Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዓድዋ ድል ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎች

የዓድዋ ድል ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎች

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

‹‹እኛ ግን እንኳን ለእልፍና ለሁለት እልፍ ሰው የጣሊያን አገር ሰው ሁሉ ቢመጣ የጣሊያን ጥገኝነት ይቀበላሉ ብለህ አትጠራጠር!››

ይኼ ኃይለ ቃል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አውሮፓ ለነበረው ለሙሴ ኢልግ ነሐሴ 23 ቀን 1887 ዓ.ም. ከጻፉት ደብዳቤ ውስጥ የተገኘና ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ የተገኘ ነው፡፡

በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል የተደረገው ጦርነት መነሻ ከአፄ ምኒልክ በፊት በነበሩት በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን የነበረ ነው፡፡ ከዓድዋ በፊት በራስ አሉላ ጠቅላይ አዝማችነት ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም. በዶጋሊ የተደረገው ጦርነትና ወራሪው ጦር የተደመሰሰበት ይወሳል፡፡ በዘመኑ የነበረው የአውሮፓውያን አፍሪካን የመቀራመት ምኞት ተንሰራፍቶ የነበረ ሲሆን፣ ብዙ የአውሮፓ አገሮችም ይህ ምኞታቸው ተሳክቶላቸዋል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ሰፊ ግዛቶች ያልነበራት ጣሊያን ምኞቷን ለማሟላት በአፍሪካ ቀንድ ማንዣበቧ አልቀረም፡፡ አሰብን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ሙሉ ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት የውጫሌ ውልን ለመፈራረም ችለዋል፡፡ ይኼ ውል አሰብ ከተያዘች ከ20 ዓመት በኋላ የተደረገ ሲሆን፣ ይኼም ውል ለዓድዋ ጦርነት መንሥዔ ሊሆን ችሏል፡፡ በጦርነቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት ለማሸነፍ ችሏል፡፡

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከዓድዋ ድል በኋላም ድምፃቸውን ያሰሙት እንዲህ በማለት ነበር፡- ‹‹ጣሊያኖች በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኋቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡››

ይኼ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. የተገኘው ድል ብዙ መስዋዕትነትን አስከፍሏል፡፡ ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የተገኘ ድል ነው፡፡  ድሉ ለትውልደ ትውልድ መኩሪያ ሆኗል፡፡ ድሉ ለአያሌ በተለይም የጥቁሮች የነፃነቶች ትግል መነሻም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ የዓድዋ ጦርነት ድሏን በየዓመቱ ታከብራለች፡፡ ዘንድሮ የዓድዋ ድልን 123ኛ ዓመት በታሪካዊ መዘክር ያሰበው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ነው፡፡

በአካዴሚው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሥነ ጥበባት ማዕከል የካቲት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የዓድዋ ድል መታሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ የዓድዋ የዘመቻው መልካም አጋጣሚዎችና የድሉ ፈተናዎች በሚል ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል የገጠሟትን ሦስት የድሉ ፈተናዎች በሚል የቀረበው የጽሑፉ ዋና አካል ነበር፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ አንድነት ለማምጣት የተሠራበት፣ ተከፋፍለው የነበሩትን አንድ የማድረግ እንቅስቃሴ የጎላበት ቢሆንም፣ በዘመኑ ኢትዮጵያ ሦስት ወራሪዎችን (ግብፅ፣ ደርቡሽ፣ ጣሊያን) ያስተናገደችበት ነበር፡፡

እንግሊዞች ግብፆችን በበላይነት መምራት ከጀመሩ በኋላ ኢትዮጵያ ያልጠበቀችውን ስምምነት ተቀበለች፡፡ ይህም እንግሊዝ ግብፅን ወክለው ዓድዋ ላይ ከአፄ ዮሐንስ አራተኛ ጋር ስምምነት መደረጉ፣ ስምምነቱም በእንግሊዝ ሥር ያላቸው ግብ በኢትዮጵያ የያዘችውን ግዛት ጥላ እንድትወጣ ቢስማሙም፣ ግብፅ ግዛቱን ከለቀቀች በኋላ በእንግሊዝ ስትተዳደር መቆየቷን (እንደ ሞግዚት ሆነው መምራታቸው) ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገልጸዋል፡፡

የዓድዋው ውል ኢትዮጵያ የከሰረችበት ውል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግብፅን በሁለት ጠላት የቀየረችበት መሆኑ፣ እንግሊዝ በምፅዋ በኩል ጣሊያን እንድትገባ መርዳቷ፡፡

እንደሚታወቀው ጣሊያኖች ብዙ ሙከራ ሲያደርጉ የነበረው በአሰብ በኩል መቆናጠጫ መሬት ይዘው መሀል ኢትዮጵያ እንጂ ከሰሜን ጀምረው እንመጣለን ብለው አላሰቡም ነበር፡፡

አንዲት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይደረግ የነበረው ትግል በፈተናዎች የታጠረ መሆኑ፣ የአገሪቱ ህልውናም በግብፅ፣ በመሐዲስቶች፣ እንዲሁም በጣሊያን ይፈተን ነበር ረዳት ፕሮፌሰሩ ሦስቱ የዓድዋ ድል ፈተናዎች ካሏቸው የመጀመርያው  የዲፕሎማሲ ፈተና ነው፡፡ ከጦርነቱ በፊት በአፄ ዮሐንስ፣ እንዲሁም በአፄ ምኒልክ ጊዜ ጣሊያን የምኒልክን ሹማምንቶች እንዲከዱና ከጎናቸው እንዳይቆሙ ማድረግና የውጫሌ ውል አምስት ዓመት እንዲቆይ የማድረግ ትልም ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ወይም የጣሊያን መንግሥት የውጫሌን ውል ማሻሻል ቢፈልግ ከአምስት ዓመት በፊት ማሳወቅ አለበት፤›› የሚል ነበር፡፡

እንደ አቶ አበባው አገላለጽ፣ ራስ መኰንን ሮም ሲደርሱ የተለየ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ አቀባበሉም  አዘናግቷቸዋል፡፡ ምክንያቱም ያለ አስተርጓሚ ውል አስፈርመዋቸዋል፡፡ ውሉ የሚለውም ‹‹በጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ወሰን በአንቀጽ ሳይሆን እግር በረገጠ ይሆናል›› የሚል ነው፡፡

በሌላ በኩል ከዓድዋ ጦርነት በፊት ኢትዮጵያ በዘመኗ አይታ የማታውቀውን ረሃብ ማስተናገዷ፣ ጣሊያን ከህንድ ያስመጠቻቸው በአባ ደስታ በሽታ የተበከሉ ከብቶች በሽታ ወደ ሌሎች ከብቶች ተዛምቶ ብዙዎች ማለቃቸው፣ እህል በአንበጣ መንጋዎች መመታቱንም ተከትሎ የስንቅ ጉዳይ ከባድ ሥጋት ላይ መውደቁ ነገሮች ውስብስብ እንዲሆኑ ምክንያት ነበሩ፡፡

ሌላው በጊዜው የነበረው የጥይት እጥረት ሲሆን፣ በጊዜው ጠብመንጃ ቢገዛም የጥይት ብዛት አነስተኛ መሆኑ እንደ ችግር ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠብመንጃ በቂ ቢኖሩትም ጥይት ግን በቂ አልነበረውም፡፡ ይህንንም ለመፍታት ምኒልክ ከጣሊያኖች 5,000 ሺሕ ጠብመንጃ ሲገዙ፣ 800 ሺሕ የማይሞላ ጥይት ነበር የገዙት፡፡ በተጨማሪም ራስ መኰንን ከሐረር ሆነው ጥይት የሚገዙበት መንገድ ለመፍጠር ጥረዋል፡፡ ለምሳሌ ከእንግሊዝ፣ ከዓረብ ሰዎች ኤደን ላይ የተወሰነ ጥይት ቢገኝም፣ በእንግሊዞች አማካይነት ሊከሽፍ ችሏል፡፡ እንዲሁም ፈረንሣይ ብትጠየቅ ፈቃደኝነቷን ነፍጋለች፡፡ የዓድዋ ጦርነት የሁለት ቀን ውጊያ መሆኑ (አምባላጌና ዓድዋ) ያን ያህል ጥይት አለመጠቀማቸው ዕድሉ ጠቅሟቸዋል፡፡   

በውይይት መድረኩ ስድስት የዓድዋ ድል መልካም አጋጣሚዎች ተቀምጠዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ዋነኛው የሰው ብዛት ሲሆን 75 ሺሕ ጦር ሠራዊት በኢትዮጵያ፣ 14 ሺሕ የሚሆን ጦረኞች ከጣሊያን ወገን መሳተፋቸውን አቅራቢው አስረድተዋል፡፡ በመሀል ያለው የጦር ሠራዊት ልዩነት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የጠብመንጃና የመድፍ ብዛት ከኢትዮጵያ በኩል 42 መድፍ፣ በጣሊያን ደግሞ 60 መድፍ ስለነበር ቁጥሩ ብዙ አለመበላለጡ ኢትዮጵያ ድል እንዲቀናት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በወቅቱ ሰይፍና ጎራዴ ታጣቂ መሆኑም በቅልቅል ውጊያ ወቅት እንደረዳው ያስረዳል፡፡ ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ተዋጊ ጦረኛ እንደሆነ፣ ቀሪው ደግሞ ስንቅ አቀባይና ተያያዥ ሥራዎችን የሚያከናውን እንደነበር ይነገራል፡፡

የጦር ሥልት ማወቅም ሌላው ኢትዮጵያ ድል እንዲቀናት ያደረገ አጋጣሚ ነበር፡፡ በጊዜው የነበረው ትውልድ በጦርነት ተወልዶ በጦርነት ያደገ መሆኑም አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

ጠላትን አሳንሶ ካለማየትና የቦታው አቀማመጥ የጣሊያን ሠራዊት ከተዘጋጀበት አኳያ የማይጣጣም መሆኑም ድል ለአርበኞች እንዲሆን አንዱ ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የጣሊያን ሠራዊት የነደፈው የውጊያ ሥልት የርቀት ውጊያ ነበር፡፡ ይህ ሥልት ደግሞ በዓድዋ አካባቢ አመቺ አለመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ጦረኞች መልካም አጋጣሚን ፈጠረ፡፡ የክተት አዋጅ ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮ የነበረው የአንድነትና የመተባበር መንፈስ፣ እርስ በርስ የነበረውን የመቃቃር ስሜት ጠፍቶ ዕርቅ እንዲወርድ የተደረጉ ጥረቶች በሙሉ ዓድዋ የጥቁር ሕዝብ ኩራት ሆኖ በየዓመቱ እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡  

በዕለቱ የዓድዋን ታሪካዊ ይዘትን የሚያጎላ የባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን  ግጥም ሲነበብ፣ ስለዓድዋና አካባቢዋ በማዕከሉ የተሠሩ አጭር ቪዲዮ ለዕይታ ቀርቧል፡፡ ከውጭ የመጡት ፕሮፌሰር መላኩ ላቀው ለማዕከሉ ስለ ጥቁር ሕዝብ ነፃነት የሚያተኩሩ ታሪካዊ ፊልሞች አበርክተዋል፡፡ በቀጣይ የካቲት 23 በሚካሄደው የማዕከሉ ፕሮግራም ላይ ከተበረከቱት ፊልሞች መካከል አንድ ፊልም ለዕይታ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት የማዕከሉ ኃላፊ አቶ እንዳለ ጌታ ከበደ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...