Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ቱሪዝምን ለማሳደግ ቱሪስትን እንብላው የሚለውን አመለካከት መቀየር አለብን›› አቶ ፀጋዬ ተስፋዬ፣ የካኔት ሆቴል (አዳማ) ባለቤት

  አቶ ፀጋዬ ተስፋዬ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ የተከታተሉ ሲሆን፣ በወጣትነታቸው ዘመን በተለያዩ አገሮች ኖረዋል፡፡ በተለይ በካናዳ ለረዥም ዓመታት ኖረው ያካበቱትን ጥሪትና የሥራ ልምድ ይዘው ወደ አገራቸው በመመለስ ሪፍት ቫሊ የተሰኘውን ሆቴል በአዳማ ከተማ ገንብተው በ1989 ዓ.ም. ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በርካታ ፈታኝ ችግሮችን ያሳለፉ ቢሆንም፣ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ቃለየሱስ በቀለ አቶ ፀጋዬን በኢንቨስትመንት ሥራቸው ስለገጠማቸው ፈተናዎችና ስኬቶች፣ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ስላሉ ተግዳሮቶች አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ስለትውልድዎና ዕድገትዎ ቢነግሩን?

  አቶ ፀጋዬ፡- የተወለድኩት በሶዶ ወረዳ ልዩ ስሙ ኮራ የሚባል ቦታ ነው፡፡ በቄስ ትምህርት ቤት ተምሬ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የገባሁት አዲስ አበባ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከዚያም የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ሄጄ በመጨረሻ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃን የተማርኩት ተፈሪ መኮንንና ነፋስ ስልክ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ትምህርቴን ተከታትዬ አጠናቅቄያለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ወደ ሥራ ዓለም እንዴት ገቡ?

  አቶ ፀጋዬ፡- በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በመሳተፍ አሁን የምኖርበት አዳማ ከተማ ጥሪኝ የሚባል ዘመቻ ጣቢያ ተመድቤ አገልግያለሁ፡፡ ይህን ሆቴል አዳማ እንድሠራ ያደረገኝ አንዱ ምክንያት በዚያን ጊዜ በዕድገት በኅብረት ዘመቻ መጥቼ ከተማውን በመውደዴና ብዙ ጓደኞች በማፍራቴ ነው፡፡ የወጣትነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት አዳማ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ከዘመቻ በኋላ ትምህርት ቤት ብንገባም በነበረው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ብዙ ልንገፋ አልቻልንም፡፡ በሕዝብ ድርጅትና በኢሕአፓ መካከል በነበረው ግጭት ትምህርት ቤት ውስጥ ገለልተኛ ሆኖ መኖር አይቻልም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርቴን ለማቋረጥ ተገድጃለሁ፡፡ በወቅቱ ራሴን ማሸነፍ ስለነበረብኝ ወደ ታክሲ ሥራ ገባሁ፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል የታክሲ ሥራ ከሠራሁ በኋላ አቋርጬ ለሆቴሎች ሥጋ ማከፋፈል ጀመርኩ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ለነበሩ ትልልቅ ሆቴሎች ዋቢ ሸበሌ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ሒልተን የመሳሰሉት ሥጋ አቀርብ ነበር፡፡ ሥራው ጥሩ ነበር ነገር ግን ሁሌም በሥጋት ነበር የምንኖረው፡፡ ከዚያ በኋላ መንግሥት ሥራ ውስጥ ገብቶ የመንግሥት ሆቴሎች ሥጋና አትክልት ከመንግሥት ግሮሰሪ መረከብ አለባቸው ብሎ በመወሰኑ ሥራ ተዳከመ፡፡

  ሪፖርተር፡- በዚህ ምክንያት ነው ወደ ውጭ አገር የሄዱት?

  አቶ ፀጋዬ፡- ይህ ከብዙ ምክንያቶች አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ወደ ውጭ ለመሄድ የወሰንኩት በወቅቱ የነበረው የደኅንነት ሥጋት ነው፡፡ በዚያን ወቅት ወጣት ሆኖ በሰላም ወጥቶ መግባት ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ታክሲ እነዳ የነበረው ቀይ ሽብር በሚካሄድበት ወቅት ስለነበር ከሞት ያተረፈኝ የታክሲ ሥራ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የመኖር ዋስትና አደጋ ውስጥ የወደቀበት ጊዜ ስለነበር ወደ ውጪ ለመሄድ ወስኛለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ስደት እንዴት ነበር? ወዴት አገር ነው የሄዱት?

  አቶ ፀጋዬ፡- ስደት በጣም ከባድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የሚከብደው የምታውቀውን ማንነት፣ የገነባኸውን ሰብዕና ታጣዋለህ፡፡ ማንነትህ ይጠፋል፡፡ ቦታ ስትለውጥ አዲስ አኗኗር፣ አዲስ ባህል፣ ሁሉ ነገር አዲስ ስለሚሆን አንተነትህ ይጠፋል፡፡ ውጪ አገር ደስ ቢልም፣ ቁሳዊ ፍላጎትህ ቢሟላም ሁሌም ውስጥህ የሚጎልህ ነገር አለ፡፡ መጀመርያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ነበር የሄድኩት፡፡ ጅዳ ሄድኩኝ፡፡ ሐሳቤ ወደ አሜሪካ መሄድ ነበር፡፡ ፓስፖርት ካወጣሁኝ በኋላ እንደተረዳሁት በአሜሪካ ሕጋዊ ፈቃድ ያልነበራቸው ኢትዮጵያውያን ከአገር እንዲወጡ እየተደረገ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ አሜሪካ መሄዴን ትቼ ወደ ጅዳ ሄድኩኝ፡፡ ጅዳ ስድስት ወር ቆይቼ ወደ ጣሊያን አመራሁ፡፡ ጅዳ አልተመቸኝም ነበር፡፡ ጣሊያን በስደት አንድ ዓመት ከስምንት ወር ከቆየሁ በኋላ ወደ ካናዳ ሄድኩኝ፡፡ 

  ሪፖርተር፡- ኑሮ በካናዳ እንዴት ነበር?

  አቶ ፀጋዬ፡- የመጀመርያው ጊዜ አስቸግሮኝ ነበር፡፡ ካናዳ ቫንኮቨር ከተማ የምዕራብ ጫፍ ነበር የምኖረው፡፡ ከኢትዮጵያ ሩቅ ነው፡፡ አገሬ ተመልሼ መግባት አለመቻሌ ይረብሸኝ ነበር፡፡ ጣሊያን ቢከፋኝ እንኳ ለኢትዮጵያ ቅርብ ነበር፣ ኢትዮጵያኖችም አገኝ ነበር፡፡ ቫንኮቨር አማርኛ ሳላወራ አንድ ወር ቆይቻለሁ፡፡ ቫንኮቨር ውስጥ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ከዚያ በኋላ እንደተረዳሁት እኔ ለቫንኮቨር 58ኛው ኢትዮጵያዊ ነበርኩ፡፡

  ሪፖርተር፡- ኑሮ በቫንኮቨር እንዴት ነበር? ወደ ታክሲ ሥራ ውስጥ ገብተው ነበር?

  አቶ ፀጋዬ፡- እየተላመድኩኝ ሄድኩ፡፡ ከታክሲ ሥራ በፊት ሌሎች ሥራዎች ሞክሬያለሁ፡፡ አዲስ አበባ ለሆቴሎች ሥጋ አቀርብ ስለነበር የሆቴል ሥራ ውስጤ ገብቶ ነበር፡፡ እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ለመሥራት ሞከርኩ አልተሳካልኝም፡፡ እንግዲህ የቋንቋ ችሎታም ችግር ነበር፡፡ እኔ ከዚህ ስሄድ እንግሊዝኛ ቋንቋ የምችል መስሎኝ ነበር፤ እዚያ ደርሼ እንዳየሁት በቂ ችሎታ እንዳልነበረኝ ተረዳሁ፡፡ የሥጋ ሥራ እሠራ ስለነበር ሥጋ ቤት ውስጥ ለመሥራት አመልክቼ ነበር፣ የላውንደሪ ቤት ውስጥ ሞክሬ ነበር አልተሳካልኝም፡፡ መጨረሻ ወደ ታክሲ ሥራ ገባሁ ተዋጣልኝ፡፡ ኮሌጅም ገብቼ ነበር፡፡ ከሥራ ጋር ሁለቱንም ማካሄድ በጣም አድካሚ ስለነበር አንዱን መምረጥ ነበረብኝ፡፡ በደንብ አስቤበት ከዕድሜም አንፃር የታክሲውን ሥራ በርትቼ ሠርቼ ገንዘብ ማጠራቀም እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ የታክሲው ሥራ ተዋጥቶልኛል፡፡

  ሪፖርተር፡- ምን ያህል ጊዜ ኖሩ?

  አቶ ፀጋዬ፡- በአጠቃላይ በስደት የኖርኩት 15 ዓመታት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- እንዴት ወደ አገር ቤት ለመመለስ ወሰኑ?

  አቶ ፀጋዬ፡- ከኢትዮጵያ ከወጣሁ ጀምሮ የሚረብሸኝ ነገር ወደ ትውልድ አገሬ መመለስ አለመቻሌ ነበር፡፡ ስንወጣ እኔና እኔን መሰል የወቅቱ ወጣቶች ቆርጠን ነው የወጣነው፡፡ መመለስ አለመቻሌ ሁሌም ይረብሸኝ ነበር፡፡ ደርግ ሊወድቅ ስድስት ወር ሲቀረው ሆፕ ኢንተርናሽናል የሚባል ተቀማጭነቱ በካናዳ የሆነ ግብረ ሠናይ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ወዳጅ ነበርኩና ዕርዱኝና በእናንተ ድርጅት ኢትዮጵያ ሄጄ ነፃ አገልግሎት ልስጥ ብዬ ጠየኳቸው፡፡ በራሴ ከሄድኩኝ ያስሩኛል የሚል ሥጋት ነበረኝ፡፡ ሆፕ ኢንተርናሽናል ጥያቄዬን ተቀብለው ቪዛ ሒደቱን ጨርሰው ላኩኝ፡፡ ኢትዮጵያ መጥቼ ለሦስት ወር የነፃ አገልግሎት ሰጠሁ፤ አገሩን በጣም ወደድኩ በመንፈሴ ደስታ ተሰማኝ፡፡ ውጭ አገር ደስ ቢልም ቁሳዊ ፍላጎትህን ብታሟላም ውስጥህ የሚጎልህ ትልቅ ነገር አለ፡፡ ቤተሰቦቼንና ወዳጆቼን በማየቴ በጣም ተደሰትኩ፡፡

  ወደ ካናዳ እንደተመለስኩ የደርግ መንግሥት ወደቀ፡፡ በሆፕ ኢንተርናሽናል ድርጅት የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ተመልሼ መጥቼ አንድ ዓመት ከእነሱ ጋር ሠርቻለሁ፡፡ የተቀመጥኩት ሆቴል ውስጥ በመሆኑ የሆቴል ኢንዱስትሪውን በቅርበት ለመመልከት ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡ የሆቴል አገልግሎት እኔ ከማውቀው ጊዜ በጣም ወርዶ ነው ያገኘሁት፡፡ አገልግሎት መስጠት ውስጤ ያለ በመሆኑ በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ መሥራት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ በደርግ ሥርዓት መውደቂያ አካባቢ ቅይጥ ኢኮኖሚ ታውጆ ስለነበር አጋጣሚውን በመጠቀም አዳማ ከተማ ውስጥ አሁን ሆቴላችን የሚገኝበት ቦታ 2,700 ካሬ ሜትር ቦታ ወሰድኩ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ስመጣ የሆቴል ግንባታ ንድፍ አሠራሁ፡፡ ቦታው እንደማይበቃኝ ስለተረዳሁ አስጨምሬ 5,000 ካሬ ሜትር አሳደኩኝ፡፡ ከዚያም ወደ ግንባታ ሥራ ገባን፡፡

  ሪፖርተር፡- ስለ ሆቴሉ ይንገሩን?

  አቶ ፀጋዬ፡- ሆቴሉ ግንባታው አልቆ ሥራ ሲጀመር 48 የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች፣ አንድ ምግብ ቤትና ቡና ቤት ያለው ባለ አራት ፎቅ ሆቴል ነበር የገነባነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ሆቴሉን ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ ፈጀብዎት?

  አቶ ፀጋዬ፡- ጊዜ የወሰደብን የሆቴል ግንባታው አይደለም፡፡ ጉዳዮች ማስፈጸም፣ በየቢሮ የነበረ ቢሮክራሲ ነው ጊዜ የወሰደው፡፡ አንዱ መሥሪያ ቤት ከሌላው መሥሪያ ቤት ጋር አይተዋወቅም ነበር፡፡ የተቀናጀ አሠራር አልነበረም፡፡ አንደኛው የፈቀደልህን ሌላኛው ይከለክልሃል፡፡ ሥራ ከጀመርን በኋላ መንግሥት የሚያወጣቸው የተለያዩ አዋጆች ሥራችንን ያስተጓጉሉ ነበር፡፡ የሆቴል ግንባታውን ከጀመርን በኋላ ለዘጠኝ ወራት ያህል አስቁመውናል፡፡ በተገጣጣሚ ሕንፃ ነበር ያሠራሁት፡፡ ሆኖም የሥራ ፈቃድ እያለን አንደኛ ፎቅ ላይ ከደረስን በኋላ ይህ ነው በማይባል ምክንያት ለዘጠኝ ወር አስቁመውናል፡፡ ማናችሁ? ከየት ነው የመጣችሁት? ምንድነው የምትሠሩት? የሚለውን እናጣራለን ብለው አንድ ዓመት የተጠጋ ጊዜ ሥራ አስቁመውናል፡፡ እሱን ጨርሰን ወደ ሥራ ስንገባ የሊዝ አዋጅ ታወጀ፡፡ ወደ ሊዝ እስከምትገቡ ብለው እንደገና አስቆሙን፡፡ በርካታ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡ በዚያን ጊዜ መንገድ የሚሄድ ባለሥልጣን ጉዳዩ የማይመለከተውም ቢሆን ሥራ ያስቆመን ነበር፡፡ ውኃና መብራት ለማስገባት ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩት፡፡

  ሪፖርተር፡- ግንባታው የተጀመረው መቼ ነበር?

  አቶ ፀጋዬ፡- ግንባታው በአጠቃላይ ሦስት ዓመት ተኩል ወስዶ ሆቴሉ በ1989 ዓ.ም. ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ ሥራ እንድናቆም ተገደናል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሥራ ማቆማችሁ የግንባታውን ወጪ አንሮታል?

  አቶ ፀጋዬ፡- አዲስ መመርያ በወጣ ቁጥር፣ ኃላፊ በተቀየረ ቁጥር አዲስ የሚመጣው ኃላፊ ያስቆመን ነበር፡፡ እስኪጣራ ድረስ ሥራ አቁሙ ይሉናል እናቆማለን፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ይጨምራል፣ እኔም ለኢንቨስትመንት ብዬ ያመጣሁትን ገንዘብ ኖርኩበት፡፡ የምኖረው ሆቴል ውስጥ ነበር ሌሎች ብዙ ወጪዎች አሉ፡፡ በታሰበው ጊዜ ግንባታው አለመጠናቀቁ ወጪያችንን አንሮታል፡፡ ክልሎች ሲዋቀሩ አዳማ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመሆኗ አዲሱ አስተዳደር እንደገና ጉዳዮችን ማየት በመጀመሩ ሥራው ከሚገባው በላይ ተጓቷል፡፡ በዚህ ምክንያት የበጀት እጥረት ገጥሞን ብዙ ተንገዳግደናል፡፡

  ሪፖርተር፡- በዚያን ጊዜ የመንግሥት የኢንቨስትመንት ድጋፍ አልነበረም?

  አቶ ፀጋዬ፡- በወቅቱ የነበረው ድጋፍ መሬት ከመስጠት የዘለለ አልነበረም፡፡

  ሪፖርተር፡- አሁን ሆቴል የሚገነባ ባለሀብት የቀረጥ ነፃ አገልግሎትና የባንክ ብድር ያገኛል፡፡

  አቶ ፀጋዬ፡- የባንክ ብድር በመጨረሻ ወስጃለሁ፣ እሱንም ቢሮክራሲ ለማለፍ ብዙ ውጣ ውረድ ነበረው፡፡ አንዱን ጨርሰህ ሌላኛውን ሒደት እስክትጨርስ የመጀመርያው ፈቃድ መጠቀሚያ ጊዜው ያበቃል፡፡ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ የሆነው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ስንሠራ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በ1989 ዓ.ም. ሆቴሉ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ በኋላ የነበረው የሥራ ሒደት እንዴት ነበር? ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ የነበረው ፈተና እንዴት ነበር?

  አቶ ፀጋዬ፡- የነበረው ፈተና አንደኛው የሰው ኃይል እጥረት ነው፤ የሠለጠነ የሆቴል ባለሙያ ማግኘት ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ለምነን ነበር የምንቀጥረው፡፡ ልጆቻቸው ሆቴል ውስጥ ተቀጥረው እንዲሠሩ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ስላልተለመደ ወላጆችን አሳምነን ነበር ልጆቻቸውን የምንቀጥረው፡፡ ድሮ ሆቴልና ቱሪዝም የሚያሠለጥናቸው ልጆች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ ለናሙና ካልሆነ አይገኙም ነበር፡፡ ስለዚህ ወጣት ልጆች ራሳችን ቀጥረን ነበር የምናሠለጥነው፡፡

  ሌላው የገበያ ችግር ነው፡፡ አንድ መኝታ ክፍል 57 ብር ነበር የሚከራየው፡፡ በወቅቱ 57 ብር ትልቅ ገንዘብ በመሆኑ በ20 ብር የሚከራዩ መኝታዎች ሲያልቁ ነበር ወደ እኛ የሚመጡት፡፡ ዛሬ ደንበኛ የአንድ ሺሕ ብር መኝታ ሲጠፋ ነው ወደ ታች የሚሄደው ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የብር የምንዛሪ ለውጥ ተደርጓል፣ የኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተያይዞ ጨምሯል፡፡ በወቅቱ የነበረው ፈተና የሠለጠነ የሆቴል ባለሙያ አልነበረም፣ የደንበኞች ቁጥር አነስተኛ ነበር፡፡ ኢኮኖሚ ውስጥ ገንዘብ አልነበረም፡፡

  ሪፖርተር፡- የሆቴሉ ግንባታ፣ የዕቃ ግዥ በአጠቃላይ ምን ያህል ገንዘብ ወስዷል በዚያን ጊዜ?

  አቶ ፀጋዬ፡- የሆቴሉ ግንባታና ዕቃ ገዝተን ለማሟላት በወቅቱ 8.3 ሚሊዮን ብር ወጪ ወስዷል፡፡ በወቅቱ 76 ያህል ሠራተኞች ይዘን ነው ሥራ የጀመርነው፡፡ ዛሬ 180 ሠራተኞች አሉን፡፡

  ሪፖርተር፡- ከሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ውጪ ሌሎች ፈተናዎች ምን ነበሩ?

  አቶ ፀጋዬ፡- የሆቴል ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ገበያ ላይ አልነበሩም፡፡ የታሸገ ውኃ እንኳ አልነበረም፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አታገኝም፣ የምግብ ማዘጋጃ ግብዓቶችና ከውጭ የሚመጡ ቅመማ ቅመሞች አታገኝም፡፡ በአጠቃላይ የአቅርቦት ችግር ነበር፡፡

  ሪፖርተር፡- ሥራ ከጀመራችሁ ብዙም ሳይቆይ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ተከፍቶ የሆቴል ሥራ ተዳክሞ ነበር፡፡

  አቶ ፀጋዬ፡- የፖለቲካ አመረጋጋት ሲከሰት ሰላም ሲጠፋ የመጀመርያ ተጎጂ የቱሪዝም ዘርፍ ነው፡፡ አንድ ሰው ለመኖር ወሳኝ ነገር በመሆኑ ጤፍ ለመግዛት በተኩስ መካከል ተሽሎክሉኮ ሄዶ ይገዛል፡፡ ወደ ሆቴል መሄድ ትርፍ ነገር በመሆኑ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ደንበኞች ወደ ሆቴል አይሄዱም፡፡ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ መጀመርያ የሚናጋው የቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ ነው፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት፣ ምርጫ 1997  ተከትሎ የተፈጠረው ግርግርና በቅርቡ ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በተደጋጋሚ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብዙ ስብሰባዎች እንዲሰረዙ አድርጓል፡፡ እንኳን የውጭ ስብሰባዎች የአገር ውስጥም ይሰረዛል፡፡ ሐረር ግጭት አለ ሲባል አዳማ ላይ ስብሰባ ለማካሄድ ቦታ የያዙ ድርጅቶች ይሰርዛሉ፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ሰላምና መረጋጋት ሲደፈርስ የመጀመርያ ተጎጂዎች ናቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የተፈጠረውን ፈታኝ ወቅት፣ የገበያ መቀዛቀዝ እንዴት ተወጣችሁት?

  አቶ ፀጋዬ፡- ቅድም እንደነገርኩህ ሆቴሉን ስንገነባ በማይረቡ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ሥራ እንድናቋርጥ በመደረጉ ከመደብነው ወጪ በላይ በማውጣታችን፣ የገንዘብ እጥረት ተፈጥሮብን ነበር፡፡ ከሱ ችግር ስናገግም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ትልቅ የገበያ መቀዛቀዝ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ምክንያት ብድር የሰጠን ባንክ ሆቴሉን ሐራጅ ለመሸጥ አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ብዙ ጥረት አድርገን የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም፣ ከባንክ የፋይናንስ ዝውውራችንን የሚቆጣጠር ባለሙያ ተመድቦ ከባድ ጊዜ አሳልፈናል፡፡

  ከዚያ ሁሉ ችግር ወጥተን በሁለት እግራችን ቆመን ውጤታማ ለመሆን ችለናል፡፡ ያን ችግር ተወጥተን የማስፋፊያ ሥራ ሁሉ አከናውነናል፡፡ ያን ችግር እንዴት ተወጣችሁት? ለሚለው ጥያቄ በዚህ ቀመር ነው ብዬ ላስቀምጥልህ አልችልም፡፡ ከካናዳ ተመልሼ ባካሄድኩት ኢንቨስትመንት ልወድቅ ጫፍ ላይ ነበርኩ፡፡ ወደ ካናዳ እንኳ እንዳልመለስ ስወጣ እንዳልመለስ አድርጌ ነው የወጣሁት፡፡ ካናዳ የነበረኝን ንብረት ሸጬ ያስቀረሁት ነገር አልነበረም፡፡ ከካናዳ በድልድይ ተሻግሬ እንደመጣሁ ቁጠረውና ድልድዩን ካለፍክ በኋላ መመለሻዬን ድልድይ አፍርሼ እንደመጣሁ ቁጠረው፡፡ የተጋፈጥኩት ሁኔታ ተመልሶ ወደ ካናዳ መሄድ ከዜሮ እንደመጀመር ነው፡፡ ችግሩ መሀል ሆኜ ወደ ፊት ወይም ወደ ኋላ መመለስ እኩል ድካም ነበረውና ወደ ፊት መቀጠሉን መርጬ ችግሮቹን ተጋፍጬ ወደ ፊት ተጉዣለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ከዚያ ፈተና ወጥታችሁ የማስፋፊያ ፕሮጀክት አካሂዳችኋል?

  አቶ ፀጋዬ፡- ከምርጫ 1997 ዓ.ም. በኋላ ብዙ ነገሮች ተለወጡ፡፡ ከቀውሱ በኋላ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መጣ፡፡ የሆቴል ሥራ ጥሩ ሆነ፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ተቃርኖ ነው፡፡ ከቀውሱ በኋላ ዕድገት መጣ፣ ኢንቨስትመንት ተስፋፋ፣ የገንዘብ ዝውውሩ አደገ፡፡ እኛም ከዕድገቱ የድርሻችንን አገኘን፡፡ ብድራችንንና የአገር ውስጥ ገቢ በአግባቡ መክፈል ጀመርን፡፡ የአገር ውስጥ ገቢ የሽያጭ ታክስ ክፍያ እስከ ስድስት ወር ይጠራቀምብን ነበር፡፡ ዛሬ ነገ እንከፍላለን እያልን ያው የገንዘብ እጥረት ስለነበረብን ነው ያን የምናደርገው፡፡ በኋላ ግን በአግባቡ በወቅቱ መክፈል ጀምረናል፡፡

  ነገር ግን ሆቴሉ ዘለቄታ ያለውና ውጤታማ ነው፣ አድጓል የምንለው አራት አንኳር ነገሮች የተሟሉ እንደሆነ ነው፡፡ አንዱ የድርጅቱ ሠራተኞች በሚሠሩበት ድባብ ከድርጅቱ ያላቸው ግንኙነት የተደሰቱ እንደሆነ፣ ደንበኛ መጥቶ ለከፈለበት ነገር ተመጣጣኝ አገልግሎት ያገኘ እንደሆነ፣ መከፈል ያለባቸው ክፍያዎች በወቅቱ የተከፈሉ እንደሆነ፣ ይህ ድርጅት በመመሥረቱ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች አኗኗራቸው ያልተናጋ እንደሆነ ነው ድርጀቱ ውጤታማ ነው የምንለው፡፡ የሠራተኛውና የአካባቢውን ሕዝብ  ተጠቃሚነት ከግንዛቤ ያላስገባ ድርጅት መጨረሻ ላይ ችግር ይገጥመዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአካባቢው ሕዝብ እየተበሳጨብህ ድርጅቴ አድጓል ብትል ዘለቄታነት አይኖረውም፡፡ በእነርሱ ኪሳራ እያተረፍክ መቀጠል አትችልም፡፡

  ሪፖርተር፡- ስለአካሄዳችሁት ማስፋፊያ ብትገልጹልኝ?

  አቶ ፀጋዬ፡- የሠራተኛ ብዛት 70 አካባቢ ነበር አሁን ወደ 180 አሳድገናል፡፡ ስንጀምር አጠቃላይ ወርኃዊ ደመወዝ ወጪ 13,000 ብር ነበር፡፡ ዛሬ ወደ 450,000 ብር ደርሷል፡፡ የመኝታ ክፍል ከ48 ወደ 108 አሳድገናል፡፡ ተጨማሪ ባለሁለት ሮክ ሕንፃ ገንብተናል፡፡ አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነበረን አሁን አምስት አዳራሾች አሉን፡፡ ምግብ ቤትና ቡና ቤት አስፋፍተናል፡፡ መናፈሻው በጣም ሰፍቷል፡፡ ግቢያችን 5,000 ካሬ ሜትር ነበር አሁን 12,000 ካሬ ሜትር፣ ከግለሰቦች ላይ ገዝተን፣ ከመንግሥት በሊዝ ወስደን አስፍተነዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ዕድገት ማለት በመጠን ትልቅ መሆን ሳይሆን በጥራት አገልግሎት መስጠት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የሠለጠነ የሰው ኃይል አሁንም የጎላ ችግር አንዳለ ይነገራል፡፡ የሆቴሎች ብዛት እያደገ ቢመጣም የሠለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር ውስንነት እንዳለና ባለሙያ እንደሚነጣጠቁ ይነገራል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

  አቶ ፀጋዬ፡- ብዙ ችግር ነው ያለው፡፡ የሆቴል ባለሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት እንደ አብዛኛዎቹ የትምህርት ተቋማት የጥራት ችግር አላቸው፡፡ የግል የሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋማት እውነት ለመናገር ዘርፉ የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ እኛ በራሳችን ከታች ጀምሮ አሠልጥነን የምናበቃቸው ልጆች ከማሠልጠኛ ተቋም ከሚመጡት የተሻለ ይሠራሉ፡፡ አንዱ ምክንያት እኛ የምናሠለጥናቸው ሠራተኞች የሆቴል ሥራ ባህል በአግባቡ በተግባር ያውቁታል፡፡ ሁለተኛ ሲሠለጥኑ በሥራ ላይ የሚሰጥ ሥልጠና በመሆኑ በተግባር የመለማመድ ዕድሉ አላቸው፡፡ ከሥልጠና ማዕከላት የምናመጣቸው ሠራተኞች ከሥራው ይበልጥ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ከፍተኛ ነው፡፡ እኛ ጋር ካሉት ልጆ ጋር ተስማምተው የመሥራት ችግር አለባቸው፡፡ እኔ እኮ ወረቀት አለኝ የሚለው ላይ ነው የሚያተኩሩት፡፡ በእኛ አገር የትምህርት ግብ መኩራት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ የሆቴልና ቱሪዝም ተመራቂዎችስ?

  አቶ ፀጋዬ፡- እነሱም ዘንድ ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ በተግባር ሥራው ላይ ከማተኮር ዲግሪ አለኝ ብሎ የመኮፈስ ችግር ይታይባቸዋል፡፡ ትምህርት በራሱ ግብ ነው ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ ትምህርት ችግር መፍቻ መሣሪያ ነው የሚሰጥህ እንጂ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ ተመርቀው የሚመጡ ልጆች እኛ ጋ ካለው የሰው ኃይል ጋር ተቀናጅተውና ተስማምተው የመሥራት ችግር አለባቸው፡፡ ተመርቀው የሚመጡት ወጣቶች አንደኛ አይቆዩልንም፣ ሁለተኛ በሆቴሉ ውስጥ የገነባነውን መልካም የሥራ ግንኙነት ያደፈርሱታል፡፡

  ሪፖርተር፡- ያለውን የሰው ኃይል የመነጣጠቅ ችግር እንዳለ ይነገራል?

  አቶ ፀጋዬ፡- እሱ ችግር ነው፡፡ እኛ አንድ እምነት አለን፡፡ ሠራተኛውን አሠልጥነን ይሄዱብናል ከምንል ሳይሠለጥን በሚሠራ ጊዜ የሚያደርሰው ጉዳት ይበልጣል፡፡ ይህን ስልህ ግን አሠልጥነን ሌሎች ሆቴሎች ይወስዱብናል የሚል ሥጋት የለብንም አልልም፡፡ አንዳንድ ሆቴሎች ሲከፈቱ በተለይ እኛ ላይ ያነጣጥራሉ፡፡ አንድ አዲስ ሆቴል ሲከፈት ከስምንት እስክ 12 ሠራተኞች ይወስዱብናል፡፡ ይህን እንደ ትልቅ ሥጋት በማየት ተተኪ ሠራተኞች እያሠለጠንን እናዘጋጃለን፡፡ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ሁሌም መኖር አለበት፡፡ ሆቴሉ የመብራት ኃይል የሚያስፈልገውን ያህል የሠራተኛ ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሪፍት ቫሊ ሆቴል ሲከፈት አዳማ ውስጥ ትልቅ ሆቴሎች አልነበሩም፡፡ ዛሬ የትልቅ ሆቴሎች ቁጥር ተበራክቷል፡፡ ሥራ እንዴት ነው?

  አቶ ፀጋዬ፡- አሁን ሥራ ጥሩ ነው፡፡ ድሮ በልምድ ይባል ነበር፣ የሆቴሎች መብዛት ገበያ ያመጣል ይባል ነበር፡፡ ኢንዱስትሪውን ያሳድገዋል፣ ይመጋገባሉ ይባል ነበር ትክክል ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ አዳማ የስብሰባ ማዕከል ናት፡፡ ቀደም ሲል አንድ ትልቅ ሆቴል ብቻ ቢኖር አማራጭ ባለመኖሩ ስብሰባው አዳማ ላይ ማዘጋጀቱን ይተዉታል፡፡ አሁን ግን በርካታ ሆቴሎች በመኖራቸው አንዱ ጋ ባይሆን ሌላው ጋ ይዘጋጃል፡፡ አንዱ ጋ ቢሞላ የተረፈውን ተሰብሳቢው በቅርብ ባለው ሌላ ሆቴል ያሳርፋሉ፡፡ መብዛታችን ችግር ሳይሆን ጠቀሜታ አለው፡፡ ለምሳሌ እኛ ጋ 400 የስብሰባ ተሳታፊዎች ይመጣሉ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማሳደር አንችልም፡፡ ስለዚህ ወደ ሌሎቹ ሆቴሎች እንበትናለን፡፡ ሆቴሎች ባይኖሩ ኖሮ ይህን ማድረግ አንችልም፡፡ ይህ ጠቀሜታ አለው፡፡ የሠራተኛ መቀማማት የጎንዮሽ ችግር ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የሆቴላችሁ ስም ተቀይሯል፡፡ ሪፍት ቫሊ ሆቴል ነበር አሁን ወደ ካኔት ሆቴል ተቀይሯል፡፡ ስሙን ለምን መቀየር ፈለጋችሁ?

  አቶ ፀጋዬ፡- በመጀመርያ ደረጃ ሪፍት ቫሊ ሆቴል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አሁንም ስሙ ያው ነው፡፡ የኩባንያው ስም ያው ነው፡፡ የተለወጠው የሆቴሉ የንግድ ስም ነው፡፡ እዚህ አገር ሠራተኛም፣ ሐሳብም መነጣጠቅ የተለመደ ነው፡፡ ሪፍት ቫሊ የሚለውን የንግድ ስም በሕጋዊ መንገድ ሄደን መጀመርያ ያስመዘገብነው እኛ ነን፡፡ በኋላ ግን ብዙ ሪፍት ቫሊዎች ተፈጠሩ፡፡ ብዙ ቦታ ንግድ ሚኒስቴርም ሄድን የተሰጠን ምላሽ ተቻችላችሁ ኑሩ ነው፡፡ ተቻችላችሁ ኑሩ የሚለው ጥሩ መልስ ስላልመሰለኝ አዲስ ስም ማውጣት የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ስም መለያ ነው፡፡ ደንበኞቻችን እኛ መሆናችንን አውቀውና አረጋግጠው እንዲመጡ ያስችላቸዋል፡፡ አዲስ ስም አውጥቶ አስለምዶ ታዋቂ ማድረግ እንደሚቻል ማሳየት አለብን ብለን ሆቴላችን ካኔት ሆቴል ብለን ሰይመን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

  ሪፖርተር፡- ካኔት ምን ማለት ነው?

  አቶ ፀጋዬ፡- ከለወጥኩ አይቀር የእኔንም የሕይወት ጉዞ የሚያሳይ መሆን አለበት ብዬ ካኔት አልነው፡፡ ካኔት ማለት ካናዳና ኢትዮጵያ ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው CAN ካናዳን፣ ETH ኢትዮጵያን ይወክላል፡፡ በትውልድ ኢትዮጵያዊ፣ በዜግነት ካናዳዊ በመሆኑ ሁለቱም የእኔ ታሪክ በመሆኑ ነው ካኔት ሆቴል ያልኩት፡፡ ሁለቱም የምወዳቸው አገሮች ናቸው፡፡ በኦሮምኛ ደግሞ ወቅታዊ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ተነስተን ማለት ነው፡፡ 

  ሪፖርተር፡- በቀጣይ ዕቅዳችሁ ምንድነው?

  አቶ ፀጋዬ፡- ፈረንጆች ሆቴል በከተማ ውስጥ ያለ ከተማ ነው ይላሉ፡፡ ከተማ ውስጥ ያሉ አገልግሎቶች ማካተት አለበት ይባላል፡፡ ከተማ፡ ሱቅ፣ ፖስታ ቤትና ሌሎች ተቋማት አለው፡፡ ካኔት ሆቴል አንድ ሆቴል ሊይዝ የሚገባቸውን ተቋማት መያዝ አለበት፡፡ የመዋኛ ገንዳ፣ የልጆች መዝናኛ ማዕከል፣ የስፖርት ማዘውተሪያ (ጂምናዚየም)፣ የውበት ሳሎንና የመሳሰሉት ማዕከላት መገንባት አለብን፡፡ ሌላ ሆቴል ከመገንባታችን በፊት ይህን ሆቴል የተሟላ ሆቴል ማድረግ አለብን ብለን በማቀድ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህን ካሟላን በኋላ ሌሎች ከተሞች ላይ ቅርንጫፍ ወደ መገንባት እንሄዳለን፡፡ የኩባንያችን ስም ሪፍት ቫሊ በመሆኑ ሪፍት ቫሊን ተከትለን እንሄዳለን፡፡

  ሪፖርተር፡- የሆቴልን ሥራ ቀደም ብለው ከአገር ከመውጣትዎ በፊት ያውቁት ነበር፡፡ በውጪም በተለያዩ አገሮች ኖረው ተሞክሮ አለዎት፡፡  ወደ አገርዎ ተመልሰው በሆቴል ዘርፍ ኢንቨስት አድርገው ከሃያ ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡ የአገራችን ቱሪዝም ዘርፍ ማደግ እንዳለበት አላደገም ይባላል፡፡ በሆቴል ዘርፍ እንደተሰማራ ባለሀብት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚታይዎ ችግር ምንድነው?

  አቶ ፀጋዬ፡- የሆቴል ኢንዱስትሪ ለብቻው ከሌላው ዘርፍ ተነጥሎ ሊያድግ አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሊያድግ አልቻለም፡፡ ለምን ቢባል ከሌሎች ዘርፎች ተነጥሎ ደሴት ፈጥሮ ሊያድግ አልቻለም፤ ተጨዋቹ፣ አሠልጣኙና ደጋፊው ከዚህ ኅብረተሰብ የሚወጣ ነው፡፡ ሌላው ነገራችን ካላደገ እግር ኳስ ተነጥሎ ሊያድግ አይችልም፡፡ ቱሪዝምም እንደዚያ ነው፡፡ ቱሪዝምን ነጥለህ ልታሳድገው አትችልም፡፡ መንገዶች ማደግ አለባቸው፡፡ የመንገድ አጠቃቀማችን መሠልጠን አለበት፣ የመስተንግዶ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ማደግ አለበት፣ ሰው ማክበር መማር አለብን፣ የውጪ ሰው እንደ ጠላት ማየት ማቆም አለብን፣ ቱሪስትን እንብላው የሚለው መጥፎ አመለካከትን መጣል አለብን፡፡ ቱሪስትን እንጋጠው የሚለው ቀርቶ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን የሚበጅ አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል በጎ አመለካከት ማስረጽ ይኖርብናል፡፡ ይህ ሰላቶ ከእኔ እኩል ነው እንዴ የሚከፈለው? የሚል አስጎብኝ ገጥሞናል፡፡ ፎቶ የማንሳት ነፃነት በሌለበት አገር ቱሪዝምን ማሳደግ የማይታሰብ ነው፡፡

  በእኛ ሆቴል ፈረንጆች በምፀት የቆዳ ቀለም ግብር የሚሉት (Skin Tax) አናስከፍልም፡፡ በአገራችን ብዙ ሆቴሎች ለኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ለሚሰጡት ተመሳሳይ አገልግሎት የተለያየ ክፍያ ያስከፍላሉ፡፡ እኛ ይህን አናደርግም፡፡ የቱሪዝምን ዘርፍ ለማሳደግ መሠረተ ልማትና አገልግሎቶችን ማሟላት ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል፡፡ ቱሪስትን በመዝረፍ ሳይሆን በአግባቡ ተንከባክበን መግበን፣ አዝናንተንና ደኅንነቱን ጠብቀን አገሩ ከመለስነው ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ እሴት ጨምሮ እንደሚሄድ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ አስደስተን ስንሸኛቸው ሄደው ስለአገራችን መልካም ነገር ስለሚመሰክሩ የሚመጣው የቱሪስት ቁጥር እያደገ ይሄዳል፡፡ እኛም ባለሆቴሎች ብቻ ሳንሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጀምሮ፣ ባለሆቴሉ፣ ምግብ ቤቱ፣ አስጎብኝውና መኪና አከራዩ  እያለ በተዋረድ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚሆን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የቱሪስቶችን ልብ ማሸነፍ ከፈለግን መልካም የሆነ ቤተሰባዊ መስተንግዶ መስጠት ይኖርብናል፡፡ መልካምነታችንን ሄደው ይነግሩናል፡፡ ይህ ከማስታወቂያ ወይም ለንደንና ኒውዮርክ ቢሮ ከመክፈት በላይ ጠቀሜታ አለው፡፡

  ሪፖርተር፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

  አቶ ፀጋዬ፡- ምንም እንኳ የሌላ አገር ዜጋ ሆነን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሠርተን የመኖር መብት ስለተሰጠን ብደሰትም ዳያስፖራውን ቅር የሚያሰኙ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ፡፡ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ተሰደን የሌላ አገር ፓስፖርት መያዛችን ኢትዮጵያዊነታችንን ሊፍቀው አይገባም፡፡ ነገር ግን የውጭ ፓስፖርት መያዛችን በብዙ የአገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዳንሳተፍ ገደብ ተጥሎብናል፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሳተፍ አንችልም፡፡ ስለምንኖርበት ቀበሌ አመራር እንኳ አስተያየትም መስጠት አንችልም፡፡ ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዙ እንባላለን፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ፋይናንስ ዘርፍ ግን ኢንቨስት እንድናደርግ አይፈቀድልንም፡፡ በግል ባንኮች አክሲዮን ድርሻ የነበራቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮኖቻቸው ተሽጠው እንዲወጡ የተደረገበት መንገድ አሳዛኝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ውጪ ሆነው ቤተሰቦቻቸውን ይረዳሉ፡፡ ያ ለመንግሥት ትልቅ እገዛ ነው፡፡ ጦርነትና ድርቅ ሲመጣ ያዋጣሉ፣ ለዓባይ ግድብ ቦንድ ይገዛሉ፣ አሁንም ለዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በማዋጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በባንክና ኢንሹራንስ የነበራቸውን አክሲዮን ተነጥቀዋል፡፡ ይህን የመሰሉ በትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደረጉ ክልከላዎች ያሳዝኑኛል፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ግለሰቦች በኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ስም የተሰጣቸውን ዕድል ያበላሹ ይኖራሉ፡፡ መንግሥት ግን ይህን ፖሊስ ሲያወጣ የረዥም ጊዜ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ጥቅሞች በመመልከት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትውልድ አገሩንና ራሱን እንዲጠቅም ስለሆነ በትናንሽ ነገሮች እልህ መጋባት ያለበት አይመስለኝም፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች