መረጃ ለመሰብሰብ ከደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ሲጓዝ የነበረ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ተሽከርካሪ በደረሰበት አደጋ፣ የኤጀንሲው የሥራ ባልደረቦችን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ አደጋው የደረሰው ተሽከርካሪው ከሲኖትራክ ጋር በመጋጨቱ ነው፡፡ በአደጋው ሦስት የኤጀንሲው ባልደረቦች፣ የሲኖትራኩ አሽከርካሪና በመንገድ ላይ ስትጓዝ የነበረች አንዲት ሕፃን ሕይወት መጥፋቱን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
ከሲኖትራክ የተጋጨው ኒሳን ተሽከርካሪ የኤጀንሲው የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ንብረት ሲሆን፣ አደጋው የደረሰውም ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ከማለዳው 2፡30 ሰዓት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡት የኤጀንሲው ሁለት የግዥ አቅርቦትና የሥምሪት ባለሙያዎችና አሽከርካሪው ናቸው፡፡ አደጋው የደረሰው ከመሥሪያ ቤቱ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ነው ተብሏል፡፡
የአደጋው መንስዔ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር እንደሆነ ኤጀንሲው ያስታወቀ ሲሆን፣ አደጋው የተፈጠረውም በፍጥነት ሲያሽከረክር የነበረው የሲኖትራክ ሾፌር ባጃጅ ለማትረፍ ሲል መስመሩን ስቶ ወደ ግራ በመታጠፉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ባለሙያዎቹ በአደጋው ሕይወታቸው ወዲያው ሲያልፍ፣ አሽከርካሪው በአርባ ምንጭ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው ቆይተው ነው ሕይወታቸው ያለፈው፡፡
በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን 22 ሰዎችን ያሳፈረ ሚኒባስ በደረሰበት የመገልበጥ አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ጪንጊ በተባለ ሥፍራ ነው አደጋው የደረሰው፡፡
የተሽከርካሪ ብዛትና እየደረሰ ያለው አደጋ ብዛት በማይመጣጠንባት ኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከቀናት በፊት የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 8,764 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሞተዋል፣ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳትም ተዳርገዋል፡፡ አደጋውን ካደረሱት አሽከርካሪዎች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት አልተያዙም፡፡
በአገሪቱ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች ከ70 በመቶ በላይ በምትይዘው አዲስ አበባ ደግሞ፣ በየዓመቱ 25 ሺሕ የሚጠጉ የትራፊክ አደጋዎች ይመዘገባሉ፡፡ በዓመት በአዲስ አበባ ከ470 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ4.3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት በመንገድ ሀብት ላይ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በመንፈቅ ውስጥ 82 ግጭቶች በቀለበት መንገድ ላይ፣ 190 ግጭቶች ደግሞ ከቀለበት መንገድ ውጪ መድረሱ ታውቋል፡፡