የተበላሸ የብድር መጠኑ ከ40 በመቶ በላይ ከሆነበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለይ ለእርሻ ሥራ ተበድረው ያልመለሱ፣ በሕግ እንዲጠየቁ በተሰጠው መመርያ መሠረት ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
ለእርሻ ሥራ ከልማት ባንክ ብድር ተበድረው ባልመለሱት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እየተወሰደ ያለው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው መመርያ መሠረት ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ብድሩን ወስደው ያልመለሱ ተበዳሪዎች በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ በልማት ባንክ በኩል ተጀምሯል፡፡
ልማት ባንክ በተለይ ለእርሻ የሰጠውን ብድር ለማስመለስ ባይችል እንኳን ተበዳሪዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፣ ይህንኑ ሥራ ባንኩ በተገቢው መንገድ እያከናወነ መሆኑን ከገዥው ለመረዳት ተችሏል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ባለፈው ሳምንት ሰጥተውት በነበረ መግለጫ ላይም፣ ልማት ባንክ ለእርሻ ከሰጠው ብድር ውስጥ 6.3 ቢሊዮን ብር መመለስ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀው ነበር፡፡
ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዳይመለስ ተደርጎ የተለቀቀውን ብድር ለማስመለስ ከባድ ቢሆንም፣ ገንዘቡን ወስደው ያልመለሱትን በሕግ የመጠየቁ ሥራ ግን ተግባራዊ መሆን ጀምሯል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሕጋዊ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ቢገለጽም፣ ምን ዓይነት እንደሆነ ግን በግልጽ አልተነገረም፡፡
ከሁሉም የአገሪቱ ባንኮች በተለየ ሁኔታ የተበላሸ የብድር መጠኑ እየጨመረ የመጣው ልማት ባንክ፣ ለእርሻ ብድር ወስደው ያልመለሱ ባለሀብቶችን ለሕግ ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ ራሱን እንደ አዲስ ሪፎርም እንዲያደርግ ተወስኗል፡፡
ልማት ባንክ አሁን እየተለቀቀለት ያለው ገንዘብ ውጤቱ እየተመዘነ የሚሰጥ እንጂ፣ እንደ ቀድሞ በጠየቀው ልክ እየተሰጠው እንዳልሆነ ታውቋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይህንኑ ጉዳይ ባለፈው ሳምንት መግለጫቸው ያስታወቁ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላም ካለበት ችግር ለመወጣት ሪፎርም ማድረግ ግዴታው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የልማት ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን አሁን ጎልቶ ይውጣ እንጂ፣ ቀደም ባሉት ሦስትና አራት ዓመታት መጠኑ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ በ2006 ዓ.ም. የተበላሸ የብድር መጠኑ 16 በመቶ፣ በ2008 ዓ.ም. 25 በመቶ፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 40 በመቶ ደርሷል፡፡
ይህንን የተበላሸ የብድር መጠን ለመቀነስና ያበደረውን የማስመለስ ሥራው ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለው ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ ሆኗል፡፡
በመንግሥት ዘንድ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አንዱ የባንኩን ሥራ አመራር ቦርድ መለወጥ ነው ተብሎ፣ ከሁለት ወራት ወዲህ በተሰጠ ሹመት አዳዲስ የቦርድ አመራሮች ተሰይመዋል፡፡
በዚህ ቦርድ ውስጥ እንዲካተቱ ከተደረጉት ውስጥ የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራው ደርበውም የባንኩ የቦርድ አባል በመሆን መመደባቸው ታውቋል፡፡