Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በሚቀጥሉት አምስትና አሥር ዓመታት ምን መልክ መያዝ እንዳለበት የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት እየተደረገ ነው›› ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ወደ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ የመጀመርያ የሆነውን መግለጫ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው በሰጡት መግለጫ በዋናነት ትኩረት ያደረጉት የአገሪቱን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በተለይም ከወጪ ንግድ ገቢ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች ላይ ነው፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ግን አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያስቃኘም ነበር፡፡ በመግለጫው ላይ የተገኙት ሪፖርተርና ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡላቸው ሲሆን፣ እሳቸውም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ዳዊት ታዬ የብሔራዊ ባንክ ገዥው የቀረቡላቸውን ጥያቄዎችና የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

ጥያቄ፡- በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል? በኢኮኖሚው በኩል ምን ለውጥ አለ? የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችትስ?

ዶ/ር ይናገር፡- አጠቃላይ ኢኮኖሚውን በተመለከተ ከሰባትና ከስምንት ወራት በፊት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበርን፡፡ በውጭ ምንዛሪ ዓለም አቀፍ ክምችትችን በጣም ያሽቆለቆለበት ወቅት ነበር፡፡ ከሞላ ጎደል የውጭ ዕዳ ለመክፈል የተቸገርንበት ወቅት ነበር፡፡ በብዙ መለኪያዎች አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የዶ/ር ዓብይ አህመድ መምጣትና ከመጣው ለውጥ ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግሮች የሚባሉት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ የመሳሰሉት መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ፣ የወዳጅ አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸው ትንፋሽ አግኝቶ ሌሎችን የሪፎርም ሥራዎች ለማሰብ ትልቅ ዕገዛ አድርጎልናል፡፡ ስለዚህ ከኢኮኖሚው ለውጥ አኳያ ሲታይ በአሁኑ ጊዜ የውጭ ዕዳችንን በመክፈል ላይ ነን፡፡ በየዓመቱ መከፈል ያለበትን እየከፈልን ነው፡፡ በእርግጥ የሚዘገይ ሊኖር ይችላል፡፡ በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚፈልጉትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ባይቀርብም፣ በተቻለ አቅም ባለው መጠን ለማንቀሳቀስ አማራጮችን በማየት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለውጡን ስናይ ወደ ከፋ ችግር ይገባ የነበረ ወይም ለመግባት የተቃረበ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ነው የተደረገው፡፡ ይህንን በተለያዩ መለኪያዎች ማየት ይቻላል፡፡  በቂ ነው ባልልም ዓለም አቀፍ መጠባበቂያችን እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በዚህ ረገድ ከሰባትና ከስምንት ወራት በፊት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የውጭ ዕዳ የመክፈል አቅማችን በየጊዜው እየተጠናከረ ነው፡፡ ይኼ በዘላቂነት ትልቅ መፍትሔ የሚያገኘው፣ በተለይ የውጭ ንግዳችን መሻሻል ካሳየ ደግሞ ከዚህም በላይ የተሻለ ነገር ማየት እንችላለን፡፡

      ስለዚህ ከዚህ አኳያ ሲታይ ኢኮኖሚው መሻሻል ቢያሳይም፣ በአጠቃላይ ግን በዚህ ዓመት ዕድገቱ ምን ያህል ይሆናል ለሚለው፣ በእኛ በኩል በዓመቱ መጨረሻ ላይ ነው የሚታወቀው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ባለን ግምት ባለፈው ዓመት ከነበረው ተቀራራቢ ዕድገት ይመዘገባል፡፡ ይኼ ዕድገት በራሱ ትልቅ ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በዓለም አገሮች ከሚታየው የዕድገት መጠን አንፃር ሲታይም ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን ካለፈው ዓመት ዕድገት አኳያ ስናየው ከዚህ በላይ ማደግ ይችል የነበረ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ሊያድግ ይችል የነበረው ለምሳሌ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ቢቻል ነበር፡፡ አሥርና አሥራ አንድ በመቶ ማደግ ይችል ነበር፡፡ በተለይ ግብርናው በታሰበው ልክ ቢሄድ ኖሮ ዕድገቱ ከፍ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ከነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ እየወጣ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የምናየው ተስፋና መሻሻል በተጠናከረ ሁኔታ በወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ካልተመሠረተ፣ ተመልሰን ችግር ላይ የመውደቃችን ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ከስድስት ወራት በፊት ደጋግማችሁ እንደምትሰሙት በርካታ ኢንዱስትሪዎች በውጭ ምንዛሪ የሚገዛ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በስፋት ያነሳሉ፡፡ በቻልነው አቅም ባለው መጠን ለመደገፍ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ሆኖም እጥረቱ ስላለ እነሱ በሚፈልጉት መጠን እየደገፍናቸው አይደለም፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚታየው ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች መፈታት ያላባቸው በርካታ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ከመብራት፣ ከሰው ኃይል አቅም፣ ከምርታማነት፣ ከካፒታል ጋር የተያያዙና ሌሎችም አስተዳደራዊ ችግሮች ያሉባቸው አሉ፡፡ ውስጣዊ ችግሮች ያሉባቸው ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በሙሉ አቅም እየሠሩ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ የሚመጣው ለውጥ ለዘላቂ መፍትሔው ትልቅ መነሻ ሆኖ ስለሚያገለግል በዚህ ላይ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ጥያቄ፡- እርስዎ ወደ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ በፋይናንስ ዘርፉ ምን ዓይነት የለውጥ ሥራዎች ተከናውነዋል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ይናገር፡- ከሰባትና ስምንት ወር ወዲህ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እየተሠሩም ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ያለቁ ናቸው፣ አንዳንዶቹ ያላለቁ ናቸው፡፡ ገና በውይይት ላይ ያሉም አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ሬሚታንስን (ሐዋላ) በተመለከተ አንዱ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ አድርገን ስለምንጠቀም፣ ከዚህ የሚገኘውን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የተለያዩ ሕገወጥ የሐዋላ ሥራ እያከናወኑ ያሉ ሰዎች ስላሉ፣ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ በአገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ሙሉ  ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሐሳቡ አለ፡፡ በእኛ በኩል አጥንተናል፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚችሉበት ዕድል እንዲኖር አጥንተናል፡፡ በሚመለከታቸው ውይይት ተድርጎ ከፀደቀ በእኛ በኩል አንድ ትልቅ የለውጥ አካል ይሆናል የሚል እምነት አለ፡፡

      በሌላ በኩል ተንቀሳቃሽ ንብረትን እንደ ዋስትና ማስያዝና ዜጎች የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ አዋጅ ዝርዝር ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ ለገጠርም ለከተማም የሚሆን ነው፡፡ ተቀባይነት ያገኛል የሚል እምነት አለን፡፡ ይህ በዓይነቱ የተለየ ነው፡፡ ከብዙ ሚሊዮን ዜጎች ጋር የተቆራኘና የተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ለድህነት ቅነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህንን ነገር እኛ ለመጀመርያ ጊዜ የምንሞክረው አይደለም፡፡ ብዙ አገሮች ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ ብራዚል፣ ህንድና ሌሎችም አገሮች ሠርተውበታል፡፡ ከአፍሪካ ጋናና ናይጄሪያ የመሳሰሉት ተግባራዊ አድርገው ብዙ ርቀት ሄደውበታል፡፡ ከፋይናንስ ዘርፉ አኳያ እንዲህ ዓይነት የለውጥ ሒደትና አዳዲስ ሐሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ አዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦችን ይዘው ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች በገንዘብ እጥረት መሬት ማስነካት ላልቻሉ፣ ለእነሱ የሚሆኑ የአሠራር ሐሳቦች እየተጠኑ ነው፡፡ ነባር የብድር ሥርዓቱን በተመለከተ የብድር መጠን እየጨመረ ነው፡፡ ከተወሰኑት የመንግሥት ባንኮች በስተቀር ባንኮች የብድር መጠናቸው ጨምሯል፡፡ ይኼ የብድር መጠን መጨመር በኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባ ስለሆነ፣ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ሁከትና ግርግር ስለነበር፣ ብዙዎቹ ተበዳሪዎች መክፈል የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የብድር መክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ከየተበደሩባቸው ባንኮች ጋር እየተነጋገሩ የብድር መክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘምላቸው የማድረግ ዕርምጃ ወስደናል፡፡ ይህንን ስናደርግ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ ጠቃሚ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እነዚህ ተበዳሪዎች ሄደው ሄደው መክፈል ካልቻሉ፣ ለፋይናንስ ዘርፉም ለባንኮችም ሸክም ነው፣ ዕዳ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ለሁለቱም ጠቃሚ እንዲሆን እነዚህ ሰዎች ተጨማሪ ዕድል ተሰጥቷቸው ተጨማሪ የመክፈያ ጊዜ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር፣ ለሁሉም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ በኩል መመርያ ተዘጋጅቶ ተልኳል፡፡ ባለፉት ስድስትና ሰባት ወራት ውስጥ ሌሎችም ለአሠራር ማነቆ የሆኑ ከአሥር በላይ መመርያዎችን አሻሽለናል፡፡ ምንም ጠቀሜታ የሌላቸውና የቆዩ መመርያዎች ተሻሽለዋል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን የተሠሩት ሥራዎች እንዳሉ ሆነው፣ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉ ሦስትና አራት ረቂቅ አዋጆች አዘጋጅተናል፡፡ በሚመለከታቸው ታይተው ውይይት ከተደረገባቸውና ከፀደቁ በኋላ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

      ሌላው ባለፉት ወራት ከተከናወኑት ሥራዎች ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ የካፒታል ገበያ መፍጠር ይቻላል ወይስ አይቻልም በሚለው ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ ካፒታል ማርኬት በብዙ አገሮች ተግባራዊ የተደረገ ነው፡፡ በእኛም አገር እንዲህ ያሉ ገበያዎች ብናቋቁምና ብንከፍት ምን ጥቅም ይኖረዋል? ምን ጥቅም እናገኛለን? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት እየተጠና ነው፡፡ ጥናቱ አልቆ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ተደርጎ ከታመነበት ወደ ተግባር ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በሚቀጥሉት አምስትና አሥር ዓመታት ምን መልክ መያዝ እንዳለበት የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ በርካታ የሪፎርም ሐሳቦች ተካተውበታል፣ ይካተቱበታል፡፡

ጥያቄ፡- ለውጭ ኩባንያዎች ሰፕላይ ክሬዲትና ኤክስተርናል ሎን እየፈቀዳችሁ ነው፡፡ በአንፃሩ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ይህ ዕድል እየተሰጠ ባለመሆኑ አድልኦ ፈጥሯል እየተባላችሁ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን እየጎዳ በአሠራሩም ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ነው፡፡ መፍትሔው ምንድነው?

ዶ/ር ይናገር፡- ይኼ እንግዲህ ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ያመጣው ነው፡፡ ሌላ ነገር የለውም፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባይኖር ኖሮ የውጭ ባለሀብቱና የአገር ውስጥ ባለሀብቱን የምንለያይበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እንዲያውም የበለጠ ማበረታታት ያለብን የአገር ውስጡን ባለሀብት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች ለአገራችን ኢኮኖሚ በጣም መሠረታዊና አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የአገሪቱን ሕግ አምነው፣ አገሪቱንና ሁሉን ነገር አምነው መጥተው ፋብሪካ ገንብተዋል፡፡ 20 እና 30 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው ፋብሪካዎች ገንብተዋል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ካልገቡላቸው የአገሪቱ ኢንቨስትመንት አጠቃላይ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚቻል መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እነዚህን የውጭ ባለሀብቶች በተገኘው አማራጭ ሁሉ መደገፍ ተገቢና አስፈላጊ ነው ተብሎ ስለታመነ ነው ተግባራዊ የሆነው፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች የውጭ ብድር የማምጣት አቅም ስላላቸው  የሰፕላይ ክሬዲት የምንለው በ180 ቀናት የሚከፈል ስለሆነና አሁን ደግሞ እጥረት ስላለብን፣ ኤልሲውን ቶሎ ለመክፈት እነዚህ አማራጮች ቢፈጠርላቸው መልካም ነው በሚል የወጣ መመርያ ነው፡፡ ይኼ መመርያ ሕጋዊ ማዕቀፍ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥልጣን አለው የለውም የሚል ጥያቄ መነሳት የለበትም፡፡ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርን የሚመለከቱት ጉዳዮች የብሔራዊ ባንክ ሥልጣን ናቸው፡፡ የሌላ የማንም ሥልጣን አይደሉም፡፡ ስለዚህ ከሕግ አንፃር የሚነሳ ነገር የለም፡፡ እኔም ዘንድ ቢሮ እየመጡ ይህንን ጉዳይ በተለያየ መንገድ ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ይህ መከራከሪያ ብዙ ርቀት የሚወስደን አይመስለኝም፡፡

ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችስ የተባለ እንደሆነ ለእነሱ ደግሞ ኤልሲ እየተከፈላቸው ባለው አቅም እንዲስተናገዱ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ለሁሉም በሚፈልጉት መጠን የሚፈልጉትን ዶላር መስጠት አልተቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ቅሬታ ያላቸው እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ በእርግጥም አለ፡፡ ይኼ አጠቃላይ እጥረቱ የፈጠረው ነው፡፡ ስለዚህ ዘላቂ መፍሔው ለአገር ውስጥ እንዲህ፣ ለውጭ እንዲህ ማለቱ አይደለም ችግሩን የሚፈታው፡፡ ችግሩ የሚፈታው ቀደም ብዬ ያነሳሁት በወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ላይ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገ እንደሆነ ነው፡፡ ትልቁ የመፍትሔ ሐሳብም ይኼ ነው፡፡ ሌሎች አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ወይም በመመርያ ደረጃ የሚታዩትን እያየን በተቻለ መጠን ሁሉንም ሊያስተናግድ በሚችል ሁኔታ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ አልፎ አልፎ ጣልቃ እየገባ በንግድ ባንክ በኩል ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አንዳንድ ድጋፎችን ማድረግን ይቀጥላል፡፡ በዚህ ደረጃ ያለባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በተቻለ መጠን ጥረት እያደረግን ነው፡፡

ጥያቄ፡- የወጪ ንግዱ ብዙ ድጋፍ እየተደረገለት ነው፡፡ ለላኪዎች ከፍተኛ የሆነ ብድር እየተሰጠ ቢሆንም የሚገኘው ውጤት እምብዛም ነው፡፡ ነገር ግን ለዘርፉ የሚደረገውን ድጋፍ የተመለከቱ በላኪነት ሥራ ላይ የሌሉ ሳይቀሩ የላኪነት ፈቃድ እየወሰዱ የውጭ ምንዛሪ ይወስዳሉ፡፡ በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጡ ችግር አለበት፡፡ በባንኮች አካባቢም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ሕገወጥ ድርጊት እንደሚከናወን ይገለጻል፡፡

ዶ/ር ይናገር፡- እንግዲህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለ በተለያዩ መንገዶች በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ የሚነሱ ነገሮች አሉ፡፡ እናንተም እንደምታነሱት እኛም እንሰማለን፡፡ መሠረታዊ ጉዳዩ የአቅርቦቱን ሁኔታ ማሻሻል ነው፡፡ ነገር ግን እስከዚያው ድረስ ሕገወጥ አሠራሮች እንዳይበረክቱ በእኛ በኩል መሠራት ያለብንን እየሠራን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከባንክ ፕሬዚዳንቶች ጋር በየጊዜው እየተገናኘን እንነጋገራለን፡፡ ማድረግ ባለባቸውና በሌለባቸው ነገሮች ላይ በግልጽ እንነጋገራለን፡፡ የእኛን አሠራር (መመርያዎቻችን ግልጽ ናቸው) ተላልፈው የሚገኙ ካሉ ይቀጣሉ፡፡ ባንኩም ይቀጣል፡፡ ሌሎችም እንዲቀጡ የሚያደርግ አሠራር አለ፡፡ ይህም ሆኖ ግን እነሱ ሕገወጥ ነገር እንዳይሠሩ የመጨረሻ መድኃኒት ሆኖ አገልግሏል የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ በተለያየ መንገድ የተለያየ ነገር አለ፡፡ ሄደን ብንመረምር ዶክመንታቸውን ብናይ የማናገኛቸው ግን ደግሞ አንዳንድ ሕገወጥ ሥራዎችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ እኛም ጥርጣሬ አለን፡፡ በማስረጃ ለማስደገፍ ግን ብዙ ጊዜ እንቸገራለን፡፡ ዋናው ነገር ይኼ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ይኼን ሁኔታ በቅርብ መከታተል ያስፈልጋል፡፡ በሰነዶቻቸው ባይገኝም በሌሎች አማራጮች እንጠቀማለን፡፡ ይህንን የሚያደርጉ ባንኮች ካሉ እየተከታተልን ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ወደኋላ አንልም፡፡

ጥያቄ፡- የውጭ ምንዛሪን በወረፋ የመስጠት አሠራር ችግር አለበት፡፡ የወረፋ አያያዙም ላይ ያሉ ክፍተቶች ተጠቃሚዎችን እያማረሩ ነው፡፡ ይህ አሠራር በእርግጥ ምን ውጤት አምጥቷል? እናንተስ ምን እያደረጋችሁ ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- ወረፋ አያያዝን በሚመለከት ተመሳሳይ ነው፡፡ አማራጭ ስላጣን ነው፡፡ የወረፋ አያያዝ መመርያ ከመውጣቱ በፊት ሁሉም ባንኮች በየራሳቸው እንዲያስተናግዱ ዕድል ሰጥተን ነበር፡፡ ነገር ግን ነገሩ ሲታይ ባንኮች ደግሞ በራሳቸው ጊዜ ለአንዱ ሰጥተው ለሌላው የመከልከል ሁኔታ ተስተዋለ፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ሁሉም በፍትሐዊነት እንዲስተናገዱ፣ በአመዘጋገቡ መሠረት መስተናገድ አለባቸው በሚል ነው መመርያው የወጣው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ወረፋ ለመያዝ በኤክስፖርት ሥራ መሰማራት ሳይሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ኤክስፖርተር ሳይሆኑ የኤክስፖርተር ፈቃድ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ኤክስፖርተር ሳይሆኑ ሄደው ወረፋ በመያዝ የመመዝገብ ሁኔታ አለ፡፡ ይኼ በጣም አጨናንቋል፡፡ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኤክስፖርተርነት ፈቃድ ያወጣሉ፡፡ ይህንን ፈቃድ ባንኮች ጋ ይዘው ይሄዳሉ፡፡ መዝግበኝ ይላሉ፡፡ ሰውዬው ኤክስፖርተር ነው ወይ? ምን አቅም አለው? ምን ታሪክ አለው? ምን ልምድ አለው? የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ሰው እየሄደ ባንኮች ላይ ከፍተኛ የምዝገባ ወረፋ እየፈጠረ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በተለይ የኤክስፖርት ፈቃድ የሚያወጡ አካላትን በሚመለከት ባለው አሠራር ላይ ውይይቶችን ጀምረናል፡፡ ከሞላ ጎደል ይህ ውይይት መስመር ከያዘ በተወሰነ ደረጃ ትክክለኛ ኤክስፖርተሮች በዚህ ወረፋ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር እያየን እንሄዳለን፡፡

      ለባንኮች የላክንላቸው መመርያ ላይ የሚያስተናግዱበት ቅደም ተከተል አለ፡፡ ለምሳሌ የመጀመርያው መድኃኒት ነው፡፡ ቀጥሎ ማኑፋክቸሪንግ ነው፡፡ ሌሎቹም በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ባንኮች ቅድሚያ የሚሰጡዋቸው የትኞቹ ናቸው ተብሎ በዝርዝር ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ነው የሚሠሩት፡፡ አንዳንድ የማይመዘግቡ ባንኮች ደግሞ ያጋጥማሉ፡፡ እኛ ጋም ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ፡፡ አየተነጋገርን የምንፈታበት ሁኔታ አለ፡፡ በጥቅሉ ግን በባንኮችም በኩል ከፍተኛ የሆነ የወረፋ ጫናና ጥያቄ አለባቸው፡፡ ሁሉንም ማስተናገድ አይችሉም፡፡ የተመዘገበ ሰው አንድ ዓመት ሊቆይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት ከባንኮች ማኅበር ጋር ተመካክረን አሁን እየተሠራበት ያለውን አሠራር የበለጠ ለማሻሻል ምን ማድረግ ይሻላል? በሚል ጥናት አጥንተን ይህንን ጥናት ወደፊት ምን ያህል ርቀት እንደሚወስደን እናያለን፡፡ ነገር ግን ይህንን ችግር ከመቅረፍ አኳያ በየጊዜው መመርያውን እናሻሽላለን ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- የባንኮች የብድር የወለድ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ብሔራዊ ባንክ ምን እያደረገ ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- የቁጠባ ወለድ መነሻውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይወስናል፡፡ ለቁጠባ የሚከፈለው ሰባት በመቶ ወለድ ነው፡፡ ባንኮች ብድር ሲሰጡ ግን የማበደርያ ወለዳቸው መጠን ክፍት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ባንኮች ከቀረበላቸው የብድር ጥያቄ አኳያ የሚያስተናግዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህንን በተመለተ ባንኮች ከፍ ያለ የማበደርያ ወለድ አላቸው፡፡ ይህ የማበደርያ ወለድ ለምን ከፍ አለ? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ የየራሳቸው ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን በእኛ በኩል ከእነርሱ ጋር ውይይት እያደረግን ነው፡፡ እነሱ መታየትት አለባቸው የሚሏቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ጊዜ ለምሳሌ አንድ ባንክ ካበደረው ብድር ውስጥ ምን ያህሉን በ15 በመቶ ወለድ፣ ምን ያህሉን በ20 በመቶ ወለድ አበደረ፣ ምን ያህሉን በአሥር በመቶ አበደረ የሚለው ጉዳይ በዝርዝር መጠናት አለበት፡፡ ከሰጠው ብድር ውስጥ ከፍተኛው ብድር በስንት ወለድ ነው ያበደረው የሚለውን በዝርዝር አጥንተን፣ ወደፊት ከማበደርያ ወለድ ጋር በተያያዘ የሚኖረን አቅጣጫ ምን ይሆናል የሚለውን በጥናቶች ላይ ተመሥርተን መነጋገር ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን በእኛ በኩል ነፃ ገበያ ስለሆነ የነፃ ገበያ አካሄዱን በተወሰነ ሁኔታ እንደግፋለን፡፡ ከቁጥጥር ውጪ የወጣ ነገር ካለ ደግሞ ባንኩ ለማየት ዝግ አያደርግም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ሁለቱንም ወገኖች ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንደተባለው የማበደርያ ወለዱ ከፍ እያለ መምጣቱን በሚመለከት ከባንኩ ጋር በስፋት መነጋገርን ይጠይቃል፡፡ በከፍተኛ ወለድ አበድረው ተበዳሪው መክፈል ካልቻለ ዞሮ ዞሮ ዕዳው ለባንኩ ነው የሚሆነው፡፡ ገንዘቡ ሊመለስለት አይችልም፡፡ ለባንኮችም ጤናማ አይሆንም፡፡ ለጊዜው ከወለዱ የሚያገኙት ገቢ ከፍተኛ ስለሆነ በጥሩ ጎኑ ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ቢዝነሱን ለማስቀጠል በዚህ መንገድ መሄዱ አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ጉዳዮችን በእኛ በኩል እናያለን፡፡

ጥያቄ፡- ስለአገሪቱ ባንኮች ጤናማነት ተናግረዋል፡፡ ጤናማነታቸው እንዴት ይገለጻል? ለምሳሌ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድሩ 40 በመቶ ገብቷል፡፡ ይህ እንዴት ይታያል? ልማት ባንክንስ እንዴት እየተጠቆጣጠራችሁ ነው? በዚህ ረገድ ሚናችሁ ምንድነው?

ዶ/ር ይናገር፡- የአገሪቱ ባንኮች ጤናማ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የግል ባንኮች ጤናማ ናቸው፡፡ ከልማት ባንክ በስተቀር ሁሉም ጤናማ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ግን ከፍተኛ ችግር አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያልተመለሰ ብድር ምጣኔው በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡ በተለይም ደግሞ ለእርሻ ያበደረውን መመለስ አልተቻለም፡፡ ወደ 6.3 ቢሊዮን ብር ለእርሻ ሥራ ተብሎ ለባለሀብቶች የተሰጠ ብድር አለ፡፡ ይኼ ብድር የሚመለስበት ዕድል በጣም የጠበበ ሆኗል፡፡ ነገር ግን እነዚህን የተበደሩ ሰዎች በተቻለ አቅም ወደ ሕግ የማቅረብ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት አለባችሁ የሚል አቅጣጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰጥቷል፡፡ ልማት ባንክ የሚመደብለት ብድር ወይም የሚወስደው ብድር በአጠቃላይ ውጤታማነቱ ምን ያህል ነው? የሚል ጥናት እየተጠና ነው፡፡ ጥናቱ ላይ ተመሥርቶ ልማት ባንክ ትልቅ የሚባል ሪፎርም ካላካሄደ ከዚህ ችግር ሊወጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ ልማት ባንክ ሪፎርም እንዲያከናውን ከብሔራዊ ባንክ ጋር የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ በሪፎርም አማካይነት ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት ይደረጋል፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር ግን ያላግባብ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለግለሰቦች የመጠቀሚያ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ አወሳሰዱ ሕጋዊ ነው፡፡ ነገር ግን የተወሰነው ብድር በጣም በተደራጀና ሕገወጥ በሆነ ኔትወርክ፣ ገንዘቡ እንዴት እንደማይመለስ በማሰብ ጭምር በተቀነባበረ መንገድ የተወሰደ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጥሩ የሆነ ብድር አለ፡፡ ብድሩን ሥራ ላይ አውለው የሚንቀሳቀሱ ጥሩ ጥሩ ፕሮጀክቶች ደግሞ አላቸው፡፡ እነዚህን ደግሞ መዝጋት አንችልም፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንኩ በሚፈቀድለት ብድር እነዚህን ፕሮጀክቶች ማካሄድ እንደሚቻል፣ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚፈለግ የውጭ ምንዛሪ ካለማቅረብ ካልሆነ በዚህ ዓመት የጠየቀው ብድርና የውጭ ምንዛሪ አልተፈቀደለትም፡፡ ይህንን የምናደርገው የሪፎርም ሥራዎችን ከሠራና ባንኩ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ከተደረሰ በኋላ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጹ ጥሩ ነው፡፡ ሌሎች የግል ባንኮች በጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ካፒታላቸው፣ ትርፋቸውና ብድር የመስጠት አቅማቸው እያደገ ነው፡፡ ብድር የመሰብሰብ አቅማቸው በየጊዜው እየተሻሻለ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ይኖራል? ጥቁር ገበያው ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ ጋር ያለው ልዩነት እየሰፋ ነው፡፡ እዚህ ብሔራዊ ባንክ አካባቢ ጥቁር ገበያ በሰፊው ይስተዋላል፡፡ ይህ ምን ያሳያል?

ዶ/ር ይናገር፡- የውጭ ምንዛሪ ላይ ለውጥ አለ የለም ለሚለው በዚህ ደረጃ የምናደርጋቸውና የምናጠናቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት፣ በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን የምንዛሪ መጠን የሚያጠበው ዋናው ጉዳይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ማሻሻል ነው፡፡ ይኼ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ በመለስ ግን ሌሎች የመፍትሔ ሐሳቦች እየታዩ ነው፡፡ ባለው መጠን መወሰድ ያለባቸው ሌሎች ዕርምጃዎች ካሉ ወደፊት በጥናት ልናያቸው የምንችላቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡

ጥያቄ፡- በባንክ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ምን እየተሠራ ነው? በተለይ ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የባንክ ድርሻ እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ እየተሠራ ነው የሚለው ጉዳይ ምን ያህል ተጨባጭ ነው? እርስዎ ገዥ ከሆኑ በኋላ እየመጡ ያሉ የሕግ ወይም የፖሊሲ ማሻሻያዎች ካሉ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ይናገር፡- በእኛ በኩል በአዋጁ ላይ ማሻሻያዎች አሉ፡፡ በአዋጁ አንኳር ከሆኑት ማሻሻያዎች ውስጥ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ሐሳብ አቅርበናል፡፡ በአዋጁ አስፈላጊ ናቸው ከሚባሉት አንዱም ነው፡፡ ሌሎችም አዳዲስ ያቀረብናቸው ሐሳቦች አሉ፡፡ የባንክ፣ የኢንሹራንስና የማይክሮ ፋይናንስን በተመለከተ የቀረቡ በርከት ያሉ የማሻሻያ ሐሳቦች አሉ፡፡ ወደ ፊት ሒደታቸው በየደረሱበት ምዕራፍ ግልጽ ይሆናል፡፡

ጥያቄ፡- የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያው ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- ይኼ መሻሻል አለው፡፡ ካለፉት ሰባትና ስምንት ወራት በፊት ከነበረው ብዙ መሻሻል አለው፡፡ ቁጥሩን መናገር ለእናንተ ብዙም አይጠቅማችሁም፡፡ ተሻሽሏል የሚለውን ዜና ከሰማችሁ ይበቃል፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፎርም ምን ደረጃ ላይ ነው? የሰው ኃይል ችግር አለበት ይባላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በባንኩ ቁልፍ የሆነውንና የማክሮ ኢኮኖሚውን በበላይነት የሚመራው የምክትል ገዥ የኃላፊነት ቦታ ላይ እስካሁን ሹመት አልተሰጠም፡፡ ለምን? የሰው ኃይላችሁ ጥንካሬስ?

ዶ/ር ይናገር፡- የባንኩን የሰው ኃይል በማጠናከሩ ረገድ እየተሠራ ነው፡፡ አመራሮችን፣ ከዚህ በላይ የባንኩን ሪፎርም ሥራ የሚደግፉ ሌሎች አካላትንም እያደራጀን ነው፡፡ በባንክ ሪፎርም ላይ በተለይ ቀደም ብዬ ካነሳሁላችሁ አንዳንዶቹ ልንጀምራቸው ወይም ልንጀምራቸው ያሰብናቸው እንደ ካፒታል ማርኬት፣ የቦንድ ማርኬትን የመሳሰሉት ላይ ዕውቀት ያላቸው ትልልቅ ባለሙያዎች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ ጀምረናል፡፡ በዚህ ደረጃ የውስጥን አቅም ብቻ ሳይሆን የውጭንም አቅም ጭምር ለሪፎርሙ ሥራ እንጠቀማለን፡፡

ጥያቄ፡- ከሬሚታንስ የሚገኘው ገቢ ምን ያህል ደርሷል? ዳያስፖራው በዚህ ዘርፍ ያለውስ ተሳትፎ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- ሬሚታንስና ዳያስፖራውን በተመለተ አጥንተን አማራጮችን መጠቀም ስላለብን፣ በዚህ ጉዳይ የተጠናውን ጥናት በቅርብ ጊዜ ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከብዙ አካላት ጋር በጋራ እንሠራለን፡፡ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እንሠራለን፡፡ እነሱ አንድ ትልቅ ሐሳብ ይዘው መጥተዋል፡፡ ሬሚታንስን በተመለተ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ሐሳቦች አሉን፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ከሞባይል ባንኪንግና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሌሎችም አማራጮች እየታዩ ነው፡፡ ሬሚታንስ በቀላሉ ወደ አገራችን የሚገባባቸውን አማራጮች ተጠንተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ተግባራዊ የምናደርገው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከኤክስፖርት በላይ ከሬሚታንስ የምናገኘው ይበልጣል፡፡ ባለፈው ዓመት ከወጪ ንግድ ያገኘነው ወደ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከሬሚታንስ ከዳያስፖራው የተገኘው ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ በዓመት ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ለነዳጅ እናወጣለን፡፡ ከወጪ ንግድ ወደ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ከሆነ፣ የወጪ ንግዱ ነዳጅ እንኳን አይሸፍንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች አማራጮችን በስፋት የመጠቀሙ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ አለብን፡፡ ሬሚታንስ ላይ በጣም ቀላል ወጪ ቆጣቢና ሳቢ፣ ሰዎች ሕገወጡን የሐዋላ አገልግሎት እንዳይጠቀሙ፣ ይልቁኑም መደበኛው የሐዋላ አገልግሎት መጠቀም እንዲችሉ በሚያስችል አኳኃን እንደ አማራጭ እንሠራለን ብለናል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ካደረግን ብዙ ርቀት ይወስደናል ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- ግብርናው ወሳኝ ሚና ካለው ዘርፉን ለማሳደግ ምን እየተደረገ ነው? ዘርፉ ወሳኝ ነው እየተባለ ግን የሚደረግለት ዕገዛ አናሳ ነው፡፡ ዘርፉ የሚያገኘው ብድርም አነስተኛ ነው፡፡

ዶ/ር ይናገር፡- ለችግራችን መፍትሔ ግብርና ከሆነ በበጀት ከመደገፍና ትኩረት ከመስጠት አኳያ፣ እንደተባለው የእኛ አገር ኢኮኖሚ በሚቀጥሉት ዓመታት ግብርና ሁነኛ ቦታ እንደሚኖረው ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ማኑፋክቸሪንግን እናሳድጋለን ካልን ዋናው ጥሬ ዕቃ ከግብርና ነው የሚመጣው፡፡ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ብዙ ባለሀብቶች መጥተዋል፡፡ በዚህ ላይ ጥጥ በአገር ውስጥ ማምረት ካልቻልን፣ ሌሎች አግሮ ኢንዱስትሪዎች የግብርና ጥሬ ዕቃ ካላገኙ ብዙ ርቀት አንሄድም፡፡ ኤክስፖርቱም አያድግም፡፡ ለአብዛኛው ሕዝብ ግብርና መተዳደርያው ስለሆነ በሕይወቱ ላይ ሁነኛ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ግብርና ላይ ርብርብ መደረግ አለበት የምንለው በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ግብርናን እስካሁን ካለው ለየት ባለ ሁኔታ ከበጀት አመዳደብም ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት በማለት መንግሥት አቅጣጫ ይዟል፡፡ በዚሁ መሠረት በተለይ በአገራችን ቆላማ አካባቢዎች ሰፋፊ የመስኖ ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዷል፡፡ ይህንን በማድረግ ከውጭ የምናስገባውን ስንዴ ሊያስቀር የሚችል የግብርና ሥራ ላይ ማተኮር አለብን ተብሎ የተያዘ አቅጣጫ አለ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት እኔ እንደምገምተው ከአጠቃላይ በጀት ቀላል የማይባለው ለግብርናው ይመደባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ይህንን ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መደገፍ ያስፈልግል የተባለው በዚህ መንገድ የማይታይ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የወርቅ የወጪ ንግድ መውደቅ በግልጽ ይታያል፡፡ የወርቅ የወጪ ንግድ ከ430 ሚሊዮን ዶላር ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር ወርዷል፡፡ ችግሩ ከኮንትሮባንድ ጋር የተያያዘ ነው ቢባልም እንደ ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ያሉት ተዘግተዋል፡፡ ይህ የራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገባ ነበር፡፡ ይህ ከሆነ እንዲህ ያሉ ኩባንያዎችን በተመለከተ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሠራ ነው? ችግሩ ከማኅበረሰቡ ጋር ከሆነስ የማኅበረሰቡን ችግር ቀርፎ ወደ ሥራ መግባት አይቻልም?

ዶ/ር ይናገር፡- ወርቅን በተመለከተ ሁለት ዓይነት አመራረት ነው ያለው አንደኛው ትልልቅ ኩባንያዎች የሚያመርቱት ወርቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በባህላዊ መንገድ በማኅበር ተደራጅተው ወይም በተናጠል የሚያመርቱና በአነስተኛ ጥቃቅን የሚመረት ወርቅ አለ፡፡ ወርቅ አሁን ባለው ሁኔታ የኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ከወርቅ የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ከጊዜ በኋላ ይኖራል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ በቂ ጥናት ተጠንቷል፡፡ በዚህ ጥናት ላይ ተመሥርተን ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ መወሰድ ባለባቸው ዕርምጃዎች ላይ በቀጣይ እናያለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ ለገደንቢና የመሳሰሉት አካባቢዎች የተዘጉ ትልልቅ ኩባንያዎችን በተመለከተ የየራሳቸው ምክንያት አላቸው፡፡ ይህም ሆኖ እነዚህ የወርቅ ኩባንያዎች ያሉባቸውን ችግሮች በዝርዝር መፈተሽና ማየት፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይትና መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ደረጃ እንዲፈቱ ወይም መፍትሔ ይሆናሉ የሚሉ ሐሳቦችን በስፋት ማየት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ከወርቅ የሚኖረን የውጭ ምንዛሪ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በቀጣይም ሌሎች አዳዲስ የወርቅ ኢንቨስትመንት መጀመር ለሚፈልጉ አካላት እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ አለ የሚባል ችግር በጋራ መፍታት፣ ሌላውን ደግሞ ወደ ሥራ ማስገባት ተመራጭነት ያለው ይመስለኛል፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሹማምንት ፖለቲከኞች ናችሁ፡፡ ባንኩ ከፖለቲካው ምን ያህል ነፃ ነው? ቀድሞም ሆነ አሁንም የገዥው ፓርቲ አባላት የቦርድ ሰብሳቢዎች  የፖለቲካ ሰዎች ናቸው፡፡ ይኼ ባንኩን በነፃነት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ እንቅፋት አይሆንም ወይ? እርስዎ በፋይናንስ ዘርፍ አቅም እንዳለዎ ጥርጣሬ ባይኖርም፣ ነገር ግን ምን ያህል ነፃ ሆነው ሥራዎን በአግባቡ ይሠራሉ?

ዶ/ር ይናገር፡- ብሔራዊ ባንክ ነፃ ነው ወይ? የሚለውን በተመለከተ እንደ አገሮች የተለያየ ተጠሪነት ነው ያለው፡፡ በተወሰኑ አገሮች ገዥው ተጠሪነቱ ለፓርላማው ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ተጠሪነቱ ለአስፈጻሚው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡  ስለዚህ ሁለቱም ያስኬዳል፡፡ እንደ አገሮች ነባራዊ ሁኔታ የብሔራው ባንክ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የሚሠራበትን ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ አገራችንን በተመለከተ ከነፃነት አኳያ ዞሮ ዞሮ ይኼ ብሔራዊ ባንክ ሌላ ተልዕኮ የለውም፡፡ ዋና ዋና ተልዕኮዎቹ ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ተመንና የውጭ ምንዛሪ ማስተዳደር፣ ሁለተኛው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባንኮችን መቆጣጠርና ጤናማነታቸውን መከታተል፣ ሦስተኛው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጤናማ እንዲሆን መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ የበኩሉን ሚና መጫወት ነው፡፡ በመሠረታዊነት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተልዕኮ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ተልዕኮዎች ስንፈጽም፣ ተልዕኮዎቹ ከመንግሥት ውጪ ሆነው የሚፈጸሙ አይደሉም፡፡ ከመንግሥት ጋር በመሆን ባሉት ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ የሚፈጸሙ እነዚህ ተልዕኮዎች ደግሞ ሌላ ዓላማ የላቸውም፡፡ ዕድገቱንና ልማቱን ለማስቀጠል ያለሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር የሚመለከታቸው የቦርድ አባላት ቢሳተፉ ባንኩ ተልዕኮውን እንዲፈጽም ያግዛሉ እንጂ፣ ብዙ ችግር ያመጣሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ ከእኛ አኳያ እስካሁን ባለው አሠራር እንደተባለው የባንክ ገዥዎችና የቦርድ አባላት በመንግሥት ተሿሚዎች መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በመንግሥት የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ናቸው፡፡ ከሥራው አንፃር እኔም እዚህ በቆየሁበት ጊዜ ብሔራዊ ባንኩ ለኢኮኖሚው መፍትሔ ይሆናል ብሎ ባቀረባቸው ጉዳዮች ላይ ይኼ አይሆንም፣ ይኼ የእናንተ ጉዳይ አይደለም ተብሎ የቀረበ እስካሁን እኔ እስከማውቀው ድረስ የለም፡፡ ያቀረብናቸው ጉዳዮች በጥናት ላይ የተመረኮዙና አሳማኝ እስከሆኑ ድረስ የሚመለከታቸው አካላትም ተቀብለዋቸው እየሠራን ነው፡፡ ወደፊትም ይህንን እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ እንደሌላው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ሌላው አስፈጻሚ ብዙ የሚገባበት ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን ባሉት አደረጃጀቶች በቦርድና በሌሎች ባለን ግንኙነት የባንኩን አፈጻጸም እናቀርባለን፡፡ በዚሁ መሠረት እንሄዳለን፡፡ ለፓርላማም እንዲሁ እናቀርባለን፡፡ ለቋሚ ኮሚቴ እናቀርባለን፡፡ የሚመለከታቸው ስለሆነ በዚህ ደረጃ የባንኩን የሥራ እንቅስቃሴ እየመራን ነው፡፡ ስለዚህ የተነሳውን ሥጋት እኔ እንደ ሥጋት አላየውም፡፡ እንደ አገሩ ተጨባጭ ሁኔታ መታየት አለበት፡፡

ጥያቄ፡- የአገሪቱ ብድር ከፍተኛ ነው፡፡ እርስዎ የዕዳ ክፍያው እየተፈጸመ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቻይና ብድር ሥጋት አለው ይባላል፡፡ ለምሳሌ ኬንያ ከቻይና የተበደረችውን ብድር ባለመመለሷ የሞምባሳ ወደብን የመውሰድ ሁኔታ አለ ይባላል፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃርስ? እንዲያውም ዕዳ ስላለብን ዕዳውን በንብረት የመለወጥ ነገር አለ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዕዳ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ልትወስድ ትችላለች የሚባለውስ? ዶ/ር ይናገር፡- በዚህ ጉዳይ የሰማሁት የለም፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ እዚህ ደረጃ ይደርሳል የሚል        እምነትም የለኝም፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ከቻይና መንግሥት የተበደርነውን እየከፈልን ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ለተበደሩት ማስያዣ እንዳደረጉ አውቃለሁ፡፡ አበዳሪዎች የአገሩን ንብረት ይዘው ብድሩ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ንብረቱን የሚያስተዳድሩበት አሠራር በአንዳንድ አገሮች ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡ በእኛ አገር ግን እዚህ ደረጃ ይደረሳል የሚል እምነት የለኝም፡፡

ጥያቄ፡- የትልልቅ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዴት ነው? የሚታጠፉ ይኖራሉ፣ ሊቋረጡ የሚችሉ አሉ ይባላልና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ እየተሻሻለ ካልሄደ በቀር አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መያዝ ያስቸግራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢኮኖሚው እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እየተሻሻለ ይሄዳል የሚለው ዕውን ካልሆነና ሌላ ካሰብነው ውጪ ከአቅም በላይ ጉዳይ ካጋጠመ፣ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ብዙም ችግር የማይፈጥሩ ከሆነ ለጊዜው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ነባር ፕሮጀክቶች ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ እዚህ ደረጃ አልደረስንም፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሁሉም በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡ ለእነሱ የሚያስፈልጋቸው ክፍያ በብርም በውጭ ምንዛሪም እየተከፈለ ነው፡፡ እንደተባለው የባሰ ነገር ከመጣ ይህም ዝግ አይሆንም፡፡ ነገር ግን እዚህ ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡

ጥያቄ፡- ፕራይቬታይዝ የሚደረጉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳይ ላይ የተቀዛቀዘ ነገር ይታያል፡፡ አሁን ምንም እንቅስቃሴ እየታየ አይደለም፡፡ ለምን ዘገየ?

ዶ/ር ይናገር፡- እንደተባለው በተለይ ትልልቆቹን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ለማዞር ከፍተኛውን ድርሻ መንግሥት ይዞ፣ አነስ ያለውን ድርሻ ለሌሎች ለማስተላለፍ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይ ከሌሎቹ የቴሌኮም የተሻለ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ በጠቅላላ ግን ሌሎቹን ያየን እንደሆነ ገና ነው፡፡ ብዙ ርቀት ሄደዋል ማለት አይቻልም፡፡ መፋጠን ግን አለበት፡፡ ትንሽ የመዘግየት ነገር ይታያል፡፡ በመሠረታዊነት ግን ፕራይቬታይዝ ይደረጋሉ የተባሉት አንዳንዶቹ ድርጅቶች ገዥ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ግን ላይኖራቸውም ይችላል፡፡ በተለይ የስኳር ፋብሪካዎች አካባቢ በተለያየ ምክንያት ፍላጎትም አያሳዩም፡፡ ሌሎች ፕራይቬታይዝ ብናደርግ ይመረጣሉ ያልናቸው የልማት ድርጅቶች ላይ እንደ ድርጅቶቹ ጥንካሬና እንደ ፈላጊያቸው ሁኔታ ስለሚታይ ይህ ብቻ ሳይሆን የእኛም የቅድመ ዝግጅት ሁኔታዎች ይወስኑታል፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ተደማምሮ ትንሽ የመዘግየት ሁኔታ እንዳለ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን መፍጠን አለበት፡፡ ይኼ ከተፋጠነ ለዶላር እጥረታችን ዕገዛም ያደርጋል፡፡ ከዚህም በላይ እነዚህ የልማት ድርጅቶች የተሻሉና ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው፣ ከያዙዋቸው የተሻለ ተወዳዳሪ የመሆን ዕድላቸው እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ የልማት ድርጅቶችን ፕራይቬታይዜሽን በተመለከተ አሠራሩ በታሰበው ልክ እየሄደ ነው ማለት አይቻልም፣ ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡

ጥያቄ፡- በጥቁር ገበያው መስፋፋት ምክንያት እየተከናወነ ያለው ቁጥጥር ውጤት አምጥቷል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ይናገር፡- ጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር በእኛ በኩል አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃዎች  እንደምትሰሙት እየተወሰዱ ናቸው፡፡ ይህንን የሚከታተሉ አካላት አሉ፣ ተቋማት አሉ፡፡ ይህን የሚሠሩ ኮሚቴዎች አሉ፡፡ ይኼ ለጊዜው እንደ ማስተንፈሻ ካልሆነ በቀር ዘላቂ መፍትሔ ግን አይደለም፡፡ ዘላቂ መፍትሔው ከውጭ ምንዛሪ አኳያ  እንዴት እንደሚሻሻል የፖሊሲ ሐሳቦችን አመንጭቶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ሌላ በውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ክፍተት እንዲኖር ያደረጉ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የመቆጣጠር አቅማችንን እያጠናከርን መሄድ ከቻልን፣ ችግሩን መቀነስ የምንችልበት አቅም ይኖራል፡፡ በጥቁር ገበያና በባንኮች መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ግን አንድ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ አንድ የሚሆኑበት ዕድል አስቸጋሪ ነው፡፡ የሚጠበቅ ምክንያታዊ ክፍተት አለ፡፡ ስለዚህ በሌሎች አገሮች እንደሚታየው ወደዚያ የማድረስ ነገር ነው የሚጠበቀው፡፡ እንደዚያ እንዲሆን የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ እነዚህ የጀመርናቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሪፎርም ሥራዎች ተቀናጅተው ተግባራዊ ከሆኑና ከተሳኩ፣ ከገባንባቸው የኢኮኖሚ ማነቆዎችና እንደ ሥጋት ከጠቀስኳቸው መውጣት የምንችልበት ዕድል በጣም ሰፊ ነው፡፡ ብዙዎቹ በእኛ የዕድገት ደረጃ የነበሩ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የነበሩ አገሮች፣ በተለይ በፈጣን ዕድገት ላይ የነበሩት እንደ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ ያሉ አገሮች ዛሬ ያነሳሁላችሁ ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ ከሞላ ጎደል እንደ መፍትሔ ወስደዋቸው የነበሩ ዕርምጃዎችም እኛ እዚህ ከምናነሳቸው የተለዩ አይደሉም፡፡ የወጪ ንግድ ላይ ተረባረቡ፣ የአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብና ቁጠባ ላይ ተረባረቡ፣ እነሱም እንደኛ በተለይ ደቡብ ኮሪያ የተለያዩ የፖለቲካ ሁኔታዎች ነበሩባቸው፡፡ ይህም ሆኖ የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ በዚያ ወቅት ፈስሶ ነበር፡፡ እነዚህ ተደማምረው እነሱ አሁን ባሉበት ሁኔታ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ችግር ከሞላ ጎደል ችግር የለባቸውም፡፡ ኢኮኖሚውን በፍጥነት ለማስኬድ የሚያስችሉ ርቀቶች ሄደዋል፡፡ ስለዚህ ሌላ አገር ያላጋጠመውና የተለየ ሊፈታ የማይችል ችግር አይደለም እኛን ያጋጠመን፡፡ ይኼ ችግር ቀደም ብዬ እንዳልኩት በተለይ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ተስፋ እየታየበት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ተስፋ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሥራዎችን አሟልተን ተግባራዊ ማድረግ ከቻልን፣ እነዚህ በተለያዩ ገጽታዎች የተነሱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት 27.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 ሂሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 27.5...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...