Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማራቶን ሞተርስ ከመኪና ባሻገር ትራክተር ለመገጣጠም ማቀዱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሃዩንዳይ ፕሬዚዳንት የመጀመርያ የአፍሪካ ጉዟቸውን በኢትዮጵያ አድርገዋል

ከወራት በፊት የሃዩንዳይ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያን ገንብቶ ያጠናቀቀው ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ፣ ወደፊት የግብርናውን ዘርፍ ለማገዝ ትራክተር ለመገጣጠም ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የሃዩንዳይ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካውን ያስመረቀው ኩባንያው፣ ሳሚ የተሰኘውን ትራክተር በኢትዮጵያ በመገጣጠም በግብርናው ዘርፍ ለመሳተፍ እንዳሰበ የማራቶን ሞተርስ የቦርድ ሊቀመንበር ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አስታውቋል፡፡ ‹‹በየዓመቱ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ወደ ግብርናው ወርደን ለመሥራት ፈር ቀዳጅ ለመሆን አቅደናል፤›› ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በቂ የሰው ኃይልና ለም መሬት ቢኖራትም፣ በየዓመቱ ከመቶ ሺሕ  ሜትሪክ ቶን የሚቆጠር ስንዴ ማስገባቷ እንዲቀር ፍላጎቱ መሆኑን የገለጸው ኃይሌ፣ ግብርናውን ማነቃቃት እንደሚያስፈልግ አክሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር ላለፉት አሥር ዓመታት ከውጭ በማስገባት ለገበያ የዋሉ የሃዩንዳይ ተሽከርካሪዎችንና መለዋወጫዎችን ሲያቀርብ የቆየው ማራቶን ሞተርስ፣ አምጥቶ መሸጥ ትርፋማ እንዳደረገው አስረድቶ፣ በአንፃሩ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመውና የምርት ሒደታቸውን ጨርሰው ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም የእሴት ጭማሪ የሚደረግባቸውን የአሠራር መንገዶች ኢትዮጵያ ማስፋፋት እንደሚገባት ኃይሌ ተናግሯል፡፡

በቡና እርሻ፣ በማር ምርትና በሪዞርት ሆቴሎች መስክ የተሰማራው የኃይሌና ዓለም ኩባንያ፣ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በእህል አምራችነት ዘርፍ ከተሳተፈ ስኬታማ መሆን የሚችልባቸው ዕድሎች እንዳሉ መገንዘቡን ገልጿል፡፡

በመገጣጠሚያ ፋብሪካው ምርቃት ላይ የተገኙትና ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ ጉዟቸውን በኢትዮጵያ የጀመሩት የሃዩንዳይ ሞተርስ ኩባንያ ፕሬዚዳንት ሊ ዎንሒ፣ በኢትዮጵያ የተገነባው መገጣጠሚያ ለጎረቤት አገሮች መኪናዎችን ለማቅረብ እንደሚያስችልና የሃዩንዳይ ተሽከርካሪዎችንም በስፋት የማምረት አቅም አገሪቱ እንዳላት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ አቅም አላት፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ላይ ያለንን ገበያ ለማስፋት ሃዩንዳይ በቂ አቅርቦት ያሟላል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሞተር አቅርቦት ትፈልጋለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ በኋላ በተሽከርካሪዎች በኩል ተመጣጣኝ አቅርቦት እንደሚኖርም አክለዋል፡፡

ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሞሮኮ፣ ከአልጄሪያና ከግብፅ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ ያለው ሃዩንዳይ ሞተር፣ በኢንቨስትመንቱ መስክ እንዲሳተፍ ከመንግሥት ጥሪ እንደቀረበለት ያስታወሱት ሊ ዎንሒ፣ ኩባንያቸው የቀረበለትን ጥያቄ እንደሚያጤነው አስታውቀዋል፡፡

ሃዩንዳይ ከዘመኑ ጋር የሚጓዙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችንና በኤሌክትሪክና በነዳጅ ኃይል የሚሠሩ (ኃይብሪድ) መኪኖችንም ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ የወደፊት ዕቅዱ እንደሆነም የዓለም አቀፉ የሃዩንዳይ ኩባንያ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ማራቶን ሞተርስ ግንባታው አንድ ዓመት ከስድስት ወራት የፈጀውንና በቀን 36 ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል፡፡

ለመገጣጠሚያው ግንባታ የግማሽ ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል በማስገንዘብ ፈቃድ የተሰጠው ማራቶን ሞተርስ፣ የኃይል መቆራረጥና የግብዓት ችግሮች ሳያስተጓጉሉት 24 ሰዓት መሥራት ከቻለ፣ በዓመት አሥር ሺሕ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረብ የሚችልበት አቅም እንዳለው የማራቶን ሞተርስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

ዘመናዊ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ቴክኖሎጂዎችን እንዳሟላ የተነገረለት ፋብሪካው፣ በኮርያ ሥልጠና የተከታተሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በፋብሪካው አሠማርቷል፡፡ ከአንድ ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የተነገረለት ፋብሪካው፣ የሙያ ሥልጠናና የዕውቀት ሽግግር መፍጠርም ዓላማው እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ከ800 ሲሲ (ሲሊንደር ካፓሲቲ) ጀምሮ እስከ 1,600 ሲሲ አቅም ያላቸው የቤት አውቶሞቢሎችን፣ ለሕዝብ ትራንስፖርት የሚውሉና አራት ቶን የመጫን አቅም ያላቸው የመስክ ተሽከርካሪዎችንም እንደሚገጣጥም ታውቋል፡፡

ማራቶን ሞተርስ ከዚህ ቀደም ለገበያ ሲያቀርባቸው የቆዩ መኪኖች ሙሉ በሙሉ በውጭ ተመርተውና ተገጣጥመው ሲገቡ ነበር፡፡ በአገር ውስጥ ለሚገጣጠሙት ተሽከርካሪዎች የአገር ውስጥ ግብዓቶችን የሚጠቀም ዕቅድ ሲኖር፣ ለጊዜው ጎማ፣ ባትሪና የተለያዩ የሞተር ቅባትና ዘይቶችን፣ ለጭነት ተሽከርካሪዎችም የጭነት አካላትን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭውን ይተካል ተብሏል፡፡ መኪኖቹ በአገር ውስጥ ሲገጣጠሙ በአንድ ተሽከርካሪ ከ15 እስከ 18 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንደሚኖራቸውም ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች