Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ገንቢና ግንባታ አይተዋወቁም

በግንባታ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታዩት ብልሹ አሠራሮች በብዙ መንገዶች ሲገለጹ ሰምተናል፡፡ በዓይናችን የምናያቸው ደረጃቸውን ያልጠበቁ ግንባታዎች ያስከፈሉትን የሕወይትና የሀብት ኪሳራ፣ ወደፊትም ሊያስከፍሉ የሚችሉት ጉዳት እንደዘበት አይታይም፡፡ ጠቅላላ ሚኒስትሩ ‹‹ሽሮ ፈሰስ መንገዶች›› በማለት የሚጠቅሷቸው ግንባታዎች ከሚያስከትሉብን አደጋና ጉዳት በተጨማሪ የሚደርሱብንን የተጋነነ ወጪና ኪሳራ መገመት ይቻላል፡፡

እንዲህ ያለውን የቀሽሞች የግንባታ ሒደትን አሳሳቢ የሚያደርገውም፣ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚፈሰው የአገርና የሕዝብ ሀብት ለሌሎች ጉዳዮቻችን ከምናውለው ገንዘብ በላይ እጅግ ከፍተኛ፣ ምናልባትም እስከ 60 በመቶውን የአገሪቱን በጀት የሚቀረጥፍ ሆኖ ሳለ፣ የይድረስ ይድረስ የሚካሔዱ ግንባታዎች የዚህችን አገር መከራ ማብዛታቸው ከአሳሳቢነት በላይ  ነው፡፡

በግልም ሆነ በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ ግንባታዎች ሲካሄዱ የሚፈስባቸውን ሀብትና የሚወጣባቸውን ወጪ ያህል ውበት፣ ጥንካሬና ምቾትና ዘላቂ አገልግሎትን ያረጋግጣሉ ማለት ሲበዛ ሞኝነት የሆነባቸውን በርካታ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች፣ በተለይም አገር በቀል ተብዬዎቹ ሙያው በሚጠይቀው ደረጃ የሥነ ምግባርና የዕውቀት ክህሎት ልክ እየሠሩ ናቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ሊከብድ ይችላል፡፡ በእርግጥ ፈጣሪንም ሕዝቡንም ፈርተው፣ ለአገር ጥምር የሚሠሩት ጥቂት አይታጡም፡፡ እነሱን ሳይጨምር ከግዙፉ የኮንንስትራክሽን በጀት መሀል ገብተውና ተሰንቅረው ሐቀኞችን አላላውስ ያሉ፣ በሕዝብና በአገር ሀብት የግላቸውን ሀብትና ንብረት የሚያጋብሱ፣ በልቶ አደሮች እንደ አሸን የፈሉባት አገር ሆናለች፡፡ ይህንን የሚያርቅ ሥርዓት መፍጠር ግን ይለናል፡፡ የአገሪቱን ሀብት 60 በመቶ ለግንባታ እያዋሉ፣ ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል›› ዓይነት ተረት የሚያስተርቱብንን አልጠግብ ባዮች መላ የሚል፣ ቆፍጠን ያለ አካለ ያሻናል፡፡

ከድሃዋ ጭሮ አዳሪ መቀነት እያስፈቱ ታክስ በማስከፈል የሚሰበሰበውን የጡር ገንዝብ ለማንም በልቶ አይጠግብ መርጨት ከግፍም በላይ ነው፡፡ የትኛው ፍትሕ እንዲህ ያለውን ተግባር ይገልጸዋል፡፡  

በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ በሽታ የሆነውና አገርን ሀብት እንደ ዘበት የማሟጠጫው አንዱ መንገድ ግንባታን በቅጡ አጠናቆ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ማስረከብ አለመቻል ነው፡፡ ይህ አንዳንዴ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ሊያጋጥም ቢችልም፣ በብዛት ግን ይሁነኝ ተብሎ በሚደፈጸም የማምታታትና የማጭበርበር ተግባር ነው አገር የምትጎዳው፡፡ ሕዝብ የሚጮኸው፡፡ ይህም ምን ያህል ኢትዮጵያን እንዳከሰራት የሚታወቅ ነው፡፡ ሙስና እጅጉን የተንሰራፋበት ዘርፍ እንደመሆነም የአደባባይ ሐቅነቱ መዘንጋት የለብንም፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያስቆጨው ግን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት፣ በብዙ ውጣ ውረድ ከውጭ በብድርና ዕርዳታ የሚመጣውን ጥሪት በማሟጠጥ ወደር ያልተገኘለት ይህ ዘርፍ ሌላው መሠረታዊ መገለጫው ግንባታቸው እንደተጠናቀቀ የሚነገርላቸው ሥራዎች ብዙ ሳይቆዩ በኋላ የሚጠበቅበትን ግልጋሎት አለመስጠጣቸው ነው፡፡ ምነው ሲባል የዲዛይን ችግር፣ የቁጥጥር ማነስ፣ የበጀት እጥረት፣ የማቴሪያል ጥራት ወዘተ. ያሉ አታካች ሰበቦች ይቀርባሉ፡፡ ይህም ሳያንስ በግንባታ ሒደትም  ችግሮች እየተበራከቱ ለዜጎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሲሆኑ ደግሞ የበለጠ ይዘገንናል፡፡

በግንባታ ወቅት ለሚፈጠር አደጋ መንስዔው የግንባታ ሥርዓቱንና ሒደቱን በአግባቡ የመምራትና የማስዳደር ብቃት ችግር መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ይህም ግንባታው ስምምነት በተደረገበት የጥራትና የልኬት ደረጃ እንደማይከናወን የሚጠቁም ነው፡፡ ይፋ ሳይወጡ በየቦታው ተድበስብሰው የቀሩትን ትተን ለሕዝብ ጆሮ የደረሱ አንዳንድ የግንባታ ክስተቶችን ብንመለከት፣ ጉዳዩን በሚገባ መፈተሽና ማስተካከል እንደሚያስፈልገው ያመላክቱናል፡፡ የኮንስትራክሽን ሠራተኞች በቂ የአደጋ መከላከያ ሳይኖራቸው፣ አደገኛ በሆነ ከፍታ፣ ያለትክክለኛ አደጋ ሥጋት መከላከያ ሳይደረግላቸው ለደህንነታቸው ከፍተኛ ተጋላጭ በሚያደርጋቸው ሁኔታ እንዲሠሩ በመገደዳቸው  በርካቶችን ለአካል ጉዳትና ለሞት ሰለባ አድርጓቸዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት አራት ኪሎ አካባቢ ግንባታ ላይ የነበረ ሕንፃ ተደርምሶ ያደረሰውን ጉዳት እናስተውላለን፡፡ በግንባታው ሒደት የደረሰው ጉዳት ተገለጸ እንጂ፣ ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር የምናውቀው ጉዳይ የለም፡፡ የዚህ አደጋ መጨረሻው ሳይታወቅ፣ ኮተቤ ወንድ ይራድ ትምህርት ቤት አካባቢ ግንባታ ላይ የሚገኝ ድልድይ ተደርምሶ በሠራተኞች ላይ አደጋ ደረሷል፡፡ የዚህም አደጋ ሰበቡና ጉዳቱ እንደዋዛ ተድበስብሶ ቀረ፡፡ ከአደጋው በኋላ በሞት የተለም ሊኖር ይችላል፡፡ ጉዳዩ ግን እንደአልፎ ሒያጅ ውኃ ተረስቶ ቀረ፡፡ በሕይወት የተረፉት ሠራተኞች ምን ተደረገላቸው? ካሣ አገኙ ወይ? ታክመው ጤናቸው ተመልሶላቸው ይሆን? የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የችግሩ መገለጫ ይኼ ብቻ ሳይሆን፣ ተደጋጋሚ ችግር የሚፈጥሩ የግንባታ ድርጅቶች ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ ተወሰደ? የሚለውንም ስንመለከት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ዜና ለመስማት አልታደልንም፡፡

ነገም ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል፡፡ ሰው ይጎዳል፡፡ ሰው እንደዘበት ወጥቶ ይቀራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ግንባታ ያስከተለው ጉዳት በማን እንደሚካስ እንኳ አይታወቅም፡፡ በተቋራጩ ችግር የተደረመሰውን ድልድይ መልሶ ለመገንባት ተጨማሪ ክፍያ ከአስገንቢው ይለቀቅለትም ይሆናል፡፡ እንዲህ ለማለት ያስደፈረን ቢያንስ የግንባታው ባለቤት የሆነ ተቋም ድልድይ ተደርምሶብኛል ብሎ አለመውጣቱ ነው፡፡ ዝምታውን መርጧል፡፡ ለምን? መልሱን ማን አውቆት፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር አንድ ቦታ ላይ ቆሞ ለሕዝብ ግልጽ የሆነ አሠራር ሠፍሮ ስለጉዳዩ በቂ ማብራሪያ መሰጠት አለበት፡፡ አደጋው የሚደርሰው በተቋራጮቹ ችግር ከሆነም መገለጽ አለበት፡፡

በአጠቃላይ በሰሞኑ በደረሰው አደጋ ሳቢያ በግንባታ ሥራው ላይ የሚሳተፈው ኩባንያ ድምፅ አልተሰማም፡፡ አስገንቢውም ቢሆን ስለሁኔታው ትንፍሽ አላለም፡፡ ችግሩ ለምን ተፈጠረ? ያለም የለም፡፡ መቼም ግንባታ የሚፈርሰው ችግር ስላለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጥራት ጉድለት እንዳለ ያመለክታልና በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲህ ያለውን ችግር በግልጽ ማሳየትና መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም አደጋ ደረሰ ሰው ተጎዳ ብቻ ማለቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ቢያንስ አስገንቢው አካል ስለደረሰበት ጉዳትና ስለሚወስደው ዕርምጃ ሊያሳውቀን ይገባል፡፡.

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት