Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አውሮፕላን አምራቹ ሚትስቡሺ ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እንዲሠራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያና በእስያ አገሮች ለከንፈርና ለላንቃ መሰንጠቅ ድጋፍ የሚሰጡት ጃፓናዊው የሕክምና ባለሙያ፣ በተሰጣቸው የክብር ቆንስላ ውክልና መሠረት በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል የንግድ፣ የባህልና የትምህርት መስኮች ላይ ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር እየሠሩ እንደሚገኙ አስታወቁ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በጃፓኑ አውሮፕላን አምራች ሚትስቡሺ ኮርፖሬሽን መካከል በጋራ መሥራት የሚቻልበትን ስምምነት ለመፍጠር እየሠሩ እንደሚገኙ ገለጹ፡፡

ዶ/ር ናጋቶ ናትሱሚ በሕክምና ሙያቸው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያላቸው ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በጃፓኗ ናጎያ ከተማ የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ በመሆን እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ሚትስቡሺ ኤርክራፍት ኮርፖሬሽን በአፍሪካ ገበያዎች ላሰበው የተደራሽነት ዕቅድና ለሚያቀርባቸው አውሮፕላኖች የጥገናና የመወለዋወጫ አቅርቦት ማዕከል እንድትሆን ኢትዮጵያን መምረጡን ገልጸዋል፡፡

እስከ 90 መንገደኞችን ማሳፈር የሚችሉ አውሮፕላኖቹን ለአፍሪካ ገበያ ማቅረብ የሚፈልገው ሚትስቡሺ ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት ቢመሠርት መላውን አፍሪካ በኢትዮጵያ በኩል ማዳረስ የሚችለበት ዕድል እንደሚፈጠርለትና ኢትዮጵያም በአቪዬሽን መስክ ከእስካሁኑም የተሻለ ውጤት እንድታስመዘገብ እንደሚያግዛት ዶ/ር ናትሱሚ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል እንዲመሠረት ስለታሰበው የሥራ ግንኙነት ገለጻ ተደርጎላቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ምናልባትም እ.ኤ.አ. ከ2022 እስከ 2023 ባለው ጊዜው ውስጥ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በሚትስቡሺ የአውሮፕላን አምራች ኮርፖሬሽን መካከል ስምምነት ሊፈጸም እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቶኪዮ የቀጥታ በረራ እያካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ከመንገደኞች በተጨማሪ ጭነትም እየተጓጓዘ ሲሆን፣ እንደ ዶ/ር ናትሱሚ ገለጻ በዓመት ከአምስት ሚሊዮን በላይ የአበባ ዘንግ ከኢትዮጵያ ወደ ጃፓን እየተላከ ነው፡፡ ይህንን መጠን እስከ ስምንት ሚሊዮን የአበባ ዘንግ ማሳደግ የሚቻልበት ዕድል እንዳለ የገለጹት የሕክምና ባለሙያው፣ ይህም ሆኖ ጃፓን የኢትዮጵያን አበቦች ከሌሎች የውጭ ኩባንያዎች የምትገዛበትና በሌሎች አየር መንገዶች የሚጓጓዝበትን አካሄድ ኢትዮጵያ መቀየር የምትችልበት አቅም እንዳላትም አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከአሥር ዓመታት በላይ የዘለቀ የላናቃና የከንፈር መሰንጠቅ በሽታ ላጋጠማቸው ሕፃናት የሕክምና ድጋፍ ሲሰጡ እንደቆዩ ያስታወሱት ባለሙያው፣ የጃፓን የላንቃ መሰንጠቅ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር በመሆናቸውም ጭምር በሕክምናው ዘርፍ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ብቻም ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያውያን ሐኪሞችም የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሲያግዙ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ በመሆን እየሠሩ የሚገኙት ዶ/ር ናትሱሚ፣ ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክብር ፕሮፌሰር በመሆን በሕክምናው መስክ ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኙ በግለ ታሪካቸው የሠፈረው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከጃፓንና ከኢትዮጵያም ባሻገር በቬትናም፣ በሞንጎሊያ፣ በማይናማር እንዲሁም በላዎስ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ሕክምናን ጨምሮ፣ በጥርስና በአፍ ክብካቤ ድጋፍ እንደሚሰጡ ማስረጃዎቻቸው ያሳያሉ፡፡

‹‹በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ጠንካራ ትብብርና ወዳጅነት እንዲጎለብት እሠራለሁ፤›› ያሉት ዶ/ር ናትሱሚ፣ በተለይም በትምህርት መስክ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጃፓን የነፃ ትምህርትና የሥራ ዕድሎችን ማግኘት በሚችሉባቸው ተግባራት ላይም ትኩረት መስጠት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች