖሩ፣ እንዲያውም ለተመሳሳይ ድርጊት እንዲዘጋጁ የተፈለጉ ይመስል በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ሠራተኞች ለሹመት መብቃታቸውና አንዳንዶቹም ቃል ተገብቶላቸው ተራቸውን እየጠበቁ መሆኑን መሰማቱ ነው፡፡ በጥቅሉ ባንኩ የተዘፈቀበት የመደንዘዝ፣ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት አለመቻልና አቅም የማጣት ችግር ያስከተለው መዘዝ ምን ያህል ሥር የሰደደ መሆኑን ለማስረዳት በሽታው ወደ ማኔጅመንቱ ተዛምቶ ቀጥሎም ወደ ሠራተኛው  እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያሳዩ መገለጫዎች እንደ ማጠቃለያ አነሳለሁ፡፡ የባንኩ የባለቤትነት ጉዳይ ውስብስብ በመሆኑና የባንኩ ‹ማይኖሪቲ› ባለአክስዮኖችም ሆኑ የተወሰኑ ‹ማጆሪቲ› ባለአክሲዮኖች ሀብቱን ያገኙት በይሁንታና በችሮታ በመሆኑ፣ ዋነኛዎቹም ባለቤቶች ትልቁን ድርሻ ያስያዙት በወኪል  ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባለቤቶቹ ከእውነታው እንዲርቁ አድርጓቸዋል፡፡ በይሁንታ የመጡትም ባንኩን ሥርዓት ባለው መንገድ በአቅምና በብቃት እየታገዙ ለመምራት የሚያስችል ተነሳሽነትም ሆነ ባለቤትነት እንዳይኖራቸውም አድርጓል፡፡

        ይበልጥ ጉዳዩን አስቸጋሪና ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ አዲስ ዕውቀትም ሆነ ሙያዊ ችሎታ ወይም የባለቤትነት መንፈስ ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ከውጭ ወደ ባንኩ እንዳይቀላቀል፣ የባንኩ አክሲዮን በግብይይት ሥርዓትና በክፍት ጨረታ የማይሸጥና የማያይለወጥ ዝግ ባንኩ መሆኑ ነው፡፡ በአቅምም ሆነ በችሎታ ወይም ከተነሳሽነት አኳያ የባንኩን ዕጣ ፈንታ መወሰን የወደቀው በከፍተኛ ባለአክሲዮኖች በተመረጡት ግለሰቦች ሰብዕና ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባንኩ ዙርያውን በማነቆዎችና በጥቅም የታጠረና የተጨነቀ እንዲሆን አደርጎታል፡፡

        ይህ የአቅም ማነስ፣ ለሕግና ለሥርዓት ቦታ አለመስጠት፣ ዘለግ ሲልም በጉዳዮች ላይ በቂ ቅድመ ዝግጅት አለማድረግን የመሳሰሉ መሠረታዊ ችግሮች ወደ ባንኩ አሠራርና አደረጃጃት እየሰረጉ በመግባታቸው ምክንያት የሠራተኛው አሿሿም ይኼንኑ መስመር ለመከተል ተገዷል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው የባንኩ ውስጥ ከፍተኛ አመራሮቹ በሁለት መሠረታዊ ማጠንጠኛዎች ላይ ተመሥርተው የሚሾሙ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ አንደኛው አንድን ከፍተኛ ድርሻ በውክልና የያዙ የቦርድ አባላት የብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ለመቆጣጠር ሲሉ ለራሳቸውና ለዘመዶቻቸው ብድርና የውጭ ምንዛሪ ያለማንገራገር ሊሰጧቸው የሚችሉ የአገር ልጆች፣ ዘመዶች፣ ወይም ታማኞችን ማሳደግ ወይም ከውጭ ማምጣት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ፀጥ ለጥ ብለው እጅ ነስተው የሚገዙትን ሠራተኞ በኔትወርክ እንዲታቀፉ በማድረግ፣ በተለይ ጥቅም ወደሚገኝባቸው ቦታዎች ማሳደግ ነው፡፡ ብቃት፣ አቅም ችሎታና ተነሳሽነት ትርጉም የሌላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

        ደጅ መጥናት፣ ወሬ ማቀበልና ትዕዛዝ እንዲወርድ ማድረግ ለሹመት ለመታጨት በቂ ምክንያት ነው፡፡ ይህ አመለካከት ደግሞ እስከ ታችኛው የባንኩ መዋቅር ድረስ በመውረድ ሠራተኛውን  እየከፋፈለና አሳዛኝ በሆነ የሞራል ውድቀት ላይ ባንኩን እየጣለው ይገኛል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ቀሪዎቹ የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተሸናፊነታቸውን በመቀበል ለባንኩ ጤናማነት ከመሥራት ይልቅ፣ ጥቅሙ ለምን ቀረብኝ ከሚል ግለኝነት በመነሳት የራሳቸውን ቡድኖች በትይዩ በማደራጀት የሚፈጥሩት ግብ ግብ ባንኩ የሥራ ቦታ ሳይሆን የማያልቅ ጦርነት አውድማ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

        የዚህ ሁሉ ግብግብ ውጤት በአንድ በኩል በቡድንተኝነት ተደራጅቶ ሀብት መቀራመቱን ማጧጧፍ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚያ የተረፈውን ሀብት በጥቅም ተጋሪነት በመመሳጠር የባንኩን ተቀማጭም ሆነ የውጭ ምንዛሪ የባንኩ ዕድገትና ቀጣይነት ለማያረጋግጡ ነጋዴዎች፣ አምራቾች፣ ኢንቨስተሮች በማበደር የራስን፣ የቤተሰብንና የአገር ልጅን ጥቅም ማደራጀት ነው፡፡ ባንኩ ለገበያው በሚመጥን ደረጃ ዕድገት ማሳየትና አስተማማኝ ደንቦችን ይዞ ለመቆየት እንዳይችል ያደረገው አንዱ ውስብስብ ችግርም ይኼው ነው፡፡ ከጥቅም ጋር በተሳሰረ የሚሰጡት ብድሮችም ሆኑ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱ የግል ጥቅምን እንጂ የባንኩን ጥቅም የማያረጋግጡ በመሆናቸው፣ የባንኩ የብድር አሰጣጥም ሆነ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሥርዓተ አልበኝነት የሰፈነበት እንዲሆን አድርገውታል፡፡     

        በመጨረሻ ላይ ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የተፈጠረ አንድ አሳዛኝ ድርጊት በምሳሌነት ላቅርብና ወቅቱን ጠብቆ በሰነድና በመረጃ ተጨማሪ ሐሳቦቼን ይዜ እስክመጣ ልሰናበት፡፡ ባንኩ የብድር አሰጣጥ ሥርዓቱን ለማዘመን በሚል ሰበብ የብድር ሥራን ሙሉ ለሙሉ በአንድ ግለሰብና በጣት ወደሚቆጠሩ ቡድኖች እንዲማከል በማድረጉ፣ የባንኩ ብድር ጥቂቶች እንዲያዙበትና እንዲናዙበት አድርጎታል፡፡ ይኼንን ችግር ደንበኞችም ሆኑ የባንኩ ሠራተኞች የተጠያቂነትን መንፈስ ያጠባል፣ ሙስናን ያስፋፋል፣ የዕዝ ሰንሰለት አሠራርን ይንዳል በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያሰሙም፣ በአዲሱ አወቃቀር በግድ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ እንደተፈራው ደካማ አሠራር እንዲሰፍን፣ ደንበኞች እንዲጉላሉ፣ ሙስና ሥር እንዲሰድና ኃላፊነት የጎደለው የብድር አሰጣጥ እንዲፋፋና የባንኩን መሠረታዊ ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲከናወን በር ከፍቷል፡፡ የባንኩ የከፍታ ጉዞም ተቀጭቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሽቆለቁልና ቦታውን ቀጥሎ በሚመጣው ባንክ እንዳይነጠቅ የሚታገል አድርጎታል፡፡

        ይህ ትልቅ የአገር ሀብት የሆነ ባንክ መፍትሔ የራቀው ጥቂት ቡድኖች ኔትወርክ ዘርግተው በጥቅም በመተሳሰር እጅ ጥምዘዛ ውስጥ በመግባታቸው፣ እነዚህን ተሿሚዎችና ቡድኖች መመከት እንዳይችል ሽባ መሆኑ ያሳደረው ፈተና ከባንኩ መሠረታዊ ችግር ይልቅ ግለሰቦች ላይ ያተኮረ ቂም በቀልን መፍትሔ ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡ ተጠያቂነት የሚጀምረው ከላይ ከቦርዱ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ አመራሩን ጨምሮ በተዋረድ ሁሉም ሠራተኛ ውጤት ለማምጣት ምን አማራጭ አቀረባችሁ? ምን መፍትሔስ ለገሳችሁ? ውጤት ላለመምጣቱ እንቅፋት የሆነው ጉዳይ የቱ ነው? የሚል ፍተሻ መፍትሔ ለጋሽ መሆን ይችል ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ባንኩን ተብትበው የያዙት ሙስናን በቁርጠኝነት መታገል አለመቻል፣ የባንኩን ጥቅም ትተው የግልና የቡድን ጥቅማቸውን በማሳደድ ማነቆ የሆኑትን፣ ለመመርያ፣ ለፖሊሲና ለሕግ እንዲገዙ በማድረግ ሥርዓት ከማስፈን ይልቅ በሠራተኛው፣ በደንበኛውና ተቆርቋሪ በሆኑ ዘንድ የሚታሙ ሠራተኞችን አናት በአናት ሹመት መስጠትና በተቃራኒው ደግሞ ሠራተኛው አንድም ዕርምጃ ለመራመድ በማያስችለው ሁኔታ ባንኩ ተተብትቦ እያለ፣ አስቀማጭና ተበዳሪ ኤክስፖርተር ውለድ በማለትና ማሸማቀቅ አንድም መፍትሔ መፈንጠቅ እንደማይችል መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እስካሁን ባንኩ የተጓዘበት ውጤት አልባ መንፏቀቅ እንዲቀጥል ከማድረግ ያለፈ የተሻለ ሁኔታን መፍጠር አያስችልም፡፡

        በየደረጃው ያለው ሠራተኛ የሚጠበቅበትን እንዲሠራና ውጤት እንዲያሳይ ለማድረግ ከተፈለገ መሆን የሚገባው በሙስና የሚታሙትንና የሚጠረጠሩትን በማሳደግ፣ ወይም ባንኩ በፈጠረው የአሠራር ውጥንቅጥና ደካማ አወቃቀር ውጤት ሊያሳኩ ያልቻሉ ሠራተኞችን ከኃላፊነት በማንሳትና ዝቅ በማድረግ ወይም አባርርሃለሁ በማለት ሊሆን አይችልም፡፡ ከበደ ተባሮ አበበ ቢመጣ ባንኩ ራሱን ካልለወጠ፣ ለሙስና ያለውን ዝንባሌ በቁርጠኝነት ካልፈተሸ፣ ለቡድንተኝነት የሚሰጠውን ትኩረት ካላጤነ፣ አሠራሩን ከኔትወርክ አውጥቶ ወደ መደበኛ አሠራር ካልለወጠ፣ የዛሬ ድርጊቱ ግማሽ ልጩ የትናንት ትልቅነቱ ግማሽ ጎፈሬ ከመሆን አያድነውም፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...