Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአትሩጥ አንጋጥ የ40/60 ማስተላለፊያ ሥልት

አትሩጥ አንጋጥ የ40/60 ማስተላለፊያ ሥልት

ቀን:

በሁሉ ዓለሙ

መንግሥት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ሠርቶ ለማስተላለፍ በ2005 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን እንዲመዘገቡ በጋበዘበት ወቅት  የቤቱን ዋጋ 40 በመቶ የከፈለ ዕጣ ውስጥ መግባት እንደሚችል፣ ሆኖም ከ40 በመቶ በላይ የከፈሉ ሰዎች እንደከፈሉት የገንዘብ መጠንና የክፍያ ጊዜ ቅድሚያ እንደሚያገኙ ተገልጾ ነበር፡፡ አሁን ግን 40 መቶና ከዚያ በላይ የከፈሉ ሁሉ  በዕጣው ይካተታሉ ተብሎ ድንገት ተገለጸ፡፡

ምዝገባው በተካሄደበት ወቅትና ከዚያም በኋላ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች በተደጋጋሚ በሰጡት መግለጫ  ደግሞ፣ መቶ በመቶ የከፈለ በቅድሚያ የቤት ዕድለኛ እንደሚሆን ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይኼንንም መሠረት በማድረግ በቅድሚያ ቤቱን የማግኘት ጉጉት ያደረባቸው ግለሰቦች በጊዜው በነበረው የቤቱ ግምት ሙሉ ዋጋውን  በምዝገባው ወቅት፣ ከዚያም በኋላ ባሉት ጊዚያት ከ20 ሺሕ ሰዎች በላይ ክፍያውን ሲፈጽሙ መንግሥት የነገራቸውን አምነው ነው፡፡ 40 በመቶ የከፈለ ሰው ሁሉ በዕጣው ይካተታል ተብሎ ቢገለጽ ኖሮ ግን፣ በዚህ ዘመን ገንዘቡን ባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ ሌሎች ሥራዎች ላይ በማዋል የተሻለ ጥቅም ሊያገኝ የሚችል መሆኑን የሚጠፋው የለም፡፡

መቶ በመቶ ክፍያውን የፈጸሙ ሰዎች የደላቸው፣ ገንዘብ የተረፋቸው ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አብዛኛዎቹ ካለባቸው የቤት ችግር አንፃር ተቸግረው ነው የቆጠቡት፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሀብትና ጥሪታቸውን ሸጠው ወይም ተበድረው በመሆኑ ምክንያት፣ ሌሎች ዕድሎቻቸውን ሁሉ ሰውተው ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም፡፡

የመንግሥት ኃላፊዎች ከ40/60 ምዝገባ ጀምሮ በመንግሥትም ሆነ በግል የመገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች በቅድሚያ የቆጠቡ በቅድሚያ የቤቱ ባለቤት እንደሚሆኑ በመግለጽ፣ ተመዝጋቢዎች የተሻለ እንዲቆጥቡ ሲያበረታቱ ቆይተዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የመጀመሪያው የ40/60 ዕጣ ከወጣ በኋላ እንኳን የአዲስ አበባ ቤቶች ቁጠባ ኢንተርፕራይዝ የኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሒደት መሪ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ዓባይነህ ግንቦት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው የማያ ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይኼንኑ አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐምሌ 2009 ዓ.ም. ስለ40/60 የቁጠባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ባወጣው ልዩ መጽሔት ላይ፣ የዕጣ አወጣጥና ማስተላለፍ በሚለው ርዕስ ሥር ለብድር ብቁ ከሆኑ ደንበኞች መካከል የመኖርያ ቤቱን መቶ በመቶ ተቀማጭ ያደረጉ ቅድሚያ የሚያገኙ ሲሆን፣ ቤት የማስተላለፍ ሒደቱ ከከፍተኛው ወደ ዝቅተኛው እንደ ቅደም ተከተላቸው የሚፈጸም ይሆናል ይላል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎቹ ይኼን መሰሉን ሐሳብ ሲሰነዝሩና ከነበረው አጠቃላይ የፕሮግራሙ ዓላማ በመነሳት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ኃላፊዎች ዛሬ በሥራቸው ላይ ይኑሩም አይኑሩም ሒደቱን ሊያስረዱና ፍትሕም ሲናድ ዝም ማለት የለባቸውም ወይም ያለ ፍርኃት እውነታውን ለሕዝብም አሁን ላሉት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችም ሁሉ የማሳወቅ የሞራል ግዴታ አለባቸው፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም ፍትሕ እንዲመጣ ባለድርሻ አካላትን ማወያየት ይገባቸዋል፡፡ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የ40/60 የቤት ፕሮግራም፣ በቅድሚያ መቶ በመቶ የቆጠቡ ቅድሚያ ቤት የማግኘት ዕድል አላቸው ሲሉ የቆዩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊዎችና የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የቤት ፕሮገራሙ ኃላፊዎች፣ ዕጣው ሊወጣ ሁለት ቀናት ሲቀረው ማን “ቹ” እንዳላቸው ባይታወቅም፣ ምን መመዘኛ እንደተጠቀሙ አሳማኝ ምክንያት ባያቀርቡም፣ በቅድሚያ የቆጠቡት ዕድል ተነፍገው ሙሉ በሙሉ ከቆጠቡት ውስጥ 11ֽ ሺሕ ተመዝጋቢዎች ዕጣው ውስጥ ይገባሉ አሉና ዕጣው ወጣ፡፡ ብዙ ሐሜት ያስተናገደው የዕጣው ማውጫው መንገድ ከሎተሪነቱ ይልቅ ቀድሞ ተዘውሮ የተወሰኑ ሰዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ አስቀድሞ የተሠራ እንደነበር የብዙዎች እምነት ነው፡፡

አሁን አገራችንን በሚመራው የለውጥ መንግሥት ባለሥልጣናቱን እንደፈለገው “ቹ” የሚል ቱባ ባለሥልጣን አለ ብዬ ለማመን ያስቸግረኛል፡፡ “ቹ” ቢባልም ደንግጦና ተርበትብቶ የተባለውንና የታዘዘውን ያልተገባ ተግባር የሚተገብር ባለሥልጣን ይኖራል ብዬም አላምንም፡፡ በሌላ በኩል ግን አሁን ያሉት የሥራ ኃላፊዎች ምስኪኑ ነዋሪ መንግሥትን እንደ ፈጣሪ አምኖ ገንዘቡን መቶ በመቶ በመክፈል፣ ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ ለመንግሥት ካስረከበ ቦኋላ፣ ደርሰው የለም 40 በመቶ የከፈለ ተመዝጋቢ በሙሉ ዕጣው ውስጥ ይካተታል ብለው አረፉት፡፡

እነዚህ ባለሥልጣናት በቁጠባው ሒደት ውስጥ የነበሩትን ሒደቶች ማስተዋል አቅቷቸው ነው ለማለት ያስቸግረኛል፡፡ ይልቁንም ያለምንም አሳማኝ ምክንያት 11 ሺሕ ሰዎች ዕጣው ውስጥ እንዲገቡ “ፈቅደናል” ብለው እንደነበሩትና እዚህ ቁጥር ላይ በዘፈቀደ የደረሱት የቀድሞዎቹ ባለሥልጣናት በዚህ ውሳኔያቸው ያመቻቹት ጥቅም እንዳለ መገመት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ያሁኖቹስ ሁሉም 40 በመቶ ይካተት ሲሉ ምን አልመው ይሆን?

በ1990 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርንበት ወቅት አንዳንድ ሥጋ ጣል ጣል ያለበት ወጥ (Therefore) ይባል ነበር፡፡ አሁንም ይባል ይሆናል፡፡ ታዲያ ማታ ከእራት የተረፈ ወጥ በማግሥቱ ምሳ ላይ ተቀይጦ ይሠራል ስለሚባል፣ ከእነዚህ ጥቂት ሥጋዎች ውስጥ በየቀኑ እየተገላበጠች ወራትን ወይ ደግሞ እንደ ዕድል ሆኖ ለዓመታት ሳትበላ የምትቆይ የሥጋ ቅንጣቢ ልትኖር እንደምትችል እናስብ ነበር፡፡ አሁንም በመጀመሪያው ቀን ወይ ደግሞ በምዝገባው ወቅትና ከዚያ በኋላም ቢሆን የቤቱን ዋጋ ሙሉ በሙሉ የከፈለ ሰው፣ ከዛሬ ዓመት ወይም ከሦስት ዓመት በኋላ ገና 40 በመቶ ከሚከፍለው ሰው በኋላ ቤት ሊደርሰው እንዲሚችል ሲያስበው እንዴት አንጀቱ ድብን ይል? አንዱ የ40/60 ፕሮግራም ዕቅድ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች   የተሻለ የመቆጠብ አቅም ስላላቸው መንግሥት የቤቱን ፕሮግራም የሚያካሂድበትን ጠቀም ያለ ገንዘብ ያዋጣሉ ተብሎ ታስቦ በመሆኑ፣ 20 ሺሕ ሰዎችም በምዝገባ ጊዜ የቤቱ ዋጋ ተብሎ የተተመነውን መክፈል ችለዋል፡፡ ይኼም ለመንግሥት የተሻለ አቅም መፍጠሩ ግልጽ ነው፡፡

ለመሆኑ 40 በመቶ በመክፈል ዕጣው ውስጥ መግባት ይቻላል የሚል አስተሳሰብ አራማጅ ባለሥልጣናት ከመጡ፣ ከአሁን በኋላ ከ40 በመቶ በላይ ለመቆጠብ የሚፈልግ ምን ያህል ሰው ይኖራል? በአጠቃላይ ቁጠባውን የሚያዳክም አቅጣጫ ነው፡፡ ከአሁን በፊት በመንግሥት ተታሎ ብሩን ከከፈለው ስለሚማር ቀሪው ሰው 40 በመቶ ከፍሎ ቀጥ ይላል፡፡ የእነዚህ ባለሥልጣናት አጠቃላይ አካሄድ ማስተዋልና ሚዛናዊነት የጎደለው፣ ቶሎ ቶሎ ቀድመው በርካታ ገንዘብ እንዲቆጥቡ መንግሥት ያበረታታቸውን ሁሉ እጅግ ያሳዘነና ያስቆጨ ነው፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ፣ ጉዳዩን እንደገና ሊያስመረምሩትና ማስተካከያ ሊያደርጉበት ይገባል እላለሁ፡፡

ከመንግሥት በፊት እንደታቀደው ቀድመው ለከፈሉ ዕድል መስጠት አለበት፡፡ ይህ የማይተገበር ከሆነ ግን መቶ በመቶ የከፈሉ፣ እንዲሁም ከ40 በመቶ ከፍ ያለ ገንዘብ የቆጠቡ ሰዎች ያላግባብ እንዲቆጥቡ በተሰጣቸው ቃል መሠረት ገንዘባቸውን ለሌላ ተግባር ማዋል ሲችሉ በባንክ በማስቀመጣቸው እስከ ዛሬ ለደረሰባቸው ጉዳት፣ ዛሬ  መንግሥትንም ከሶ ፍትሕ የማግኛ ጊዜ ስለመጣ ተበዳዮቹ ሁሉ ከወለድ ባሻገር ተገቢውን ከፍተኛ ካሳ የመጠየቅ መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የቤቱን መቶ በመቶ የከፈለ የለም የሚለው የአሁኑን የቤቱን ዋጋ መሠረት ያደረገ ሐሳብ ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ለኅብረተሰቡ ያሳወቀውና ክፈሉ የተባለው የአሁኑ ወይም የቅርብ  የቤት ዋጋን የለም፡፡ የአሁኑ የቤት ዋጋ ከመጀመሪያው ከፍ እንደሚል የሚጠፋው የለም፡፡ የዋጋ ግሽበት አለና፡፡

ነገር ግን ቤቶቹን በፍጥነት ሠርቶ ማስረከብ  ያለበት መንግሥት ከአምስት ዓመት በላይ (በ20/80 እስከ አሥራ ሦስት ዓመት) አዘግይቶ ሲያበቃ፣ በ40/60 ፕሮግራም መቶ በመቶ የከፈለ የለም የሚል አስተያየት ከመንግሥት ኃላፊ መስማት አሳዛኝና የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ 40 በመቶውንም የከፈለው እኮ በአሁኑ የቤት ዋጋ ሲታይ ከ40 በመቶ በታች ነው የከፈለው፡፡ ታዲያ መቶ በመቶ ቢከፍሉም የቤቱ ዋጋ ስለጨመረ መቶ በመቶ ከፍላችሁ ማለት አይደለም የሚሉት ኃላፊዎች ስተዋል፡፡ ዛሬ የተሾመ ባለሥልጣንም ቢሆን የመንግሥት ኃላፊነት እስኪያዘ ድረስ የመንግሥት የቀድሞ ኃላፊዎች የሠሯቸው ጥፋቶች ካሉ የመሸከም፣ የማስተናገድና መፍትሔ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡

በተለይም በ2010 ዓ.ም. ከተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ በፊት የነበረው የመንግሥት የማስፈጸም ብቃት በተስፋፋው ሙስና ምክንያት የቤቶቹ ግንባታ በመጓተቱ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ፣ በቤት ዕድለኞች ላይ ለመጫን የሚደረግ ሐሳብ መወገዝ አለበት፡፡ ግንባታውን አጠናቆ በጊዜው ማስረከብ የነበረበትን ባለመተግበር ሕዝብ ላይ ዋጋ በማናለብኝነት መጫን አማራጭ የሌለውን ምስኪን ሕዝብ አጎብድዶ ውሳኔ እንዲቀበል ከማድረግ ባሻገር ተጠያቂነት ሊበጅለት ይገባል፡፡ የዋጋ ጭማሪውንም በአብዛኛው መንግሥት የሚሸፍንበት ሥሌት መሠራት ይገባዋል፡፡

በሌላ በኩል ለመንግሥት ሠራተኞች የተሰጠው ልዩ ኮታ ተገቢ ነው ወይ? ዕጣ ሲወጣ ለመንግሥት ሠራተኛው የተሻለ ኮታ የሚሰጠው የመንግሥት ቅጥር በመሆኑና ዝቅተኛ ገቢ አለው ተብሎ ብቻ ድጋፍ ለማድረግ ከሆነ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በግል መሥሪያ ቤትናመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ተቀጣሪዎች፣ ከመንግሥት ሠራተኞች በታች የሚከፈላቸው ብዙ ናቸው፡፡ ከነጋዴውም የንግድ ቤት ኪራይ ከፍሎ ወይም ዓመታዊ የመንግሥት ግብር ከፍሎ በትንሽ ትርፍ የሚንቀሳቀሰው ብዙ ነው፡፡ ከናካቴው የሚከስርም አለ፡፡ ሌላው በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተሠማራው ሁሉ፣ ከመንግሥት ሠራተኛ የተሻለ ገቢ አለው ብሎ ለማለት አያስደፍርም፡፡

የመንግሥት ሠራተኛ ያልሆኑ የተሻለ ገቢ የማግኛ መስክ ያላቸው እንዳሉ ሁሉ፣ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ሆነው ኃላፊነታቸውን በመጠቀም ያላግባብ በመበልፀግ ሀብት ያካበቱ እንዳሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በአንፃሩ እጃቸውን ሙስና ውስጥ ሳያስገቡ በራሳቸው የኑሮ ደረጃ ከፍ ያለ ሀብት ያላቸው፣ በመንግሥት ቤት ተቀጥረው መሥራትን የመረጡም መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ታዲያ የቤት ዕጣ ሲወጣ መንግሥት “ለራሱ” ሠራተኞች ለምን ያደላል? የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የቆመው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው እንጂ ለመንግሥት ሠራተኛው ባለመሆኑ፣ ለሁሉም ዜጋ እኩል ምልከታ ሊኖረው ይገባል፡፡

የመንግሥት ሠራተኛውም የመንግሥት ቅጥር ያልሆነውም ዜጋ ለአገሩ የየራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ለሠራተኛው ልዩ ጥቅም ይገባል ብሎ ቢያምን እንኳን ሌላ ፕሮግራም ቢያዘጋጅ ይሻላል እንጂ፣ በአንድ መሮጫ ላይ የተለያየ ዕድል መስጠቱን እንደገና ቢቃኘው መልካም ነው፡፡ በ20/80 ተመዝጋቢዎችና በ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ከዚህ በፊት በወጡ የቤት ዕጣዎች ሴቶች የተሻለ የ30 በመቶ ዕድል እንዲያገኙ የተሠራበት ነበር፡፡ ባለፈው ጊዜ በወጣው የመጀመሪያ የ40/60 የቤቶች ዕጣ ለሴቶች የተሰጠው ዕድል ተዘንግቷል ወይም ሆን ተብሎ ምናልባትም አብዛኞቹ ዘዋሪዎችና ያላግባብ ጥቅም አቀናባሪዎች ወንዶች በመሆናቸው፣ ዕድሉ ሊነፈጋቸው ችሏል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ያለው የለውጥ መንግሥት ለሴቶች የተሻለ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ፣ በቀጣዩ 40/60 ዕጣ ውስጥ ሴቶች የተሻለ ዕድል ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ