Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየጤና ጣቢያዎች ጓዳ

የጤና ጣቢያዎች ጓዳ

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ እና ተመስገን ተጋፋው

ዕረፍት የነሳቸው ሕመም ምን መሆኑን ለማወቅ የሠገራ፣ የሽንትና የደም ናሙና የሰጡ ታማሚዎች የላቦራቶሪውን ክፍል ከበዋል፡፡ ‹‹ውጤት በጊዜ አላገኘንም›› በሚል የሚያጉረመርሙና የሚቁነጠነጡ ብዙ ናቸው፡፡ የላቦራቶሪው የማስተናገድ አቅም ከተገልጋዮች ቁጥር ጋር አልተስማምና ወረፋው አሰልቺ ነው፡፡ ጥበቃው ያሰለቻቸው ባለሙያዎችን ያማርራሉ፡፡ በዚህ መሀል ይብሱን ተስፋ የሚያስቆርጥ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ድንገት መብራት ጠፋ፡፡ ወረፋ ሲጠባበቁ የነበሩ ተገልጋዮች በሸቁ፡፡ አንደኛው ድምፁን ከፍ አድርጎ ባለሙያዎችን የሚያጥላላ ንግግር ተናገረ፡፡ በዚህ የተቆጣው  የላቦራቶሪው ባለሙያ ወረፋ ወደሚጠብቁት ዞሮ መቆጣት ጀመረ፡፡ ‹‹ማነው አሁን ኃይለ ቃል የተናገረው እኔ ምን ላድረግ›› እያለ ተመልሶ ወደ ክፍሉ አመራ፡፡

ኤሌክትሪክ በጠፋና በመጣ ቁጥር የላቦራቶሪ ሥራ መቋረጥና ያለው የሥራ ጫና ግን ብዙም የሚያሳስብ አይመስልም፡፡ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጤና ጣቢያ ኃላፊ እንደ ችግር ያነሱት የበጀትና አንዱ ሲገኝ አንዱ የሚጠፋውን የሆነ የመድኃኒት እጥረት ነው፡፡

- Advertisement -

የጤና ተቋሙ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በጤና ጣቢያ ደረጃ የማይሰጡ የሕክምና ዓይነቶችን ለመስጠት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ጀምሯል፡፡ የዓይን፣ የጥርስ፣ የሥነ አዕምሮና በቀዶ ሕክምና የማዋለድ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ይኼንንም አገልግሎት የሚሰጠው በሳምንት ሁለት ቀን ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል እየተዋሰ እንደሆነ የጤና ጣቢያው፣ ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ደመቀ ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡

በ1964 ዓ.ም. እንደተቋቋመ የሚነገርለት የየካ ወረዳ 5 ጤና ጣቢያ፣ በዓመት ከ150 ሺሕ በላይ ተገልጋዮችን ያስተናግዳል፡፡ በወረዳው ብቻ ሳይሆን ከክልልና ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች አገልግሎቱን ለማግኘትም ይመጣሉ፡፡ በክትባት አገልግሎትም አንድ ሺሕ ስምንት መቶ ሕፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች እስከ አንደኛ ፎቅ ድረስ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣  አገልግሎቱም በአንድ ቦታ ላይ የሚያልቅ ነው፡፡

የቲቢ ታካሚዎችም መድኃኒት እያገኙ ሲሆን፣ የኤችአይቪ ሕሙማንም የምክርና ሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በዓመት ለመድኃኒት ተብሎ የሚመደበው 1.5 ሚሊዮን ብር ቢሆንም በመንፈቅ አገልግሎት የቀረው ሦስት መቶ ሺሕ ብር ብቻ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ሁለት ጠቅላላ ሐኪም፣ 12 ጤና መኮንኖች በዲግሪ ደረጃ፣ 17 ነርስ በድግሪ ደረጃ፣ 19 ክሊኒካል ነርስ፣ 10 ሚድዋይፈሪ፣ 8 ላቦራቶሪ ቴክኖሺያል፣ 8 የፋርማሲ ባለሙያዎች፣ ሁለት የሥነ አዕምሮ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም 66 ድጋፍ ሰጪዎች በአጠቃላይ 155 ሠራተኞች ያሉት ጤና ጣቢያው 24 እስከ 40 ዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙም የስኳርና የደም ግፊት ሕክምናም ለ400 ለሚሆኑ ታካሚዎች ሕክምናም ይሰጣል፡፡

ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው የአራዳ ጤና ጣቢያ፣ በየጊዜው አዳዲስና የተሻሉ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የጣቢያው ሜዲካል ዳይሬክተር ሲስተር ወርቅ አንጥፉ ቦጋለ ገልጸዋል፡፡

ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለአጎራባች ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው  ጤና ጣቢያው የማህፀን በር ካንሰር ምርመራና ሕክምና በመስጠትም በከተማዋ ከሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የመጀመርያው መሆኑን ሜዲካል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ሕጋዊ የፅንስ ማቋረጥ አንዱ ሲሆን፣ ከተለያዩ ሆስፒታሎች ጋር በመቀናጀትም የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ከጥቁር አንበሳና ከራስ ደስታ ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር በሳምንት ሁለት ቀን የጤና ጣቢያውን ሙያተኞች በማሠልጠን ቀላል ቀዶ ሕክምና ለምሳሌ ግርዛት በጤና ጣቢያው መስጠት መጀመሩን ሲስተር ወርቅ ያንጥፉ ገልጸዋል፡፡

   የፋርማሲ አገልግሎትን በዘመናዊ መንገድ ለመጀመር ዝግጅት መጨረሱን፣ በኤችአይቪ ዙርያ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለሴተኛ አዳሪዎችና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ላላቸውም ጭምር ምርመራና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በጤና ጣቢያው ባለፈው ስድስት ወር፣ ለ1,626 ሰዎች የኤችአይቪ ምርመራ አድርገው 39 ሰዎች በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ ተገኝቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 13 ሴቶች ሲሆኑ፣ አምስቱ ወንዶች ናቸው፡፡ ዕድሜያቸውም ከ25 እስከ 49 ይደርሳል፡፡ በጤና ተቋሙ በቀን 60 የሚደርሱ ታካሚዎችም ፀረ ኤችአይቪ እየወሰዱ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ ያለው ሕንፃ ለአካል ጉዳተኞችና ለደካሞ ምቹ አይደለም፡፡ በመሆኑም አገልግሎቱን ታች በሚገኙ ቤቶች ውስጥ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ ይህን ችግር ይቀርፋል የተባለው ባለ አምስት ፎቅ (ወለል) ሕንፃም እንደሚገነባ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

የተቋሙ የስድስት ወር ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ (ከሐምሌ 2010 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2011 ዓ.ም.) 20,957 ታካሚዎች አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ በቤተሰብ ምጣኔ 660 ቤተሰቦችና 233 የወሊድ ክትትል ያደረጉ ሲሆን፣ በተቋሙ የወለዱትም 48 ናቸው፡፡

በዓመት በአማካይ ከ60 ሺሕ በላይ ታካሚዎች አገልግሎትም የሚያገኙበት የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 ጤና ጣቢያ ከሚሰጧቸው የጤና አገልግሎት መካከል ለእናቶች ብቻ የሚውል አልትራሳውንድ ይገኝበታል፡፡

በምግብ መበከል (ታይፎድ)፣ በቅማል የሚተላለፈው (ታይፈስ)፣ የመተንፈሻ አካል ላይ እንደ ጉንፋን (ኢንፉሉዌንዛ)፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የመሳሰሉት የበሽታ ዓይነቶች በጤና ጣቢያው በተደጋጋሚ የሚመዘገቡ ናቸው፡፡

የጤና ጣቢያው ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ሰማኸኝ አባተ ኃላፊ በመድኃኒት አቅርቦት ደረጃ ከቲቢና ከፀረ ኤችአይቪ ላይ ውጭ ያሉት መድኃኒቶች የመቆራረጥ ሁኔታ እንደሚያጋጥም ገልጸዋል፡፡

ጤና ጣብያው ለወረዳ 3፣4 እና 5 አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ጤና ተቋሙ የሚመጡ ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም አገልገሎቱና የሕዝብ ቁጥሩ እንዳይመጣጠን ማድረጉን አቶ ሰማኸኝ ገልጸዋል፡፡

እየተገለገሉበት ያለው ሕንፃ በመሰነጣጠቅ ላይ ሲሆን፣ የቦታ ጥበት እንዳለም አስተውለናል፡፡

ሜዲካል ዳይሬክተሩም አሁን የሚጠቀሙበት ሕንፃ ፈርሶ ሁሉንም ተገልጋይ ያማከለ ባለ ስድስት ወለል ሕንፃ እንደሚገነባ አክለዋል፡፡

ከ30 ዓመታት በላይ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ጤና ጣቢያ የተገልጋይና የሠራተኞች ቁጥር ሊመጣጠን አልቻለም፡፡

ጤና ጣቢያዎችን በጎበኘንበት ወቅት ከዚህ ቀደም ከነበረው አገልግሎት የተሻለ እየተሰጠ መሆኑን ብናስተውልም፣ በአንዳንዶቹ ሰዎች ሲጨናነቁ በአንዳንዶቹ ደግሞ ጥቂት ተገልጋይ ብቻ እንደሚገኙ አስተውለናል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ችግር ያለ ሲሆን፣ ፅዳትና  የውኃ አቅርቦትም በተሻለ መልኩ መገኘቱን አስተውለናል፡፡ ብዙዎቹ ግን ቀዶ ሕክምና አገልግሎት አይሰጡም፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ጣቢያዎች ሲሠሩ የቀዶ ሕክምና አገልግት ይሰጣሉ ስላልታሰበ ቀዶ ሕክምና የሚሠሩ ሐኪሞች፣ ለቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ላይ እጥረት እንዳለ፣ ከእነዚህ እጥረቶች ውስጥ ሰመመን ባለሙያዎችና ማሽኑን ማግኘት ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የባለሙያን እጥረት በተውሶም ቢሆን ለማካካስ ከየሆስፒታሉ በማቀናጀት በየጤና ጣቢያው እንዲሠሩ እየተደረገ ቢሆንም፣ የሕክምና መስጫ መሣርያ ችግር መሆኑን ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጤና ጣቢያዎቹ ከአቅም በላይ ሕክምና መስጠት ላይ በተመለከተ ኃላፊው ‹‹ምጥ የያዛት እናት ወይም በጣም ታሞ ለመጣ ሰው ወረዳህ አይደለም ተመለስ ማለት አይቻልም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ በየቦታው የጤና ተቋም መክፈትና አሁን የቀላል ቀዶ ሕክምና የሚሰጡትን ስድስት ጤና ጣቢያዎች ወደ 12 ከፍ ለማድረግ ታስቧል›› ብለዋል፡፡

ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ  ለሁሉም ጤና ተቋሞች መድኃኒቶች ቢደርሱም እጥረት ስለሚያጋጥም፣ በጨረታ የሚገዛበት አሠራር አለ፡፡

ሆኖም የጨረታው ዋጋ ለመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ ጥያቄ ቀርቦ የዶላር ወረፋ ላይ መሆኑን ታውቋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት፣ የጤና ቢሮው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ብሔራዊ ባንክ ቅድሚያ ለዚህ ጉዳይ እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጤና ጣቢያዎች የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላትም፣ በቀጣይ ሁሉን ያማከለ ግንባታ እንደሚኖር ኃላፊው አክለዋል፡፡

ጤና ሥርዓት ደረጃ መሠረት በአማካይ 100,000 ሕዝብ የሚይዘው አንድ ወረዳ በአማካይ 20 ጤና ኬላዎች፣ አራት ጤና ጣቢያዎና አንድ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ ጤና ጣቢያ በሥሩ ካሉት አምስት ጤና ኬላዎች ጋር እንደ አንድ የመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አኃድ እንዲተሳሰሩ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሠረት የገጠር ጤና ታቢያ በአማካይ ከ15,000 እስከ 25,000፣ እንዲሁም በከተማ እስከ 40,000 ለሚደርሱ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ አንድ ጤና ኬላ ከ3,000 እስከ 5,000 ሕዝብ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ጤና ጣቢያ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ፓኬጆችን የሚሰጥ ሲሆን፣ ከጤና ኬላዎች ለሚላኩ ታካሚዎች የሪፈራል ማዕከልና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የተግባር ማሠልጠኛ ተቋም በመሆንም ያገለግላል፡፡

አንድ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል በአማካይ ከ60,000 እስከ 100,000 ሕዝብ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል በጤና ጣቢያ ደረጃ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ የመለስተኛ የድንገተኛ የቀዶ ሕክምናና ለሕሙማን የደም መስጠት አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎትን በማጠናከር ለሁሉም ማኅበረሰብ መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን በጥራትና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለማድረስ የተለጠጠ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህን ዕቅድ በላቀ ደረጃ ለማስፈጸም አራት የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ተቀርፀዋል፡፡

እነዚህም የወረዳ ትራንስፎርሜሽን፣ የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ የመረጃ አብዮት መፍጠርና የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊነትን ማፍራት ናቸው፡፡   

ከተሞች ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ የጤና ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ የመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ አንድ ጤና ጣቢያ ለ40 ሺሕ ሰዎች እንዲያገለግልና በአማካይ ከ20 እስከ 25 የከተማ ጤና አክስቴንሽን ባለሙያዎች ተመድበው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡

የሚሰጡት አገልግሎት የተቀረፀው ከገጠር የተገኘውን ልምድ ታሳቢ በማድረግ በጣም ወሳኝ በሆኑ በተመረጡ በ15 የጤና አገልግሎት ፓኬጅ ነው፡፡

በከተማ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት በተከናወኑ የዳሰሳ ጥናቶችና ግምገማዎች የመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አጋዥ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በርካታ ክፍተት እንዳሉት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ለአብነት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ከጤና ጣቢያዎች ጋር የሥራ ግንኙነት የላላ መሆኑ፣ ከትምህርት ቤቶች፣ ከወጣት ማዕከላትና ሌሎች ከሚመለከታቸው ጋር አልፎ አልፎ ከሚደረግ ግንኙነት በስተቀር በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የሥራ ትስስር እንደሌላለቸው፤ ተለይቷል፡፡ በከተሞች አንድ ጤና ጣቢያ ለ40 ሺሕ ሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ቢቀመጥም በአብዛኛው ከተጠቀሰው ደረጃ በላይ  እያገለገሉ በመሆናቸው ጫና መፈጠሩ፣ የመጀመርያ ደረጃ የጆሮ፣ የአፍ፣ የዓይንና የመሳሰሉት አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ቢጠበቅባቸውም ወጥነት እንደሌለ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...