Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዴሞክራሲያችን ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል አውታረ መንግሥት ይሻል

ዴሞክራሲያችን ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል አውታረ መንግሥት ይሻል

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ላለፉት 11 ወራት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በፊት ከጎደለን፣ ኢትዮጵያን ካጎደሏት ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን ለማቋቋም አለመቻላችን መሆኑን፣ በተለይም በዚህ ጋዜጣ በዚህ ዓምድ ደግመን፣ ደጋግመን አውርተናል፣ ተናግረናል፣ ጽፈናል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ በተለይም ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፊት በነበሩት ጊዜያት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ጋር የማይወግን የለም፣ የኢትጵያን ሕዝብና የኢትዮጵያን ጠላቶች በአንድ ዓይን የሚያይ የለም በሚል ‹‹ብልጣ ብልጥ›› እና ‹‹ጮሌ›› ማወናበጃ ጭምር ጉዳዩ ተድበስብሶ የኖረው፣ ሌላው ቀርቶ ከዓብይ አህመድ ጋር ውድድር ገጥመው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበር፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ ለምርጫ ቀርበው በነበሩት በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ዓይነት ሰዎች ጭምር ነበር (ቅድመ ዓብይ በነበረው የ‹‹ፓርቲዎች ድርድር›› ዜናና ዘገባን ያስታውሷል)፡፡

ዛሬ ዕድሜ ለዓብይና ለሚመሩት ለውጥ እንጂ ለውጡ ገለልተኛና ቋሚ ተቋማትን እንገንባ የሚል መፈክር ይዞ መጥቷል፡፡ ከፓርቲ ታማኝነት የተላቀቁ አድርጎ መንግሥታዊና መብት ነክ ተቋማትን የማነፅ ቁርጠኝነት ማየት በራሱ ለውጥ ነው፡፡ መፈክር ከማንገብ በላይ መከላከያን፣ ደኅንነትን፣ ምርጫ ቦርድን፣ ወዘተ በዚህ ቅኝት የማዘመን ሥራ ውስጥ ሁሉ ተገብቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  የለውጥ መፈክር ቁርጠኝነትና መሃላ የለውጥ ኃይሎች የጋራ መግባቢያና መገናኛ ከሆነ፣ ቢያንስ ቢያንስ የማይደናቀፍ ከሆነ የተጀመረው ለውጥ ከመንግሥትና ከመንግሥት መሪዎች መሃላና ቁርጠኝነት ውጪና በተጨማሪ ዋስትና ያገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ዓብይ መከላከያን፣ ደኅንነትንና ፖሊስን፣ እንዲሁም (በዚህ ጉዳይ ላይ ንቅናቄውንና መፈክሩን እንደ ሌሎቹ ባናይም) ቢሮክራሲውን ማለትም ሲቪል ሰርቪሱን ከፓርቲ ፖለቲካ የፀዳና ቋሚ ማድረግ አለባቸው፡፡ አዲስ ነገርና ለውጥ፣ እንዲሁም መንግሥት በመጣ ቁጥር የማያበራዩት ቢሮክራሲ፣ የማይበተን የጦር ኃይልና የማይፈርስ ፖሊስ ሊኖረን ይገባል፡፡ እነዚህ ሦስት አካላት የአገር ከፍተኛ አስፈጻሚና አስተዳደራዊ የሥልጣን አካል ቋሚ ክፍሎች ናቸው፡፡ መሆን ስላለበትና በሕገ መንግሥቱ በተለይም በአንቀጽ 56 ስለተደነገገው መናገር ከተፈለገ፣ ጊዜያዊውና በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚተካካውና የሚለዋወጠው ፖለቲካዊው አስፈጻሚ አካል ብቻ ነው፡፡ የአገራችን ችግርና በሽታ ሆኖ የቆየው መሆን ያለበትንና በሕግ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕገ መንግሥት የተደነገገውን እንዳይሆን የሚያደርጉ ችግሮችን መለየትና ችግርነታቸውን፣ ችግር መሆናቸውን ለማስወገድ የሚከናወኑ ተግባራትን ዘርዝሮ መወሰንና ማስቀመጥ፣ እንዲሁም ሒደቱን መጀመር አለመቻል ነበር፡፡ የተቃውሞ ግርግርና ሴራ ካላደናቀፈው፣ በለውጥ ደጋፊዎች ውስጥ ያለ ቅደም ተከተል የማምታታት፣ ‹ሱሪ በአንገት አውጡ› እያሉ ማዋከብና እንዲያ እንዲያ እያሉ ከተቃውሞው ጋር ማበር ካላጨናገፈው በቀር፣ ዛሬ ዓብይ አህመድ ዴሞክራሲን ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ላይ እንገንባ እያሉ እየጮኹ ነው፡፡ ጩኸታቸውንም የመንግሥታቸው ፖሊሲ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ቀን ሲከበር የሰማነውም ይህንኑ ነው፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን በተለይም የለውጥ ኃይሎች የጠያቂነትና የአጋዥነት ሚና መጠናከሩ፣ ይህንን እንቢ ብሎ ከቆየው ከኢሕአዴግ ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣውን ዓብይ የሚመራውን አመራር ያግዛል፣ ያበረታታል፡፡ ወገቤንም ሲል ይጠይቃል፣ ያሳጣል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 የሕገ መንግሥቱን የበላይነት ይደነግጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም ይላል፡፡ ማናቸውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው ሲል ይደነግጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነውም ይላል፡፡ ሥልጣን ይዞ መቆየትም የተከለከለ ነው ማለት ጭምር ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱን ‹‹የማስከበር›› እና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነትና ግዴታ ካለባቸው መካከል የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ክፍል ናቸው፡፡ ሕጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ከፖለቲካና ከሕግ ሌላ ኃይል የላቸውም፡፡ ሕግን ቢደፍሩና ድንገትና እንደ አጋጣሚ (አሁን ከውጭ የመጡት አንዳንዶቹ እናድርግ እንዳሉት) በጉልበት እንጠቀማለን፣ ከዚያም አልፎ በጉልበት ሥልጣን እንይዛለን ለማለት ቢሞክሩ የሕግና የፀጥታው አካል ይቆነጥጣቸዋል፣ ይገታቸዋል፡፡ በዚህ በሽግግር ወቅት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የአንዳንዶቹ ጉዳይ ሲያስቸግር የታየበት ምክንያት ‹‹ሽግግር›› በመሆኑ ነው፡፡ ለውጡ ግለቱንና እንድርድሪቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ተብሎ የተደረገ ልዩ ጥንቃቄና ሆደ ሰፊነት፣ ወዘተ ነው፡፡    

ችግር የሚሆነው በሥልጣን ላይ የሚገኘው ፓርቲ ሕግን ልተላለፍ ቢል በሕግ መከላከል የሚያስችል ፍጥርጥር አለን? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው፡፡ በአገራችን አሁንም ድረስ የመንግሥት ዓምድ (State) እና የመስተዳደር ልዩነት በወጉና በደንቡ መሠረት ተፈልቅቆ አለመውጣቱ የችግራችን ሁሉ መነሻ ሆኗል፡፡ መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄም ይኼኛው ነው፡፡ ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን እንገንባ የሚሉ የለውጥ ኃይሎች በአንድ ልብ አንድ ላይ መግጠምና መረባረብ ያለባቸውም በዚህ ላይ ነው፡፡

በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ የትኛውም ፓርቲ ሥልጣን ቢይዝ ከአውታረ መንግሥቱ ጋር ልዩ ትስስር በማበጀትና ባለማበጀት ተብሎ፣ ወይም በዚህ ምክንያት ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ ለምሳሌ የዴሞክራቲክና የሪፐብሊካን ፓርቲዎችን ብንወስድ፣ ሁለቱም በሕግና በምርጫ ወጪና ወራጅ በመሆን ረገድ አይበላለጡም፡፡ በኢትዮጵያ ችግር ሆኖ የኖረው ከመቶ በመቶ የምርጫ አሸናፊነትና ውጤት በኋላ በማግሥቱ ለፈነዳው አገር ያንቀጠቀጠ አመፅ ምክንያት የሆነው፣ የሥርዓት አተካከላችን ገዥውን ፓርቲ በዚህ ዓይነት መመዘኛ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እኩል አድርጎ ማነፀፃር የሚያስችል ባለመሆኑ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ነው በኢሕአዴግ እጅ በአመፃዊ ትግልም ሆነ በምርጫ አሸናፊነት የወደቀ መንግሥት፣ በአንድ ጊዜ መስተዳድር ብቻ ሳይሆን ዓምደ መንግሥት ጭምር (State) የሚሆነው፡፡ ገለልተኛና ቋሚ በሆኑ ተቋማት ላይ በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚለዋወጥ የመንግሥት ሥርዓት እናቋቁማለን ስንል፣ ከሥር ከመሠረቱና በውል መረዳት ያለብን ይህንን ችግራችንን ነው፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለማይከሰስና ከሰማይ ለተሰጠ ፍፁማዊ ገዥነት መሣሪያ ያደረጉትን አውታረ መንግሥት ገነቡ፡፡ ደርግም የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ተመላኪነትና ተቆጣጣሪነትን በኢሠፓ መረቡ አማካይነት በመላው ኅብረተሰብ ላይ አዋቀረ፡፡ ኢሕአዴግ ሲመጣም አውታረ መንግሥትን በግልና በፓርቲ አምሳል የመቅረፅ ታሪክን ማስቆምና ማቋረጥ አሻፈረኝ አለ፡፡ ሥልጣን እንደያዘ፣ የቅልበሳ አደጋ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ጭምር የነበረውን የአገዛዝ (ማለትም የደኅንነትና የጦር አውታር) አፍርሶ የራሱን ታጋዮች አከርካሪው ያደረገ የሠራዊትና የተቋም ግንባታ አካሄደ፡፡ ከፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ የአገዛዝ አውታር ግንባታን ተጨባጭነት ፉርሽ ያደረገው ይኼው ጅምሩ፣ አካሄዱና ሙያዬ ብሎ ይዞት የነጎደበት ሥራ ነው፡፡

በአጠቃላይ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አንስቶ እስከ ዛሬም ድረስ በገዥው ክፍልና በሥልጣን ማስከበሪያው የታጠቀ ኃይል ትስስር ላይ የቆመ ሆኖ ኖሯል፡፡ የመንግሥትም የደፋ ቀና ጉዞ ከታጠቀ ኃይልና ከተመላኪነት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በወታደራዊ ግልበጣ የተወገደው የታጠቀውን ኃይል መቆጣጠር ሲሳነውና የንጉሡም ተመላኪነት ሲቦተረፍ ነበር፡፡ ወታደሩንና ሕዝቡን በተለያዩ መንገዶችና መሣሪያዎች አፍዝዞ የአንድ ሰው ተመላኪነትና አምባገነንነት ሆኖ ያደገውና ያረፈው ደርግም፣ ብሎ ብሎ የወደቀው በአመለካከቱ የቀረፀውን የወታደርና የደኅንነት ኃይል ታማኙ አድርጎ ማንቀሳቀስ ሲሳነው ነው፡፡ ደርግን የተካው ሕወሓት/ኢሕአዴግም ከተከታታይ መንግሥታት ጋር አንድና ተመሳሳይ ያደረገው፣ የደርግን ሠራዊትና የደኅንነት መረብ አፍርሶ የራሱን በሠራዊት ላይ የተማከለ የሥልጣን ማስከበሪያ አውታር በማቋቋሙ ነው፡፡

ችግሩ የሥራ አስፈጻሚ አካል፣ የመስተዳድሩ ማለትም በሕግ የአገሪቱ ከፍተኛ አስፈጻሚና አስተዳደራዊ የሥልጣን አካል የሚባለው አካላት የሆኑት የቋሚዎቹ የቢሮክራሲው፣ የፖሊሱ፣ የወታደሩና የደኅንነቱ ጭምር ነው፡፡ የመከላከያ አዋጅ (ነባሩም አዲሱም) ተቋሙ ከፖለቲካ ድርጅት ወገናዊነት ነፃ በሆነ ሁኔታ ተግባሩን የሚያከናውን ሆኖ መደራጀት አለበት ይላል፡፡ የምርጫ ሕጉም በምርጫ የሚወዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞችን መብት ሲደነግግ፣ የመንግሥት ሠራተኛ በግሉ ወይም የፖለቲካ ድርጅት አባል ሆኖ ለምርጫ መወዳደር እንደሚችል ይወስናል፡፡ ዳኛ፣ ወታደር ወይም ፖሊስ ግን በራሱ ወይም በፖለቲካ ድርጅት አማካይነት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ከቀረበ የያዘውን የመንግሥት ሥራ መልቀቅ እንዳበት፣ እንዲሁም ማንኛውም ወታደር ወይም ፖሊስ በፖለቲካ ድርጅት ስብሰባ ወይም በምርጫ እንቅስቃሴ መለዮውን አድርጎ መሳተፍ እንደማይችል ይደነግጋል:፡ በተጨማሪም ዳኛ፣ ወታደርና ፖሊስ በምርጫ ውድድር ጊዜ ማንኛውንም ተወዳዳሪ ለማስመረጥ በመደገፍ፣ በመናገር፣ በመጻፍና በመሳሰሉት ተሳታፊ አይሆንም ይላል፡: በተጻፈ ሕግ ደረጃ የተጠቃቀሱትን የመሰለ (የተልኮሰኮሰም ቢሆን) የክልከላ ‹‹ወግ›› ያልጎበኘው የደኅንነቱ ክፍል ነው፡፡ ገና የሕግ ረቂቅ ሲዘጋጅለት ባናይም፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ግን ብዙ ብዙ ማሻሻያዎችን ነግረውናል፡፡ የመረጃና የደኅንነት አገልግሎቱን ኢፖለቲከኛነት የሚያረጋግጥ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ሌሎችን ተቋማት ከ‹‹ደባበሳቸው›› የተሻለና የላቀ ጠንካራ ክልከላ እንደሚኖር ገልጸውልናል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠላትነት ያልተጠማመዱ የወንበርና የሥልጣን ተፎካካሪዎች በሆኑበት፣ እንዲሁም የመንግሥት ሥራ ማካሄጃ ቋሚ አውታራትም በምርጫ አሸንፎ ለመጣ ለየትኛውም ቡድን ሙያተኞች ታዛዥ እንዲሆኑ ተደርገው በተቀረፁበትና በታነፁበት ሥፍራ የአንዱ ወይም የሌላው የፖለቲካ ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦች እዚህም እዚያም (በወታደሩ፣ በፖሊሱ፣ በዳኝነቱ የሥራ ገበታ ጭምር) መኖር ጉድለትም ጉዳትም አይደለም፡፡ የፖለቲካ ዝንባሌ የሥራ ኃላፊነትን ቢያፈርስና ቢጫን እንኳ ጥፋቱና ተጠያቂነቱ የግለሰቦች ጉዳይ ብቻ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ተቋማቱ ራሳቸው በአንድ አመለካከለትና ፖለቲካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ (በኢትዮጵያ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜና ሁልጊዜ በቀጥታ) የተጠረነፉ፣ የተሞሉና ያንኑ እንዲያገለግሉ የሚጠበቁና የሚጠየቁ ሲሆን ግን ነገሩ ሁሉ ይቀየራል፡፡ ችግሩ ከግለሰቦች ባለፈ ደረጃ ሥርዓታዊ ሆኖ የፖለቲካ አቋም የሥራ ኃላፊነትን ለመቃኘት ሥልጣን ያገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ ተዘፍቆ የኖረው እዚህ ዓይነት ሽምቀቃ፣ አፈና፣ ጫናና ብከላ ውስጥ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ነው እስካሁን በኖርንበት ሁኔታ ኢሕአዴግ በየአምስት ዓመት በምርጫ እያሸነፈ ወንበሩን የግድ የሚያፀና ቡድን/ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሚቀመጥበትን ወንበር ከእነ ካስማና ማገሩ፣ ሕዝቡን ከእነ አገሩ የገዛ ራሱ ንብረት አድርጎት የኖረው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሲወጣና ሥልጣኑንም በምርጫ እያደስኩ ለአምስት ጊዜ ተመረጥኩ ብሎ በሥልጣኑ ሲቀጥል፣ በምርጫ ከሚወርድና ከሚወጣ መንግሥትነት በላይ አልፎ ራሱን አውታረ መንግሥት (State) አድርጎ አረፈው፡፡

ኢሕአዴግ አውታረ መንግሥት ከመሆን አልፎ ተርፎ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላትም ውስጥ መረቡን ዘርግቶ፣ የሙያና የሕዝብ የሚባሉ ማኅበራት ውስጥም ዓይን፣ ጆሮና አንደበቱ ገብቶ መዋቅራቸውን ተብትቦ፣ ሌላው ቀርቶ በዓመት አንድ ጊዜ እንኳን በሠራተኛ ቀን ሠልፍ መውጣት እስኪጠፋ ድረስ የሕዝብ እንቅስቃሴን አኮማትሯል፡፡

ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠ ትዕዛዝ ለአንድ ወር የታገደው/የተከለከለው የሠልፍና ከቤት ውጪ የሚደረግ ስብሰባ እስከ 2008 ዓ.ም. እንደደነገጠ ኖሮ አፈር ልሶ የተነሳው፣ ከአሥራ አንድ ዓመታት አካባቢ በኋላ ነው፡፡ እንደ የፍትሕና የዳኝነት ሥርዓቱ ያለ ‹‹ልብ አውቃ›› ስለሌለ ደግሞ ነሐሴ 2 ቀን 1984 ዓ.ም. በልዩ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ለዚያውም የልዩ ዓቃቤ ሕጉን ጉዳይ ብቻ በሚመለከት ለስድስት ወራት የታገደው ‹ሀብየስ ኮርፐስ› መብት እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ለፍርድ ቤት የሚቀርብ የመብት ጥያቄ መሆኑ ቀርቷል፡፡

ይህንን በመሰለ ኢሕአዴጋዊ ባህር ውስጥ ተኖሮ ተቃዋሚዎችን አሸባሪዎች፣ ጠላቶቻችን. እንዲህና እንዲያ ናቸው የሚል ፖለቲካ የተሞላ ‹‹የፖሊሲ ሥልጠና›› እና ‹ኢንዶክትሪኔሽን› እየተዋጠ፣ ወታደሩም ዓቃቤ ሕጉም፣ ዳኝነትና ምርጫም ውኃው የማይነካቸው ደሴት መሆን የሚችሉት በምን አቅማቸው ነው?

ኢሕአዴግ እንዲህ ሆኖ የተቀመጠበትን ወንበር በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ እንደማይለቅ አድርጎ የአገሪቱን ፍጥርጥር እንደገና ከመቀያየሩም በላይ፣ በዚያ ሁኔታ ቀጥሎ የከፋ ሁኔታ ቢመጣ የዚያን ጊዜው ኢሕአዴግ የት ድረስ ሊሄድ እንደሚፈቅድና እንደሚችል የጠቆመ አንድ የምርጫ 97 ወቅት የቅስቀሳ ክርክር (እሰጥ አገባ) በምሳሌነት ላቅርብ፡፡ ተቃዋሚዎች በቀድሞ ሠራዊት አባላት ላይ የተፈጸመ በደልን እያነሱ ይቆጥራሉ፡፡ ኢሕአዴግም ‹‹ይችን ይወዳል!›› ይልና ተቃዋሚዎች ሠራዊት ሊበትኑ ነው ከሚል የውስጥ ቅስቀሳ አልፎ በይፋ መግለጫ የኢሕዴግን ሠራዊት ነባር የትግል ውለታ የሚቆጥር አስመስሎ፣ መከላከያ ሠራዊቱን በአመጣጥ በዕይታና በተልዕኮ ከኢሕአዴግ ጋር ያጣበቀ ቅስቀሳ ሲያካሂድ ተሰማ፡፡ ኢትዮጵያ መውጣት ያለባት ከዚህ የእከሌ ሠራዊት፣ የእንቶኔ ሰንደቅ ዓላማ፣ የዚህ ወይም የዚያ ሕገ መንግሥት ከሚል በተደጋጋሚ አገር ሲያጠፋ ከኖረ አሠራርና ሥልጣን አያያዝ ነው፡፡

ብዙ ሰዎች በተለይም አሁን በለውጡ ወቅት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 9 እየጠቀሰ ሕገ መንግሥት ይከበር ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር ማለት ከሁሉም በላይ ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን ሥልጣን መያዝ››፣ እንዲሁም ሥልጣን ይዞ መቆየት የተከለከለ ነው የሚለው ጭምር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለምሳሌ የመከላከያ ኃይልን ለመንግሥት ግልበጣ መገልገል መፈቀድ እንደሌለበት ሁሉ፣ ያለ እኔ ገዥነት ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት አደጋ ላይ ይወድቃል፣ እኔ የጀመርኩትንም ልማት ውኃ ይበላዋል በማለት የጨነቀው ገዥ ሥልጣን ላይ በግድ ለመቆየት የሚያካሂደውን ሕገወጥነትና አመፅ ጭምር መከላከልና መቋቋም ማለት ነው፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝቦችና በወጣቶች ትግልና በገዥው መንግሥት የድቆሳ መስተጋብር መካከል የተወለደው ለውጥ ኢሕአዴግን ወደ ኢሕአዴጎች ለዋውጦታል፡፡ በኢሕአዴጎች ውስጥ መገለባበጥና መሸጋሸግ አምጥቷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፎ በ2008 ዓ.ም. ሥልጣን እንደገና የያዘው ፓርቲ፣ ሁሉንም ወንበር ጠቅልሎ የመዘባነንና አድራጊ ፈጣሪ የመሆን ዕድሉን የዘጋና የአባል ድርጅቶችን ‹‹እኩያ››ነት እና ሚና ግልብጥብጡን ያወጣ ያልተጠበቀና ያልታወቀ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

በዚህ ሒደትና መገለባበጥ ውስጥ የግልበጣ አደጋ (የመፈንቅለ መንግሥት) ወይም ወታደራዊ የፀጥታ ኃይሉ ቢያንስ ለሁለት ተከፍሎ አገሪቱ በጦርነት ቀውስ ውስጥ ልተገባ የምትችልበት አደጋ፣ ምናልባት በጣም ሲበዛ ወለል ብሎ መታየቱ አልቀረም ነበር፡፡

የትኛው ነው ይበልጥ የመሆን ምናልባት ያለው እያልን ስንጨነቅ፣ ከሁለቱም ተርፈን ለጊዜው ላለንበት አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ለቀረው ለዓብይ አህመድ መንግሥት በረከት በቅተናል፡፡

አስፈሪውን አደጋ ያስቀረውንና ለዚህ እስካሁን ለስላሳ የለውጥ ጉዞ ዕድል የሰጠንን ምክንያት ውስጥ አዋቂዎች ቢነግሩን ጥሩ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ከአደጋው ተርፈናል ማለት ግን ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን የመገንባት ግዳጃችን ቀልሎልናል፡፡ እንዲህ ዓይነት መደላደል ከሌለ የምንፈልገውን ዴሞክራሲ እንገነባለን ማለት አይቻልም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...